Sunday, July 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሞሪንጋ ሻይ ቅጠልና ዱቄት ደረጃ ወጣላቸው

የሞሪንጋ ሻይ ቅጠልና ዱቄት ደረጃ ወጣላቸው

ቀን:

በዱቄትና በሻይ ቅጠል መልክ ወደ ገበያ እየወጡ የሚገኙ የሞሪንጋ ምርቶችን ምንነትና የምርቱን ባህሪ የተጣጣመ ለማድረግ የሚያስችል ደረጃ ወጣላቸው፡፡

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩትና የተባበሩት መንግሥታት ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) በጋራ በመሆን ያዘጋጁት የሞሪንጋ ደረጃዎች ምደባ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች ተመርተው ወደ ገበያ የሚገቡና በሞሪንጋ ስም ተጭበርብረው የሚሸጡ ምርቶችን ለማስቀረት እንደሚያግዝ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የደረጃዎች ዝግጅት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ይልማ መንግሥቱ እንዳሉት፣ የወጡት ደረጃዎች ተመሳስለውና ተጭበርብረው ወደ ገበያ የገቡ ምርቶችን ከመከላከል ባለፈም፣ በኢትዮጵያ ተመርቶ ወደ ውጪ የሚላክ የሞሪንጋ ምርት ጥራትና ደረጃን በማረጋገጥ ለገበያ እንዲቀርብ ያስችላል፡፡

የደረጃው መውጣት ወደ ውጪ ከሚላኩ የሞሪንጋ ምርቶች የሚገኘውን ገቢ ከመጨመር ባሻገር፣ በአገር ውስጥ ገበያ በአምራቹና በሸማቹ መካከል መተማመን እንዲፈጠር፣ ሞሪንጋን ከባዕድ ነገሮች ጋር በመላቀል የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመከላከልና ምርታማነትን ለማሻሻል እንደሚረዳም ገልጸዋል፡፡

የዩኒዶ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስ አውሮሊያ ካላብሮ በበኩላቸው፣ የደረጃው መውጣት በዘርፉ ተሰማርተው እየሠሩ የሚገኙ ሴቶችን ለማበረታታት፣ የሞሪንጋ እርሻን ለማስፋፋትና አገሪቷ ከሞሪንጋ ምርቶች ወጪ ንግድ ገቢ እንድታገኝ ያስችላታል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥት በቀረበ ጥሪ መሠረት በደቡብ ኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የገጠሩን ማኅበረሰብ ሕይወት ለማሻሻል የሞሪንጋ ልማት እሴት ሰንሰለት ፕሮጀክት፣ በጣልያን የልማት ተራድኦ ድርጅት (ኤአይሲኤስ) የሚደገፍ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ለሁለተኛ ዙር እየተተገበረ ያለው የሞሪንጋ ፕሮጀክት፣ በኤአይሲኤስ የአራት ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ የተደረገለት ሲሆን፣ ፕሮጀክቱም የሞሪንጋ ምርቶችን እሴት በመጨመር ዘላቂ ለማድረግ፣ በተመጣጠነ ምግብ የበለፀገውን ሞሪንጋ በምግብ ሥርዓት ውስጥ ለማስገባትና ግንዛቤ መፍጠር ላይ የሚሠራ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በሞሪንጋ ዙሪያ የሚሠሩ ሴቶችን አቅም በመገንባት፣ የመሪነትና የተሳትፎ ሚና እንዲኖራቸው በማስቻል፣ በውሳኔ ሰጪነትና በገበያ ልማት ሥልጠና ዙሪያም የሚተገበር ነው፡፡

እንደ ሚስ አውሮሊያ፣ ፕሮጀክቱ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በወዚቃ ቀበሌ ለሚገኙ አርሶ አደሮች 30 ሄክታር መሬት ያገኘ ሲሆን፣ በሥፍራው በሚተገበረው ፕሮጀክትም 90 በመቶ ሴቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በፕሮጀክቱ የሚደገፉ አርሶ አደሮች ሞሪንጋን ለግብዓትነት ከሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ጋር ለማስተሳሰር በተለይም ከምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪዎች ጋር ተመጋጋቢ ሆነው እንዲሠሩ ለማስቻል ስምምነት ተፈጽሟል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጥናትና ምርምር ሥራዎች የፕሮጀክቱ አጋር ሆኖ እየሠራ እንደሚገኝ፣ የእንሰት ውጤቶች የተሟላ ንጥረ ምግብ ይዘት እንዲኖራቸው በሞሪንጋ ለማበልፀግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየተሳተፈ መሆኑንም ሚስ አውሮሊያ ተናግረዋል፡፡

ድርቅ፣ በሽታና የተለያዩ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትሉትን ችግሮች የሚቋቋመው ሞሪንጋ (ሽፈራው) በኢትዮጵያ የሚታየውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለመፍታት እንደሚያስችል ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሞሪንጋ የምግብ ይዘትና በኢኮኖሚ ፋይዳ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት እንዳለ አማረ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ሞሪንጋ ዚንክ፣ ሲለንየም፣ አይረን፣ ፎስፈረስ፣ ካልሽየም፣ ፕሮቲን፣ ፎሌት፣ ቤታካሮቲንና ሌሎች ወሳኝ የምግብ ንጥረ ነገሮችን የያዘ መሆኑንም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...