Sunday, December 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በመንግሥት የግዥ ሒደት እስከ 90 በመቶ ሙስና የሚፈጸመው በኮንስትራክሽን ዘርፍ መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በመንግሥት የግዥ ሒደት እስከ 90 በመቶ የሚሆነው ሙስና የሚፈጸመው በኮንስትራክሽን ዘርፍ መሆኑን፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ ይህን ያስታወቀው ትናንት ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በዘንድሮ በጀት ዓመት በ169 የፌዴራል ተቋማት የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሲስተም ተግባራዊ ተደርጎና አፈጻጸሙን ለማሳደግ፣ ከንግድ ማኅበረሰቡ ጋር በተደረገ ውይይት ላይ ነው፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ በመንግሥት በግዥ ሥርዓት ውስጥ፣ ከ80 እስከ ከ90 በመቶ በላይ ሙስና የሚፈጸመው በኮንስትራክሽን ዘርፍ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በመንግሥት የግዥ ሒደት እስከ 90 በመቶ ሙስና የሚፈጸመው በኮንስትራክሽን ዘርፍ መሆኑ ተገለጸ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
አቶ ሐጂ ኢብሳ

 

ዋና ዳይሬክተሩ፣ ስሙን መጥቀስ ያልፈለጉት የመንግሥት ተቋም በጨረታ አንደኛ የወጣ ድርጅት እያለ ሦስተኛ ከወጣው ጋር ውል መግባቱን፣ በዚህም ምክንያት ባለሥልጣኑ እስከ ፍርድ ቤት በመሄድ ሒደቱ እንዲቋረጥ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚከናወኑ ግዥዎች በኤሌክትሮኒክ ሥርዓት የተደረገው ዘርፉ ለሙስናና ለብልሹ አሠራር ተጋላጭ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነና ይህም መታየት እንደሚኖርበት አንድ የንግድ ማኅበረሰቡ አባል ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ምላሽ የሰጡት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር፣ ከመድረኩ የተነሳውን ችግር ትክክል እንደሆነና ከኮንስትራክሽን ጋር ተያይዞ ጨረታ የሚያወጡ የመንግሥት ተቋማት የሚፈልጉዋቸው ተጫራቾች ካልመጡ እስከ መሰረዝ እንደሚደርሱ አስረድተዋል፡፡

እነዚህ የመንግሥት ተቋማት ተጫራቾችን ሆን ብለው ከጨረታ ውጪ እንዲሆኑ ሕጎችን እንደ ምክንያት እንደሚጠቀሙ፣ ያሸነፉ ተጫራቾችንም እንዲሰላቹ በማድረግ ከጨረታ ውጪ እንዲሆኑ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በመንግሥት የግዥ ሥርዓት ምክንያት የሚመጡ ክሶች መኖራቸውን፣ በዓመት እስከ 150 የሚደርሱ ክሶች እንደሚስተናግዱ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በአብዛኛው ጨረታ የማውጣትና የሚገመገምበት መሥፈርት በመለያየቱ ምክንያት በርካታ ተጫራቾች ክስ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኢጋድ አባል አገሮችና የነጋዴ ሴቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ እንግዳዬ እሸቴ፣ በኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት ከታዩ ክፍተቶች አንዱ በጠቅላላ የመንግሥት ግዥ መባሉ ትክክል እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ግዥ ተብሎ ስያሜ ቢሰጠውም የመንግሥት ተቋማትና የንግዱ ማኅበረሰብ የሚገናኙ በመሆናቸው ከስያሜ ጀምሮ ማስተካከያ ይፈልጋል ብለዋል፡፡

የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት ሙስናን ለመቅረፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው፣ ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲዎች በሚደረጉ ግዥዎች ጥራታቸውን ያልጠበቁ ምርቶች እየቀረቡ እንደነበርና ሥርዓቱ መዘመኑ በተወሰነ መንገድ ችግሩን መቀረፉን አስረድተዋል፡፡

በተለይም በኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት ለሚታዩ የሙስና ብልሹ አሠራርን ከሥሩ ማድረቅ እንደሚገባ፣ በተለይ ተጫራጮች ወደ ተቋማት ሲሄዱ ሲስተም የለም የሚለው ቋንቋ የችግሩ መጀመርያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተጫራቾች ወይም የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ለሙስና እንዳይጋለጡ መብቶቻቸውን ለማስጠበቅ ሞጋችና ተከራካሪ መሆን እንዳለባቸው ፕሬዚዳንቷ አስረድተዋል፡፡

የመንግሥት ግዥ የንብረት ባለሥልጣን የመንግሥት ግዥ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ከበደ፣ ከአጠቃላዩ የመንግሥት በጀት 70 በመቶ ለግዥ ሥርዓት እንደሚውል ገልጸዋል፡፡

የወረቀት የግዥ ሥርዓት ለሙስና ምን ያህል ተጋላጭ እንደሆነ ከሪፖርተር ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጁ፣ የነባሩ አሠራር የሙስና ተጋላጭነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት እየተደረገበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይሁንና የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት መኖሩ የሚቀርፏቸው ችግሮች ሰፊ ከመሆናቸው ባሻገር፣ ለብዙ ተጫራቾች ዕድል ከመስጠት አኳያ ትልቅ ሚና እንዳለው አክለዋል፡፡

የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት በ2015 ዓ.ም. ሲጀመር የተመዘገቡት የንግድ ማኅበረሰብ አባላት 100 ብቻ እንደነበሩ፣ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በጥቅሉ ከ15‚000 በላይ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ በጀቷ 70 በመቶ የሚውለው ለግዥ ሥርዓት መሆኑን፣ ይህም በገንዘብ ሲቀየር 560 ቢሊዮን ብር ለግዥ ይውላል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ 169 የፌዴራል ተቋማት የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት የሚተገብሩ በመሆናቸው፣ ከክልሎች ሲዳማና አዲስ አበባ መጀመራቸውንና በቀጣይ ደግሞ በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት ከተጀመረ በኋላ የመጡ ለውጦች ምንድናቸው በማለት ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ያለውን ውጤት የሚያሳይ ጥናት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የዓለም አገሮች በኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓት በመጠቀም ብቻ ከአምስት እስከ 25 በመቶ ወጪ እንደሚቆጥቡ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሐጂ አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚደረገው ጥናት ሥርዓቱ በአገር ደረጃ ያመጣውን ለውጥ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች