በገለታ ገብረ ወልድ
ይህን የግል አስተያየት እንድከትብ ያነሳሳኝ ጥቅምት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. በሪፖርተር ዕትም ላይ የሠፈረውን ርዕሰ አንቀጽ መመልከቴ ነው፡፡ ‹‹በሰላምና በምግብ ዕጦት ለሚፈተኑ ወገኖች መፍትሔ ይፈለግ!›› በሚል አገራዊ ጥሪ ላይ የተመሠረተው ይህ ወቃሽና መካሪ ሐሳብ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻችንን ተነጋግሮ ለመፍታት አለመቻላችን ቀውሱን እያባባሰ መሄዱን ክፉኛ ይኮንናል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ምድር ግጭትን በዘላቂነት ለማስቆም የሚያስችሉ በቂ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው በእኩልነት ለመቀራረብ፣ ለመነጋገርና ለመደራደር ፈቃደኛ ሆኖ መገኘት ነው…›› የሚለው ርዕሰ አንቀጹ፣ ‹‹ፈቃደኝነቱ የሚመነጨውም በመከባበር ስሜት በጋራ አገርን ለማስቀጠል ከሚኖር ፍላጎት ነው፡፡ ይህ ፍላጎት መመሥረት ያለበት ከምንም ዓይነት ዓላማ በላይ አገርን በማስቀደም ነው…›› በማለትም ያስታውሳል፡፡
በዚህ ጸሐፊ ዕይታም ቢሆን መነጋገር፣ መደማመጥና በሰጥቶ መቀበል ተከባብሮና ተቻችሎ መኖር ባለመቻሉ ጥፋት እየደረሰ ነው፡፡ በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት በታሪክ ተደማምረው ከቆዩቱ ችግሮቻችን በሚመነጩ ዕሳቤዎችም ሆነ አዳዲስ ትርክቶችን በማስፋፋት በየአካባቢው ግጭቶች፣ የሰላም መደፍረሶችና ጦርነቶች በማያቋርጥ አኳኋን መቀጠላቸው አገርን ወደ ቀውስ እየገፉ ነው፡፡
ከሦስት ዓመታት በፊት በትግራይ ክልል በተነሳው ጦርነት በአጠቃላይ ሰሜን ቀጣና (አማራና አፋርን ጨምሮ) ያደረሰው ጉዳት እጅግ አሰቃቂ ከመሆኑ ባሻገር፣ በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት የአገር ሀብት መብላቱ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይህ አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት ጋብ ያለ ቢመስልም፣ አሁንም የጦርነት አዙሪቱ ቀጥሎ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በርካቶችን ለሕልፈተ ሕይወት እየዳረገ ነው፡፡ ለአሁኑ የአማራ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ ለመፈተሽ እሞክራለሁ፡፡
ባለፈው ሰሞን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ የአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች በተለያየ ደረጃና ጊዜ የትጥቅ ግጭት ተካሂዶባቸዋል። በተጨማሪም እነዚህ አካባቢዎችና ወረዳዎች በአንድ ወቅት በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች፣ በሌላ ወቅት ደግሞ በታጣቂው ቡድን (በተለምዶ ፋኖ በመባል የሚታወቀው) በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
የትጥቅ ግጭቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያና አልፎ አልፎ በአየር/ድሮን ድብደባ ጭምር የታገዘ ነው ያለው መግለጫው፣ በግጭቱ ዓውድ ውስጥ የአየር/ድሮን መሣሪያን ጨምሮ በከባድ መሣሪያዎች ጥቃት ሳቢያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሞትና የአካል ጉዳት የደረሰ መሆኑን፣ መኖሪያ አካባቢያቸውን ጥለው ለመሸሽ የተገደዱ ሰዎችም በርካታ መሆናቸውን ኢሰመኮ በመግለጫው አስታውቋል።
ለአብነት ሲጠቀስም በሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ወረዳ ‹መጥተህ ብላ› ከተማ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በተፈጸመ የድሮን ጥቃት የአንድ ዓመት ከሰባት ወር ሕፃንን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ያለው ኢሰመኮ በደብረ ማርቆስ ከተማ ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ቢያንስ ስምንት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውንም ነው ያረጋገጠው። በተመሳሳይ በደንበጫ ከተማ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በከባድ መሣሪያ ድብደባ ምክንያት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ደርሷል ብሏል።
ኮሚሽኑ እነዚህን መረጃዎች ያገኘው የአካባቢውን ነዋሪዎችና የዓይን ምስክሮችን በማነጋገር መሆኑን አስታውሶ፣ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ጥቃትን አልያም ግጭትን በመሸሽ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማረጋገጥ መቻሉንም በመግለጫው አካቷል።
በምንጃር ወረዳ ውስጥ የአውራ ጎዳና ጎጥ ነዋሪዎች ከመስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከቀዬአቸው ተፈናቀለው ቢያንስ 3‚000 ያህሉ አሞራ ቤቴ ቀበሌ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤትና ክፍት ሜዳ ላይ (በዛፍ ሥር) ተጠልለው የሚገኙ መሆናቸውን፣ ሌሎች ቁጥራቸው ያልታወቀ መተሐራና አዋሽን ጨምሮ ወደ የተለያዩ አካባቢዎች መፈናቀላቸው ለማኅበራዊ ቀውሱ እንደ ማሳያም ጠቅሶታል።
ለተፈናቃዮች የተወሰነ ድጋፍ በማኅበረሰቡና በአንድ ተራድኦ ድርጅት የተደረገ ቢሆንም፣ በቂ ባለመሆኑ በአሳሳቢ ሁኔታ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል ያለው ኢሰመኮ የነዋሪዎችን መፈናቀል ተከትሎ ሰብላቸው እንደ ወደመ፣ ንብረታቸው እንደ ተዘረፈ፣ የቤቶቻቸው ጣሪያና በር እየተነቀለ እንደ ተወሰደ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቤቶቻቸውን ከአጎራባች ክልል በመጡ ኃይሎች በኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ጭምር ማፍረስ እንደ ተጀመረ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና የመንግሥት ኃላፊዎች አስረድተዋል ብሏል።
በመንግሥት የፀጥታ ኃይል አባላት የሚፈጸሙ ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች አሁንም መቀጠላቸውን ኢሰመኮ ተዓማኒ መረጃዎችን እየተቀበለ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ ግጭት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሰዓት ዕላፊ ገደብ፣ በኔትወርክና በስልክ መቋረጥና በምርቶች መንቀሳቀስ አለመቻል ሳቢያ የብዙዎች ሕይወት እየተመሰቃቀለ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
በእርግጥ አንደ የአሜሪካ ድምፅ፣ የጀርመን ሬዲዮና ቢቢሲ አማርኛ ላይ እየተስተናገዱ ያሉ የሕዝብ አስተያየቶች እንደሚያስረዱት በክልሉ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በከባድ መሣሪያና በአየር ድብደባ መታገዙ ብቻ ሳይሆን፣ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለም ነው፡፡ ለሕፃናትና ለአረጋዊያን ጉዳት፣ ለእምነት ተቋማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች መፍረስና ውድመት በር እየከፈተ ያለው ይህ አደጋ ክልሉን ለከፋ ማኅበራዊ ቀውስና መከራ እንዳይዳርገው ሥጋት ያደረባቸው ጥቂት አይደሉም፡፡
ሌላው ቀርቶ ከዋና ከተማዋ በመቶ ኪሎ ሜትር ዙሪያ (ሬዲየስ) በሚገኙ አካባቢዎች ንፁኃን፣ ፖለቲከኞችና የመንግሥት አመራሮች ሲገደሉ መታየቱና እንደ ደራ ወረዳን በመሳሰሉ የሰሜን ሸዋ አካባቢዎችም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕልፈትና የበርካቶች ሀብትና ንብረት ውደመት መፈጸሙን የሚያሳዩት ዘገባዎቹ፣ በየትኛውም አካባቢ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት የሚያግዙ የፖለቲካ ምክክሮችና የጋራ መፍትሔዎች ካልተፈለጉ ቀውሱ እንደሚባባስ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሰሞኑን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ግን የኢሰመኮን መግለጫ የገለልተኝነት ጥያቄ አንስተውበታል፡፡ መንግሥተ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲያብቡ ካለው ፍላጎት አንፃር ብቻ ሳይሆን፣ ባለው ቁርጠኝነተ ኢሰመኮን የመሰሉ የሰብዓዊና የዴሞክራሲ ተቋማትን እየገነባ ቢሆንም ገለልተኝነታቸው የሚንፀባረቀው ከአስፈጻሚው ተፅዕኖ ነፃ በመሆን ብቻ መሆን የለበትም ብለዋል፡፡
ባዕዳን የውጭ ተቋማትና የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በኃይል መጫን የሚፈልጉ ኃይሎች በአገር ህልውና ላይ የሚጋርጡትን አደጋ ለመሸፈን ተቋሙን ሊጠቀሙበት እንደማይገባም አሳስበዋል፡፡ ያም ሆኖ መንግሥት በየትኛውም አካባቢ ግጭቶች ንፁኃንን እንዳይጎዱ፣ በሰላም ዕጦት ምክንያት ማኅበራዊ ቀውስ እንዳይባባስ ኃላፊነቱን ከመወጣት እንደማይዘናጋም ነው የተናገሩት፡፡
በአማራ ክልል በተለይ ግጭቶች በበረቱባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች እንግልትና መቸገር ግን ከሚባለውም በላይ እየተባባሰ መምጣቱን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡ በተለይ ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑት የዋግህምራ ዞን፣ የሰሜን ወሎና ሰሜን ጎንደር አካባቢዎች በርከት ያሉ ዜጎች ለከፋ ረሃብና ለሕልፈተ ሕይወት እየተጋለጡ መሆናቸውን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጭምር ተናግረዋል፡፡
እንደ ጎጃም፣ ሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎን በመሳሰሉ ወረዳዎችም ምርቶችም ሆነ ሸቀጣ ሸቀጦች ከገበያ መጥፋታቸው ነዋሪዎችን ለችግር አጋልጠዋል፡፡ የጥሬ ብር መጥፋትና የገበያ ሰላማዊ መስተጋብር መዳከም በተለይ ዝቅተኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ለከፋ ችግር እየዳረገው ነው፡፡ አንዳንድ ጦርነቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎችም የከባድ መሣሪያና የአየር ድብደባ በመሥጋት ገበያ መሄድ እንዳልተቻለ ለማረጋገጥ ችያለሁ፡፡
ገንዘብ ባንክ ውስጥ ያላቸው ሰዎችም አውጥተውም ሆነ መንዝረው መጠቀም ካለመቻላቸውም በላይ፣ ብዙዎቹ የመንግሥትና የግል ድርጅት ተቀጣሪዎችና መምህራን ሳይቀሩ ደመወዝ ማግኘት አቅቷቸው ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ነው የሚያስረዱት፡፡ የመማር ማስተማር ሒደቱንም በአግባቡ መምራት እንዳልተቻለ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡
ቀላል ግምት በማይሰጠው የእርስ በርስ ጦርነት ከአማፅያኑም ሆነ ከመንግሥት የፀጥታ አካላት በኩል፣ እንዲሁም በርከት ባሉ የመንግሥት አመራሮች ላይ ሞትና የአካል ጉዳት ማድረሱም ሌላው አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ በየአካባቢው ሕግና ሥርዓት እየተገደበ፣ ኃይልና ጉልበት መድረኩን እየተቆጣጠረ መምጣቱ በሕዝብ ላይ ከፍተኛ መሳቀቅና ፍርኃት ማሳደሩም አይቀሬ ነው፡፡
ይህም በአገራችንም ሆነ በርከት ባለው የአፍሪካ ምድር ለዓመታት ሲሆን እንደታየው ወንድም በወንድሙ ላይ ዘምቶ ግዳይ ከማስቆጠርና ምርኮ ከማሳየት በላይ ሌላ የሚያሳፍር ነገር እንደሌለ አመላካች ነው፡፡ እውነት ለመናገር አገራችን ከአምስት ዓመታት በፊት ከነበረችበት ሰላምና የፀጥታ ደረጃ ላይም ሆነ የተዳከመ የዴሞክራሲ ምኅዳርና የመልካም አስተዳደር ሁኔታ ውስጥ እንድትገኝ ያደረገ ፍልሚያ ውስጥ መግባቷ ሁላችንንም ሊያስቆጭ ይገባል፡፡
በአማራ ክልል የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ለመባባሱም ሆነ በኦሮሚያና በሌሎች አካባቢዎችም የተረጋጋ ሰላማዊ ምኅዳር ላለመታየቱ ሌላው ማረጋገጫ እንደ አሜሪካ፣ ካናዳና ብሪታኒያ የመሳሰሉ የምዕራብ መንግሥታት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዜጎቻቸውን የሚያስጠነቅቅ የጉዞ ገደብና ክልከላ እያደረጉ መሆናቸው ሲታይ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ከፍተኛ የገጽታ ግንባታ ጉዳት ያለው፣ ለቱሪዝማችንም ሆነ ለኢንቨስትመንት ከባድ እንቅፋት የሚሆን ነው፡፡
መረጃዎቹ በገለልተኛ ወገን እየተረጋገጡ ባይሆንም በየአካባቢው አምራች ኃይል፣ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በታጠቁ ተፋላሚዎች ላይም እየደረሰ ያለው ሰብዓዊ ኪሳራ ቀላል አይደለም፡፡ በደፈጣም ሆነ በፊት ለፊት ውጊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች መሞታቸውም ሆነ በርካቶቹ ለአካልና ለሥነ ልቦና ጉዳት መዳረጋቸው አገራዊ ኪሳራው ቀላል አይደለም፡፡ የሀብት ውድመቱም ለደሃ አገር በቦሃ ላይ ቆረቆርን የሚያስተርት ነው፡፡
በአማራ ክልል የሚገኙ አሥር ዩኒቨርሲቲዎች አሁን ተማሪዎችን እንደማይቀበሉ ያስታወቁበት የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ዘገባ ደግሞ ሌላኛው የአገር ጉዳት ማሳያ ነው። በአማራ ክልል ወደ ትምህርት ገበታ መግባት ከነበረባቸው ተማሪዎች መካከል ሰባት ሚሊዮን ያህሉ ወደ ትምህርት ቤት ሄደው አለመመዝገባቸውና ብዙዎቹ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ከትምህርታቸው መስተጓጎላቸው አንሶ፣ ሁሉም በክልሉ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች በያዝነው ዓመት ሥራ አለመጀመራቸው ያለውን ቀውስ አመላካች ነው፡፡
እንደ ዘገባው በአማራ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ዋና ጸሐፊ አስማረ ደጀን (ዶ/ር) እንዳሉት፣ የክልሉ ፀጥታ እስኪሻሻል ድረስ ተማሪዎቻቸውን እንደማይጠሩና የጋራ መግባባት ላይ እንደደረሱ ተደርሷል፡፡
ተማሪዎች ወደ ግቢ ከገቡ በኋላ ግጭት ቢነሳ ዩኒቨርሲቲዎቹ ኃላፊነት መውሰድ አይችሉም። ከምግብ ጀምሮ ለዩኒቨርሲቲዎች ልዩ ልዩ ግብዓቶችን ያቀርቡ የነበሩ አካላት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንደተቸገሩ ተናግረዋል። በዚህ መነሻ ፎረሙ ውሳኔ አሳልፏል ብለዋል። የፎረሙን ውሳኔ ተማሪዎችም ሆኑ ወላጆች እንደሚጋሩትም ነው ዘገባው ያመላከተው ።
በአጠቃላይ በጽሑፉ የተዳሰሰውን አማራ ክልልን ወደ ተባባሰ ቀውስና ማኅበራዊ ችግር እየዳረገው ያለው ግጭትም ይባል ጦርነት፣ ከቀደመው የሰሜን ጦርነት የቀጠለ እንጂ ብቻውን የቆመ አይደለም፡፡ ወደፊትም ሊነሱ ለሚችሉ ማኅበረ ፖለቲካዊ ፈተናዎች መዘዝ እየሆነ መሄዱም የሚቀር አይመስልም፡፡ ስለሆነም እንዲህ ያሉ ችግሮችን በፖለቲካው ድርድርም ይባል ሰጥቶ የመቀበል ምክክር ለመፍታት ማሰቡ ነው የሚበጀው፡፡ ካልሆነ ግን ተያይዞ መውደቅ አይቀሬ ነው፡፡
ለመንግሥትም ሆነ ለመላው ተፋላሚ አካላት መባል ያለበትም ተነጋገሩ፣ ሰላም አምጡና ሕዝብ ታደጉ ነው፡፡ ማንኛውም ፖለቲካዊ ሥርዓትም ሆነ አገር ከሁሉ በላይ ያለ ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ብሎም ያለ እውነተኛ ዴሞክራሲ ስለማይረባ፣ ለሰላምና ለዴሞክራሲ መስፈን ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡ እነዚህ መሠረታዊ የሕዝብ ጥቅሞች ለድርድር ሳያቀርቡ በፅናትና በጥልቀት መትጋትም የሁላችንም ታሪካዊ አደራ ሊሆን ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሰላም ድርድሩም ሆነ ምክክሩ የብሔር፣ የሃይማኖትም ሆነ የእኔ እኔ ባይነት ዓይነ ጥላችንን ገፍፎ፣ ሁሉንም ወገኖች ባካተተ መንገድ አገርን ወደ ደልዳላው ሜዳ እንዲያደርስ ምኞቴ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡