ከ60 ሚሊዮን ሥራ አጥና በሥራ ላይ የሚገኙ ዜጎችን መመዝገብ የሚያስችል የሥራ ገበያ የመረጃ ቋት ወይም (E-LMIS) የተሰኘ ቴክኖሎጂ መዘጋጀቱን፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ከሥራ ገበያ መረጃ በተጨማሪ የኢንተርፕራይዞች የግብይት ሥርዓት፣ የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሦስት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅምት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በሥራ ላይ ማዋሉ ተገልጿል፡፡
ወደ ሥራ የገባው የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ የመረጃ ቋት (E-LMIS) በሥራና ተያያዥ ጉዳዮች የሚነሱ የመረጃ ክፍተቶችን ይቀርፋል ተብሏል፡፡
በሥራና ክህሎች ሚኒስቴር የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ አለቃ፣ የሥራ ገበያ የመረጃ ቋት 60 ሚሊዮን ዜጎችን፣ ያስተማሩባቸውን የሥራ ዘርፎችና ክህሎታቸውን ጭምር መመዝገብ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመረጃ ቋቱ በዋናነት የሚቆጣጠረው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መሆኑንና እስካሁን 25 የመንግሥትና የግል ቀጣሪ ተቋማትን እንዳስተሳሰረ አስረድተዋል፡፡
የመረጃ ቋቱ በኢትዮጵያ ለሥራ ብቁ የተባሉ ከ15 እስከ 60 የዕድሜ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን እንደሚመዘግብ፣ ለዚህም አገልግሎት የሚሆኑ 21 የተለያዩ ተጨማሪ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ማካተቱን አቶ ብርሃኑ አክለዋል፡፡
በሥራ ገበያ ቋት አንድ ሰው መመዝገብ የሚችለው ለአንድ ጊዜ ብቻ መሆኑን የገለጹት አቶ ብርሃኑ፣ ዜጎች ያላቸውን የክህሎት ደረጃ፣ የኋላ ታሪክና መሰል የደኅንነት መረጃዎች ያካተተ ነው ብለዋል፡፡
በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የሚገኙ የሥራ ዕድሎች በመረጃ ቋቱ እንደሚካተቱ፣ ይህም ዜጎች በቀላሉ የሚፈልጉትን የሥራ ዘርፍ በቀላሉ እንዲያገኙ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ፣ ቀጣሪዎች የሞባይል መተግበሪያ በመጠቀም ብቻ በተለያዩ አካባቢዎች (ክልል፣ ከተማ፣ ወረዳ) ከሚገኝ የሰው ኃይል በየትኛው የትምህርት ዘርፍ የተማሩ ይበዛሉ የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ነው፡፡
የሥራና ሠራተኛ የፖሊሲ መሠረታዊ ጉዳዮችን የሚመልስ መሆኑን፣ በምሳሌነት የጠቀሱት ተቀጣሪ ሠራተኞች የኋላ ታሪካቸውን ለቀጣሪ ተቋማት በቀላሉ እንደሚያሳዩበት አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡
ስልሳ ሚሊዮን ዜጎች ያሉበትን የሥራና የክህሎት የመረጃ ቋቱ ያሳያል ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ የሥራ መረጃ ሥርዓት በተለይም ለማክሮ ኢኮኖሚ የሚፈለገውን መረጃ በቀላሉ እንደሚያስገኝ ገልጸዋል፡፡
የ20 ሚሊዮን ዜጎችን ባዮሜትሪክ መረጃ በአምስት ደቂቃ ውስጥ መለየት እንደሚችል ያስረዱት አቶ ብርሃኑ፣ ከብድር አገልግሎት አኳያ ደግሞ ለፋይናንስ ተቋማት ደኅንነቱ የተጠበቀ ብድር ለመስጠት የመረጃ ቋቱ ትልቅ መፍትሔ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለሥራ መረጃ ሥርዓቱ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች 2‚200 ሲስተም መዘርጋቱን፣ ነገር ግን በጊዜያዊነት አገልግሎት እየተሰጠበት ያለው በ1‚000 ነው ብለዋል፡፡
እስካሁን በዚህ ሥርዓት የተመዘገቡ 270‚000 ዜጎች መሆናቸውን፣ ከዚህ ቀደም ደግሞ በሥራ መረጃ ቋት አማካይነት ለውጭ አገሮች የሥራ ዕድል ያገኙ ዜጎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
የሥራ ገበያ መረጃ ቋቱ የተዘጋጀው በማይክሮ ሰርቪስ አርክቴክቸር መሆኑን፣ ይህንን ቴክኖሎጂ ሌሎች አገሮችም እንደሚጠቀሙበትና በአማካይ እስከ 50 ሚሊዮን ብር የሚያስወጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡