ብዙ ጊዜ የመንግሥትና የፓርቲ አመራሮች ሥልጠና ተሰጣቸው የሚሉ ዜናዎች እንሰማለን፡፡ ከሹማምንቱ በተጨማሪ የፓርላማ አባላት ሥልጠና እንደተሰጣቸውም ባለፈው ሰሞን ሰምተናል፡፡ ሥልጠናው ለአገር የሰጠው ጥቅም ምን እንደሆነ ባላውቅም፣ ከሥልጠናው በኋላ ለሕዝብ ጠብ የሚል ነገር ካልታየ ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለአዳዲስ ተሿሚዎች የሚሰጥ ሥልጠና ላይ ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ፣ ሹማምንቱ ሕዝብን በተመለከተ ያላቸው አተያይ ገዘፍ እንዲል ማብራሪያ ሰጥተው እንደነበር አልዘነጋም፡፡ በዚህ መነሻ እኔ ደግሞ ከዚህ ቀደም የማስታውሳቸውን ገጠመኞች እንዲህ አድርጌ አቀረብኩ፡፡
‹‹ሕዝብ የወደደው እግዜር የወደደው›› የሚባለው አባባል በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ይህ አባባል ለራስ ወዳዶችና የሕዝብ ክብር ለማይገባቸው የማይዋጥ ቢሆንም፣ እኔ በበኩሌ እንደ ሕዝብ የማከብረውና የምፈራው የለኝም፡፡ በአንድ ወቅት ሕዝብ በሙያቸውና በሥነ ምግባራቸው ያደነቃቸው ሰዎች፣ ሁሌም ያንን ክብርና ሙገሳ ላለማጣት ሲሉ በጨዋነት ይዘልቃሉ፡፡ የሕዝብ ነገር ከልባቸው ሳይሆን ከአንገታቸው የሆነባቸው ደግሞ ወደ ላይ የወጡበት መሰላል ተንሸራቶ ወድቆ ሲከሰክሳቸው በዓይናችን ዓይተናል፡፡ ፖለቲከኛ፣ መምህር፣ ሐኪም፣ መሐንዲስ፣ ጋዜጠኛ፣ ኢንቨስተር፣ ሙዚቀኛ፣ ቴአትረኛ፣ ወዘተ. እያልን በየተራ ብንቆጥር ከሕዝብ ፍላጎት ሲያፈነግጡ መግቢያና መውጪያው ይጠፋቸዋል፡፡ ሕዝብ ካመነና ካከበረ በኋላ አይሆኑ ሆኖ መገኘት የሚያስከትለው ውርደት ነው፡፡ ለዚህም ነው፣ ‹‹ሕዝብ የጠላህ ዕለት አበቃልህ…›› የሚባለው፡፡
ለዚህ መነሻ ሐሳብ ምክንያት የሆነኝ በአንድ ወቅት አንድ ጨዋ የሚባሉ የቀድሞ ኢሕአዴግ ፖለቲከኛ በአንድ የፓናል ውይይት ላይ እንዲህ ተናግረው ነበር፡፡ ያን ጊዜ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተሳተፉበት ውይይት ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ፖለቲከኛ በስፋት ብዙ ነገሮችን ቢያነሱም፣ እኔ ደግሞ ሕዝብን በሚመለከት የተናገሩትን ትኩረት አድርጌበታለሁ፡፡ እኝህ ሰው ግልጽና ቀጥተኛ በመሆናቸው ድብብቆሽ አያውቁም ነበር፡፡ ‹‹ባለፉት 27 ዓመታት ብዙ ተግባራት ቢከናወኑም፣ መሠራት ባለበት ደረጃ ግን አልሠራንም…›› ሲሉ ጀመሩ፡፡ ‹‹የሚጠበቅብንን ሠርተን ቢሆን ኖሮ ሕዝቡ ለምን ይቆጣል? ለምንስ ይነሳብናል? ብንሠራማ ኖሮ ያመሠግነን ነበር… ለራሳችን ምስክር ከመሆን ይልቅ ሕዝብ ይመሰክርልናል… ሕዝብ ለሥራችን የመመስከር ችግር የለበትም…›› ነበር ያሉት፡፡
ሰውየው ቀጠሉ፡፡ ‹‹…ትናንት የተነሳንለትን የሕዝብ ተቆርቋሪነት ሜዳ ላይ ጥለን የቆምን ብዙ ነን፡፡ አንዳንዱ የራሱን ጌታ ፈጥሮ ይሰግዳል፡፡ ጌታ መፍጠር ለምን አስፈለገ? የድርጅታችን ዓላማ ይኼንን ይላል? ሕዝቡስ ይኼንን ይፈልጋል? በጭራሽ፡፡ ችግሩ የድርጅታችን ነበር? አዎ፣ ሕመማችን እዚህ ጋ ነበር መደባበቅ የለብንም፡፡ አንድ ሕዝብ እያለን ለምን እንባላለን? አንድ አገርና አንድ ዓላማ ነው ያለን፡፡ ለምን አንደኛችን በሌላችን ላይ ደባና ሸር እንፈጽማለን? አዎ፣ ይህ የሕዝባችን ችግር ሳይሆን የግል ጥቅም ጉዳይ ነው፡፡ ከአገርና ከሕዝብ የሚቀድም የግል ጥቅም ስላለ ነው፡፡ የራሱን ጌታ የፈጠረ ደግሞ በየደረሰበት ጉልበቱ ይከዳዋል፡፡ የሥልጣን ወንበር ላይ የምንቀመጠው ለስም መሆን አልነበረበትም፡፡ ወንበሩ የሚፈልገውን መሥራትና መወሰን ካልተቻለ ዕርባና የለውም፡፡ በእንዲህ ዓይነት ችግሮች ሳቢያ ነው ከ27 ዓመታት በኋላ ከታገልንለት ሕዝብ ጋር የተቃቃርነው፡፡ ምክንያቱ ሌላ አይደለም፡፡ ሕዝቡ የመጨረሻ ዕድል የሰጠን እነዚህ ሰዎች ምን እንደሚሠሩ እንይ ብሎ ነው፡፡ በሌላ አቅጣጫ ካሰብን ግን ተሳስተናል፡፡ ይህ ይሰመርበት…›› ነበር ያሉት፡፡
እኝህ ሰው እጅግ አስተዋይና ኃላፊነት የሚሰማቸው ይመስላሉ፡፡ ለእኔ እንደገባኝ እኝህ ሰው ፖለቲካው በሚገባ የገባቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ ነገ ተነገ ወዲያን እያሸጋገሩ እያዩ ያሉ ብልህ ሰው ናቸው፡፡ ‹‹የእኛ ጌታ ሕዝብ ነው…›› ሲሉ የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነትና በፈለገ ጊዜ የፈለገውን የማድረግ ችሎታም ተገንዝበዋል፡፡ ‹‹ከሕዝብ በስተቀር ሌላ ጌታ የለንም…›› ሲሉ ተወደደም ተጠላም ሕዝብን ይዞ አሸናፊ መሆን እንደሚቻል ነው በግልጽ ያስቀመጡት፡፡ ‹‹ሕዝብ ተይዞ የምን መብረክረክ ነው?›› ሲሉም ማየትም ማዳመጥም ተገቢ የሚሆነው ሕዝብን ነው ማለታቸው ነው፡፡ አገር ችግር ውስጥ ገብታ እንዳትፈርስ ያለው ምርጫ ጥርስን ነክሶ ከሕዝብ ጋር መሥራት ብቻ ነው የሚያዋጣው መንገድ ያሉት፣ ሕዝብን ሳይዙ የትም መድረስ አይቻልም ለማለት ነው፡፡ በቃ፣ የመታገል ዓላማው የሕዝብን ኑሮ መለወጥና ለሕዝብ ፈቃድ መገዛት ነው፡፡ ሌላ ነገር የለም፡፡
በወቅቱ የእኝህን የተከበሩ ሰው ንግግር ሳዳምጥ ውስጤ ያቃጭል የነበረው ከሕዝብ የተራራቁ ባለሥልጣናትን ጉዳይ ነው፡፡ የሚናገሩትና የሚሠሩት የማይገናኝ ባለሥልጣናት ስማቸው በጉቦ፣ በትልልቅ ግዥዎችና ኮንትራቶች የሌብነት ኮሚሽን፣ በቤተሰቦቻቸውና በዘመዶቻቸው ስም ባሉዋቸው ንግዶችና ንብረቶች፣ በዕብሪታቸውና ከመጠን ባለፈ ውሸታምነታቸው ስማቸው ይነሳል፡፡ አንድ ቀን ደፍረው ወጥተው፣ ‹‹የሚወራብኝ አሉባልታ ነው…›› ብለው ማስተባበል የማይችሉ ናቸው፡፡ ደፈር ሲሉ ዓይተንም ሰምተንም አናውቅም ነበር፡፡ በእርግጥ በየመድረኩ፣ ‹‹የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋዎች…›› እያሉ ለይስሙላ ይደሰኩሩ ነበር፡፡ ላይ ላዩን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመደስኮር ወጥተው፣ ‹‹ችግራችን በግልጽ ይኼ ነው…›› ብለው ለመናገር ድፍረቱ አልነበራቸውም፡፡ ሁልጊዜ በዚያ መከረኛ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሾላ በድፍኑ ያቅራራሉ፡፡ ሥርዓቱ የገባበትን ችግር በማድበስበስና ራስን በማሞኘት ከመመፃደቅ ውጪ ጥሬ ሀቅ አልነበራቸውም፡፡ በዚህ የተነሳ ሕዝቡ ጥልትና ጥምድ አደረጋቸው፡፡ ሕዝብ ሲጠላ ደግሞ መልዕክቱ ግልጽ ነበር፡፡ በትግሉ ፈጥፍጦ ጣላቸው፡፡ እነሱና መሰሎቻቸው ናቸው አገራችንን የጦርነት አውድማ ያደረጉት፡፡
ከዛሬ 37 ዓመት በፊት ፒያሳ ጣይቱ ሆቴል አጠገብ የሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ፣ ምራቃቸውን የዋጡ ሰዎች የሚገናኙበት የከረንቦላ መጫወቻ ትዝ ይለኛል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከተለያዩ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች፣ ከተለያዩ የንግድ ሥራዎች፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ከሕክምና ተቋማት፣ ወዘተ የሚሰባሰቡት እነዚህ ሰዎች በዕድሜና በትምህርት ደረጃ ጥሩ ይዞታ ላይ የሚገኙ ነበሩ፡፡ በከረንቦላ ጨዋታ ጊዜ ጥርስ የማያስከድኑ ቀልደኞችና ተረበኞችም ነበሩ፡፡ ቦታው ትኩረት ስለሚስብ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ሰዎችም ብቅ ጥልቅ ይሉ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን በሹክሹክታም ቢሆን የደርግ መንግሥት እስኪበቃው ይቀረጠፍ ነበር፡፡
በወቅቱ በደርግ መንግሥት ሲበሳጩ ከነበሩበት መካከል አንቱ የተባሉ ነበሩበት፡፡ ደርግ ተወግዶ ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ እነዚህ ሰዎች ተፈልገው ሹመት እንደ ተሰጣቸውም አስታውሳለሁ፡፡ እነዚያ ለሕዝብ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ግለሰቦች ሕዝብ ረስተው አዲሱን መንግሥት ለማስደሰት ይናገሩ የነበሩትን በቴሌቪዥን ስሰማ ከመጠን በላይ ይደንቀኝ ነበር፡፡ ሌሎችም በጣም ይከፉ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ሁሉም በጊዜ ሒደት ከሥልጣኑ ላይ ሲራገፉ ቀስ በቀስ የተመለሱት ወደዚያች የረሷት ከረንቦላ መጫወቻ ቤት ነበር፡፡ ሲመለሱ ግን የነበረው አቀባበል እንደ በፊቱ አልነበረም፡፡ የተከፉ ፊቶች ነበሩ ያስተናገዷቸው፡፡
ሕዝብ የጠላውን ማን ይወዳል? ሕዝብ ነዋ የሁሉም ነገር የበላይ፡፡ አሁንም እነዚያን መሰል ሰዎች በብዛት አሉ፡፡ ሥልጣኑ ሕዝብ ማገልገያ እንጂ ራስንና ቢጤን ማገልገያ እንዳልሆነ ያልገባቸው ጉዶች ብዙ ናቸው፡፡ ከመጣው ጋር ተለጥፈው ጥቅም ማግበስበስ እንጂ ለእነሱ አገርም ሆነች ሕዝብ ደንታቸው አይደሉም፡፡ ስለዚህ ሥልጠናው እዚህ ላይ ቢያተኩር ይመረጣል፡፡ በአስመሳይነትና በአድርባይነት የተካኑ ግለሰቦች የፓርቲያቸውን መመርያና ደንብ ለማንበብና ለመረዳት ቀርቶ፣ በተራ ውይይት ሳይቀር የፓርቲያቸውን ተገዳዳሪዎች ሙግት ዓውድ ለመረዳት እንኳ ያዳግታቸዋል፡፡ ይህንን አቅመ ቢስነት ደግሞ እንኳንስ የበቁና የነቁት ቀርተው ተርታው ዜጋ በሚገባ ያውቀዋል፡፡ ስለዚህ በይስሙላ ሥልጠና የአገር ጊዜ፣ ሀብትና ኢነርጂ አይባክን፡፡ ማን ምን ዓይነት አቅምና ብቃት እንዳለው በተግባር ይረጋገጥ እላለሁ፡፡ ሕዝብ ሁሉንም ነገር እየታዘበ መሆኑም አይረሳ፡፡
(ረታ ይርጉ፣ ከሳሪስ)