Sunday, December 10, 2023
Homeስፖንሰር የተደረጉሴት ተማሪዎችን የማብቃት ትልም አንግቦ እየሠራ የሚገኘው ዲሳቱ አይስ ፋውንዴሽን

ሴት ተማሪዎችን የማብቃት ትልም አንግቦ እየሠራ የሚገኘው ዲሳቱ አይስ ፋውንዴሽን

Published on

- Advertisment -

በየዓመቱ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡም ሆነ ከገቡ በኋላ በጥሩ ውጤት ተመርቀው ለቁም ነገር የሚበቁ ሴት ተማሪዎች ቁጥር ከወንድ ተማሪዎች ቁጥር ጋር ሲሰላ እጅግ አናሳ እንደሆነ ይስተዋላል።

ችግሩ በዚህ ብቻ አይቋጭም ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ከወጡ በኋላም በተለያዩ የሥራ ዘርፍ የሚሰማሩ ሴቶችም ቢሆኑ ዝቅተኛውን አኃዝ ይይዛሉ።

የችግሩ ምንጭ ናቸው ተብለው ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች ይቀርባሉ፡፡ ሴት ልጆች በቤት ውስጥ ያለባቸው የሥራ ጫና በተለይ በገጠራማው የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ ወላጆች ከሴት ልጆቻቸው ይልቅ ወንድ ልጆቻቸው ለትምህርታቸው ትኩረት ሰጥተው እንዲማሩ ያበረታታሉ። 

ምንም እንኳን ቀደም ሲል ከነበረው መሻሻል ያሳየ ቢሆንም፣ ዛሬም ብዙ ሴት ልጆች የልጅነት ጊዜያቸውን ሳያጣጥሙ የወጠኑትን የትምህርት ቤት ጉዞአቸውን ሳያጋምሱ በቤተሰብ ጫና ወደ ትዳር የሚገቡት እንዲሁም በገንዘብ እጥረትና ስለመማር ጠቀሜታ ካላቸው ዝቅተኛ ግንዛቤ የተነሳ ከትምህርት ጋር ተለያይተው የሚቀሩት ብዙዎች ናቸው ።

በእነዚህና መሰል ምክንያቶች ተምረው የወጡበትን ማኅበረሰብ በእውቀት ማገልገል እንዲሁም የተማረ ማኅበረሰብን ማፍራት የሚችሉ ሴቶች ዛሬም በቤት ውስጥ ተከልለው ይኖራሉ።

ተማሪ ሰቦንቱ በይራ የእነዚህ ዕጣ ፈንታ ሊደርሳት ለትንሽ እንዳመለጠች ታስረዳለች።

ሰቦንቱ የተወለደችው በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አሜያ ወረዳ ቤሬ ጭርጭራ ከተባለች አካባቢ ነው።

 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ላይ በነበረችበት ወቅት ስለትምህርት አስፈላጊነትም ሆነ ጠቀሜታ ሳታውቅ፣ እንዲሁ እኩዮቿ ሲመላለሱ አብራ ትመላለስ እንደነበር የምታስታውሰው ሰቦንቱ፣ የኋላ ኋላ ግን ጠንክሮ መማር ለራስና ለቤተሰብ ያለው ኩራት ለአገርም ቢሆን ያለው ጠቀሜታ እየገባት እንደመጣች ትናገራለች ።

ከዚያም በኋላ ለትምህርቷ ትኩረት ሰጥታ በመከታተል ጥሩ ውጤት ስታስመዘግብ ቤተሰብ ሲደሰት መምህራንም ደስታቸውን በሽልማት ሲገልጹ የአካባቢ ሰውም እያየንሽ እደጊ ብሎ ሲመርቃት፣ ሰቦንቱ ለትምህርት ያላት ጉጉት በጣም ይጨምራል።

የሰቦንቱ ቤተሰቦችም ሆኑ ትምህርት ቤቷ ጎበዝ ተማሪ መሆን ጥሩ እንደሆነ እንጂ ጎበዝ ለመሆንና ተምሮ ነገ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ምን ያስፈልጋል የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ ሊመልሱላት አልቻሉም።

ሴት ተማሪዎችን የማብቃት ትልም አንግቦ እየሠራ የሚገኘው ዲሳቱ አይስ ፋውንዴሽን | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ትምህርት ቤት በቂ የኮምፒውተር መማርያም ሆነ የተሟላ መጽሐፍ የለም፡፡ ወላጆቿም ቢሆኑ ተደራራቢ ሥራን ከማሠራት አልተቆጠቡም፡፡ እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብም ጎበዝ ተማሪ ለትዳር ጥሩ ነው የተባለ ይመስል ከየአቅጣጫው ጫና መምጣቱ አልቀረልኝም ነበር የምትለው ወጣቷ፣ በወቅቱ በነበረችበት ሁኔታ ብትቆይ ኖሮ ዛሬ ካለችበት ደረጃ ስለመድረሷ እርግጠኛ አይደለችም።

ለጋብቻ የሚጠይቋት በሴትነቷ የሚጎነትሏት በመብዛታቸውና በዚህም ሥጋት የገባቸው ቤተሰቦቿ፣ የዱርም ሆነ የቤት ውስጥ ሥራው ይቅርብን ብለው ወሊሶ ከተማ ትኖር ከነበርች እህቷ ጋር የመሆን ዕድሉ እንደገጠማት የምትናገረው ሰቦንቱ፣ ኢፋ ቦሩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት ትምህርቷን መቀጠሏን ተናግራለች።

ወጣቷ የሥራ ጫናውና ሌሎች ተፅዕኖዎች በመቃለላቸው በትምህርቷ ከወትሮው በተሻለ እየጠነከረች ከሌሎች ጋርም ተወዳዳሪ እየሆነች መምጣቷን ትገልጻለች።

አስረኛ ክፍል እንደጨረሰች አብሯት እያደገ የመጣው ጥንካሬዋ ለሌላ ትልቅ ዕድል እንድትታጭ ስላደረጋት፣ በትምህርት ቤቱ ከሚገኙ አሥር ጀግና እንስት ተማሪዎች መካከል በቀዳሚነት ተመርጣ ‹‹ዲሳቱ አይስ ፋውንዴሽን›› በተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ከመደበኛ ትምህርቷ መልስ ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ብቁ የሚያደርግ የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የኮምፒዩተርና የቋንቋ ሥልጠናን ከክረምት እስከ በጋ የመማር ዕድሉን አግኝታ በመማር ላይ እንደሆነች ተናግራለች።

ሰቦንቱ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን በቀጣይ ወደ ዩኒቨርሲቲ በጥሩ ውጤት ለመግባት ከወዲሁ በርትታ እየተማረች እንደሆነ ተናግራ ለጥንካሬዋም ፕሮጀክቱ ጉልህ አስተዋፅኦ እያደረገላት እንደሆነ ትመሰክራለች።

ዲሳቱ አይስ ፋውንዴሽን እ.ኤ.አ በ2018 የተመሠረተ በጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን፣ እንደ ሰቦንቱ ያሉ ባለራዕይ ሴት ተማሪዎችን በማሰባሰብ የሚደርስባቸውን ጫና ተቋቁመው ነገ የተሻለ ደረጃ በመድረስ አገራቸውን እንዲያገለግሉ ከወዲሁ በማዘጋጀት ከሌሎች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል አልሞ የተነሳ ነው የሚሉት የድርጅቱ አስተባባሪ አቶ ሽመልስ እሸቴ ናቸው።

ሴት ተማሪዎች በተለይ በትምህርታቸው ጥሩ ውጤትን በማስመዝገብ ወደ ፊት እንዲመጡ በጤና፣ በኢንጂነሪንግ ዘርፍ፣ በሕግና ፍትሕ እንዲሁም በመሪነት ደረጃም ትልቅ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ የተጀመረ ውጥን ፕሮጀክት ነው።

ችግሩ እንደ አገር ካለው ስፋትና ግዝፈት እንዲሁም ድርጅቱ ካለበት የቦታና የገንዘብ እጥረት አኳያ አጥጋቢ መፍትሔ ይሰጣል ተብሎ ሳይሆን፣ አሁን ላይ በጣም በተጣበበ ዕድል አልፈው በገቡ ሴት ተማሪዎች የሚታየውን አበረታች ለውጥ መነሻ በማድረግ መሰል በጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲስፋፉ፣ እንዲሁም የሴት ተማሪዎች ውድቀት የአገር ውድቀት ነው ብለው የሚያስቡ ማናቸውም መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች እንደ አርአያና ምሳሌ ለመሆን እየሠራ ያለ በጎ አድራጎት ድርጅት ስለመሆኑ አቶ ሽመልስ ያብራራሉ።

መሰል ድርጅቶች እንዲበዙና በትምህርት ዘርፉ እያጋጠመ ያለው መዋዠቅ መሰል መፍትሔዎችን ያገኝ ዘንድ፣ ያላቸውን ምኞት የሚገልጹት አቶ ሽመልስ፣ ዲሳቱ አይስ ፋውንዴሽን ካለው የተደራሽት አቅም አኳያም ሆነ ውስንነት፣ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን በተለይ የሴት ተማሪዎች ቁጥር መቀነስም ሆነ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ማነቆ እየሆኑ ያሉ ችግሮችን ይፈታል የሚል እምነት ባይኖርም ‹‹ጋን በጠጠር ይደገፋል›› እንደሚባለው ለብዙዎች ተምሳሌት መሆን የሚችሉ ተማሪዎችን ለማፍራት እየሠራ ነው።

 ፋውንዴሽኑ ባለፉት አምስት ዓመታት ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ብቁ በማድረግ እንዲፈተኑ ካቀረባቸው 75 ተማሪዎች መካከል 61 ተማሪዎች ጥሩ ውጤትን በማስመዝገብ ወደ ዩኒቨርሲቲ የተቀላቀሉ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ሬሚዳል ፈተና ወስደው ማለፋቸውን አብራርተዋል፡፡

ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ብቁ እንዲሆኑ ከማብቃት ጀምሮ ተመርቀው በሥራ ላይ እንዲውሉ እስከ ማድረስ ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ሽመልስ ይናገራሉ።

ሴት ተማሪዎችን የማብቃት ትልም አንግቦ እየሠራ የሚገኘው ዲሳቱ አይስ ፋውንዴሽን | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ወደ ዲሳቱ አይስ ፋውንዴሽን የሚመጡ ሴት ተማሪዎች ከሚሰጣቸው የትምህርት ድጋፍ ባሻገር ሲመላለሱ የድካም ስሜት እንዳይሰማቸው ድንገት ከቤታቸው ሲወጡ ቁርሳቸውን ሳይቀምሱ ቢወጡ ሻይ በዳቦ ይቀምሱባት ዘንድ በየወሩ ወደ ኪሳቸው የምትደርስ 300 ብር ይሰጣቸዋል። እንደ አቶ ሽመልስ ገለጻ የገንዘብ ድጋፉ የሚደረገው በጣም ለተቸገሩ ተማሪዎች ሲሆን ከእነዚህ ውጭ ደግሞ ፋውዴሽኑ ካለበት የገንዘብ እጥረት አኳያ ተወዳድረው ከመካከላቸው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች የሚሰጥ ዕድል ነው።

እንደ ዲሳቱ አይስ ፋውንዴሽን ርዕይ ቢሆን ኖሮ ሴት የተባሉ ተማሪዎች ሁሉ ሳይቸገሩ ገንዘብ እየተከፈላቸው በተማሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ፋውንዴሽኑ ካለበት የገንዘብ ውስንነት አንጻር የገንዘብም ሆነ የትምህርት ዕገዛ የሚደረግላቸው ተማሪዎች ቁጥር የተገደበ ሊሆን እንደቻለ አቶ ሽመልስ ያስረዳሉ።

ይሁን እንጂ እነዚህ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብታችኋል በቃችሁ ተብለው   የሚደረገው ድጋፍና ክትትል ችላ አይባልም የሚሉት አቶ ሽመልስ፣ በመጀመሪያ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ስድስት ሺሕ ብር ከዚያ በኋላ ደግሞ በየዓመቱ አምስት ሺሕ ብር የኪስ ገንዘብ እየሰጠ የሞራል ድጋፍ እያደረገ ተመርቀው እስኪወጡ ድረስ አብሯቸው እንደሚዘልቅ ተናግረዋል።

ጥሩ ውጤት አስመዝግበው የሕክምና ትምህርት ለማጥናት የበቁ ተማሪዎች ደግሞ ተጨማሪ ላፕቶፕ ይሸለማሉ።

‹‹ከፍዬ ሳይሆን እየተከፍለኝ ተምሬ አሁን ላለሁበት ደረጃ በቅቻለሁ›› በማለት ምስክርነቷን የምትሰጠው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን እየተከታተለች የምትገኘውና የፋውንዴሽኑ ፍሬ ከሆኑት መካከል አንዷ የሆነችው ሪሐና ሸምሱ ናት።

በ2011 ዓ.ም. ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተውጣጥተው ወደ ዲሳቱ አይስ ፋውንዴሽን ለመግባት ለፈተና ከቀረቡት 50 ሴት ተማሪዎች መካከል አሸናፊ በመሆን ዕድሉን እንዳገኘች የምታስታውሰው ሪሐና፣ በወቅቱ በአጠቃላይ ከራሷ ጋር 16 ተማሪዎች እንደነበሩ ታስታውሳለች።

ይሰጥ የነበረው የትምህርት ድጋፍ በእውቀት የተመሠረተና በተግባር የተደገፈ እንደነበር የተናገረችው ሪሐና፣ የቀሰመችው እውቀት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዋን ቀላል እንዲሆን እንዳደረገላትና ነገ በጥሩ ውጤት ተመርቃ ወጥታ ህልሟን እንደምታሳካ ያላትን ተስፋ ገልጻለች።

ፋውዴሽኑ በተለይ ለሴቶች ነጋቸውን የሚያዩበት፣ ያሰቡትን የሚያሳኩበትና የከበዳቸውን የሚያቀሉበት ነው ያለቸው ወጣቷ፣ ሴት ተማሪዎች በርትተው በማጥናት ጥሩ ውጤትን አስመዝግበው ከሌሎች ተሽለው በመገኘት የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምክርና ተሞክሮዋን ታጋራለች።

በተያዘው የትምህርት ዘመን እንደ ሪሐና ያሉ 20 ሴት ተማሪዎች ጥሩ ውጤት አስመዝግበው ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ ከወዲሁ ድጋፍ እየተሰጣቸው ሲሆን፣ የተሻለ የትምህርት ግንዛቤን ይዘው እንዲያድጉ ታሳቢ ተደርገው ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ሌሎች 44 ሴት ተማሪዎችም በተለይ የአይሲቲና የቋንቋ ትምህርት እየተሰጣቸው እንደሆነ አስተባባሪው አቶ ሽመልስ ገልጸዋል።

ሪፖርተር ቅኝት ባደረገበት ወቅት ተማሪዎችን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት በማስተማር ላይ የነበሩት መምህር እንደዕድሉ ደጀኔ፣ ፋውንዴሽኑ ለማኅበረሰቡ እየሰጠ ስላለው ዕገዛ፣ ለተማሪዎች የሰነቀው ተስፋ እንዲሁም ለወላጆች የፈጠረው እፎይታ በቀላል መታየት የለበትም ባይ ናቸው።

በተቋሙ ሥራ ከጀመሩ አምስት ዓመታት እንደሆናቸው የሚናገሩት መምህር እንደዕድሉ፣ ከእርሳቸው ጋር በማስተማር ላይ የሚገኙ ሰባት መምህራን ከሁሉም ተማሪዎች ጋር ቤተሰባዊ ቅርርብና አሠራር እንዳላቸው ይናገራሉ።

ስለእውነቱ ከሆነ ፕሮጀክቱ እየሠራ ያለው ኅብረተሰብን ለማገልገል ከመነጨ ቅን አስተሳሰብ የተነሳ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በተለይ ደግሞ ድጋፉ በእውነትም መበረታታት ለሚገባቸው ነገ ተምረው ለአገር ተስፋ ለሚሆኑት እንዲሁም ኅብረተሰብን በተለያየ አቅጣጫ ማገዝና ሌሎችን የማስተማር ዕድሉ ላላቸው ድጋፍ ማድረጉ ሴቶችን ከማበረታታት ባለፈ ለትውልዱም አስፈላጊ እንደሆነ ያብራራሉ።

ለተማሪዎቹ የሚደረግላቸው የገንዘብ ድጋፍ በትምህርታቸው ጎበዝ፣ በሥነ ልቦና ጭምር ጠንካራና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል ያሉት መምህር እንደዕድሉ፣ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወላጆችም ትልቅ እፎይታን እንደፈጠረላቸው ለመገንዘብ እንደቻሉ አስረድተዋል።

እነዚህ ተማሪዎች ከዚህ ማኅበረሰብ ወጥተው በዚህ መልኩ ተምረው ማለፋቸው ነገ የወጡበትን ማኅበረሰብ በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ዛሬ ላይ በውስጣቸው ያደረው ሲደረግላቸው በተግባር ያዩት ድጋፍ መሠረት እንደሚሆናቸው ለማወቅ አይከብድም የሚሉት መምህር እንደዕድሉ፣ ወደ ፕሮጀክቱ ገብተው ማገልገል ከጀመሩ ጀምሮ ቢደክማቸው እንኳን አይቀሩም፣ በጠና ካልታመሙ በትንሽ በትልቁ በሰበባ ሰበቡ አመካኝተው ክፍለ ጊዜ መዝጋት አይፈልጉም፡፡

ለዚህም ምክንያታቸው የፕሮጀክቱ ዓላማ የእኔም ዓላማ ነው ይላሉ፡፡ የተማሪዎችን ውጤታማነት ያስተዋሉ የአካባቢው ወላጆች ልጆቻችው ወደ ዲሳቱ አይስ ፋውንዴሽን ገብተው የማጠናከሪያ ድጋፍ እንዲያገኙላቸው በፅኑ እንደሚሹና ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እንደሚያቀርቡ የተረዱት መምህሩ፣ ነገር ግን ካለው የመማሪያ ክፍልና ሌሎች ግብዓቶች እጥረት ሁሉንም ማሳተፍ አለመቻሉ እንደሚያስቆጫቸው አክለዋል።

በየዕለቱ ፋውንዴሽኑን ‹‹ሴት ተማሪዎች አስገቡን እኛም በዚህ መማር እንፈልጋለን›› ብለው እንደሚማፀኑ አስተባባሪው ይናገራሉ፡፡

ሌሎች ወላጆችም ልጆቻችን በፕሮጀክቱ ታቅፈው ይማሩልን በማለት ጥያቄ እንደሚያቀርቡ የሚናገሩት አስተባባሪው ይሁን እንጂ አሁን ላይ ከመያዝ አቅሙ በላይ ተቀብሎ ማስተናገድ አይችልም ብለዋል፡፡

ሴት ተማሪዎችን የማብቃት ትልም አንግቦ እየሠራ የሚገኘው ዲሳቱ አይስ ፋውንዴሽን | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

 በዓመት 1.3 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ እያደረገ ተማሪዎችን ለቁምነገር የሚያበቃው ዲሳቱ አይስ ፋውንዴሽን በርከት ያሉ ተማሪዎችን አሰባስቦ ለማስተማር ታላቅ ራዕይ ቢኖረውም፣ የተለያዩ መሰናክሎች እያደናቀፉት እንዳሰበው እንዳይራመድ እንዳደረጉት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሽመልስ እሸቴ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ እንዳይሰፋና እንዳይፋፋ የኋሊት ጠፍረው ከያዙት ሳንካዎች መካከል አንዱ የቦታ ማጣት ሲሆን፣ የከተማው አስተዳደርም ሆነ የትምህርት ጥራት ይመለከተኛል የሚሉ አካላትም ቢሆኑ ፕሮጀክቱ ለአገር የሚጠቅሙ ዜጎችን ለማፍራት እየተጋ ያለ መሆኑን የዘነጉት ይመስል ወይም ችላ ብለው በመተው ‹‹ቀና ትብብራቸው አለመታየቱ ሌላው ፈተና ነው›› ያሉት አቶ ሽመልስ፣ ፕሮጀክቱ የመሥሪያ ቦታ ለማግኘት በተደጋጋሚ እስከ አዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ቢሮ ድረስ ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ሰሚ በማጣቱ ለአራት ዓመታት ለቤት ኪራይ በወር 20 ሺሕ ብር በመክፈል አገልግሎቱን ሲሰጥ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ዘላቂ መፍትሔ ባለመሆኑ በአሁኑ ወቅት የዲሳቱ ፋውንዴሽን ዋና መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ሽፈራው ገብረማርያም (ዶ/ር) በገዙት ቦታ ላይ የተወሰኑ ክፍሎችን ፋውንዴሽኑ በተመጣጣኝ ዋጋ ተከራይቶ እየተማሩ ይገኛሉ።

 ተጨማሪ መማሪያ ክፍሎችን መገንባትና በቀጣይ እስከ 200 የሚደርሱ ጠንካራ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለተሻለ ደረጃ እንዲበቁ ማድረግ የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዕቅድ እንደሆነ አቶ ሽመልስ አስታውቀዋል።

ስራችንን ለማየት እና ለመለገስ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ https://eyes.foundation

የቅርብ ጊዜ መጣጥፎች

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል ለሰማይ ለምድር ሲል፣ በየወንዙም በየአጋጣሚም...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመቋቋም ላይ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ ነው፡፡ በእነዚህ ወቅቶች...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም ከየአካባቢው ወረዳና ቀበሌ አመራሮች ጋር...

ተመሳሳይ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና ላለፉት አመታት ዘመናዊ እና ጥራት...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች 6ኛ መደበኛ...

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ መደበኛ እና ድንገተኛ ጠቅላላ...