- ‹‹በማንኛውም ከሕግ አግባብ ውጪ የሚንቀሳቀስ አካል ካለ ዕርምጃ እንወስዳለን፤›› የክልሉ ፀጥታ ቢሮ
በዳንኤል ንጉሤ
የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ (ሲፌፓ) ወደ አሥራ ስምንት የሚጠጉ የፓርቲው አባላትና ኃላፊዎች ላለፋት 40 ቀናት ያለ ምንም ክስና ፍርድ መታሰራቸውን ገለጸ።
የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የድርጅት ጉዳይ አስፈጻሚ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ደሳለኝ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የክልሉ ፀጥታ ቢሮ ያለ ምንም ክስ የሰው መረጃ እናቀርባለን በሚል ምክንያት አባላቶቹ በጊዜ ቀጠሮ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ እንዳሉ ጠቅሰው፣ የታሰሩበት ወንጀል ምን እንደሆነ ሳይነገራቸው ከሕግ አግባብ ውጪ እየተንገላቱ መሆኑን ጠቁመዋል።
››ፓርቲው በሕጋዊ መንገድ ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና አግኝቶ በ2015 ዓ.ም. የተቋቋመ ነው፤›› ያሉት አቶ ደሳለኝ፣ በክልሉ መንግሥት ዕውቅና እንዳለው ገልጸው፣ እስካሁንም በፓርቲው ላይ ምንም ዓይነት ጫና ሳይደርስበት ሲንቀሳቀስ እንደቆየና ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአባሎቻቸው ላይ መጥሪያ በማውጣት ምንም ባልፈጸሙት ወንጀል እየታደኑና ቤታቸው እየተበረበረ መሆኑን አስረድተው፣ በየጊዜው ፍርድ ቤት ቢቀርቡም፣ ምንም ክስ በሌለበት ሁኔታ በጊዜ ቀጠሮ ሰበብ ሰብዓዊ መብታቸውን በጣሰ መልኩ እየተጉላሉ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ደሳለኝ የዚህን ሁሉ ችግር መንስዔ ሲያስረዱ፣ ከዚህ በፊት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ጴጥሮስ ዲቢሶ ከፓርቲው ሕግና ደንብ አፈንግጠው ከክልሉ መንግሥት አካላት ጋር ፓርቲውን ለማሽመድመድ ሲሠሩ እንደነበር በድምፅና የተለያዩ መረጃዎችን በማደራጀት በመረጋገጡ፣ ለምርጫ ቦርድ ክስ እንዲገባ በማድረግ፣ ምርጫ ቦርድም በሥነ ምግባር ጥሰት ይከሰሱ ብሎ ጉዳያቸው በሚታይበት ወቅት፣ ዋና ሊቀመንበሩ ሰጥተው ለትምህርት ወደ ውጭ ሊሄዱ ሲዘጋጁ ጥቅምት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. የክልሉ ፖሊሶች ከአቶ ጴጥሮስ ጋር በመሆን ወደ ፓርቲው ጽሕፈት ቤት በመሄድ ከፓርቲው ሠራተኛ ቁልፍ በመንጠቅ በመስጠቱ መሆኑን ገልጸዋል።
‹‹አቶ ጴጥሮስ የፖርቲው የበፊቱ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ነበሩ፤›› ያሉት አቶ ደሳለኝ፣ በምን አግባብ እንደሆነ ሳይታወቅ ለእሳቸው በዚህ መልኩ የጽሕፈት ቤቱ ቁልፍ መስጠቱ እንዳሳዘናቸውና የክልሉ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ በቂ ትኩረት እያደረገ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።
‹‹የሲዳማ ክልል ቢሮ መዋቅር በዚህ ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ባይሆን ኖሮ፣ ሕግ ሲጣስ ዝም ብሎ አያይም፤›› ያሉት አቶ ደሳለኝ፣ ‹‹የፀጥታ አካላቶች ለሁሉም ወገን በእኩልነት ሕግ ማስከበር ሲገባቸው ወደ አንድ ወገን አጋድለው እየሠሩ እንደሆነ ተችተው፣ የክልሉ መንግሥት ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆኑ የሚያሳዝን ነው፤›› ብለዋል።
‹‹የታሰሩት የፓርቲው አባላት ያለ ወንጀላቸው ከመታሰራቸው ባሻገር የአካል፣ እንዲሁም የሥነ ልቦና ጥቃት ደርሶባቸዋል፤›› ያሉት አቶ ደሳለኝ፣ የአካል ጉዳታቸውን በታሰሩበት ቦታ ድረስ በመሄድ መመልከት መቻላቸውን ጠቅሰዋል።
ከ30 ሺሕ በላይ አባላት አለው ያሉት ሲፌፓ ፓርቲ፣ በመንግሥት በወጣው መሥፈርት ፈቃድ አውጥተን ሲንቀሳቀሱ እንደቆዩ ገልጸው፣ በዚህ መንገድ ስለማንችል የምርጫ ቦርድ የሰጠንን ፈቃድ ለመመለስ እንደ መፍትሔ እያሰቡ መሆኑን ገልጸዋል።
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የክልሉ ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ጢሞቲዎስ በበኩላቸው፣ ስለጉዳዩ ሲያብራሩ፣ ‹‹በፓርቲው አባላት መካከል የተፈጠረ አለመግባባት ነው፤›› ያሉ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ፓርቲውን ሲመራ የነበረው የፓርቲው ሊቀመንበር ከአገር በመውጣቱ አቶ ጴጥሮስ፣ ‹‹እኔ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር እያለሁ ለሌላ ውክልና መስጠት የለበትም በሚል ምክንያት ለሁለት በመከፈላቸው የመጣ አለመግባባት ነው፤›› ብለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ አቶ ጴጥሮስ ከግብር አበሮቹ ጋር በመሆን ቢሮ የመግባት ሙከራ አድርጓል ያሉት ኃላፊው፣ በዚህም ምክንያት አትገቡም ብሎ አላስፈላጊ ግብግብ ለማድረግ የሞከረ የፓርቲው ሠራተኛ መታሰሩንና ከፓርቲው ጋር የሚያገናኘው ነገር እንዳልሆነ አስረድተዋል።
‹‹የፓርቲ አባል መሆን ከወንጀል ነፃ አያደርግም፤›› ያሉት አቶ ዓለማየሁ፣ በፓርቲ ስም ተከልሎ የሕዝብን ሰላም ለመንሳት፣ ብሔር ከብሔር ለማጋጨት የሚሠራ ማንኛውም ዜጋ የሕግ ዕርምጃ ይወሰድበታል ብለዋል።
እየታሰሩ ያሉት የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ (ሲፌፓ) አባላት ብቻ ሳይሆኑ የብልፅግና አመራርና አባላትም እንደሆኑ አቶ ዓለማየሁ ገልጸው፣ ‹‹የእኛ ሥራ ከየትኛውም ፓርቲ ገለልተኛ በመሆን ወንጀል የሚፈጽም ማንኛውም አካል መጠየቅ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል።