Monday, December 11, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የአፍሪካን ቀንድ የጋራ ልማትና የዕድገት ፍላጎቶችን ለማሳካት የፌዴራሊዝም ዕሳቤዎች አስፈላጊነት

በኃይለየሱስ ታዬ (ዶ/ር)

በአፍሪካ ቀንድ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ሕዝቦች የዘላቂ ሰላም፣ የልማትና የዕድገት ተስፋቸው በጥብቅ የተሳሰረ መሆኑን ሳይታለም የተፈታ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ምክንያቱም በቀጣናው በሚገኙ አገሮች የሚኖሩ ሕዝቦች አሰፋፈርና ትስስር፣ በጋራ እያሳለፏቸው ያሉ ሰው ሠራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋዎች በጋራ ጥቅም ላይ ቢውሉ ቀጣናውን ይበልጥ ሊያስተሳስሩና ለሰላምና ለዕድገት ሊውሉ የሚችሉ ሀብቶች መኖር ተስፋቸው የተሳሰረ መሆኑን አመላካቾች ናቸው፡፡

የትስስሩ አስፈላጊነት በዚህ ብቻ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ ቀጣናው ከሚታወቅበት ተከታታይነት ካላቸው ግጭቶች፣ ሥር የሰደደ ድህነት፣ ስደት፣ መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎቶችን እንኳ ለማሟላት፣ ከለጋሽ አገሮችና ድርጅቶች ላይ ያለና የተጣባ ጥገኝነት ለመላቀቅ አገሮች በጋራ የሚያስተሳስራቸው ጠንካራ ሥርዓት ማበጀት አሁን በምንገኝበት ክፍለ ዘመን የግድ ይላቸዋል፡፡

አገሮች በየራሳቸው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንደተጠበቀ ሆኖ በተመረጡና ለቀጣናው መሠረታዊ ለውጥ በሚያመጡ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ፍላጎትን መሠረት በማድረግ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መሠረታዊ የሆነ ጉዳዮች በጋራ የሚመሩበት የጋራ አስተዳደርን፣ በፌዴራላዊ ዕሳቤ የሚመራ አደረጃጀት ፈጥረው መንቀሳቀስ ካልቻሉ ለቀጣናው ማኅበረሰብ እንደ ጥቅልም ሆነ በየአገሮቹ የሚኖሩ ዜጎችን ዘላቂ ሰላም፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ ዕድገትና የኑሮ መሻሻል ምላሽ እየሰጡ ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ጋር እኩል የሚራመዱበት ሁኔታ ሊኖር የማይችል መሆኑ፣ ቀጣናው ካሳለፋቸውና እያሳለፋቸው የሚገኙ ነባራዊ ሁኔታዎች ግልጽ ምስክሮች ናቸው፡፡

ሉዓላዊ በሆኑ አገሮች መካከልም የሚኖር ዘላቂና በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ፣ በጋራ በተሻለ መልኩ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን የሚፈታ፣ በጋራ ቢለሙና የጋራ ተጠቃሚነት ቢያረጋግጡ የተሻለ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ፣ እንዲሁም የግጭት ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን በጋራ ስምምነት ግልጽ በሆነ አግባብና አደረጃጀት የሚመራበት ሥርዓት ፈጥሮ ለመንቀሳቀስ ፌዴራላዊ ዕሳቤዎችን መከተል የግድ ይላል፡፡

ፌዴራሊዝም በባህሪው በአብሮነት የግልና የጋራ ፍላጎቶችን ዴሞክራሲያዊና ሚዛናዊ በሆነ አግባብ አቀናጅቶ ለሰው ልጆች ነፃነትን፣ እኩልነትን፣ ሰላምንና ዕድገትን  እየረጋገጡ የሚሄዱ አደረጃጀቶች በየደረጃው ተደራጅተው ወደ ሥራ መግባትን የሚደግፍና የተለያዩ ቅርፅ ያላቸው ፌዴራላዊ የፖለቲካ ሥርዓቶችን አቅፎ የሚያያይዝ  ፍልስፍና ነው፡፡ ፌዴራሊዝም የሁሉም መብትና ፍላጎት የሚከበርበት በውይይት፣ በንግግርና በመተማመን የጋራ የሆነ ሥርዓት የሚፈጠርበት ዕሳቤ ነው፡፡

ፌዴራሊዝም አገር እንደ አገር፣ በቀጣና ደረጃ፣ በአኅጉር፣ እንዲሁም በዓለም ደረጃ በግልና በጋራ ቢከናወኑ የተሻለ ውጤት ሊያመጡና የሰው ልጅንና የሚኖርበትን ምኅዳር አሰናስለው የበለጠ ተጠቃሚ ሊደረጉ የሚችሉ ጉዳዮች በየደረጃው ተለይተውና ተሳስረው የሚፈጸሙበትን አሠራር፣ ሥርዓትና አደራጃጀት የሚደግፍ ዕሳቤ ነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አገራዊ ጉዳዮቻቸውን ከጋራ ጉዳዮቻቸው ጋር አስተሳስረው በቅንጅትና በትብብር ካልሠሩ አገሮች ችግሮቻቸውን ቀርፈው በጋራ የማደግ ተስፋቸው  የተመናመነ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ በከፋ ችግርና ድህነት ውስጥ ባለው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ችግሩ ይበልጥ እየተባባሰ በከፋ መልኩ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ካልሆነ በስተቀር፣ ሌላ መውጫ በር ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡

በዓለም ላይ ካሉ የፌዴራሊዝምን ዕሳቤ ከሚጋሩ አደረጃጀቶች የአውሮፓ ኅብረትን የአጀማመር ሁኔታ በአጭሩ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ አንድ የችግር ምንጭ ሆኖ በተለየ ጉዳይ የችግሩን ምንጭ በጋራ በማስተዳደር ለጋራ ጥቅም በማዋል፣ ትልቁን የአውሮፓን የጋራ ጉዳዮቹን በጋራ የመምራት ዕሳቤ በመያዝ የተጀመረው ሥራ አሁን የአውሮፓ ኅብረት የደረሰበትን የራስ አስተዳደርና የጋራ አስተዳደር፣ አስተሳስሮና አናቦ በተለያዩ ዘርፎች እየሄደበት ያለውን እርቀት ሲታይ አጀማመሩና አስተማሪነቱ ከፍ ያለ ነው፡፡ 

እንደሚታወቀው የአውሮፓ ኅብረት ጥንስስ እ.ኤ.አ. በ1951 በስድስት የአውሮፓ አገሮች የተመሠረተው የአውሮፓ የድንጋይ ክሰልና ብረት ማኅበረሰብ (European Coal and Steel Community) መሆኑ ይታወቃል፡፡ መነሻ ሐሳቡ አውሮፓዊያኑ በተከታታይ ግጭቶችና በሁለት የዓለም ጦርነቶች ያሳለፋቸውን ችግሮች ላለመድገም አገሮች ያላቸውን የዴንጋይ ክሰልና ብረት አስተዳደር ወደ ጋራ አስተዳደር በማምጣት በአገር መካከል የግጭት ፍላጎት በመቀነስ በጦር መሣሪያ የታገዘ ኃይል የተቀላቀለበት ግጭትን ለማካሄድ የሚያስችል ማቴሪያል ማግኘትን፣ የማይታሰብ ማድረግና በተለይ በፈረንሣይና በጀርመን መካከል የነበረውን ግንኙነት በትብብር ላይ የተመሠረተ በማድረግ የጋር የሆኑ ጉዳዮችን በጋራ ማከናወን ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡

ለእዚህ ለአውሮፓ ኅብረት መጀመር መነሻ የሆነ እንቅስቃሴ በፈረንሣይ በወቅቱ የውጭ ጉደይ ሚኒስትር የነበሩት ሮበርት ሹማን ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ፣ በስማቸው የሚጠራው የሐሳብ መግለጫ ሰነድ (Shuman Declaration) ለማኅበረሰቡ መመሥረት መነሻ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ጀን ሞኔት ደግሞ የማኅበረሰቡ አደረጃጀት ነዳፊ ተደርገው የሚወሰዱ ሲሆን፣ የመጀመርያው ፕሬዚዳንቱም ነበሩ፡፡ የእነዚህ ቁልፍ ሰዎች ተግባር የሚያመላክተን ለቀጣናቸው ሰላምና ዕድገት አርቀው የሚያስቡና የፌዴራሊዝም ዕሳቤ የተላበሱ መሪዎች የአውሮፓን ዘላቂ ሰላምና የጋራ ዕድገት አሻግረው በማየት የመነሻ ጥንስሱን የጠነሰሱ የፖለቲካ መሪዎች መሆናቸውን ነው፡፡ ከእነዚህ መሪዎች የአፍሪካን ቀንድ ሰላም፣ ደኅንነት፣ ልማትና ዕድገት የሚመኙና የወደፊቱን የቀጣናውን ብሩህ ተስፋ አሻግረው የሚያዩ የፖለቲካ መሪዎች ብዙ ሊማሩና የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የፌዴራሊዝም ዕሳቤን መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴ ሊያደርጉ እንደሚገባ ማመላከቱ፣ በአገራችን ለሚነሱ ቀጣናዊ የጋራ ልማትና የጋራ ተጠቃሚነት ዕሳቤዎች መሠረት ይሆናል፡፡

በአገራችን ወቅታዊ የሆነው ሁሉም የቀጣናው አገሮች ተጠቃሚ የሚሆኑበትና በጋራ ፍላጎት መመለስ የሚችለው የወደብ ጥያቄና ሌሎች ቀጣናውን ለማስተሳሰር የሚችሉ እንደ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመንገድ፣ የባቡር፣ የአየርና የባህር ትራንስፖርት፣ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች፣ ለመጠጥም ሆነ ለግብርና ሥራ የሚውል ውኃ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የጋራ ገበያ፣ ወዘተ. የመሳሰሉት በጋራ ቢመሩ የበለጠ አዋጭና ለሁሉም  የመጠቀም ዕድል ይፈጥራሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮችን በጋራ ማስተዳደር የሚችል አካል የፌዴራሊዝምን ዕሳቤ መሠረት በማድረግ በማቋቋም ጥንስሱን መጀመር፣ ወይም ለጥንስሱ ኢጋድ አለ ከተባለም ኢጋድን ሙሉ በሙሉ አደረጃጀቱንና አሠራሩን በመለወጥ ለቀጣናው መጪ ዘመናት ተስፋ ያለውና ቀጣናውን ከሚታወቅበትና መገለጫው እየሆነ ከመጣው ግጭት፣ ሥር የሰደደ ድህነትና ስደት ለማላቀቅ ተስፋ የሚሰንቅ ተግባርን ማከናወን ይገባል፡፡ የቀጣናው በሁሉም ዘርፍ የሚገኙ ልሂቃንና የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግመው ደጋግመው ሊያስቡበት የሚገባ ተግባር ነው፡፡

በፌዴራሊዝም ዕሳቤ በማንኛውም ደረጃ የሚገኝ የማኅበረሰብ አደረጃጀት በየደረጃው በራሱና በአካባቢ ቢከናወኑ አዋጭና የተሻለ ውጤት ያመጣሉ፡፡ ማኅበረሰቡ በቅርበት አገለግሎት እንዲያገኝ ያስችላሉ የሚላቸውን ተግባራት በራስ አስተዳደሩ ማዕቀፍ በራሱ እየፈጸመ፣ በጋራ ቢፈጽሙ የተሻለ ውጤትና የበለጠ የጋራ ተጠቃሚነት ያመጣሉ የሚባሉ ተግባራት ቀጥሎ የሚገኘው አካል እንዲያከናውናቸው ማድረግ ያስችላል፡፡  የራስና የጋራ አስተዳደርን በተለያዩ የፌዴራል ሥርዓቶች ቅርፅ በማደራጀት አካባቢያዊ፣ አገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ ብሎም አኅጉራዊና ዓለማዊ የሆኑ ትስስሮችን በመፍጠር የጋራ ችግሮችን መፍታትና የጋራ ዕድሎችን መጠቀም የሚያስችል ዕሳቤ ነው፡፡

ስለሆነም የአፍሪካ ቀንድም የጋራ ችግሮቹን ለመፍታትና የቀጣናውን ሰፊ የጋራ መልማት ዕድሎች በመጠቀም፣ በቀጣናው ተዓምራዊ ለውጥ ለማምጣትና ለቀጣይ ትውልድ የተሻለ በጋራ ችግሮችን መፍታትና በጋራ ማደግ የሚያስችሉ ቀጣይነት የሚኖራቸው መሠረቶችን ጥሎ ማለፍ የእዚህ ዘመን ትውልድ ግዴታ ሆኖ ይታያል፡፡

እስካሁን በቀጣናው ሴራውም፣ መጠላለፉም፣ መጋጨቱም ተሞክሮ አዋጭ ሆኖ አልተገኘም፡፡ በግል እንደ አገር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከአገር አገር የሚለያዩ አፈጻጸሞች ያሏቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የጋራ የሆኑ ቀጣናዊ ችግሮችን ለመፍታትና የጋራ ዕድገትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቻለበት ሁኔታ አለ ብሎ ለማለት አያስደፍርም፡፡

በመሆኑም አሁን በምንገኝበት ክፍለ ዘመንና ነባራዊ ሁኔታዎች ለውጥ ማደግና የፌዴራሊዝምን ዕሳቤ መሠረት ያደረጉ ተግባራትን በመፈቃቀድ፣ በመተባበር፣ በመከባበር ላይ ተመሥርቶ ለመሥራት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን መፍጠር የግድ ይላል፡፡ ከዚያ ውጪ ያሉ አማራጮች በሙሉ በአንድም ሆነ በሌላ ተሞክረው የፈቱትም ችግር ሆነ ያመጡት የጋራ ልማት ከዚህ ግባ የማይባል መሆኑን መስካሪው የቀጣናው ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በፌዴራሊዝም ጥናት በረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግ መምህርና አሠልጣኝ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው tayehaileyesus3@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles