- የኢትዮጵያ ሕግንና የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅን በሚቃረን ውስጠ ደንብ እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል
- ‹‹ከዱባይ የሚወጣ የአሠራር ሥርዓት ቢኖርም ከአገሪቱ ሕግ ጋር ስለማይሄድ እሱን አንጠቀምም››
ኦላ ኢነርጂ ኢትዮጵያ ሊሚትድ
የአገሪቱን ሕግና አሠራር በጣሰ ሁኔታ ከፍተኛ በደል እየተፈጸመባቸውና ለዓመታት እንዲስተካከልና መፍትሔ እንዲሰጣቸው በተለያዩ ጊዜያት ላቀረቡት ጥያቄ ‹‹ምላሽ ተነፍጎናል›› ያሉ፣ ንብረትነቱ የሊቢያ ሕዝብ በሆነው የቀድሞ ሊቢያ ኦይል ኢትዮጵያ ሊሚትድ፣ በአሁኑ አጠራር ‹‹ኦላ ኢነርጂ ኢትዮጵያ ሊሚትድ›› ሠራተኞች፣ የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ እየተዘጋጁ መሆኑን አሳውቀው፣ ያ ከመሆኑ በፊት ግን መንግሥት ጣልቃ ገብቶ የተፈጠረውን ችግር እንዲፈታላቸው ጥሪ አቀረቡ፡፡
ድርጅቱ በበኩሉ በሰጠው ምላሽ፣ ጥያቄያቸው ቀላል፣ በቅርቡ ምላሽ የሚያገኝና እየተነጋገሩበት ያለ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ሠራተኞቹ በተለይ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ በኦላ ኢነርጂ ኢትዮጵያ ሊሚትድ በነዳጅ ሥርጭትና የመኪና ዘይት ሽያጭ ላይ ተሰማርተው በመሥራት ላይ የሚገኙ ሠራተኞች፣ ሥራቸውን አክብረውና ድርጅቱ ከሌሎች ተወዳዳሪ ድርጅቶች በተሻለና ቀልጣፋ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት እንዲሆን እየሠሩ ቢገኙም፣ የድርጅቱ አመራሮች ግን የአገሪቱን ሕግ የጣሰ አሠራር በመዘርጋት በደል እየፈጸሙባቸው ነው፡፡
ድርጅቱ ግልጽነትና ፍትሐዊነት የጎደለው፣ የኢትዮጵያ አሠሪና ሠራተኛ ሕግን የሚፃረር የሠራተኛ መተዳደሪያ የውስጥ ደንብ በማውጣት፣ ተግባራዊ አድርጎ በሠራተኛው ላይ በደል እየፈጸመ መሆኑን ሠራተኞቹ ተናግረዋል፡፡
ኦላ ኢትዮጵያ የሠራተኛ ማኅበር እንዳለው የተናገሩት ሠራተኞቹ፣ እየደረሰባቸው ያለውን በደል በማኅበሩ በኩል ውይይት ተደርጎ እንዲፈታላቸው ጥረት ቢያደርጉም፣ የድርጅቱ አመራሮች ጉዳዩን ከምንም ባለመቁጠር መፍትሔ ሊሰጧቸው እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኦላ ኢነርጂ ሊሚትድ ሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር ወ/ሪት ሜሮን ብርሃኑ፣ ሠራተኛው የሚያነሳው ቅሬታ ብዙ መሆኑንና እውነትነት ያለው መሆኑን አረጋግጠው፣ ነገር ግን የድርጅቱ አመራሮች ከዋና ሥራ አስኪያጁ (በአገር ውስጥ ያሉ) እስከ ዋና መሥሪያ ቤቱ (ዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ ዱባይ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ድረስ በተደጋጋሚ ለማነጋገር የተቻለ ቢሆንም፣ ‹‹ምንም ዓይነት አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን›› ተናግረዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ሠራተኛውን በአገሪቱ ሕግ ከማስተዳደር ይልቅ፣ ለሠራተኛው ዝርዝር የመተዳደሪያ ደንቡን ባለመስጠት፣ ሠራተኛ፣ ማኅበሩና ድርጅቱ በጋራ ተስማምተው ያፀደቁትን የመተዳደሪያ ደንብ በጣሰ ሁኔታ በውስጥ ያወጡት ደንብ ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑን አክለዋል፡፡
ሠራተኛው በዋናነት ለድርጅቱ የሚያቀርባቸው ጥያቄዎች፣ ‹‹የኑሮ ውድነቱን ያማከለ የደመወዝ ማስተካከያ፣ የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ የትራንስፖርት አበል ጭማሪ፣ ድርጅቱና ሠራተኛ ማኅበሩ ከደረሱበት የኅብረት ስምምነትና የአገሪቱ አሠሪና ሠራተኛ ሕግን በሚፃረር ሁኔታ፣ ሠራተኛ ዕድገት ሲሰጠው ለቦታው ከሚገባው የደመወዝ ጭማሪና ጥቅማ ጥቅም ውጪ ተደርጎ፣ በያዘው ደመወዝ ለሦስት ዓመታት እንዲሠራ የሚደረገው አሠራር እንዲቆምና ሕጉን ተከትሎ እንዲሠራ፣ የሥራ ሰዓት ሕጉን ያገናዘበ እንዲሆን የሚሉና ሌሎችም ከሠራተኛው መብት ጋር የተያያዙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ሠራተኞቹ እንደተናገሩት፣ ድርጅቱ አንድን ሠራተኛ ተወዳድሮና መሥፍርቱን አሟልቶ ከፍ ወዳለ የሥራ መደብ ሲዘዋወር፣ ያለ ምንም የደመወዝ ጭማሪና ለቦታው የሚገባውን ጥቅማ ጥቅም በመከልከል ለሦስት ዓመታት እንዲሠራ በማድረግ፣ የሠራተኛውን መብት የሚጥስ ተግባር መፈጸም፣ ሕገወጥ አሠራርና የአገሪቱን የሕግ የሚጥስ ነው፡፡
አንድ ሠራተኛ ሥራውና ለሥራው ያለው ዝግጁነት ተገምግሞ፣ ብቃት ካለው ለቀጣይ የደረጃ ዕድገት አወዳድሮ መለየት ሲቻል፣ የቅርብ አለቃን ይሁንታና መልካም ግንኙነትን ተመርኩዞ የሚፈጸም ዝውውር፣ የሥነ ምግባር ጉድለት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግንና የሠራተኛ መተዳደሪያ ደንብን የጣሰ አሠራር መሆኑን ሠራተኞቹ አብራርተዋል፡፡
ሠራተኞቹ ለሚያቀርቡት ጥያቄ ድርጅቱ ምላሽ ከመንፈጉም በተጨማሪ፣ ‹‹ስለሠራተኛው ጥቅም የማውቀው እኔ ነኝ›› በማለት፣ አንድን ሠራተኛ ዕድገት ሰጥቶ ያለ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ለሦስት ዓመታት ማሠራት፣ ‹‹ሕግ ባለበትና ሉዓላዊነቷን አስከብራ በምትኖር አገር›› በተዘዋዋሪ መንገድ ‹‹ቅኝ የተገዙ›› ያህል እንደተሰማቸው ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ ለዓመታት ትርፋማ መሆኑን የሚናገሩት ሠራተኞቹ፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት የኑሮ መደጎሚያ እንኳን አድርጎላቸው እንደማያውቅ፣ ቀደም ባሉት ዓመታት የወቅቱን የመኪና ዋጋ ያገናዘበ፣ የመኪና መግዣ ብድር ይሰጥ የነበረ ቢሆንም፣ (ከአለቆች በተጨማሪ የሥራ ባህሪያቸው መኪና ለሚያስፈልጋቸው የሥራ መደቦች)፣ ለአለቆች ብቻ በማሻሻል፣ ለከፍተኛ ሠራተኞች ግን ከዱባይ ተቀድቶ እንደመጣ የሚነገረውና ለሠራተኛው የተደበቀው ‹‹ውስጠ ደንብ መመርያ›› አይፈቅድም በማለት መከልከሉ፣ ሠራተኛውን ቅር እንዳሰኘም ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ የአብዛኛውን ሠራተኛ ጥቅም መጋፋቱ ሳያንስ በፈለገው ውስጠ ደንብ ሠራተኛውን እያስተዳደረ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ሠራተኞቹ ያነሱት ጥያቄ በድርጅቱ ምላሽ ሊያገኝ ባለመቻሉ፣ የሠራተኛ ማኅበሩ ጉዳዩን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ማቅረቡን የማኅበሩ ሊቀመንበር ወ/ሪት ሜሮን ተናግረዋል፡
ቢሮው የሠራተኛ ማኅበሩንና የድርጅቱን ተወካዮች በአካል ያወያየና ቃለ ጉባዔም የያዘ ሲሆን፣ የድርጅቱ ምላሽ አሉታዊና በተሰጠው የጊዜ ገደብ ያልተመለሰ በመሆኑ፣ ቃለ ጉባዔው ወደ ሠራተኛና አሠሪ አስማሚ ቦርድ መላኩንም ወ/ሪት ሜሮን አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን በአስማሚ ቦርድ ለመጨረስ ጠበቃ የሚያስፈልግ በመሆኑና ጠበቃ የሚጠይቀውን ክፍያ ሠራተኛውም ሆነ ማኅበሩ ለመክፈል አቅም ስለሌለው፣ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ከመሄዱ በፊት፣ የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ መብቱን ለማስከበር ሠራተኛው የተስማማና ዝግጁ ቢሆንም፣ በቅድሚያ ግን የሠራተኛውን ጥያቄ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ተመልክቶ ጣልቃ በመግባት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ሠራተኞቹ በሙሉ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡
ሠራተኞቹ ለድርጅቱ ያቀረቡትን ጥያቄና እየተተገበረ ነው ስለተባለው የአገሪቱን ሕግ የጣሰ የሥራ መመርያ (ውስጠ ደንብ) በሚመለከት ማብራሪያ ለማግኘት፣ ሪፖርተር የኦላ ኢነርጂ ኢትዮጵያ ሊሚትድ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ሹኩሪ ዲሪዲን አነጋግሮ የነበረ ቢሆንም፣ ጉዳዩን በደንብ ማብራራት ይችላሉ የተባሉትን የሰው ሀብት አስተዳደር አቶ ይልማ ዘውዴ ምላሽ እንዲሰጡ ጉዳዩን ወደ እሳቸው መርተውታል፡፡
አቶ ይልማን በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸው ደውለን ያገኘናቸው ሲሆን፣ ሠራተኛው ተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረቡን አረጋግጠው፣ ድርጅቱ ጥናት እያደረገባቸው ያሉ ሒደቶች ስላሉ በቅርቡ መፍትሔ እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡ እንደ አጠቃላይ ግን ሠራተኛው ከየትኛውም ድርጅት ወይም ተቋማት ጋር ቢነፃፀር፣ እጅግ የተሻለና ጥሩ ነገሮች እየተደረገለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ምንም እንኳን በዱባይ የሚወጣ ሠራተኞች የሚተዳደሩበት ሕግ ወይም አሠራር ያለ ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ ጋር የሚሄድ ስላልሆነ እሱ እንደማይተገበርና በውስጥ አሠራር እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡