መንግሥት በሕግ ሽፋንና በኮንትሮባንድ በገፍ እየገባ ያለውን የብረት ምርት ካላስቆመ ከ70 የሚበልጡ የአገር ውስጥ ብረት አምራቾች በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ሊዘጉ እንደሚችሉ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር አስታወቀ፡፡
ማኅበሩ ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ፣ በሕጋዊ ሽፋንና በኮንትሮባንድ ብረት ገበያው መጥለቅለቁን፣ ለገበያ የቀረበውም ምርት ከገበያ ዋጋ በታች በመሆኑ የአገር ውስጥ አምራቾችን ከገበያ ውጪ ማድረጉን ገልጿል።
ማኅበሩ 74 ከፍተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን መያዙን፣ በቅርቡ የብረታ ብረት ገበያው ያጥለቀለቀው ምርት ሳቢያ ሊዘጉ የተቃረቡ ድርጅቶች መኖራቸውንም አስታውቋል፡፡
ሐሰተኛ የግዥ ሰነድ በማቅረብ የሚገባ የብረት ምርት ገበያውን ማጥለቅለቁን የተናገሩት የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ፣ በአንድ አስመጪ ብቻ የሚገባው የብረት ምርት ሁሉም የአገር ውስጥ አምራቾች የሚያመረቱት ድምር መጠን ጋር እያከለ መሆኑን ገልጸዋል።
በሕገ ወጥ መንገድ እየገቡ ያሉት የግንባታ ግብዓቶች መካከል የአርማታ ብረት፣ ጋልቫናይዝ ቆርቆሮ፣ ቱቦላሬና ሌሎችም ተጠቅሰዋል።
የአገር ውስጥ አምራቾች አሁን ባሉበት ሁኔታ ሠራተኛ ለመበተን ከጫፍ መድረሳቸውን ገልጸው፣ በእነዚህ ድርጅቶች ሥር ከ60‚000 ያላነሱ ዜጎች ተቀጥረው እንደሚሠሩ አስረድተዋል፡፡
የብረታ ብረት አምራቾችን በምርት ጥራት፣ በአቅርቦት ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ፣ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡት ያለቀላቸው ምርቶች እንደተፈተኑና ህልውናቸው አደጋ ላይ መውደቁንም ጠቁመዋል፡፡
እነዚህም ምርቶች ልዩ ልዩ የማጭበርበሪያ ሥልቶችን በመጠቀም በሕጋዊ ሽፋን ጭምር ወደ አገር እየገቡ መሆኑን የደረሳቸውን መረጃ ዋቢ አድርገው ጠቅሰዋል፡፡
በሕጋዊና በኮንትሮባንድ መንገድ ያለቀላቸው የብረታ ብረት ምርቶች የሚገቡ በመሆኑ፣ በገበያው ላይ ኢፍትሐዊ የንግድ ውድድር እንዲሰፍንና ለኢንዱስትሪዎቹ ደግሞ የህልውና አደጋ እንዲጋረጥባቸው ምክንያት መሆኑን አቶ ሰለሞን አስረድተዋል፡፡
ይህንን ተከትሎ በቢሊዮን ብር የሚገመት የመንግሥት ገቢ የሚያስቀርና የአገር ውስጥ አምራቾችን ሙሉ በሙሉ እንዲዘጉ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አምራቾች በአሁኑ ጊዜ ሽያጭ መፈጸም ባለመቻላቸው በምርት ክምችት ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውንና ከማምረቻ ዋጋ ውጪ መሸጥ በሕግ የሚያስጠይቅ በመሆኑ መቸገራቸውን ገልጸዋል። በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ መውደቃቸውን አስረድተዋል።
በመንግሥት በኩል አጣዳፊ መፍትሔ ካልተወሰደ ችግሩ ኢንዱስትሪዎችን ከመዘጋታቸው ባሻገር የፋይናንስ ተቋማትን፣ የኮንስትራክሽን ዘርፉንና በዚህ ዘርፍ ተጠቃሚ የሆነውን ማኅበረሰብ ክፍል ለከፋ ችግር የሚያጋልጥ ነው ብለዋል፡፡
ይህንን ችግር ለሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች በግንባር በመቅረብና በደብዳቤ ጭምር በማሳወቅ የመፍትሔ ዕርምጃ እንዲወሰድ መጠየቃቸውን ጠቁመዋል፡፡
ማኅበሩ የተጠቀሰውን ችግር በተለይም በሀሰተኛ የግዥ ሰነድ በማቅረብ በሕግ ሽፋን የሚገባውን ምርት በተመለከተ ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር የተወያየ ቢሆንም የጉምሩክ ኮሚሽን ከውይይቱ በኋላ በጉዳዩ ላይ መግባባት እንደተደረሰ አድርጎ በማኅበራዊ የትስስር ገጹ ያሰራጨው መረጃ ተገቢነት የለውም ብሏል። ይህንንም የሚያስረዳ ግልጽ ደብዳቤ ለጉምሩክ ኮሚሽን መላኩን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በቅርቡ በድሬደዋ ጉምሩኩ ተቀርጦ በአንድ ባለሀብት ወደ አገር እንዲገባ የተደረገ 300,000 ቶን የአርማታ ብረት ሀሰተኛ ሰነድ በማቅረብ የተስተናገደ መሆኑን የሚያመለክት አቤቱታ በማኅበሩ የቀረበ ሲሆን ይህንንም የጉምሩክ ኮሚሽን ለማኅበሩ ተወካዮች ሁኔታውን ለማስረዳት ጥረት አድርጓል። በዚህም መሠረት የማኅበሩ ተወካዮች በኮሚሽኑ የኦንላይን ሲስተምን እንደሚለከቱ ዕድል ተሰጥቷቸው የነበረ ሲሆን በወቅቱም አስመጪው ያቀረበው የመጀመሪያ የግዥ ደረሰኝ ላይ አንድ ቶን ብረት በ0.87 ዶላር መገዛቱን ተወካዮቹ እንደተመለከቱ ማኅበሩ ይገልጻል።
የተጠቀሰው የአርማታ ብረት ዓለም አቀፍ ዋጋ በአንድ ቶን ከ600 እስከ 800 ዶላር መሆኑ እየታወቀ በዚህ መጠን ወርዶ በአንድ ቶን 0.87 ዶላር/ቶን እንደተገዛ ተደርጎ መቅረቡ ሊታመን የማይችል ሆኖ ሳለ ሰነዱ በኮሚሽኑ ተቀባይነት አግኝቶ መስተናገዱ ግርምትን እንደፈጠረበት ማኅበሩ ገልጿል።
ይህ የመጀመሪያ የግዥ ሰነድ ለኮሚሽኑ ቀርቦ ሳለ የማኅበሩ ተወካዮች ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ደግሞ በጉምሩክ ኃላፊዎች በኩል ሌሎች አባሪ ሰነዶች አሉ ተብሎ እንዲመለከቱ መደረጋቸውን፣ ነገር ግን አንድ የግዥ ሰነድ (ዲክላራሲዮን) በራሱ የተሟላ ሰነድ ሆኖ ሳለ ሌሎች አባሪ ሰነዶች መቅረባቸው ያልተለመደና ከራሱ ከዲክለራሲዮኑ ዓላማና ይዘት ጋር የሚስማማ ሆኖ እንዳላገኘው ማኅበሩ አስረድቷል።
በመጀመሪያው የግዥ ሰነድ ላይ የተከፈለው ቀረጥ 11.9 ሚሊዮን ብር መቀረጡ የተገለጸ ሲሆን፣ በኋላ ላይ የማኅበሩ አባላት እንዲመለከቱ በተደረገው አባሪ ሰነድ ላይ ደግሞ 276 ሚሊዮን ብር መቀረጡ መጠቀሱን መታዘባቸውን ይገልጻል። ይሁን እንጂ አሁን ባለው አማካይ የዓለም የአርማታ ብረት ገበያ ተሰልቶ ቢሆን ኖሮ መንግሥት 11 ቢሊዮን ብር ገቢ ከቀረጥ ሊያገኝ እንደሚችል ማኅበሩ ለኮሚሽኑ የላከው ደብዳቤ ያመለክታል።
የተጠቀሰው የአርማታ ብረት የገባው በፍራንኮ ቫሉታ መሆኑን፣ ይሁን እንጂ መንግሥት ፍራንኮ ቫሉታን የፈቀደው እጥረት ላለባቸው በግልጽ ለሚታወቁ ምርቶች መሆኑን፣ ይሁንና በሁለቱም አካላት የነበረው ውይይት መንግሥት ማግኘት የሚገባውን 11 ቢሊዮን ብር ማጣቷን አሳውቀዋል።
ዝርዝር እውነታዎች እያሉና ጉዳዩ ምርመራና ክትትል የሚያስፈልገው ጉዳይ ቢሆንም ለጉምሩክ ኃላፊዎች ገለጻ ሰጥተው ግብረ መልስ እንዳልተገኘ ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ያሰፈረው ‹‹ከእውነት የራቀና ሐሰተኛ›› በሚል ያሠራጨው መረጃ ከማኅበረሰብ የሚነሱ ጥያቁዎችን የሚያድበሰብስ በመሆኑ እንዲታረም እንዲሁ በወቅቱ በኮሚሽኑና በማኅበሩ መካከል የነበረው ውይይት ባለመግባባትና ባለመተማመን የተጠናቀቀ እንጂ መግባባት የተደረሰበት ባለመሆኑ በዚሁ አግባብ እንዲስተካከል ማኅበሩ በደብዳብ ጠይቋል።
ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ የጉምሩክ ኮሚሽንን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።