Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የቱሪስት መስህቦች

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የቱሪስት መስህቦች

ቀን:

ቱሪዝም የገቢ ምንጭ ከመሆኑም ባለፈ አገርን ከሌሎች የዓለም አገሮች ጋር ለማስተዋወቅ፣ የአገርን በጎ ገጽታ ለማሳየት እንዲሁም ተፈጥሮን በዝምታና በአግራሞት እያስተዋሉ ለማድነቅ ይረዳል፡፡ ከተፈጥሮ ደግሞ ሁሉም ይገኛል፡፡ በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ የቱሪዝም ሀብት በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምሥራቅና በምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አስደናቂ ቦታዎች በስፋት ሊጎበኙ የሚችሉ ናቸው፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የቱሪስት መስህቦች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ መስህቦች

በሚሊዮን የሚቆጠሩ የውጭ አገር ጎብኚዎች የጎበኟቸው ጥናትና ምርምር የሚያደርጉባቸው ብርቅዬ ቦታዎች አሉ፡፡ ጊዜና ሁኔታ የተመቻቸላቸው የአገር ውስጥ ጎብኚዎችም ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የታደሙባቸው በርካታ ሥፍራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በተለይ ካለው የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ የውጭ አገር ዜጎች ይቅርና ተወልደው ባደጉበት አካባቢ እንደፈለጉ ለመውጣትና ለመግባት የሚቸገሩ ሰዎች ተበራክተዋል፡፡

የተኩስ ድምፅ ባለበት ለመዝናናት የሚሄድ ቱሪስት ይቅርና የሰማይ ወፎችም ድርሽ አይይሉም፡፡

በዚህም ከሰሜኑ ካለው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ደቡብ አካባቢ ያለው ቱሪስት ፍሰት የተሻለ እንደሚሆን ይገመታል፡፡

ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በቅርቡ ከተመሠረቱ ክልሎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በርካታ የቱሪዝም መስህቦችን አካልሎ የያዘ እንደሆነ ይነገራል፡፡

እነዚህን ባህላዊና ተፈጥሯዊ መስህቦችን ለመጎብኘት የፈለገ ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋም ሆነ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች መምጣት ከፈለጉ ምንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ድምፅ የማይሰማበት፣ እጅግ ሰላም የሆነ ቦታ ስለመሆኑ የክልሉ ባህል፣ ታሪክና ቅርስ ቢሮ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ለማ ይናገራሉ፡፡  

ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሰው ከሰው ይቅርና የዱር አውሬዎች ከሰዎች ጋር ተላምደው የሚገኙበት ቦታ ነው የሚሉት አቶ ወንድሙ፣ የቱሪስት መዳረሻዎች ለማንኛውም ተመራማሪ፣ ጎብኚዎችና መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ አድርገው ማልማትና መሳተፍ ለሚፈለጉ ሰዎች በሩ ክፍት እንደሆነም አክለዋል፡፡

ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ለሚመጣ ሰው በፍቅር የተዘረጉ እጆች ግማሽ መንገድ ተጉዘው ይቀበሉታል፣ ለአምራቾችም ወርቅ፣ የድንጋይ ከሰልና ከፍተኛ የብረት ክምችት፣ ቡና፣ ቅመማ ቅመምና መሰል ሀብቶች በስፋት ይገኛሉም ብለዋል፡፡

በክልሉ ለ250 ዓመታት 14 የዳውሮ ነገሥታት ተፈራርቀው ያስተዳደሩትና የግንባታ ሥራው 30 ዓመታትን የፈጀው በንጉሥ ሀላላ ስም ‹‹ሀላላ ኬላ›› ይገኛል፡፡

በንጉሥ ሀላላ ስም የሚጠራውና በዳውሮ ዞን የሚገኘው ሀላላ ኬላ ታሪካዊ የድንጋይ ካብ ስለመሆኑ አቶ ወንድሙ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ወንድሙ፣ የሀላላ ኬላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹ገበታ ለአገር ኮይሻ ፕሮጀክት›› ተብሎ ዘመናዊ ሎጅ ከመሥራቱ በፊት ለሁለት ነገሮች ያገለግል ነበር፡፡ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ይጎበኙት እንደነበርና ከፍተኛ ጥናትና ምርምር ይደረግበት ነበር ሲሉ ይናገራሉ፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ፀጋ ሲሉ አቶ ወንድሙ የሚጠቅሱት፣ በዳውሮ ዞንና በኮንታ ዞን መካከል 1,410 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ አካሎ የሚገኘውንና የበርካታ ዝሆኖችና ጎሾች እንዲሁም ከ28 በላይ አጥቢ የዱር እንስሳትና ከ158 በላይ የአዕዋፍ ዝርዎች፣ ጋራ ጨበራ የተባለ ብቸኛ የዓሳ ዝርያ የሚገኝበት የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክን አንዱ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡  

አንበሳ፣ ነብርና የመሳሰሉ በርካታ አጥቢ የዱር እንስሳትን አቅፎ የያዘው ኦሞ ብሔራዊ ፓርክ በዚሁ ክልል የሚገኝ ሲሆን፣ በዚህ ሥፍራ ወደንቢ የሚባል የኢትዮጵያ ብቸኛ የዱር እንስሳ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ጎራ ያለ ጎብኚ፣ ተመራማሪ፣ ባለሀብት ድንገት አዳልጦት መሬት ላይ ቢወድቅ ሊደነግጥ አይገባውም ይላሉ አቶ ወንደሙ፡፡ ለዚህ አባባልም ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡ፣ አዳልጦት የወደቀ ሰው ቅቤ ላይ ወይም ማር ላይ ነው ማረፊያው ሲነሳም ቢሆን በአንድ እጁ ቡና በሌላ እጁ ኮረሪማና ሌሎች ቅመማ ቅመም ጨብጦ፣ የቤሮ ወርቅን ይዞ ነው የሚነሳው ሲሉም የአካባቢውን የተፈጥሮ ፀጋ ያወሳሉ፡፡

በክልሉ ካሉ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ፀጋዎች ባሻገር፣ አሥራ ሦስት ብሔረሰቦች ተዋደውና ተፋቅረው የሚኖሩበት፣ ከእነዚህ ውስጥ ዝልማም፣ ማጃንኮ፣ ሱሪና ሜህኒት የናይሎ ሰሃራን ቋንቋ ተናጋሪዎች እንዲሁም ዱዚ፣ ሼኮ፣ ሸካ፣ ቤንች፣ ካፋ፣ ኮንታ፣ ዳውሮ ሜትና ፃሪ የኦሞቲክ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደሆኑም አክለዋል፡፡

አሥራ ሦስቱም የራሳቸው የሆነ በርካታ ባህላዊ እሴቶች አሏቸው የሚሉት አቶ ወንድሙ፣ የየራሳቸው ባህላዊ የአመጋገብ የአስተራረስ፣ የለቅሶ፣ የጋብቻ፣ የጭፈራ፣ የጎዳና ላይ ትርዒቶችና የመሳሰሉት ባህሎች የቱሪስት መዳረሻ ናቸው ብለዋል፡፡

በየዞኑ ያሉ የባህል ማዕከላት በብሔረሰቦቹ ልዩ ልዩ መገለጫዎች ተሰንደው ለጎብኚዎች ክፍት ሆነው ቱሪስቶችን ይጠብቃሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በሻካ ዞን የሸካና የማጃንግ ብሔረሰብ ተንቀሳቃሽ ሙዚየም ሲኖር፣ ቤንች ሾኮ ዞን ላይ የቤንችና የሸኮ ብሔረሰብ ጥንታዊ መገልገያዎች በሚዛን አማን ሙዚየም ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

በከፋ ዞን ደግሞ የከፋ ቤንች ሸንበጡ ኢትኖግራፊክስ ሙዚየም፣ የከፋ ብሔራዊ ቡና ሙዚየምና ሌሎች ታይተው የማይጠገቡ ቅርሶች የሚገኙበት ነው ብለዋል፡፡

የሸካና የከፋ ጥብቅና ጥቅጥቅ ደኖች ሌላው የአገር ሀብትና የክልሉ መስህብ ሲሆኑ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ የትምህርትና ባህል ድርጅት ለምርምር ማዕከል የተመዘገበ ደን መሆኑን ገልጸዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...