ኅብረት ኢንሹራንስ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የዓረቦን ገቢውን በ57 በመቶ በማሳደግ በዓመቱ መጨረሻ ላይ 327 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
የኢንሹራንስ ኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ወንድወሰን ተሾመ ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት ኩባንያው በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው ትርፍ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኩባንያው በ2015 የሒሳብ ዓመት ያገኘው 327 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ በ2014 የሒሳብ ዓመት አግኝቶት ከነበረው 181.2 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃጸር በ80 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም አመልክተዋል፡፡
ኩባንያው የካፒታል መጠኑን እያሳደገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የባለአክሲዮኖች የትርፍ ድርሻ ምጣኔ እንደሚቀንስ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም በዓመቱ የተመዘገበው ከፍተኛ ትርፍ የባለአክሲዮኖች የትርፍ ድርሻ መጠን እንዳይቀንስ ማድረጉን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ አቶ ወንድወሰን በሪፖርታቸው እንደጠቀሱትም የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል መጠን በተጠናቃቀው የሒሳብ ዓመት በ68 በመቶ አድጓል። ይህ ቢሆንም በ2014 የሒሳብ ዓመት አንድ አክሲዮን አግኝቶት የነበረው 37.8 በመቶ የትርፍ ድርሻ በ2015 የሒሳብ ዓመት ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየት 48 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
‹‹የአንድ ኩባንያ ካፒታል ሲጨምር በአንድ አክሲዮን የሚገኘው የትርፍ ድርሻ ሊቀንስ እንደሚችል የሚጠበቅ ቢሆንም ኩባንያችን የዓመቱ ትርፍ ግን በተቃራኒው ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግቧል፤›› በማለት የተገኘው ውጤት አስደሳች ስለመሆኑ አመልክተዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው ከፍተኛ ትርፍ የተገኘው ከመደበኛው የኢንሸራንስ ሥራ ዘርፍ (Underwriting Profit) መሆኑ በጥንካሬ የሚታይ ነው ሲሉ የኅብረት ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ መሠረት በዛብህ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ኅብረት ኢንሹራንስ በተናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከዋናው የኢንሹራንስ ሥራ ዘርፍ ያገኘው ያልተጣራ ትርፍ 471.7 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የጠቀሱት ወ/ሮ መሠረት፣ ይህ በቀዳሚው ዓመት ከተገኘው ትርፍ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በ2014 ኩባንያቸው ከዋናው የኢንሹራንስ ሥራ ዘርፍ ያገኘው ያልተጣራ ትርፍ 226.24 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የገለጹት ወ/ሮ መሠረት በ2015 የሒሳብ ዓመት የተገኘው ገቢ ከእጥፍ በላይ ብልጫ ያለው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ኩባንያው ከኢንቨስትመንት ካገኘው ገቢ ሌላ በኢንሹራንስ ሥራው ብቻ ውጤታማ መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ኩባንያው ከተሰማራባቸው ከኢንሸራንስ ዘርፍ ውጢ ከሆኑ ኢንቨስትመንቶቹ 255.5 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱ ተገልጿል፡፡
ይህ የኢንቨስትመንት ገቢ ከቀዳሚው ዓመት በ47 በመቶ ዕድገት ያሳየ ሲሆን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ገቢው በመሆን የተመዘገበው ደግሞ በጊዜ ገደብ በባንክ ከተቀመጠ ገንዘብ፣ ከኅብረት ባንክና ከኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ የትርፍ ድርሻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኩባንያው በሐበሻ ሲሚንቶ ላይ ካለው ኢንቨስትመንት ድርሻ ምንም ትርፍ አለማግኘቱ ተጠቅሷል፡፡
ኅብረት ኢንሹራንስ በተናቀቀው የሒሳብ ዓመት በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የዓረቦን ገቢውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ስለመቻሉ በተገለጸበት የዘንድሮ አፈጻጸሙ በሁለቱም የኢንሹራን ዘርፎች ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግቤያለሁ ብሏል፡፡ ኅብረት ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ ከሁሉም የመድን ዘርፎች ያሰባሰበው አጠቃላይ የዓረቦን ገቢም 1.5 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ የዓረቦን ገቢ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከተገኘው 953.9 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ58 በመቶ ዕድገት ያሳየ ሆኗል፡፡ ኩባንያቸው ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የዓረቦን ገቢ ያገኘበት ዓመት መሆኑንም የቦርድ ሊቀመንበሩ ጠቅሰዋል፡፡
ዓመታዊ የዓረቦን ገቢውን በተመለከተ በተሰጠ ተጨማሪ ማብራሪያም በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ኩባንያው ሕይወት ነክ ካልሆነው የመድን ዘርፍ 1.35 ቢሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ የሰበሰበ ሲሆን ይህ ገቢው በቀዳሚው ዓመት አግኝቶት ከነበረው 860.8 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ57 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበበት ነው ተብሏል፡፡ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ለተገኘው ከፍተኛ ዕድገት የሞተር ኢንሹራንስ የሽፋን ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ለዚህም በሒሳብ ዓመቱ ከኅዳር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገው የዓረቦን ተመን ጭማሪ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት 77 በመቶ ዕድገት ሊያስመዘግብ ችሏል፡፡ በሌሎች የመድን ሽፋኖችም ከፍተኛ ዕድገት የተመዘገበ ሲሆን፣ በተለይ በሕጋዊ ኃላፊነት ኢንሹራንስ ሽፋን የ76 በመቶ የዓረቦን ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ ከዚህም ሌላ በእሳትና በድንገተኛ አደጋና በአቪዬሽን የመድን ሽፋን ደግሞ የ37 በመቶ፣ ዕድገት ስለመመዝገቡ በቀረበው ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል፡፡ ከሌሎች የመድን ሽፋኖች አነስተኛ የዓረቦን ገቢ ዕድገት የታየው በማሪን ኢንሹራንስ ነው፡፡ የዚህ ዘርፍ የዓረቦን ገቢ ዕድገት የስድስት በመቶ ብቻ መሆኑ ታውቋል፡፡
የማሪን ኢንሹራንስ የዕድገት ምጣኔ ከሌሎች ተለይቶ አነስተኛ የሆነበት ዋናው ምክንያት የመድን ሽፋኑ ዓይነት በቀጥታ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን የማሪን የመድን ሽፋን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደሩ እንደሆነ ወ/ሮ መሠረት በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
ሌሎች ምክንያቶች ቢኖሩም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የማሪን ኢንሹራንስ በአዝጋሚ በሆነ ጉዞው ሊቀጥል እንደሚችልም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
በሒሳብ ዓመቱ ኩባንያው ለካሳ ካዋለው ገንዘብ ውስጥ ከፍተኛ ወጪ ያወጣው ለተሽከርካሪ አደጋ ጉዳት መሆኑ ታውቋል፡፡ ከተከፈለው አጠቃላይ የጉዳት ካሳ ውስጥም የሞተር ኢንሹራንስ 61 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል፡፡
በሕይወት የመድን ሽፋን ዘርፍም ኩባንየው ያገኘው የዓረቦን ገቢ በ65 በመቶ ማደጉን አመልክቷል፡፡ በዚህ ዘርፍ የተገኘው የዓረቦን ገቢ 153.9 ሚሊዮን ብር ሲሆን ይህ ገቢ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ጭማሪ ማሳየት ችሏል፡፡
ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ለካሳ ክፍያ ያዋለው የገንዘብ መጠን 33 በመቶ ማደጉ ታውቋል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የሕይወት ነክ ባልሆነው እና በሕይወት ነክ የመድን ዘርፎች ለካሣ ክፍያ ወጪ ያደረገው 463.54 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ኩባንያው ለካሳ ካዋለው ገንዘብ ውስጥ ከፍተኛ ወጪ ያወጣው ለተሽከርካሪ አደጋ ጉዳት መሬት ታውቋል፡፡ ከተከፈለው አጠቃላይ የጉዳት ካሳ ውስጥም የሞተር ኢንሹራንስ 61 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል፡፡
ይህም በዋነኝነት እያደገ ከመጣው የኩባንያው የዓረቦን ገቢ፣ ከተሸከርካሪ አደጋ መብዛትና አጠቃላይ የዕቃዎች ከፍተኛ የገበያ ዋጋ ጭማሪ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ይሁንና በ2015 የሒሳብ ዓመት ኅብረት ኢንሹራንስ አጠቃላይ የከፈለው የካሳ ክፍያ ምጣኔ (Loss Ratio) በ2014 የሒሳብ ዓመት ከነበረው 61 በመቶ ጋር ሲነፃፀር በ23 በመቶ ቅናሽ በማሳየት 47 በመቶ ሆኖ መመዝገቡንም የቦርድ ሊቀመንበሩ ጠቅሰዋል፡፡ ይህም በአጠቃላይ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ከተመዘገበው የ59 በመቶ አማካይ የካሳ ክፍያ ምጣኔ ጋር ሲነፃፀርም የተሻለ ሆኖ የሚገኝ ነው ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለይ ነባር በሆኑት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሪፖርት ላይ እየተጠቀሰ እንደሚገኘው የገቢዎች ሚኒስቴር የትርፍ ግብር እንዲከፍሉ የተጠየቁትን ጥያቄ ጠቅላላ ጉባዔው እንዲየውቀው ተደርጓል፡፡ ገቢዎች ሚኒስቴር ከ2011 እስከ 2014 ዓ.ም. ድረስ ለካፒታል እድገት በዋለ የትርፍ ድርሻ ላይ ግብር ሊከፈል ይገባ ነበር በሚል ግብሩን እንዲከፈል ውሳኔ ያሳለፈ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ወንድወሰን ኩባንያው በዚህ ውሳኔ ላይ ይግባኝ አቅርቦ ጉዳዩ በሕግ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም በመሆኑ በሕግ የተያዘው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ኩባንያው መጠባበቂያ ገንዘብ እንዲቀመጥ ውሳኔ ማሳለፍ መቻሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህም መጠባበቂያ ገንዘብ ከአዲስ አክሲዮኖች ሽያጭ የተገኘው ከ21.8 ማሊዮን ብር ፕሪሚየም በመጠባበቂያነት እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡
21.8 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ፕሪሚየም የተሰበሰበው ኩባንያው በ2014 የሒሳብ ዓመት ጠቅላላ ኩባዔው ላይ ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ላላቸው አዳዲስ ባለአክሲዮኖች የአክሲዮን ሽያጭ ላይ ነው፡፡
ኩባንያው ካፒታል ከ500 ሺሕ ብር ወደ ብር 1.5 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት እያደረገ ባለው የአክሲዮን ሽያጭ እስከ 2015 መጨረሻ ድረስ የተከፈለ ካፒታሉን 840.59 ሚሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ68 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ያመለክታል፡፡ ኅብረት ኢንሹራንስ አጠቃላይ የባለአክሲዮኖቹ ቁጥር የኩባንያችን ጠቅላላ 704 ደርሷል፡፡ ኅብረት ኢንሺራንስ በአሁኑ ጊዜ ያሉት ሠራተኞች ቁጥር 493 ሲሆን ቅርንጫፎቹንም ወደ 61 ማሳደግ ችሏል፡፡