Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ተገልጋዩን ማኅበረሰብ አስደስተው የማያውቁት የመንግሥት ተቋማት

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ማኅበረሰቡን በእጅጉ በማማረር ስማቸው ተደጋግሞ የሚጠቀስ ሦስት መንግሥታዊ ተቋማት ነበሩ፡፡ አንዱ ቀድም ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ተብሎ የሚጠራውና አሁን ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተባለው ተቋም ነው፡፡ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን አሁን ላይ ኢትዮ ቴሌኮም የሚባለው ሲሆን፣ ሦስተኛው የውኃና ፍሳሽ አገልግሎት በሚል ይታወቅ የነበረው መሥሪያ ቤት ነው፡፡ እነዚህ ሦስት ተቋማት በቀጥታ ከሁሉም ኅብረተሰብ ጋር ከሚገናኙበት አገልግሎታቸው ባሻገር ከመሠረተ ልማት ግንባታዎች ጋር በተያያዘ አንዱ ሲገነባ ሌላው ሲያፈርስ፣ አንዱ ለመገንባት ሲሻ ሌላው ሲከላከል ይፈጥሩ የነበሩትን ውዝግቦች እናስታውስላቸዋለን፡፡ 

ተናበው መሥራት አቅቷቸው ሲፈጠር የነበረውንም ችግር አንዘነጋውም፡፡ ይህ አሁን ላይ ብዙም አንገብጋቢያችን ባይሆንም ከአጠቃላይ አገልግሎት አሰጣጣቸው ጋር በተያያዘ የእነዚህ ተቋማት ተገልጋዮች ዛሬም ድረስ እርካታ የማያገኙባቸው ሆነው ዘልቀዋል፡፡ ከሦስቱ ተቋማት ውስጥ ግን አንዱን ተቋም ለይቶ ማየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ 

ይህም ኢትዮ ቴሌኮም ነው፡፡ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖሪያ ቤቶችና ለመሥሪያ ቤቶች የመስመር ስልክ ማግኘት እጅግ ከባድ የመሆኑን ያህል ዛሬ ለውጥ እያሳየ መምጣቱን ስለማንክድ በአንድ ላይ መጨፍለቅ ትክክል አይሆንም፡፡ በቴሌኮም ዘርፍ የታየው ለውጥ ከሚታሰበውም በላይ ሆኗል፡፡ ዛሬ የመስመር ስልክ እንደ ቀድሞ ደጅ አይጠናበትም፡፡ በራችን ተንኳኩቶ ጭምር ውሰዱ የተባለበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ዘርፉ ከዚህም በላይ አድጎ የቴሌኮም ሥራ ብዙ ትሩፋቶችን ይዞ መጥቷል፡፡ ዘመኗል፡፡ አገልግሎት ለማግኘት በእጅ በእግር የሚባልበት ዘመድ የሚፈለግበትም መሆኑ ቀርቷል፡፡ ጊዜውም ተቀይሮ ሞባይል ስልክ ባሻን ጊዜ የምንወስደው እስከመሆን መድረሰ በቴሌኮም ዘርፍ የሚሰጠውን የአገልግሎት አሰጣጥ በእጅጉ ቀይሮታል፡፡ ዛሬ ላይ ኔትወርክ ችግር ካልሆነ በቀደመው ጊዜ ምሬታችን ልክ የምናማርርበት ብዙም ነገር የለም፡፡ ውኃና ፍሳሽና የኤሌክትሪክ አገልግሎት በተለየ አገልግሎቱ ተሻሽሏል ሊባል ይችላል፡፡ 

በተለይ አዲስ አበባ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚሰሙ ምሬቶች ብዙ ናቸው፡፡ ሌላ ሌላ ነገሩን ትተን ከኃይል አለቃቀቅ ጋር ያለው ችግር ሊፈታ አልቻለም፡ በተለይ አሁን አሁን የኃይል መቆራረጥ ተደጋግሞ መስተዋል ያልተገባ ፈረቃ እየተተገበረ ያለ እስከ መምሰል ደርሷል፡፡ ደንበኞች ባልጠበቁት ሰዓት ኃይል ይቋረጣል፡፡ መብራት የሚጠፋበትና የሚመጣበት ሰዓት ስለማይታወቅ ተገልጋዮችን በእጅጉ ከማመረር በላይ ላልታሰበ ወጪ እየዳረጋቸው ነው፡፡ 

አንዳንድ የከተማው ክፍሎች ላይ ለቀናት የሚጠፋባቸው አጋጣሚዎች ይከሰታሉ፡፡ መምጫውና መሄጃው ያለመታወቁ ደግሞ ጠዋት ላይ ለልጆች ምሳ ዕቃ ለማሰር ካልቻሉ ወላጆች ጨምሮ በኤሌክትሪክ ዕጦት ሳቢያ የሚበለሻሹ ቢዝነሶች ብዙ ናቸው፡፡ ፋብሪካዎች በሥራ ላይ እያሉ መሀል ላይ የሚቋረጠው ኃይል ሊባክን የሚችለውን ሀብት መገመት አያቅተም፡፡ ለፋብሪካዎቹ ዕቃዎች ብልሽት ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም መገመት ይችላል፡፡ አንዳንዶች በአማራጭነት ጄኔሬተር የሚጠቀሙ ቢሆንም ለነዳጅ እየወጡ ያሉት ወጪያቸውን እያናረ አገልግሎታቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ እያደረጋቸው መሆኑንም እየታዘብን ነው፡፡ 

ይህ ሁሉ ሲሆን ኤሌክትሪክ በፈለገው ጊዜ የሚለቅልን፣ ሲያሻው የሚከለክለን የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎቱ ለምን ሲስተጓጎል እንደቻለ እንኳን አይነግረንም፡፡ በዚህ አካባቢ ኃይል ይቋረጣል ብሎ እንደ ደንበኛ ዓይቶን ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ አይጠይቅም፡፡ 

ያልተቆራረጠ አገልግሎት ማቅረብ የማይችል ከሆነ በዚህ ሰዓት በዚህ አካባቢ መብራት ይቋረጣል ብሎ ቀድሞ ማሳወቅ ምን ያዳግታል፡፡ ካልሆነ የኃይል አቅርቦቱን እንደ ቀድሞ በፈረቃ ቢያደርግ ይሻለው ነበር፡፡ 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየሞላው በሳምንት ውስጥ በቋሚነት አንድ ሁለቴ የሚጠፋበት አካባቢ መኖራቸው ግን አገልግሎቱን በአግባቡ ለመስጠት ያለውን ችግር ያሳያል፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ጭራሽ አገልግሎቱ የማይቋረጥባቸው መሆናቸው ደግሞ ጉዳዩን ከብልሹ አሠራር ጋር ብናያይዘው አይፈረድብንም፡፡ በተቋሙ የሚሠሩ ኃላፊዎች ባሉበት አካባቢ መብራት አይጠፋም የሚለው ሀሜት በእርግጥም ስላለመሆኑ እርግጠኛ ስለማንሆን ነው፡፡ 

ስለዚህ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አገልግሎቱን በአግባቡ መስጠት ባልቻለበት ወቅት ለደንበኞቹ ማሳወቅ ያለመቻሉ የቆየ ችግሩ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ድረስ አብሮት መኖሩ ደጋግመን ብንወቅሰው ትክክል ነን፡፡ 

የአዲስ አበባ የውኃ አቅርቦት ጉዳይ ብዙ የሚያነጋግር ነው፡፡ ምናልባትም ከኤሌክትሪክ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከምናነሳው ችግር በላይ እየሆነ መጥቷል፡፡ ችግሩ ከፍቷል፡፡ በሳምንትና በአሥራ አምስት ቀን አንዴ ውኃ የሚለቀቅለት የከተማው ነዋሪ ቁጥሩ ብዙ ነው፡፡ 

የውኃ ፍጆታቸው ከፍተኛ የሆኑ ድርጅቶች ሳይቀሩ ውኃ በጀሪካን ይሸምታሉ፡፡ ለአንድ ጀሪካን ውኃ 25 እና 30 ብር እየተከፈሉ ይጠቀማሉ፡፡ ምናልባትም ለአንድ ቀን ለጀሪካን ውኃ የሚከፍሉት ክፍያ ውኃ ቢኖር ለወር የሚከፍሉት ይሆናል፡፡ 

በመኖሪያ ቤቶች አካባቢም እንዲሁ ችግሩ ገዝፎ እየታየ ነው፡፡ ውኃ የሚገኘው ቀናት ጠብቆ በመሆኑ በእያንዳንዱ ደጃፍ ትልልቅ የውኃ ማጠራቀሚያ ማኖር ግድ ሆኗል፡፡ በተለይ ደግሞ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ውኃ በጠፋ ቁጥር ያለው ችግር የበዛ ነው፡፡ መፀዳጃ ቤቶች የሚፈጥሩትን ሽታ ብቻ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ 

በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ ያለው የውኃ መስመር ዝርጋታ እንደነገሩ መሆን ደግሞ ችግሩን አብሶታል፡፡ ይህም ውኃ በመጣ ቀን እንኳን ሦስትና አራተኛ ፎቅ ላይ ላሉ ነዋሪዎች ውኃው ሳይደርስ የሚቀርበት አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡ ውኃው ወደላይ ለመውጣት ኃይል ስለሌለው በመስመር አዘረጋጉ ምክንያት ውኃ ለማግኘት ችግር እየሆነ ነው፡፡ 

አሳዛኙ ነገር ደግሞ በወር ሁለት ቀን ለተወሰነ ሰዓት ለሚሰጥ አገልግሎት ክፍያ አዘገያችሁ ብሎ ቆጣሪ ለመቁረጥ ሲሯሯጡ ማየት ነው፡፡ 

በአጭሩ የአዲስ አበባ ከተማ የውኃ አቅርቦት ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ከገልግሎት አሰጣጥ ግድፈት ብቻ ሳይሆን የከተማዋን የውኃ ፍላጎት የሚመጥን ውኃ ያለ አይምስልም፡፡ ከዚህ ቀደም መጪውን ጊዜ በማሰብ የከተማዋን የውኃ ፍላጎት እንዲሸፍኑ ተቀርፀው የነበሩ ፕሮጀክቶች ዛሬ ምን ላይ እንዳሉ እንኳን አይታወቅም። አቅርቦቱን የሚያሳድግ አዲስ ነገር እያየን ባለመሆኑ ምናልባት የአዲስ አበባ የውኃ አቅርቦት ጉዳይ ነገ ከዛሬው የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ እየተማረርንበት በሳምንትና በአሥራ አምስት ቀን የሚገኘው የውኃ አቅርቦት ነገ ጨርሶ ሊጠፋ ይችላል፡፡ ስለዚህ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ያለው ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ መጪው ጊዜ ውኃ የበለጠ ተግዳሮት እንዳይሆን በብርቱ ታስቦበት ሊሠራበት ይገባል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት