- ክልሎች የገጠር መሬትን የሚያስተዳድር ተቋም እንዲያቋቁሙ ያስገድዳል
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተመራው የገጠር መሬት አስተዳደር አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ፣ የመሬት ይዞታን በማስያዝ ብድር ለማግኘት የሚያስችል ድንጋጌ ተካቶበት ቀረበ፡፡
በረቂቅ አዋጁ እንደተብራራው አርሶና አርብቶ አደሮች ከመሬታቸው ያለ መፈናቀል መብታቸውን ማስከበር አስፈላጊ በመሆኑ ምክንያት፣ በመሬት የመጠቀም መብትን በማስያዝ ብድር ማግኘት እንዲችሉ ከአገሪቱ የመሬት ፖሊሲ ጋር በማጣጣም በጥንቃቄ ታስቦ የተዘጋጀ አዋጅ ነው፡፡
የገጠር መሬትን ዋስትና አድርጎ ማስያዝን የሚመለከት የሕግ ድንጋጌ እስካሁን አለመኖሩ በረቂቁ ተገልጿል፡፡ በዚህም በአሁኑ ጊዜ በአሠራር እየታዩ ያሉ የአነስተኛ የገንዘብ ተቋማት የገጠር መሬት ይዞታ መብትን በመያዝ ብድር የመስጠት ተግባር፣ ለሕጉ መሻሻል አስፈላጊ መሆኑ በረቂቁ ተመልክቷል፡፡ የገጠር መሬት ባለቤት የመጠቀም መብቱን በየክልሉ በሚወጡ ሕጎች በሚወሰን የጊዜ ገደብ አማካይነት፣ ለፋይናንስ ተቋማት ለብድር ዋስታና ማስያዝ እንደሚቻል ተገልጿል፡፡ ባለይዞታዎች በመሬታቸው የመጠቀም መብታቸውን በማስያዝ፣ የዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችና ግብዓቶችን የሚያገኙበት አሠራር ማመቻቸትን ያለመ ስለመሆኑ በረቂቁ ተብራርቷል፡፡
አበዳሪዎች ሕጋዊ የፋይናነስ ተቋማት ብቻ ሲሆኑ፣ አራጣ አበዳሪነትን ለመከላከል ግለሰቦች በሕጉ መሠረት አበዳሪ ሆነው በመሬት የመጠቀም መብትን እንደ ማስያዣ ሊይዙ እንደማይችሉ በረቂቁ ተደንግጓል፡፡ ግብዓት ለመግዛት የገንዘብ እጥረት የሚያጋጥማቸው መሬታቸውን ያከራዩ ወይም ያስጠምዱ የነበሩ ባለይዞታዎች፣ በመሬት የመጠቀም መብታቸውን በማስያዝ ብድር ወስደው አምርተው ብድራቸውን እንዲመልሱ የሚያስችል መብት ስለመሆኑም በረቂቁ ተጠቁሟል፡፡
ባለይዞታው ብድሩን መመለስ ባይችል ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ በማሰብ አበዳሪው በመሬቱ የሚጠቀምበት የጊዜ ጣሪያ ከአሥር ዓመት መብለጥ እንደሌለበት የተደነገገ ሲሆን፣ ክልሎች እንደ ክልላቸው ተጨባጭ ሁኔታ ከአሥር ዓመት ማሳነስ እንደሚችሉ ተቀምጧል፡፡ ከአሥር ዓመት ከበለጠ ግን ውሉ ሕገወጥ እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡ የመሬት ባለይዞታ የመጠቀም መብቱን በየክልሉ በሚወጡ ሕጎች በሚወሰን የጊዜ ገደብ ለፋይናንስ ተቋማት ለብድር ዋስትና ማስያዝ እንዲችሉ የሚያደርግ ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ይሁን እንጂ ድንጋጌው ከዚህ በፊት የብድርና ቁጠባ ተቋማት የሚሰጡትን ብድር የሚተካ ሳይሆን እንደ አማራጭ የመጣ ስለመሆኑ ተብራርቷል፡፡
በሌላ በኩል በረቂቅ አዋጁ እንደተመለከተው፣ የገጠር መሬት ባለይዞታ የመጠቀም መብትን ሌላ ሰው ከፋይናንስ ተቋማት ለሚበደረው ገንዘብ ዋስትና ማድረግ ይቻላል፡፡
የዚህ ድንጋጌ ዋነኛ ምክንያት፣ መሬት የሌላቸው ሰዎች ብድር ለማግኘት ሲፈልጉ ዋስ የሚሆናቸው ባለመብት ካገኙ፣ የመሬት መብት በማስያዝ ብድር እንዲያገኙ ለማድረግ፣ መሬት በመከራየት በእርሻ ሥራ ወይም ከእርሻ ሥራ ውጪ በሌሎች የግብርና ሥራዎች ላይ ተሳትፈው ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ያለመ መሆኑ ተብራርቷል፡፡
በረቂቁ አንድ የገጠር መሬት ባለይዞታ ከሌላ ባለይዞታ መሬት ጋር መሬት መለዋወጥ እንደሚቻል የተደነገገ ሲሆን፣ ልውውጡ በክልል ሥልጣን በተሰጠው ተቋም በጽሑፍ ቀርቦ መረጋገጥ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡
መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ማኅበራዊ ተቋማት፣ ክልሎች በሚያወጧቸው ሕጎች መሠረት ለዓላማቸው ማሳኪያ የሚል የገጠር መሬት የሚያገኙበት አሠራር በረቂቁ ቀርቧል፡፡
ረቂቅ አዋጁ እንደሚያሳረዳው ለእነዚህ ተቋማት የሚሰጠው የመሬት ስፋት የሚሠሩትን ሥራና ዓላማ ታሳቢ በማድረግ እንደሚወሰን የተብራራ ሲሆን፣ የመሬት የመጠቀሚያ ጊዜ በክልሎች ሕጎች ይወሰናል ይላል፡፡
ድርጅቶች መሬቱን ከወሰዱ በኋላ ያላቸው መብት የመጠቀም ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ የማከራየት፣ ለጋራ አራሽ የመስጠት፣ የማውረስ፣ በስጦታ የማስተላለፍ፣ ከባለሀብት ጋር በጋራ የማልማት፣ ለብድር ዋስትና የማስያዝ መብት እንደሌላቸው ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ በገጠር ልማት ለተሰማሩ ባለሀብቶች የገጠር መሬት ሲያገኙበት የነበረው አሠራር መቀጠሉ በረቂቁ ተገልጾ፣ የመጠቀም መብታቸው ግን መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶችና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ባላቸው መብት ልክ መሆኑ ተደንግጓል፡፡
የገጠር መሬት ኪራይን በተመለከተ በሚያብራራው የረቂቁ ክፍል ክልሎች የኪራይ ጊዜን በሚገድቡበት ወቅት፣ የኪራይ ዘመኑ ለዓመታዊ ሰብል ከአሥር ዓመታት እንዲሁም ለቋሚ ተክል ከ30 ዓመታት እንዳይበልጥ ከፍተኛ ጣሪያ እንዲሆን ተደንግጓል፡፡
በረቂቅ ሕጉ መሠረት መሬት የሌላቸው ተጋቢዎች መሬት ካላቸው ተጋቢዎች ጋር ትዳር በሚመሠርቱበት ወቅት፣ የትዳር አጋራቸው መሬት አለው በሚል ታስቦ መሬት የሚያገኙበት ሁኔታ ያልነበረው አሠራር፣ አሁን እንዲያገኙ የሚያደርግ ሆኖ ተዘጋጅቷል፡፡
በዚህም ትዳሩ በሞት ወይም በፍቺ በሚፈርስበት ወቅት ተጋቢዎች ከትዳር አጋራቸው ጋር መሬት ሳይካፈሉ ስለሚለያዩና መሬት አልባ የሚሆኑበት አጋጣሚ ብዙ በመሆኑ፣ ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት ሰዎቹ መሬት እንዲያገኙና በግል ስማቸው እንዲመዘገብ፣ ፍቺ ሲፈጸምም ይዞታቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ የሚያስችል ድንጋጌን መሆኑ ተብራርቷል፡፡
በረቂቁ ላይ በወንጀልና ቤተሰብ ሕጉ ከአንድ በላይ ሚስት ማግባትን በሚመለከት ያለው ክልከላ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በባህል ወይም በሃይማኖት ምክንያት ከአንድ በላይ ሚስቶች በሚኖሩበት ጊዜ፣ በመሬቱ ለመጠቀም ሲባል የሴቶችን መብት በሚያስጠብቅ መንገድ ምዝገባ መደረግ እንዳለበት ተቀምጧል፡፡ በመሆኑም ከዚህ ሕግ መውጣት በኋላ አንድ ሰው ከአንድ በላይ ጋብቻ የሚመሠርት ከሆነ ከመጀመሪያ ሚስቱ ጋር ያለው ጋብቻ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ያላቸውን የመሬት ይዞታ ክፍፍል ለማድረግ የመሬቱ መረጃ እንደየድርሻቸው ወቅታዊ መደረግ አለበት ይላል፡፡
መሬት አልባ ሰዎች መሬት የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንዲቻል፣ ለአንድ ባለይዞታ የሚኖረው ከፍተኛ የይዞታ መጠን በክልል ሕጎች እንደሚወሰን በረቂቁ ተገልጿል፡፡ ከፍተኛው የይዞታ መጠን እንደ ክልሎቹ ተጨባጭ ሁኔታ በጥናት ላይ ተመሥርቶ እንደሚወሰን ተደንግጓል፡፡
አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ከይዞታቸው ላይ የተወነውን በኪራይ ማስተላለፍ እንዲችሉ፣ ክልሎች ይህን ሁኔታ የሚያመቻችላቸው ተቋም እንዲያቋቁሙና ድጋፍ እንዲሰጡ በረቂቁ ተደንግጓል፡፡ የሚቋቋመው ተቋም በዋነኝነት የሚሠራው ከባህላዊ ተቋማት መሪዎችና ከአካባቢ ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ለኪራይ የተለዩ መሬቶችን መመዝገብ፣ ተከራዮችን መመዝገብ፣ ስለሚከራዩ መሬቶች መረጃ መስጠትና የአካባቢውን ወቅታዊ የመሬት ኪራይ ዋጋ ጥናት ማካሄድ የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡
በገጠር መሬት የሚነሱ ክርክሮች በመጀመሪያ ደረጃ በተከራካሪ ወገኖች ስምምነት እንዲፈቱ የሚደረግ መሆኑ የተደነገገ ሲሆን፣ ተከራካሪ ወገኖች በስምምነት መፍታት ካልቻሉ ራሳቸው በሚመርጧቸው አስማሚ ሽማግሌዎች ጉዳዮቻቸው እንዲፈታ ይደረጋል ይላል፡፡ ይሁን እንጂ አስማሚ ሽማግሌዎችን ለመምረጥ ፈቃደኛ ያልሆነ ወገን በሚኖርበት ወቅት ወይም አስማሚ ሽማግሌዎች በሚሰጡት የውሳኔ ሐሳብ ያልተስማማ ወገን፣ ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት መውሰድ እንደሚችሉ ተደንግጓል፡፡
ለመከራከር የገንዘብ አቅም የሌላቸውን ሴቶችና ድጋፍ የሚሹ ሰዎችን በመሬት የመጠቀም መብት ለማስከበር የሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ተቋማት እነሱን ወክለው ሊከራከሩ እንደሚችሉ ተመልክቷል፡፡
በረቂቅ ሕጉ ክልሎች የገጠር መሬትን የሚያስተዳድር ራሱን የቻለ ተቋም እንዲያቋቁሙ የተደነገገ ሲሆን፣ ይህ ተቋም በራሱ በጀት የሚተዳደርና መሬት ለማስተዳደር የተቋቋመ የራሱ የሰው ኃይልና ቢሮ ያለው እንዲሆን ይደረጋል ተብሏል፡፡