ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ከዊነር የስፖርት ውርርድ ተቋም ጋር የስፖንሰርሺፕ የስምምነት ውል ማሰሩን አስታወቀ፡፡ ሁለቱ ተቋማት ለሦስት ዓመታት የሚቆይ የአጋርነት ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዓመት 25 ሚሊዮን ብር ያገኛል ተብሏል፡፡
ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ስምምነታቸውን ይፋ ያደረጉት ሁለቱ ተቋሞች፣ ስምምነቱ በክለቡ ታሪክ ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኝ ስፖንሰርሺፕ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
የዊነር ኢቲ ስፖርት ውርርድ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ንጋት ሙሉጌታና የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን በቀለ ስምምነታቸውን ፈጽመዋል፡፡
የዊነር ኢት ስፖርት ውርርድ ተቋም ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ንጋት ስምምነቱን አስመልክተው እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ግዙፍ ስምና ዝና ካተረፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ለሦስት ዓመታት የሚዘልቅ የላቀ አጋርነት ስምምነት መፈራረም መቻላቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት ተቋሙ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ለገባውና ለሦስት ዓመታት ለሚዘልቀው የላቀ አጋርነት ጥምረቱ፣ በቀዳሚው ዓመት የ25 ሚሊዮን ብር ክፍያ ይፈጽማል ተብሏል፡፡ ከዚያም የተከታዮቹ ሁለት ዓመታት ጥምረትም በክለቡና በኩባንያው መካከል በሚደረጉ ውይይቶች በሚደረስባቸው ስምምነቶች መሠረት የሚቀጥል እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ከዚህም ባሻገር የስፖርት ውርርድ ተቋሙ ለቅዱስ ጊዮርጊስ በሦስት ዓመታት ውስጥ ከሚያቀርበው ፋይናንስ ባሻገር፣ የስፖርት ክለቡን የጨዋታና ልምምድ ትጥቆች ምርት ሙሉ ወጪ እንደሚሸፍን ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ከመደገፍ በዘለለ፣ ተቋሙ ከፍተኛ ቁጥር ካለው የክለቡ ደጋፊ ለማስተዋወቅ አመቺ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን በቀለ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ ከተመሠረተ 88 ዓመታት ያስቆጠረው አንጋፋው ክለብ፣ ሁሌም ማሸነፍን ዓላማው አድርጎ የሚጫወት፣ የኢትዮጵያን እግር ኳስ በአኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረክ ከፍ አድርጎ ለማሳደግ የሚተጋ የሕዝብ ክለብ መሆኑን አንስተዋል፡፡
እንደ አቶ ሰለሞን ማብራሪያ፣ ስፖርት ክለቡ ከዚህ ስምምነት በታሪኩ ትልቁን የፋይናንስ ስፖንሰርሺፕ ጥቅም እንደሚያገኝ ጠቅሰው፣ ይህም ክለቡ የውስጥ አቅሙን በማሳደግ የቡድኑን ውጤታማነት ለማስቀጠል ይጠቀምበታል ብለዋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚጠቀምባቸው የጨዋታም ይሁን የልምምድ ማሊያዎች ላይ ዓርማው በጉልህ የሚታተም ሲሆን፣ ክለቡ በሚያካሂዳቸው ማናቸውም ሁነቶች፣ የፕሬስ መግለጫዎች፣ የሕዝብ ግንኙነት መድረኮች፣ እንዲሁም የሥራ አመራሩ፣ አሠልጣኞችም ሆኑ ተጫዋቾች የሚሰጧቸው መግለጫዎች የተቋሙን ዓርማ እንዲተዋወቅ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡