- ኦሮሚያና ድሬዳዋ ምሥረታው ሕገወጥ ነው ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል
በቅርቡ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ዕውቅና አግኝቶ፣ በአገር ደረጃ 32ኛ ፌዴሬሽን ሆኖ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ጁዶ ፌዴሬሽን፣ ከዓለም አቀፉ የጁዶ ፌዴሬሽንና ከአፍሪካ ጁዶ ዩኒየን ዕወቅና አለማግኘቱ ተጠቆመ፡፡
ጥቅምት 4 ቀን 2016 ዓ.ም. የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ተወካዮች፣ መሥራችና አስመራጭ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት የተመሠረተው ፌዴሬሽኑ፣ ከፍተኛ ቅሬታ ተነስቶበታል፡፡
አገር አቀፍ የፌዴሬሽን ምሥረታው በተለይም የሥራ አስፈጻሚ ምርጫው ሕግና ደንብን ያልተከተለ፣ እንዲሁም ስፖርቱ በብዛት የሚወከልበትን ክልልና ከተማ አስተዳደር ያላካተተ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በዚህም መሠረት ስፖርቱ የሚዘወተርባቸው፣ እንዲሁም አብዛኛው ስፖርተኛና ባለሙያ የሚገኝባቸው የኦሮሚያ ክልልና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በምሥረታው ላይ ውክልና አለማግኘታቸው ቅሬታ አስነስቷል፡፡
እንደ ባለሙያዎቹ አስተያየት ከሆነ፣ ምርጫው ክልሎች በቀጥታ ስፖርቱን በሙያቸው እያገለገሉ ያሉና በፌዴሬሽን ደረጃ እያገለገሉ የቆዩ ባለሙያዎችን ያገለለና ምንም እንቅስቃሴ የሌላቸው የክልል ተወካዮች ለምርጫ ፍጆታነት የተመደቡበት ምሥረታ መሆኑን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም መሥረታው ሕጋዊ ዕጩነት ያላሟሉ ግለሰቦችን ሳያጣራ ያካተተ እንደሆነ፣ የድሬዳዋና ኦሮሚያ የጁዶ ፌዴሬሽን ባለሙያዎች አንስተዋል፡፡
ሆኖም 32ኛው ፌዴሬሽን በኢትዮጵያ መቋቋሙን የሚገልጽ የዕውቅና ደብዳቤ በባህልና በስፖርት ሚኒስቴር፣ ለዓለም አቀፉ ጁዶ ፌዴሬሽን ቢላክም፣ እስካሁን ሕጋዊ ዕውቅና እንዳላገኘና የተመረጡት የሥራ አስፈጻሚ አባላትና ፕሬዚዳንት ዕግድ ሊጣልባቸው እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
የጁዶ ስፖርት ከ60 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ይታወቅ የነበረ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና እንድታገኝ የተደረገው እ.ኤ.አ. ከ2003 ጀምሮ መሆኑ ይነገራል፡፡
ይህም እ.ኤ.አ. 2001 ጀምሮ በግልና በኢትዮጵያ ኤምባሲ አበረታችነት ለዕውቀት ሽግግርና በስፖርቱ ለመሥራት ኢትዮጵያ ቀድሞ ‹‹ጁዶ ኮማንዶ›› የነበረውን ‹‹ጃጂትሱ››፣ እንዲሁም ከ2003 ጀምሮ ተረስቶ የነበረውን ተመሳሳዩን እህት ስፖርት ‹‹ጁዶን ለኢትዮጵያ›› በሚል ሲንቀሳቀስ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
በዚህ መሠረት ስፖርቱ በክልልና በከተማ አስተዳደሮች ውስን ተሳትፎ ስለነበረው፣ እንዲሁም በርካታ ክለቦች ባለመኖራቸው ማኅበር ሆኖ እንዲቆይ በዓለም አቀፍ የጁዶ ፌዴሬሽን ዕውቅና ማግኘቱ ተነስቷል፡፡
እንደ ባለሙያዎች አስተያየት ከሆነ፣ በኢትዮጵያ የስፖርት ክለቦችና ዕውቅና ያላቸው ማኅበራት እንዲመሠረቱ፣ ኢትዮጵያ የዓለም ፌዴሬሽን አባል እንድትሆን፣ እንዲሁም ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያ አትሌቶችን በጁጂትሱ ሻምፒዮና እንድታካሄድ ያደረጉ ግለሰቦች መኖራቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ሆኖም በኢትዮጵያ ሠልጣኝ በሌለባቸው ክልሎች ማለትም አፋር፣ ደቡብ፣ ሶማሌ፣ እንዲሁም ጋምቤላ ስፖርቱ እንዳለ ተደርጎ አዲስ አበባ በሚኖሩ ተወካዮች ድምፅ እንዲሰጥበት ተደርጓል የሚል፣ የኦሮሚያና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የስፖርት አመራሮች ቅሬታ አንስተዋል፡፡
ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ለዓለም አቀፍ ጁዶ ፌዴሬሽን ምሥረታውን ተከትሎ በላከው ደብዳቤ መሠረት፣ በኢትዮጵያ ውስን እንቅስቃሴ እንዳለው በሚነገረው የጁዶ ስፖርት፣ 5,500 የጁዶ አዘውታሪዎች እንዳሉ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ይህ የሐሰት ቁጥር በመሆኑ ኢትዮጵያን ሊያሳግድ ይችላል የሚል አስተያየት ተሰንዝሯል፡፡
ከዚህም ባሻገር በምሥራቁ ላይ ስፖርቱ የሚዘወተርባቸው በባለሙያዎች ሥልጠና የተሰጣቸው ኦሮሚያና ድሬዳዋ ከምርጫው መገለላቸውን የገለጹ ሲሆን፣ የአማራ ክልል በምሥረታው እንዳልተጋበዘ ተጠቁሟል፡፡
ሪፖርተር ከባለሙያዎች ባገኘው መረጃ መሠረት አዲስ ለተመሠረተው ፌዴሬሽን በወጣው መተዳደሪያ ደንብ ላይ፣ ሥራ አስፈጻሚ ሆኖ መመረጥ የሚችለው አዲስ አበባ የሚኖር መሆኑን በመግለጽ፣ የክልሎችን ተሳትፎ በማገድና ስለትውልደ ኢትዮጵያውያን የወጣውን ሕግ መጣስ እንደሆነ ያስረዳል፡፡
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ስለዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን ሥልጣን በተመለከተ የተዛባ ዕይታ እንዳለ የሚገልጹት ባለሙያው፣ በዓለም አቀፍ ስፖርትና ኦሊምፒክ ቻርተር መሠረት መንግሥት ለፌዴሬሽኖች ዕውቅና መስጠት እንጂ ጣልቃ ገብቶ ይህንን ፌዴሬሽን ምረጡት፣ እንዲሁም ፕሬዚዳንቱን ዕወቁት ወይም አባል አድርጉት ብሎ ማመልከት እንደማይችል ያስረዳሉ፡፡
የፌዴሬሽኑ መመሥረትን በተመለከተ ኦሮሚያና ድሬዳዋ ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ቅሬታቸውን ማስገባታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ቅሬታውን ተቀብሎ ጉዳዩን እያጤነው መሆኑን አሳውቋል፡፡
የዓለም አቀፍ ጁዶ ፌዴሬሽን በኢትዮጵያ የጁዶ ስፖርት በማኅበር ተቋቁመው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ግንዛቤው እንዳለው ተጠቅሷል፡፡
በዓለም አቀፍ ጁዶ ፌዴሬሽን ዕውቅና ያለው ፌዴሬሽኑ ለማቋቋም በመረጃ የተደገፈ የክለቦች፣ የክልሎች፣ እንዲሁም የባለሙያዎች ቁጥር ከታወቀ በኋላ፣ የዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን በሚሰጠው አቅጣጫና አካሄድ መሠረት ፌዴሬሽን ማቋቋም እንዳለባት ሕገ ደንቡ እንደሚደነግግ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በዚህም መሠረት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቀረቡለትን ቅሬታዎች ተመልክቶ ውሳኔውን እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል፡፡