Wednesday, December 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብርሃን ባንክ አቶ ኤርሚያስ ተፈራን በዕጩ ፕሬዚዳንትነት ሰይሞ ሹመቱ እንዲጸድቅለት ጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብርሃን ባንክን በፕሬዚዳንትነት ለአንድ ዓመት ተኩል የመሩት አቶ ግሩም ፀጋዬ በፈቃዳቸው ከኃላፊነት መልቀቃቸውን ተከትሎ የባንኩ ቦርድ በምትካቸው አዲስ ፕሬዚዳንት በማጨት ሹመቱ እንዲጸድቅለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማመልከቱ ተጠቆመ፡፡ 

የብርሃን ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የአቶ ግሩምን የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ ከተቀበለ በኋላ በምትካቸው ቀደም ሲል የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩትን ኤርሚያስ ተፈራ በፕሬዚዳንትነት በማጨት ብሔራዊ ባንክ እንዲያጸድቅለት ጠይቋል። አቶ ኤርሚያስ ከሁለት ዓመት በፊት በግል ምክንያት ከሥራቸው ተገልለው ቆይተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ የአቶ ግሩምን መልቀቂያ ጥያቄ ላይ ከተወያየ በኋላ ያቀረቡትን መልቀቂያ የተቀበለው ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ነበር፡፡ ከዚሁ ውሳኔው ጎን ለጎን ባንኩን በቋሚነት በፕሬዚዳንትነት የሚመራ እስኪሰየም ድረስ በአገልግሎት ላይ የሚገኙት የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አሰፋን በተጠባባቂ ፕሬዚዳንትነት መድቧል።

የብርሃን ባንክ ቦርድም ሆነ እራሻቸው አቶ ግሩም ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ የወሰኑት በፍላጎታቸው መሆኑን አሳውቀዋል።

አቶ ግሩም የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲያገለግሉ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ካጫቸው በኋላ ሹመቱ እንዲፀድቅ በቀረበው ጥያቄ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሹመታቸውን አፅድቆላቸው ሥራ የጀመሩት የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ነበር፡፡ 

አቶ ግሩም በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ29 ዓመታት በላይ ያገለገሉ ሲሆን በተለይ ከዘጠኝ ዓመታት በላይ የኅብረት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ማገልገላቸው ይጠቀሳል፡፡ ከዚህም ሌላ የኢትዮ ሊዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን አገልግለዋል።

ባንኩ በዕጩ ፕሬዚዳንትነት ያቀረባቸው አቶ ኤርሚያስ ተፈራም በተመሳሳይ በአገሪቱ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም ማካከል በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በእናት ባንክ በተለያዩ ኃላፊነቶች ማገልገላቸው ይጠቀሳል፡፡ 

ብርሃን ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ26.03 ቢሊዮን ብር ወደ 33.78 ቢሊዮን ብር ያደረሰ ሲሆን፣ ዓመታዊ የብድር መጠኑንም በ30 በመቶ ማደጉን የባንኩ የ2015 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ይጠቁማል። በዚህም መሠረት ባንኩ እስከ 2015 ሒሳብ ዓመት መጨረሻ ድረስ ያቀረበው ብድር ክምችት 27.3 ቢሊዮን ብር ሆኖ ተመዝግቧል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች