Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትከብሔር ፖለቲካ እስረኝነት ለመገላገል መዘጋጀት እንደምን?

ከብሔር ፖለቲካ እስረኝነት ለመገላገል መዘጋጀት እንደምን?

ቀን:

(ክፍል ሦስት)

በበቀለ ሹሜ

እስካሁን የተነጋገርነው ድክመትን በርብርብ በማካካስና ሰፊ የጥፋት ተጋሪነታችንን በማስተዋል፣ በቅርብ እውነታችን ላይ ልናመጣው በምንችለው መሻሻል ላይ ነው፡፡ ትግላችን ግን ገና ረዥም ነው፡፡ በዝቅጠት ራሱን ያቆሰለውና እኛንም እንደ ኅብረተሰብ ያቆሳሰለን ብሔርተኝነት፣ በአንዴ እንትፍ ውልቅ የሚል ቀላል ችግር አይደለም፡፡ ብሔርተኝነት በረዥም ዓመታት ውስጥ እንደሰረፀብን ሁሉ የመላቀቅ ሕክምናውም በደንብ የነቃና በረዥሙ የታቀደ ትግል ይጠይቃል፡፡

1) ግለሰቦች ራቁታችንን አናድግም፣ አንኖርም፡፡ ከፅንሰት ጀምሮ የምንኖረው በማኅበራዊ ቡልኮዎች ውስጥ ነው፡፡ በሰዎች፣ በቋንቋ፣ በአስተሳሰብ፣ በባህል፣ በድርጊት መስተጋብር ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡ ለኑሮ ቡልኳችን ልናዋጣው የምንችለው ነገር እንዳለ ሁሉ ፈርጀ ብዙ በሆነው ማኅበራዊ ቡልኳችንም ዕለት በዕለት እንኮተኮታለን፡፡ ዛሬም ነገም የሚራቡ ተመሳሳይ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ፣ ኢምንት በኢምንት የሚቀየሩም አሉ፡፡ ፊት ያልነበሩ አዳዲስ ነገሮችም ነባራዊና ህሊናዊ ሀብቶቻችን ውስጥ ይታከላሉ፡፡ እየተደጋገመ በሚራባ ተመሳሳይነት ውስጥ ልዩነቶችና ለውጦችም ይጠራቀማሉ፣ ጥርቅማቸው በጊዜያት ውስጥ ተበራክቶ የአጠቃላዩ ሁለመናዊ ገጽታ የመሆን እመርታን እስከ መደገስም ሊረዝም ይችላል፡፡

ብሔርተኝነት የፖለቲካ ትግል ሆኖ በይፋና በሥውር እየቀሰቀሰ አዕምሮን ለማሟሸት ሠርቷል፡፡ ከትግልነትም ተሻግሮ ሥልጣን በመያዝና መዋቅር በመሥራት በኢትዮጵያ ሕዝቦች ኑሮ ውስጥ ቡልኳዊ ሚና ይዞ ቆይቷል፡፡ ይህንን ጊዜ በጥቅሉ ብናስበው 50 ዓመታት ያህል ነው፡፡ ብሔርተኝነት ሥልጣን ይዞ መኗኗሪያ በመሆን እውነታ ውስጥ፣ የመደበኛና የኢመደበኛ ትምህርት አተያይ ሆኖ ሁለት ትውልድን አጥቧል፡፡ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ያገኘውን ወጣት በውድም በግድም እየቦረቦረ ብሔርተኛ ሙሽት የማስያዝ ሥራ ሠርቷል፡፡ በብሔርተኛ ቡልኮ ውስጥ የተወለዱ አዲስ ልጆችንም ሰብዕና ልሷል፣ ሌሎች ተቀናቃኝ አስተሳሰቦችን እየተናነቀ፡፡

ይህ ሰብዕናን እስከ መቅረፅ የጠለቀ ሥርፀቱ (ዛሬ በፖለቲካ በከሰረበትና በዘቀጠበት ደረጃ ላይም ሆኖ) ‹‹በቃኸኝ ዘወር በል›› በማለት ብቻ የማንገላገላው ችግራችን እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ‹‹በቃኸኝ›› ባለው ህሊና ውስጥ ተሸሽጎና አሸልቦ ለመኖር ያስችለዋል፡፡ ከላይ ‹‹ብሔርተኛ አይደለሁም›› በሚልና ብሔርተኝነትን ‹‹በሚታገል›› አቋም ውስጥ ተደብቆ እንዲሠራ ያስችለዋል፡፡ ብሔርተኝነትን ‹‹እስካሁን ያቆሳሰልከን ይበቃናልና በቃኸን›› ስንልም፣ ጊዜ በወሰደና በሰላ የማመናመን ሥራ፣ ሥር የያዘ ሥርፀቱን የመነቃቀልና እንዳያገረሽ በሌላ ሥርፀት የመተካት ከባድ ሥራን እንደሚጠይቀን ማወቅ ይኖርብናል፡፡

ይህ ከባድ ሥራ ከፋፋዮችን እያዝረከረከ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን በሁሉም ፈርጅ በሚያግባባና ዝምድናን በሚያጠናክር የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል መስተጋብርና ግስጋሴ ውስጥ የማስገባት ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ባለው ጎልማሳና ወጣት ኅብረተሰባችን ውስጥ ብሔርተኝነት የፈጠረውን አሉታዊ ሙሽት እየናዱ በአዎንታዊ ሙሽት የመተካት ትግልን የሚጠይቅ ነው፡፡ የዛሬና የነገ ሕፃናትን ከብሔርተኝነት ጠብቆ የማነፅ ጉዳይ ነው፡፡ ህሊናን ሲያባትቱ የኖሩ (ከፋፋይ ብሔርተኝነት እንዲያገረሽ ለማድረግ የሚጠቅሙ) አሮጌ ሐሳዊ ትርክቶችን፣ ምክንያታዊነትና የታሪክ ምርምር የማይነካቸውን ጭፍን ግንዛቤዎችንና ወደ ሰማይ ለማድረግ ትንሽ የቀራቸውን ውዳሴዎች በብልኃት አበጥሮ የማራገፍና በአዲሱ ትውልድ ሁለንተና ላይ የመጠበብ ጉዳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ በብሔርተኝነትም ዘንድ በኢትዮጵያዊነትም ዘንድ ያሉ የጦዙና በሐሰት የተሞሉ ግንዛቤዎችን ከማራገፍ ጋር፣ ዕውናዊ እሴቶቻችንንና ቅርሶቻችንን ኩልል እያደረጉ የማደራጀትና የኅብረተሰባችን ንቃተ ህሊና እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ነው፡፡

‹‹‹ኢትዮጵያዊ› የሚባል እሴት ለመሆኑ አለ ወይ?›› የሚል ጥያቄያዊ ሙግት ከፋፋዮች ሲያነሱባቸው ብዙ ሰዎች መልስ ይቸግራቸዋል፡፡ ይህ በአግባቡ በተካሄደ ጥናት ሀብትን የማደራጀትና ለኅብረተሰብ የማቅረብ ሥራ ባለመሠራቱ የሚመጣ ችግር (የዕውቀት ድህነት) ነው፡፡ ይህንን ድህነት ለማሰናበት ከባድ አይደለም፡፡ ሠለጠኑ በሚባሉ አገሮች ያሉና ለእኛ እንግዳ የሆኑ ‹‹ሥልጣኔዎችን›› ማነፃፀሪያ አድርገን ራሳችንን ለመመልከት ብንሞክር እንኳ የራሳችንን ማወቅ ይቻለናል፡፡ ለምሳሌ ፈረንጆቹ ዘንድ በግለሰብ ደረጃ ዘመድንና ወላጅን የመርዳት ኃላፊነት ፈራርሷል፣ በኢትዮጵያስ ይህ ኃላፊነት ሁላችንም ዘንድ መኖሩ ይካዳል? ፈረንጆቹ ጋ ታላቅነታዊ ተደማጭነት/ተከባሪነት በማይኖርበት አኳኋን ሽማግሌና ወጣት ጓደኛ ይሆናሉ፡፡ እኛ ጋ ይህ አለ? የዚህ ዓይነት ሥልት በንፅፅር ራሳችንን ለማወቅ ቢያግዘንም፣ ዋናው ራስን የማወቅ ሥራ የሚከናወነው ግን ኅብረተሰባችን ውስጥ ከቦታ ቦታ ከማኅበረሰብ ማኅበረሰብ ያሉ ባህሎችንና የኑሮ ዘይቤዎችን በአግባቡ እያጠኑ መረጃዎችንና የኋላ ታሪኮችን አደራጅቶ በማገናዘብ ነው፡፡ በዚህ የማገናዘብ ሥራ ውስጥ በዘመናት ውስጥ የተወራረስነውን ያህል የጋራችን የሆኑትንና ያልተወራረስነውን ያህል የየብቻ የሆኑትን፣ (በሁለቱ ጥጎች መሀል የጋራ የመሆን ጉዞ ውስጥ የሆኑትንና ከግማሽ መንገድ በላይ የተጋራናቸውን) እየለዩ የማደራጀት ተግባር ይመጣል፡፡ በዚህ መልክ የተደራጀ መረጃ ደግሞ ከአንዳችን ወደ ሌላችን ቢወራረሱ የበለጠ ትስስራችንንና የኑሮ ክህሎታችንን ይበጃሉ የሚባሉትን ለይቶ ለማስፋፋት ስንቅ ያስገኛል፡፡

ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን በድፍናቸው ከሰው ሰው ተወራርሰው የየእያንዳንዳችን መተዳዳሪያ ሊሆኑ የሚችሉ አይደሉም፡፡ መወራረስን ማገድ ባይቻልም በየፊናቸው መጠበቅን የሚሹም አሉባቸው፣ ለምሳሌ እምነት ነክ፡፡ ይህ ልዩነት ግን ኢትዮጵያዊ ሀብት (ቅርስና እሴት) ከመሆን አያግዳቸውም፡፡ የሁላችን የተግባር መጠቀሚያ ማድረግ ሳያሻን የአገር ልጆች ሀብት መሆናቸው በራሱ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ሀብት ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ የጋራችን ስሜት ከግለሰባዊ ፈቃደኝነት አልፎ ማኅበራዊ ‹ደመ ነፍስ› እስከመሆን የሚዘልቅ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ወጣ ባልንበት ሁኔታ፣ ቋንቋቸውንና ኑሯቸውን በውል የማናውቃቸውን የአገራችን ማኅበረሰቦችን የሕይወት ቁራሽ በተንቀሳቃሽ ምሥል ለማየት ዕድል ሲገጥመን በግብታዊነት ስሜታችን የሚተራመሰውና በናፍቆት የሚሞላው ለዚህ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የመወራረሱ ተግባር የሚካሄደውና ያልወረስነውን ባህልና ቋንቋ የእኛ ያለ መውደድ ነፍሳችን ውስጥ የሚገባው፣ በታቀደ መርሐ ግብር ብቻ አይደለም፡፡ የኅብረተሰብ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስተጋብራችንና የትስስራችን መጨመርም ይህንን ሥራ በግብታዊነት ያካሂደዋል፡፡

2) እነዚህን ነገሮች ዛሬ ያለው መንግሥት በወጉ አጢኗቸዋል፡፡ በወጣቶች ላይና በሕፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ የአዲስ ትውልድ አዲስ ሙሽት ላይ አቅዶ እየሠራ መሆኑና በሁለገብ ልማትና ኢትዮጵያን በአግባቡ በሚያንፀባርቅ ትርክት ህሊናን ለማያያዝ የሚያካሂደው እንቅስቃሴ የዚህ ምስክር ነው፡፡ ይህ በነባራዊና በህሊናዊ ሕይወታችን ላይ እየተሠራ ያለው ልማት፣ ከፋፋይ ብሔርተኝነትን ለዘለቄታው ለማሰናበት አንድ ሁነኛ የጉልበት ምንጫችን ነው፡፡

በውስጥም፣ በአኅጉራችንም፣ በዓለማችንም ላይ ያለ ልምድም ሌላ ጉልበታችን የሆነበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ ዓለማችን ዛሬ ትጥቅ፣ ትግልና ጦርነት የሚባል ነገርን ፋይዳ ቢስ ኪሳራ እያደረገው ነው፡፡ በዩክሬንና በሩሲያ መሀል የሚካሄደው ረድፍ የያዘ ጦርነት ሁለቱንም አገሮችና ዓለምን እንደሚጎዳና እየጎዳ እንዳለ ታሪክ በሽንቆጣ እየነገረችን ነው፡፡ ከዕለት ወደ ዕለት ከሚሰነዘር ሽንቆጣዋ ባሻገር የሚጠራቀም ቅጣትም ታሪክ አላት፡፡ የሳውዲ ዓረቢያ፣ የኢራንና የግብፅ ወደ ብሪክስ ማዘንበል ለፍልስጤማውያን ትግል ትኩስ ብርታት ይሆናል መስሎት (ምናልባትም ዓረቦችን ለመከፋፈል ባቀደ ወጥመድ ተጠምዶ)፣ ሐማስ ከሰሞኑ የከፈተውን ጥቃት ታሪክ ለእስራኤል መንግሥት የጠላት ወዳጅ በመሆን ሚና ተርጉማበታለች፡፡ ይህ ትርጓሜዋ የጀመረው ዛሬ አይደለም፣ ውሎ አድሯል፡፡ የፍልስጤም ሕዝብ ጥቅምን፣ ተሰሚነትና ትሩፋት ወደፊት ያራምዳል ወይ በሚል ሚዛን የማይለካ የትግል ሥልቱ፣ በእስራኤል ፓርቲዎች ዘንድ የነበረውን የአቋም መራራቅ እንዲጠብ ረድቷል፡፡ ለፍልስጤማውያን ፍትሐዊ የመሆን ዕይታ በእሥራኤል ይሁዲዎች ዘንድ ኮስሶ የሌለ ያህል እንዲሆን አድርጓል፡፡ የእሥራኤል ፖለቲካና መንግሥት በአንድ የፖለቲካ መስመር ቁጥጥር ውስጥ እንዲወድቅ ረድቷል፡፡ የፍልስጤሞች ትግል ማለቂያ የሌለው፣ የመፍትሔና የዓለምን ልቦናን የመቆጥቆጥርምጃ የማያሳይ፣ እንዲያውም ጆሮ ያታከተና ተቆርቋሪነትን ያዛለ ጉዳይ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ‹የሁለት አገረ መንግሥት መፍትሔ›ን የተዘነጋ ጉዳይ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ከእናካቴውም የፍልስጤሞች ይዞታና ሕይወት ከድጡ ወደ ማጡ እንዲወርድ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በአሁኑም ግጭት ለፍልስጤሞች ያሳቀፋቸው የስቅየትና የውድመት ሀብት ነው፡፡ በዚህ ግፍና ውድመት ውስጥም ‹‹እስራኤል ራሷን መከላከል መብቷ ነው›› የሚል አቋም መያዝ ታላቋን አሜሪካን አላሳፈራትም፡፡ ስለዕርዳታ ከማውራት ውጪ ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ከመወትወት ይበልጥ፣ ‹‹ሐማስ መጥፋት አለበት›› የሚል አቋምና ወታደራዊ ዕገዛ መስጠት በለጠባት፡፡ እዚህም ላይ ታሪክ እየተናገረች ነው፡፡ ኃያላን ለሰው ልጅ የተቆርቋሪነት ልብሳቸው ምን ያህል እንደነተበና በንትበቱ ውስጥ ያፈጠጠ አካላታቸው ምን ያህል እንደሚኮሰኩስም ታሪክ እያጋለጠች ነው፣ እያጋለጠችም ግዙፎችን ማቅለል ከጀመረች ውላ አድራለች፡፡

ታሪክ መልዕክቷ ቢገባንም ባይገባንም አልሰሙኝም አልገባኋቸውም ብላ ዝም አትልም፡፡ ከእሷ ጋር መሳመርን እስካላወቅንበት ድረስ በዓለማችንም በቤታችንም መሳለቋና ግርፊያዋ አይቀርም፡፡ ሾጥ በማድረግና ድብን አድርጎ እስከ መለምዘግና እዬዬ እስከማሰኘት ትከፋለች፡፡ ይህ አባባል ቅጣቷን ገር በሆነ መልክ የሚገልጽ ነው፡፡ ከመራር ቅጣቷ ለመትረፍ ከእኛ የሚፈለገው የቅጣት ቋንቋዋን አውቆ ማዳመጥ/ማንበብና ችግሮችን በሁለንተና ፈርጃቸው ተረድቶ መፍትሔ መፈለግ ነው፡፡ በሳህል አገሮች ግድም የፈረንሣይን ከቅኝ ገዥነት ተያይዞ የመጣ ናዛዥነት የመገላገል ትግል፣ ከወታደራዊ ግልበጣ ጋር የተጎዳኘው ችግሮችን በሁለንተና ፈርጆቻቸው ተረድቶ ለመፍትሔ የሚንቀሳቀስ ሕዝባዊ ትግል በመጉደሉ ነው፡፡ ይህ ሲጎድል የማይዳበሉ ነገሮች ሊዳበሉ፣ የትግሉ ሁለ ነገርም ከመንፈራፈር ላይርቅ ይችላል፡፡ በዚሁ ምክንያት ጥቂት የማይባሉ አገሮች በዓለማችንም በአፍሪካም እየተንፈራፈሩ ነው፡፡ ጎረቤታችን ሱዳንም ከመንፈራፈር ማለፍ አልቻለችም፡፡ ሱዳን የምዕራባዊ ሕዝቧን የፍትሐዊነት ሮሮና ትግል በድቆሳ አቃልላለሁ ብላ፣ ከጦር ኃይሏ ውጪ በሚሊሻነት የጀመረ መቺ ኃይል ስታሰናዳና ስታጎለብት፣ በግፍ የጎደፈ የታጠቀ ኃይልና አጠቃላይ የግፍ ነውሯ፣ ነገ ተጠያቂ ላለመሆን ሱዳንን ከማላመጥ እንደማይመለስ አልታያትም ነበር፡፡ ዛሬ ካርቱምን ጦር ሜዳ ያደረገው የሁለት ወገን ውጊያ የዚያ ውጤት ነው፡፡ ታሪክ ይህንኑ ይዛ ለእኛም ‹‹ከሱዳን ግርፋት ተማሩ፣ የመከላከያ ሠራዊታችሁን ሕዝባዊነት በደንብ ተንከባከቡ›› የሚል ማሳሰቢያ እየሰጠችን ነው፡፡

3) ከቤታችን ደግሞ የ2015 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል የፈተና ውጤትን እንውሰድ፡፡ ተፈታኞች 96 በመቶ ገደማ ማለፊያ ያላመጡበትን ውጤት በተመለከተ ‹‹በገልተኛ አካል ይጠናና ተጠያቂው ይታወቅ›› ብሎ ማለትንም ሆነ ውጤቱን ከ‹‹ፖለቲካ ጥገኛነት›› ጋር ማያያዝንና ‹‹እንደገና ፈተና ይሰጥ›› የሚል ሐሳብን ላላ በሉ፣ ፈተናው ቀለል ይበል/ኩረጃንም በአንዴ መድረሻ አታሳጡት ችግሩ የተጠራቀመ ነውና  እንደማለት አድርጎ መተርጎም ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ትምህርት ላይ የደረሰው ጉዳት በፖለቲካ ሩኅሩኅነት የሚፈታ አለመሆኑን አለመረዳት፣ ወይም እንደ ነገሩ ተረድቶ ችግሩን ጊዜያዊ ድጋፍ ለማፈስ መነገጃ ማድረግ፣ ሁለቱም የፖለቲካ ድህነት መገለጫዎች ናቸው፡፡ የፈተና ውጤቱን ከፖለቲካ ደባ ጋር አያይዞ የመረዳት ችግር የአንድ ፓርቲና የአንዳንድ ግለሰቦች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የብዙ ፖለቲከኞችንም አስተሳሰብ የሚያንፀባርቅ ነውና ስለፖለቲካችን ድህነት ሌላ ምስክር ነው፡፡ የተሰጠው ፈተና ደረጃውና ሥልቱ ሳይለወጥ መልስ ለማባዛትና ለኩረጃ ያለው ዕድል በመዘጋቱ ብቻ፣ ውጤቱ ጠቅላላ የመውደቅ ያህል መሆኑ የሚነግረን ችግራችን ምን ያህል የከፋ (ወዳቂ በመቀነስ የማይስተካከል) እንደሆነ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ትምህርት ውስጥ የደረሰውን ስብራት በደንብ ያጠና የፖለቲካ ሰው፣ ውጤቱ የሚናገረውን መልዕክት ማንበብ አይቸግረውም፡፡ ኢሠፓአኮ/ኢሠፓ ከተመሠረተበት አካባቢ አንስቶ በሕወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን ውስጥ በትምህርት ላይ የደረሰው ልሽቀት ሳያስተምሩ ገፍቶ ማሳለፍን፣ መኮራረጅን፣ በአስፈታኝነትና በፈታኝነት መኮራረጅን ማገዝን፣ ሐሰተኛ ምስክር ወረቀት እየገዙ ሳይማሩ ‹‹አዋቂ/ባለሙያ›› መሆንን፣ ወይም ያልደረሱበት የትምህርት ደረጃ ላይ በአቋራጭ መግባትን ‹‹እሴቶቻችን›› የሆኑ እስኪመስሉ ድረስ ሥር እንዲይዙ ያደረገ ነበር፡፡ በዚህ ጥፋት ውስጥ ከአፍንጫ ርቆ ማሰብ የሚቸግረው (ልሽቀትን መጠቃቀሚያ እስከ ማድረግ የዞረበት) ብሔርተኛ ወገንተኝነትና ደንታ ቢስነት ትልቁን ጥፋት ፈጽሟል፡፡ የፈተናው ውጤት ይህንን ጉዳችንን ነው ያወጀልን፡፡ ይህ አዋጅ በሌላ መልኩ ይህንን የዝቅጠት ገመናችሁን ከሥሩ ለመንቀል ተረባረቡ የሚልም ጥሪ ነው፡፡ ጥሪው አሁን በየክፍል ደረጃዎች ውስጥ ያሉ ተማሪዎቻችን ዘንድ ያሉ ከደረጃዎች በታች የሆኑ የዕውቀት ክፍተቶችን መርማሪ በሆነ ፈተና እየለየን በትምህርት ቤት ውስጥና ከትምህርት ቤት ውጪ በተማሪዎች የእርስ በርስ መማማርና በአስተማሪዎች ዕገዛ የሚሟላበትን ሥልት እንድናስብ፣ የተማሪዎችን የአጠናን ዘዴ ለማትባትም እንድንሠራ የሚጎተጉትም ነው፡፡

ወጣቶቻችንና ታዳጊዎቻችን ላይ የደረሰውና እየደረሰ ያለው ጉዳት፣ በቀለም ትምህርት ላይ የአጭር ጊዜና የረዥም ጊዜ መርሐ ግብር ቀይሶ ለውጥ ለማምጣት በመሥራት ብቻ የሚፈታ አይደለም፡፡ ፈረንጅ የያዘውን ሁሉ ከሥልጣኔ ቆጥሮ በመቅዳት ድክመት በኩል እየገቡ ወጣቶቻችንን የሚያበልዙ/የሚያሰናክሉ የሱስና የልሽቀት ችግሮች እንደ ቀላል የሚታለፉ አይደሉም፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ውስጥ ለውስጥ እየፈጠነ ያለው የተመሳሳይ ፆታ ወሲብን ሞክሮ የማወቅ (ኤክስፐርመንት የማድረግ አምሮት) ነው፡፡

ፈጣሪን ምርኩዝ አድርጎ ለማውራት አይመችምና አካሄዴን ቀይሬ ስለተፈጥሮ ላውራ፡፡ ተፈጥሮ ሕግና ሥርዓት አላትና በአያሌው እናምናታለን፡፡ ትናንትና እንደሆነው ዛሬም ነገም ዕፅዋት ምግባቸውን ለመሥራት የፀሐይ ብርሃን ይሻሉ፡፡ በአንድ ወንዴ አባላዘር የዳበረ ሴቴ (ዕንቁላል) ሁለት ቦታ የተፈነከተ የፅንስ ዕድገት ውስጥ ሲገባ አምሳያ ልጆች እንደሚሰጥ፣ ከትናንትናና ከዛሬ ልምድ ተነስተን ነገም ከነገ ወዲያም እንደሚፈጸም እንተማመናለን፡፡ ነገር ግን በተፈጥሮ የምናገኘውና የሚሆነው በጥቅል እውነትነት የምናውቀው ነገር ብቻ አይደለም፡፡ ከፍተኛ ሙቀት ባለበትና በጨለመ የውቅያኖስ አዘቅት ውስጥ የሚኖሩ ‹‹ተክሎች›› አሉ፡፡ ተፈጥሮ ሕግና ሥርዓት ተከትላ ብትሠራም ስህተት (‹ኤረር›) ከብዙ በጥቂቱ አያጣትም፡፡ በዚያ ዕንከን ውስጥ የሰው ልጅ ልማትና ጥፋቶች ሚና ሊኖራቸውም ላይኖርቸውም ይችላል፡፡ በመዋለድ ውስጥ የሚመጣ ተወላጅ ባለ አንድ ፆታ መሆኑ የሚጠበቅና ትክክል የሚባል ውጤት ነው፡፡ ግን ተፈጥሮ ስቷት፣ በአንዴ ሁለት ፆታ ያለው ልጅ ወይም ላዩ የሴት አካል ይዞ  ከውስጥ ወንድ የሆነ፣ ወይም ከላይ ወንድ የመሰለና ከውስጥ ግን ሴት የሆነ ልጅ ሊወለድ ይችላል፡፡ አካላዊ መሳከር የሌለ ሆኖ የባህርይ መዛባት ችግርም ሊመጣ ይችላል፡፡ የወንድ ሙሉ አካላዊ ቁመናን ይዞ ሴቴ ፀባይ ማሳየት፣ የሴት ሙሉ ቁመናን ይዞ ወንዳ ወንድ ፀባይ ማሳየት ያጋጥማል፡፡ እንደ እነዚህ ለመሳሰሉ ችግሮች ዘመናዊ የሕክምና ጥበብ ማቃኛ አነሰም በዛ አላጣም፡፡ በዚህ አቅጣጫ ምርምሩ ጠንክሮ ገፍቶ ቢሆን ኖሮም የሕክምናው ፍቱንነት የት በደረሰ ነበር፡፡

ዛሬ ‹‹በሠለጠነው›› ዓለም ያለው የተመሳሳይ ፆታ ወሲብ፣ ላይ ከተጠቀሰው ችግር ጋር ብቻ የተገናኘ አይደለም፡፡ ‹‹የፆታ ነፃነት››፣ ያልተሞከረን የመሞክር ፍላጎት ከፍተኛ መባጠጥ ውስጥ በመግባቱም እየሾረ ያለ የልሽቀት ልሽቀት ነው፡፡ ዋና መመዘኛውም ‹‹ከሕፃንነት ጀምሮ ‹ወንድ ነህ/ሴት ነሽ› ተብሎ የልጅ ፆታ በሌላ ሰው ሊወሰን አይገባም፡፡ ፆታን መምረጥ ግለሰባዊ (ሰብዓዊ) መብት ነውና ልጅ ራሱ ፆታውን እንዲወስን ሊተውለት ይገባል›› የሚል ሆኗል፡፡ ተፈጥሮ የፈለገውን ያህል ስህተት ብትሠራ የፆታን ነገር ዘፈቀዳዊ ምርጫ አታደርገውም፡፡ ፆታን ዘፈቀዳዊ ምርጫ አድርገን እንድንይዝ ያደረገው ምዕራባዊ ሠለጠንኩ ባይነት ነው፡፡ ይህ ሠለጠንኩ ባይነት ከሰሜን ዋልታ አካባቢ አገሮች እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ እየተዛመተ ያለ ነው፡፡ ኃያላኑ ‹‹ሥልጡኖች›› ለዚህ ‹‹ሰብዓዊ መብት›› ያልገበረን አገር በዕርዳታና በኢኮኖሚ ማዕቀብ እስከ መቆንጠጥ ደርሰዋል፡፡ አስፈሪው ጣጣ ግን ይህ አይደለም፡፡ በእጅጉ መፍራት ያለብን፣ የፈረንጅ አምላኪነታችንን ቀዳዳ በመጠቀም በገፍና በርካሽ እየገቡ የተላመዱን ፊልሞች ወጣቶች ላይ የሚያደርሱት አጠባ ውስጥ ለውስጥ እንዳይጨርሰን ነው፡፡

አሁን አሁን ከሆሊውድ እስከ ኖርዲክ ሠፈር የሚሠሩ ፊልሞች ሥውር ቃል ኪዳን ያላቸው ይመስላሉ፡፡ አጠባቸው በአፏዊ ልፍላፎ የተሞላ አይደለም፡፡ ልፍላፏቸው በዝምታ የተሞላና በውስጠ ታዋቂ መንገድ የሰዎችን አመለካከት የመቀየር ቅያስ ያለው ነው፡፡ ዋና ዒላማቸው በሚያቀርቧቸው የፈጠራ ኑሮዎች ውስጥ የተመሳሳይ ፆታ ተራክቦና ፍቅር እንደ አየርና እንደ አፈር የትም ያለ ‹‹ኖርማል››/ጤናማ የሆነ ነገር አድርገን እንድንላመደው ማድረግ (ድርጊቱ ሲያጋጥመው የሚሰቀጠጥ ስሜታችንን ቀስ በቀስ ለማዳ ማድረግ) እና የተመሳሳይ ፆታ ሥጋዊ ተራክቦን ከመሸሽ ፈንታ ሞክሮ ወደ መቅመስ እንድንዞር ማባበል ነው፡፡ ይህን ውጤት ለማሳካት እያንዳንዱ ፊልም አይቁነጠነጥም፡፡ የሚፈለገው ውጤት በብዙ ብዙ ፊልሞች አማካይነት ልብ ሳይባል እንዲከናወን ነው ታቅዶ የሚሠራው፡፡ በወሲብ ቴክኖሎጂ በኩል ይህንን ዓላማ እንዴት እንደሚያግዙት እዚህ ለማውሳት አልደፍርም፡፡

ይህ ወረራ ወጣቶቻችንን እንዳያጠናቅቅ ምን መከላከያ አለን? አሁንም አካሄዴን ቀየር ላድርገው፡፡ የአገራችን ከግጭትና ከቁርቁስ አልላቀቅ ያለ ኑሮና ይህንኑ ማባዘት የሚጣፍጠው አሉባልታ መድረሻ ሲያሳጣኝና ልቦናዬ ሲደክም መዝናኛ ፍለጋ እሄዳለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ፊልሞችን ለማየት ስሞክር ብዙ ጊዜ እዚያ ውስጥ የሚደነጎር ጥራዝ ነጠቅ ቡትለካ፣ ከፈረንጅ ፊልም የሚቀዳ የታሪክ መዋቅር ኩረጃና የገጸ ባህርይ ኩረጃ፣ ቃላት ላይ የሚጫወት ‹‹የአራዶች ፍተላ›› አበሳጭቶ ያባርረኛል፡፡ ‹‹ግራ ቀኝ››ን እና ‹‹በሕግ አምላክ››ን የመሳሰሉ ስብከት ሳያካሄዱ ልቦናን የሚያነቁ ድራማዎች ብርቅ ናቸውና እንደ ልብ አይገኙም፡፡ እነ ‹በስንቱ› ከብርቆቹ ውስጥ ቢሆኑም ብዙ ፍተጋ የሚሹ፣ በየጊዜው ከሚያቀርቧቸው የኑሮ እንጎቻዎች ይበልጥ የዓለማየሁና የመስከረም ትወና ገዝፎ የሚናፈቅባቸው ናቸው፡፡ የአገራችን ‹ኮሜዲ› ፊልሞች ብዙዎቹ ከሆሊውድ ‹ኮሜዲ› ተብዬ ፊልሞች የባሱ የኮሜዲ ምንነት ያልገባቸው አናዳጆች ናቸው፡፡ ከክላሲካል ኮሜዲ ጋር የተዋወቀ ሰው ዛሬ እዚያም እዚያም ከሚያገኘው የኑሮ/የሰብዕና ዕንከንን በኑሮ ፍሰት እየተረተረ የማንከትከት ሥራን ከማይሠራ (የቃላትን ትርጉም በማፍተልተል ላይ ከተንጠለጠለ) መገለፋፈጥ ጋር እንዴት እንደሚኳኋን ይቸግረዋል፡፡ ዛሬ ታይቶ ለነገ የሚረሳ የፈረንጅ ድርጊታዊ ፊልም እያየሁ ለአንድ ሁለት ሰዓት ያህል እንኳ ኑሯችንን ልርሳ ሲባል፣ ቅድም ያነሳሁት የተመሳሳይ ፆታ ነገር ብቅ ይላል፡፡ ከአገራችን ዝግጅቶች አናዳጅ ነገር ከሞላ ጎደል የሌለበት፣ ዕርቃን ሳቅ የሚሸጥበት መዝናኛ ያገኘሁት ‹‹ዋሸሁ እንዴ››ን ነው፡፡ የ‹‹ዋሸሁ እንዴ›› ዓይነት መዝናኛ የድሎት መዝናኛ አይደለም፡፡ የተጣራ ስኳር እንደ መቃም መሳይ ነው፡፡ እኔ ክፉና ደግ የለየሁ ስለሆንኩ ራሴን ስኳር በመላስ ስደልል አውቄና ፈልጌ ነው፡፡ የመንፈስን ግት ሞልቶ ብርታት የሚሆንና የመንፈስ ቁስለትን የሚያሽር የጥበብ ሥራ ባጣ፣ ራሴን በሌላ መንገድ መገንባት እችላለሁ፣ ራሴን ከዝቅጠት መጠበቅ እችላለሁ፡፡ ክፉና ደግ ያላወቁ ወጣቶቻችንንና ታዳጊዎቻችንን እንደ ደረጃቸው ምን ዓይነት አበልፃጊ ሥራዎች ብናቀርብላቸው ጣዕማቸውን ማርከን ልንንከባከባቸው እንችላለን? ከእኛ ተንከባካቢነት ባሻጋር እነሱ ራሳቸውን በራሳቸው ለመንከባከብ የሚያስችላቸውን ንቃተ ህሊናና የአኗኗር ክህሎት በውስጣቸው እንደምን ልናሳድግ እንችላለን? ይህ የሥራ አደራ የሥነ ጥበብ ሰዎች ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ በዋናነት የወጣቶችና የሕፃናት ጉዳይ የሥራ ኃላፊነታቸው የሆኑ መንግሥታዊ ተቋማት ተባብረው መላ ሊፈልጉለት የሚገባ አደራ ነው፡፡

4) ወጣት የተማሩ ሰዎቻችንን በለውጥ አመለካከት፣ በዕውቀት/በክህሎት እያተቡ በመልካም አስተዳደርና የልማት ትግል ውስጥ እያሰማሩ ትጉህ ሠራተኛነትንና ሠርቶ ማሠራትን ማለማመድ በሁሉም የሥራ ዘርፍ ያስፈልገናል፡፡ እዚህ ላይ ሥራዎች ለአዲስ መጦች እንካችሁ እየተባሉ በመደናበርና በብቃት ማነስ መጎሳቆል የለባቸውም፡፡ አዲሶች መትባት ያለባቸው በበሳሎች ምሪት ሥር ነው፡፡ ከታች ወደ ላይ ማደግ ያለባቸውም በሥራ ውጤታማነታቸውና በአበሳሰላቸው እየተመዘኑ ነው፡፡ ይህ ሒደት የትጉህ፣ የቀልጣፋና የትሁት ሥራ ባህል ቅብብሎሹን ከዛሬ ወደ ነገ ለማሸጋገር ያስችለናል፡፡ የዚህ ሒደት መቃናት በሌላ ፈርጁ፣ የውስጥ ክፍፍልንና ግጭትን መባዛትና በዚህ ገመና ምክንያት ለዘዋራና ለቀጥተኛ የውጭ ጥቃት የመጋለጥ አደጋንም የሚያዳክም ነው፡፡

የመጨረሻው ነጥብ የውስጥ ጉዳያችንና የውጭ ጉዳያችን የተጣበቁ መሆናቸውን ይናገራል፡፡ ጣብቂያውም ‹‹ሁለት አፍ ያለው ወፍ›› እንደሚባለው ምሳሌያዊ ታሪክ ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ትስስር ለአገሮቹ ጂኦ ፖለቲካዊ ጥንካሬና ደኅንነት፣ ልማትና ግስጋሴም የመሆኑ ነገር ተብሎ ያለቀ ነው፡፡ በዚህ ዕይታ ውስጥ የኢትዮጵያ የባህር በር ጉዳይ ቁልጭ ብሎ መቀመጡም ተገቢ ነው፡፡ ማለትም ኢትዮጵያ በጎረቤቶቿ ወደቦች ዓይኗ የሚቀላ አፍጣጭ አይደለችም፡፡ የረዥም ታሪክ መብት ያላት ተበዳይ ነች፡፡ በበደሉም ውስጥ የገዛ ገዥዎቿ (ሕወሓት/ኢሕዴግን ጨምሮ) አሉበት፡፡ ይህንን ለማወቅ የሚሻ ማንም ሰው የኢትዮጵያ ሕዝቦችንና የአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች ጥንቅርን አገናዝቦ፣ ከባህር በር ያለንን ርቀት አስተውሎና ይዞ፣ ከጥንት እስካሁን ያለውን የኢትዮጵያንና የአካባቢዋን ከውጭ ኃይሎች ጋር የተገናኘ ረዥም ታሪክ መመርመር ይችላል፡፡ ይህንን ቁልጭ አድርጎ ማስቀመጥ በቂያችን ነው፡፡ ከዚህ አልፈን የታሪክ ቁስል ማከክም፣ ማላዘንም አያስፈልገንም፣ ወደፊት ማየትና ለወደፊታዊ ህልውናችን መሥራት እንጂ፡፡ ይህ እውነት በይፋ መታወቁ (ማለትም የባህር በር እየተገባን ያጣነው ትልቅ ጉዳያችን መሆኑ መታወቁ) ከእኛ ጥቅም እየፈለጉ የእኛን ታሪካዊ ዕጦት ለማካከስ አለመፈለግን ኃፍረት ውስጥ ለመጣል ያስችላል፣ ይህ ትንሹ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ስለቀጣናዊ ትስስር የምትለፈልፈው ወደብ ባገኝ ብላ ነው የሚል ትዝብት ውስጥ እንዳትወድቅም፣ የአፍሪካ ቀንድ እውነታ የትስስርን ጉዳይ ዘፈቃዳዊ አለመሆን እየለፈፈላት ነው፡፡ ትስስር የሰላምና የደኅንነት ጉዳይ፣ ድርቅንና ረሃብን የማሸነፍ ጉዳይ፣ የግስጋሴ ጉዳይ ስለመሆኑ እውነታ ጮኾ እየተናገረላት ነው፡፡ በትስስር ላይ መለገም እያንዳንዱ የቀንዱ አገር የገዛ ብሔራዊ ጥቅምን መበደል ሆኖ ልግመትን ያጋልጣል፡፡ የአሁኑ የወደብ ፍላጎታችንም በራስጌ በግርጌ እያሉ መማፀን የማያስፈልገው፣ የዚህ የትስስር ግቢ አካል ነው፡፡

የእኛ ልሂቃንም ማሰብና ማውራት ያለባቸው በዚህ ግቢ ውስጥ ነው፡፡ የቁጭት ትርክት ይዞ ‹‹አቅም ኖሮን በጉልበት ወደብ ብንይዝ እንኳ መብታችሁ አይደለም የሚለን የለም›› የሚል ሐሳብን ለኢትዮጵያ በሚቆርቆር የተማረ ሰው ደረጃ መናገር (በፕራይም ቲቪ) ኃላፊነት የጎደለው ዘባሪቆነት ነው፡፡ ዓብይ አህመድን ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በመከላከያ ቀን ላይ ኢትዮጵያ ማንኛውንም ፍላጎቷን በጦርነት ማግኘት እንደማትሻ እንዲናገሩ ያደረጋቸውም፣ ተንኮለኞችን ኩም ከማድረግ በላይ እንዲህ ያለ ለከት ያላወቀ ንግግርን የማቃናት አስፈላጊነት ይመስለኛል፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ጉዳይዋ የማትሸፋፍነውና የብልጣ ብልጥነት ነገር አለመሆኑ ከታወቀላት፣ ቀሪው ነገር ለትስስር በተግባር መሥራት ነው፡፡ ይህ ተግባር ከዚህ ቀደም በሌላ ጽሑፍ እንደጠቆምኩት ጎረቤቶችን ለማሳመን የውትወታ ሥራ መሥራት አይደለም፡፡ እኛ መንደር ውስጥ የምናሳየው የኑሮ ለውጥ የጎረቤት መንደር መዝጊያን የማንኳካት (የዶሚኖ ተጋቦት) አለው፡፡  በዋቢ ሸበሌና በቦረና ምድር ላይ የሚከናወን ድርቅ አመጣሽ ረሃብን የረታና በረሃነትን ለመጋተር የደፈረ ልማት በስተግርጌ የሚያነሳሳው የተጋቦት ግፊት ቀላል አይደለም፡፡ በአፋርም የሚመጣ የኑሮ ለውጥ በሁለት አቅጣጫ ቆሌው የቅኝ ‹‹ድንበር››ን ተሻግሮ ሕዝብንም መንግሥትንም ‹‹እህሳ?›› ማሰኘቱ አይቀርም፡፡ ለቀጣናው ሰላም ከማይመቸው ከሕወሓታዊ አፈና የተላቀቀ የትግራይ ልማትም የዚያው ዓይነት ነባራዊ ጉትጎታ ይፈጥራል፡፡

የኤርትራው መሪ ከዚህ ቀደም ከአንድ የውጭ መገናኛ ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ከኤርትራ የዛሬ የኑሮ እውነታ ጋር ሳገናዝብ፣ ነፃነትነትን ባከበረ ቅርፅ የሁለቱ አገሮች መያያዝ አቤት አቤት የሚል ጉዳይ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ሁለቱ አገሮች የአንድ ደረት ሁለት ጡትነት ህልውናቸውን በይፋ የሚያውቁበትን ጊዜም ዘወትር ስናፍቀው ቆይቻለሁ፡፡ በሁለቱ አገሮች ዝምድና ውስጥ የባህር በር ጥቅም ትንሽ ነገር ነው፡፡ የሁለቱ ሕዝቦች ዝምድና በጠብና በመለያየትም በቅያሜና በኩርፊያም ሊበጠስ እንደማይችል፣ ከዓድዋ ጦርነት በፊት አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ በክፉ ቀን ሲያሳዩ የቆዩት የትግግዝ ታሪክ ብቻውን ምስክር ነው፡፡ በኢትዮጵያዊነትና በኤርትራዊነት እዚያና እዚህ ለተራራቁ የሥጋና የባዳ ዘመዳሞችም የሁለቱ አገሮች የገረረ መለያየት፣ በደቡብና በሰሜን ኮሪያ እንዳሉ ዘመዳሞች ያለ መነፋፈቅ ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ ኤርትራ ያሉ ዘመዶቼን ደግና ክፉ ወሬ እንኳ በሰማሁ ያልኩባቸው ዓመታት አልፈው በሕይወት ስለመኖራቸው ማወቅ በራሱ በዓይን ዕንባ የሞላ ትልቅ ደስታ ነበር፡፡ ከዚያ ታልፎ በስልክ የመነጋገርም ፎቶ የመለዋወጥም ዓለማችንን ዓይተናል፡፡ ከዚህም ተሻግረን የተወሰንነው በዓይነ ሥጋ ለመገናኘት በቅተናል፣ ተመሥገንም ብለናል፡፡ ግን ዝምድና ይህችን ታህል ቅርበት ይበቃኛል አይልምና የቅርብ ሩቅነታችን እንዲቀየር እንጓጓለን፡፡

ኤርትራን፣ ጂቡቲንና ኢትዮጵያን ይዞ የቀጣናችን መልክ ያበጀ መያያዝ፣ ከሕዝብ ዝምድናና ከልማት ነክ ጥቅም ባሻገር ሌላ ታሪካዊ ዋጋም አለው፡፡ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ በአካባቢው በተከናወነው ከበባና ቅኝ ግዛታዊ መቆራረስ ላይ ድል የመታ ሌላ የነፃነት ትሩፋትን ቀጣናችን ይቀዳጃል፡፡ በዚህ ትሩፋት ውስጥ ሌላም ትሩፋት አለ፡፡ ኤርትራና ኢትዮጵያ በስተሰሜን የነበረባቸውን የቅኝ ግዛት አጥር እስረኛነታቸውን በመሻርና የጋራ ጥቅማቸውን እንደ ውዴታቸው ከካርታ በላይ በማዋቀር የጋራ ነፃነትን ድል ይቀዳጃሉ፡፡ በዚህም የነፃነት ድል አማካይነት ከቅኝ ገዥዎች ጊዜያት አንስቶ ያለፉባቸውን የታሪክ ጉዞዎች በአዲስ ስሜትና ነባራዊነት መጻፍ ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያና ሶማሊያም በግዛት ጉዳይ ከመዋጋት ወጥመድ ነፃ ይወጣሉ፡፡ መልክ ያበጀ ትስስሩ በሁለት አገሮች ቢጀምር እንኳ የዚህ የዚያ ሕዝብ ነፃነት ታጋይ ነኝ ባይ የመነጠል ፍላጎት እንደ ቅቤ የመቅለጥ ሒደት ውስጥ ይገባል፡፡ ከጎረቤት ጋር የሚፈጸም ጉድኝት ከፋፋይ ብሔርተኝነትን እስከ ወዲያኛው ለመሸኘትም በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለኢትዮጵያ መጥቀሙ አይቀርም፡፡

በትንሹ ጆርጅ ቡሽ ጊዜ ፏ ያለው የአሜሪካ የ‹ታዳጊ› አገሮች አያያዝ ብልሽትና የጦርነት ክስረት፣ በኦባማ መምጣት ሊጠገን አልቻለም፡፡ በዶናልድ ትራምፕና በጆ ባይደን ጊዜም እያየን ያለነው፣ በምዕራባዊ ኃያልነት ውስጥ ክስረት እየጨመረ መሄዱንና ልዕለ ኃያላዊ ጥቅምን የማይበጅ ጥፋት የሚያሠራ መወራጨት አግጥጦ መምጣቱን ነው፡፡ በኢትዮጵያም ላይ ተካሂዶ የነበረው ርብርብ የዚሁ መገለጫ ነበር፡፡ ነገም ምን እንደሚደረግ መገመት ከባድ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ቀጣናችን በተለይም ኤርትራና ኢትዮጵያ በጋራ ዕድላቸው ላይ በነፃነት መወሰን የመቻላቸውን ነገር ጊዜ የረፈደበት የሚያደርግ ፈተና እንዳይገጥማቸው ፈጥነው መሰናዳት ሳያስፈልጋቸው አይቀርም፡፡

ከጎረቤቶቻችን ራቅ ባለ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነታችን ውስጥም ልሂቃኖቻችን አስተዋይ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ዛሬ የውጭ ግንኙነት ጉዳይ፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የአገር አቋም የሚለካው መንግሥት በይፋ በሚወስደው አቋም ብቻ አይደለም፡፡ በልሂቃንና በጋዜጠኞች አካባቢ የሚነፍስ የአስተሳሰብ ዝንባሌም አገርን ለመለካት ይውላል፡፡

የብሪክስ አባል መሆንና ከቻይና ጋር ምንም የአየር ለውጥ የማይበግረው የአጋርነት ግንኙነት ውስጥ ኢትዮጵያ መግባቷ፣ በምዕራቡ ኃያላን አካባቢ ኢትዮጵያ ለምዕራብና ለአሜሪካ የማትመች እየሆነች ይሆን የሚል ዓይነት ጥርጣሬን መፈንጠቁ አይቀርም፡፡ እንዲህ ያለውን ጥርጣሬ በጥንቃቄ ማስወገድና አንድ ጎራ ላይ ያልተጣበቀ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለኢትዮጵያ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተና ሉዓላዊነትን የማይተናነቅ ግንኙነት (እስከ አጋርነት ድረስ)፣ ከማንኛቸውም ትልቅና ትንሽ ወዳጅ አገሮች ጋር ማበጀት ፍላጎቷ መሆኑን፣ የውጭ ፖሊሲዋ በቃልና በተግባር ማንፀባረቁ ለኢትዮጵያ ይበጃታል፡፡ በዚህ ረገድ ህንድ የነበራት የኃያላኖች አያያዝ ታሪክ ትምህርት ሰጪ ነው፡፡ አሁንም ኢትዮጵያ ከምዕራብ አውሮፓ አገሮች፣ ከጃፓንና ከደቡብ ኮሪያ ጋር ግንኙነቷን የሰመረ ለማድረግ የምትጣጣር እንደሆነችና አሜሪካን ችላ የማለት ፍላጎት እንደሌላት አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ይህ ነጥብ በአግባቡ በልሂቃኑ አካባቢ ግንዛቤ ማግኘቱ ያጠራጥራል፡፡ ከምሁራን እስከ ጋዜጠኞች ድረስ ኢትዮጵያን የአንድ ጎራ አካል አድርጎ የሚያስብ ግንዛቤ እንዳይፈጠር፣ በዚህ ዓይነት ወገንተኛ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ የአወቅኩሽ ናቅኩሽ ዓይነት ትችት እንዳይስፋፋ ከወዲሁ ህሊናዊ ዓውዱን መግራት አስፈላጊ ነው፡፡

ከዚህ ሌላ ‹‹በዕርዳታ ያደገ የለም›› የሚል ጅምላ ዕሳቤን ማስተካከልም ይገባል፡፡ እንዲህ ያለ ጥያቄ አይነካሽ እስበት አዕምሮን የማስተኛት ሥራ ይሠራል፡፡ ለሙሰኞችና ለአድፋፊዎችም ጥሩ ሽፋን እንደሚሆን ልብ ይሏል፡፡ በነፍስ አድን ዕርዳታና ጥሪትን በሚያልብ ብድር አለመታደጉ እውነት ነው፡፡ ከዚያ በዘለለ ግን ልማትን ልጥቀም ባለ ዕርዳታና በቆፍጣና የገንዘብ አጠቃቀም ብርታታቸው ያደጉ አገሮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ታገኝ የነበረው ወደ ቢሊዮን የሚጠጋ የበጀት ድጎማ ዛሬ ተገኝቶ ቢሆን ኖሮ ስንት ነገር ባየን ነበር፡፡ ከእስያ ኃያሎች ጋር የሚኖረን ወዳጅነትና ከምዕራባዊ ኃያሎች ጋር ያለን ወዳጅነት ሊያስገኝልን የሚችለውን የዕገዛ ልዩነትና ዓይነት በቅጡ ተረድቶ ከሁለቱም ግንኙነቶቻችን አትራፊ ለመሆን መጠበብ ዛሬ አስፈላጊያችን ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...