በተሾመ ብርሃኑ ከማል
መንደርደሪያ
የቁጥጥር ሥርዓቱ በደከመ መንግሥት ውስጥ ሌብነት፣ አጭበርባሪነት፣ አድሏዊነት፣ ተውሳክነት (ጥገኝነት)፣ ከሃዲነት፣ አስመሳይነት፣ ጉቦኝነት፣ ሙሰኝነት ተስፋፍቶ ሊገኝ ይችላል፡፡ መንግሥቱ እየተዳከመ በሄደ መጠን የመቆጣጠር አቅሙ እየቀነሰ ስለሚሄድ የተጠቀሱት ማኅበራዊ ቀውሶች እያደጉ ይሄዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሕዝቡ መማረር ይጀምራል፡፡ ለመሆኑ ሌብነት፣ ሙሰኝነት፣ ጉቦኝነት፣ ብልሹ አስተዳደር፣ የውሸት ባለሥልጣንነት ስንል ምን ማለታችን ነው? በዚህ ጽሑፍ ጽንሰ ሐሳቡን ቀለል ባለ መንገድ ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡ ጽሑፉ የተጻፈበት መሠረታዊ ምክንያት በአገራችን ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና አሳታፊነት የሰፈነበትን ሥርዓት ለማስፈን ምን መደረግ እንዳለበት አነስተኛ ሐሳብ ለመሰንዘር ያህል ነው፡፡
ሌብነት
ሌባ ባለሥልጣን ማለት በቀጥታ የሰው ኪስ ወይም መጋዘን፣ ወይም ባንክ ገብቶ የሚሰርቅ አይደለም፡፡ ሌባ ባለሥልጣን ማለት በተለይም በመንግሥት እምነት ተጥሎበት፣ የተጣለበትን እምነት አሽቀንጥሮ በመጣል የመንግሥትን ሀብት ለራስ ጥቅም ለማዋል ከስፒል ጀምሮ በሚሊዮኖች እስከሚቆጠር ድረስ የሚሰርቅ ማለት ነው፡፡ በቢሮ እንዲጽፍበት የተሰጠውን እስክሪብቶ ለሌላ መሥሪያ ቤቱ ለማይመለከተው ሰው የሰጠም ከሌባ ይመደባል፡፡ ለሥራ የተሰጠውን መኪና አሥር ሜትር ተጉዞ እንኳን ቢሆን ለመንግሥት አገልግሎት ካልሆነ በስተቀር ለግሉ ጥቅሙ ከተጠቀመበት ያው ሌባ ነው፡፡ ለሥራ የተሰጠውን ላፕቶፕ ወይም ሌላ ነገር ለልጁ፣ ለጓደኛው፣ ለወዳጁ የሰጠም ያው ሌባ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡
ሌባ ባለሥልን የግል ጥቅሙን ለማካበት ሲል ሥልጣኑን በመጠቀም፣ ሰነድ በማዘጋጀት፣ የጥበቃ ኃይል በማዘጋጀት፣ ልዩ ልዩ ሕጋዊ ሽፋኖችን በመስጠትና ሕጋዊ በማስመሰል የኮንትሮባንድ ሥራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ይኸው ሌባ ባለሥልጣን ሁሉም ነገር የእሱ አይደለምና መረጃ እንዳይገኝበት ማንኛውንም ሰነድ ድምጥማጡን ሊያጠፋው ይችላል፡፡ ብዙውና ትልቁ ሌብነት ሰነድ በመሰረዝ፣ በመደለዝ፣ እስከ ጭራሹም በማጥፋት የሚከናወን ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ከማጭበርበር ጋር የሚያያዝ ይሆናል፡፡
ረቀቅ ያለው ሌባ ባለሥልጣን ሥልጣኑን በመጠቀም የመንግሥትን ንብረትን ከቀላል እስከ ውስብስብ ዘዴዎችን በመጠቀም ጭምር ወደ ግል ንብረትነት ሲቀይር የሚገኝበት ሁኔታም አለ፡፡ እንዲህ ያለው ሌባ ባለሥልጣን የሌብነት ተግባሩን የሚያከናውነው እጅግ በተራቀቀ ዘዴም ሊሆን ስለሚችል ሕገወጥ ተግባሩ ሕጋዊ እስኪመስል የተራቀቀ ነው፡፡ ሌባ ባለሥልጣን በቀጥታ ራሱን ተሳታፊ በማድረግ ሳይሆን በእጅ አዙርና በሥውር የጨዋዎች ጨዋ በመምሰልም ሊመነትፍ ይችላል፡፡ ሌባ ባለሥልጣን ከብዙዎች ጋር ይወዳጃል፡፡ ይህ ሰው የሚፈልገውን እስኪያገኝ ድረስ በብዙ ሰዎች ዘንድም ጥሩ፣ የዋህ፣ ታማኝ፣ ቃሉን የሚፈጽም መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ ነገር ግን አይደለም፡፡
ሙሰኝነት
በኢትዮጵያ ሙስና የሚለው ቃል አመጣጡ ከግዕዝ ቋንቋ ነው፡፡ ይህ ቃል «ጥፋትና ብልሽት» ከሚለው ግርድፍ ፍቺው በላይ ሰፍቶ «ኮራፕሽን» ከሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ጋር ተመሳሳይ ትርጉም ይዟል፡፡ በመደበኛ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ትርጉም ኮራፕሽን (ሙስና) ማለት ከጥሩ ወይም ከጤነኛ ሁኔታ መለወጥ፣ ከነበረበት የጥራት ደረጃ መቀነስ፣ የሞራል ውድቀት፣ ዋጋ ማጣት፣ መቆሸሽ፣ በጉቦ መላሸቅ፣ ታማኝ አለመሆን፣ በስህተት ወይም በመጥፎነት መበከል እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ከጽንሰ ሐሳብ አኳያ ሙስና በውስጡ የሚያካትታቸው ገጽታዎች በተመለከተ ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ በዚህም ምክንያት በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ትርጉም ማግኘቱ ቀላል አልሆነም፡፡ ይህ ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ ሙስናን የመንግሥት ሥልጣን ተጠቅሞ፣ ሀቀኝነትና ታማኝነት ገሸሽ አድርጎ መልካም ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት በመፈጸም የሕዝብ ሀብትን ለግል ጥቅም በማዋል በሕዝብና በመንግሥት ላይ የሚፈጸም ጥፋት/ጉዳት በሚለው አገላለጽ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ ምክንያትም ሙስና በፖለቲከኞች፣ በመንግሥት ሠራተኞችና ባለሥልጣናት የሚታይን በሥልጣን ያላግባብ መገልገልን ለመግለጽ የምንጠቀምበት ቃል ነው፡፡ ከዚህም በላይ ሙስና በየትኛውም የሕይወት ዘርፍ የሚታይን ብልሹ አሠራር የሚያመለክት ነው (የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ስለሙስና ካዘጋጀው አንድ ጽሑፍ የተወሰደ)፡፡
ዊልያም ፒት የተባለው እንግሊዛዊ መስፍን (1708 እስከ 1778)፣ «ወሰን የሌለው ሥልጣን የባለሥልጣናትን አመለካከት እንደ ብል ወይም ምስጥ እንክት አድርጎ የሚበላ ሲሆን፣ ይህም የሕጋዊ ሥርዓት ማክተሚያ የሕገወጥነት መጀመርያ ይሆናል፤» ሲል ይገልጸዋል፡፡ በእርግጥም የሕጋዊ ሥርዓት ማክተሚያ ሲቃረብ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሕገ መንግሥታቸውን የሚፃረር ተግባር ያከናውናሉ፡፡ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ባህሪ ያለው ጉቦና ሙስና ይስፋፋል፡፡ የበደል መረቡ በሰፊው ይዘረጋል፡፡ ኤድዋርድ ጊቦን የተባለው ኢጣሊያዊም (1737 እስከ 1794) «ሙስና አስተማማኝ የሕገ መንግሥት ልቅነት ዋነኛ መገለጫ ባህሪ ነው፤» በማለት የሮማውያን ዘውዳዊ ሥርዓት መዳከምና መውደቅን አስመልክቶ ባዘጋጀው መጽሐፉ ላይ እንደጠቀሰውም፣ የወጣው ሕገ መንግሥት ከወረቀት ያለፈ ፋይዳ ላይኖረው ይችላል፡፡ ሎርድ አክቶንም (1834 እስከ 1909) «ሥልጣን ለሙስና እንደሚዳርግ የታወቀ ሲሆን ፍፁም ሥልጣን ደግሞ ፍፁም ሙሰኛ ያደርጋል፤» በማለት ለአቡነ ማንዴላ በጻፉት ማስታወሻ መግለጻቸውን ከሥራዎቻቸው እንረዳለን፡፡
ሙሰኝነት ተዛማጅ ዕውቀት የሌላቸውን የቤተሰብ አባላት፣ ዘመዶች፣ አብሮ አደጎች፣ የጥቅም ግንኙነት ያላቸው የመሥሪያ ቤት አባላት፣ የወንዝ ልጆች ወዘተ. በማይገባቸው የሥልጣን ቦታ ማስቀመጥ ማለት ሲሆን፣ ዋነኛ ሥራቸው ባለሥልጣናት በሚፈጽሙት ስህተትና መድልዎ እንዳይጠየቁ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደ ሃይማኖት አባቶች፣ ተቀናቃኝ የፖለቲካ መሪዎች፣ የሚዲያ ሰዎች፣ የታወቁ ምሁራን፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች ከሚችሉት በላይ ድርጎ እንዲሰፈርላቸው በማድረግ አፋቸውን ማስያዝም ከሙሰኝነት ጋር ይያያዛል፡፡
ሙሰኝነት ሥልጣንን ያላግባብ ከመጠቀም ጋርም ሊያያዝ ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ባለሥልጣን ከሌላ አገር ባለሥልጣን ጋር እንዲገናኝ ወደ ውጭ ቢላክና ያን አጋጣሚ ተጠቅሞ የግሉን ተግባር ቢያከናውን፣ ለምሳሌ ‹‹ልጄ የውጭ ትምህርት እንዲያገኝ አድርግልኝ››፣ ‹‹ቤተሰቤ እዚህ እንዲኖር ሁኔታዎችን አመቻችልኝ››፣ ‹‹አንድ የቤተሰቤ አባል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ስላለው የመንግሥት ድጋፍ እንዲያገኝ ተባበረኝ›› ቢልና በሥልጣኑ አማካይነት በግሉ ተጠቃሚ ለመሆን ቢሞክር፣ ወይም ተጠቃሚ ቢሆን ትልቅ የሙሰኝነት መገለጫ ነው፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅሞ በሚስጥር ገንዘብ ተከፍሎ አንዳንድ ነገሮችን እንዲፈጽም ቃል ቢገባ የከፋ የሙሰኝነት ወንጀል ነው፡፡ በጥቅሉ ሙሰኝነትና ጉቦኝነት እጅግ ከፍተኛ ቁርኝት ያላቸው ሲሆኑ የዕድገት ማነቆዎችም ናቸው፡፡
ጉቦኝነት
‹‹ጉቦ›› የሚለው ቃል አዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ‹‹ፍርድን ለማጣመምና ሐሰትን ዕውነት ለማስመሰል ለሐሰተኛ ዳኛ የሚሰጥ መማለጃ ነወ፡፡ ጉቦ ቁሳዊና መንፈሳዊ በረከት ሊሆን ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ሕገወጥ ድርጊትን ለመሸፋፈን ለመፈጸም ለጥፋት ፍርድን ለመገምደል ያገለግላል፤›› በማለት ይገልጸዋል፡፡ በዚህ ትልቅ መዝገበ ቃላት የምናገኘው ታላቅ የሚስጥር ፍቺ፣ ‹‹ጉቦ ቁሳዊና መንፈሳዊ በረከት›› ከሚለው አገላለጽ ነው፡፡ ጸሐፊው ይህን ትርጉም ሲሰጡ ዘርዘር አድርገው የመስጠት ዕውቀት ሳይኖራቸው ቀርቶ ሳይሆን፣ በፊውዳሉ ሥርዓት መልዕክቱ በዚያ መንገድ ተሸፍኖ ካልተላለፈ በስተቀር በምልጃ፣ በደጅ ጥናት፣ በማወደስ፣ በማስቀደስ፣ በመስገድ፣ ወዘተ የሚገለጽ መንፈሳዊ በረከት ተብሎ ቢነገር የሳንሱርን መቀስ ማለፍ ስለማይችል እንደነበረ ልብ ይሏል፡፡ ይሁንና «ጉቦ ቁሳዊና መንፈሳዊ በረከት ሊሆን ይችላል፤» በሚል የቀረበ ስለሆነ ቁሳዊው በገንዘብ፣ በንብረት፣ በከብት፣ በምርት፣ በልዩ መልክ በተዘጋጀ ስጦታ ሲሆን፣ መንፈሳዊው ደግሞ በማይጨበጥ፣ በማይዳሰስና በማይታይ መንገድ የሚሰጥ መሆኑ ነው፡፡
ስለዚህም የአዲስ አማርኛ መዝገበ ቃላትን ፍቺ ተከትለን የጉቦን ትርጉም ለማብራራት ስንሞክር፣ በአብዛኛው «ቁሳዊና መንፈሳዊ በረከት» የሚባለው በዓይነት የሚሰጥ ሲሆን ከጥቃቅን በረከቶች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ እንደሆነ በማያሻማ ሁኔታ እንረዳለን፡፡ ፍርድን ለማጓደል፣ ለመገምደል፣ ሕገወጥ ድርጊትን ለመፈጸም፣ ለመሸፋፈን፣ ወዘተ ሐሰትን እውነት ለማስመሰል ከሆነ በስጦታ መልክም ይምጣ፣ በበረከት፣ በእጅ ማራሻም ሆነ በጉርሻ፣ በምልጃም ይሁን በደጅ ጥናት፣ በማሞገስም ሆነ በማሞካሸት፣ የቅዱሳን ሁሉ ቅዱስም ሆነ የብፁዓን ሁሉ ብፁዕ አድርጎ በግልም ሆነ በጋራ ማቅረብ የማይገባን ጥቅም ለማግኘት ከሆነ ያው «ጉቦ» ነው፡፡
ይህንኑ ቃል ዌብሰተር የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ መስረቅ፣ መዝረፍ፣ ማጭበርበር፣ ማታለል፣ ከፍተኛ እምነት የተጣለበትን ዳኛ ወይም ባለሥልጣን ኃላፊነቱ እንዲዘነጋ የሚሰጥ ሽልማት፣ ስጦታ፣ ውለታ በማለት ያፍታታዋል፡፡ ብላክስ ሎው የተባለው የታወቀ መዝገበ ቃላት ደግሞ (አነስተኛም ይሁን ከፍተኛ) በሕጋዊ ኃላፊነት ያለን ባለሥልጣንን (በአንድ ጉዳይ ላይ ያለውን) አመለካከት፣ አስተሳሰብ በተፅዕኖ ለማሳመን ሲባል ማንኛውንም ዋጋ ያለውን ነበር በስጦታ፣ በበረከት፣ በድርጎ፣ ወይም በሌላ መልክ መስጠትና መቀበል እንደሆነ ይገልጸዋል፡፡ እንደዚሁ በሌላ መዝግበ ቃላት ትንታኔ «የራስ ያልሆነን ሀብትና ንብረት በተለያየ መልኩ መውሰድ» ማለት እንደሚሆኑ በቀጥታ እከስ ውስጥ ዘው ብሎ ባይገባ፣ ቤት ሰርስሮ ሳጥን ሰብሮ በድፍረት ባይሰርቅ፣ አሳቻ ቦታ ቆሞ ባይነጥቅ፣ የዚያን ከዚህ አምጥቶ የማይሆነውን ይሆናል የሚሆነውን አይሆንም በሚል ወይም ልብን አፍዝዞና አደንግዞ ባይወሰድ፣ ጉቦ የራስ ሀቅ ያልሆነን ሀብት፣ ንብረት ወይም ሌላ መንፈሳዊ ስጦታ፣ በሥልጣን ተጠቅሞ መቀበል፣ መሥረቅ፣ መዝረፍ፣ ማጭበርበርና ማታለል መሆኑን እንረዳለን፡፡
ጉቦኝነት ማለት ደግሞ አዲስ ነገር ለማግኘት ወይም ካለው ለመጨመር፣ ግብር ለማስቀነስና ለመታለል፣ የንግድ ተቀናቃኞችን ለማጥፋትና የራስን ሥራ ለማስፋፋት፣ በጨረታ ለማሸነፍና ሚስጥሩን ለመሸፋፈን፣ ከተመን በላይ ለመሸጥና ለመግዛት፣ ገበያ ሞቅ ወዳለበት አካባቢ ለመሄድና ለመመለሰ፣ ጥሬ ዕቃን ከአገር ውጭ ለማስወጣትና ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት፣ መናኛ ሸቀጦችን ለመሸጥና ለመለወጥ፣ በሥራ ላይ የማይውሉ የመለዋወጫ ዕቃዎቻቸው ዋጋ እንዲያወጡ ለማድረግ፣ ጥሬ ዕቃዎቻቸው በገበያ የማይገኝ ፋብሪካዎችን ለማስገዛት፣ ወዘተ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመገናኝት ሁኔታዎችን በማመቻቸት ጉቦ መቀበል ሊሆን ይችላል፡፡
በአገራችንም ሆነ በሌላ በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች በግብር መታለፍ ወይም አለመሰብሰብ ሳቢያ የሚቦጠቦጠው የመንግሥትና የግለሰብ ወይም የቡድን ሀብት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ የዛሬ 30 ዓመትና ከዚያ በፊት የደርግ የሠርቶ አደሩ ቁጥጥር ኮሚቴ መዛግብት ያመለክቱት እንደነበረው ሁሉ፣ ከአንድ እስከ አሥር ሚሊዮን ብር የሚደርስ የመንግሥት ውዝፍ ግብር የሚፈለግበት ግለሰብ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ጉቦ እንዲከፍል ይጠየቅ እንደነበረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከአሥር ሚሊዮን ተነስተን እስከ መቶ ቤት ያለውን ስናሰላ በጉቦ ምክንያትና ለጉቦ የሚወጣው ገንዘብ ብዛት ምን ያህል እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡ ይህም ኃላፊነታቸውን ለዘነጉ ሰዎች የሚሰጠው ደመወዝ፣ አበል፣ ትራንስፖርት፣ ሌላም ሌላም የሚፈሰው የብር መጠን ሳይጨመር ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ ወደ ‹‹ነፃ ኢኮኖሚ›› የገባን ስለሆነ ማለትም ከብዙ ልማት ጋር ብዙ የሥልጣን መባለግና ማባለግ ዘዴው እጅግ ብዙ ስለሆነ ሊጨምር እንጂ ሊቀንስ አይችልም፡፡ ለምሳሌ አንድ ከውጭ የሚመጣ የንግድ ዕቃ ለማምጣት ከታሰበበት ጊዜ ጀምሮ ትርፍና ኪሳራው ስለሚታሰብ የት ቦታ በዝቅተኛ ዋጋ እንደሚገዛ፣ ምን ዓይነት ደረጃ ሊጻፍበት እንደሚገባ፣ እንዴት እንደሚጫን፣ እንዴት እንደሚራገፍ፣ እንዴት የቀረጥን መስመር ሰብሮ ወይም ሕጋዊ ካባ ለብሶ ግለሰቡ መደብር እንደሚገባ ሲሰላ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በቁሳዊና መንፈሳዊ ሙስና ታጅቦ የሚሆንበት ጊዜ ይኖራል፡፡
ሁሉንም የሙስና ብልግና ወይም የሥልጣን ብልግናን ለመግለጽና አፀያፊነቱን ለመግለጽ በእጅጉ ሰፊ ቦታና ጊዜ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ እንዲያው ለመሆኑ አገራችን የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው አስመጪና ላኪዎች የሚነግዱባትና የትርፍ ትርፍ የሚዝቁባት፣ በአጭር ጊዜም በሙስና ሮኬት ተወንጭፈው በከፍተኛ የብልፅግና ደረጃ የሚደርሱባት፣ በሀቅ ሲሠሩ የሚከስሩባትና የሚደኸዩባት፣ ሞላጫ ሌቦች በቁጥጥር አካል ቢጠየቁ ያለምንም ተፅዕኖ እንዲለቀቁ ለማድረግ፣ የሐሰት ሰነድ አዘጋጅቶ የተለየዩ እርከኖችን እንዲያልፉ ለማስቻል፣ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ንብረት አስመስሎ ከቦታ ቦታ ለማዘዋወር፣ ወዘተ. ጥረት የማይደረግባት ናትን? ለመሆኑ ሰዎች በተሾሙ ማግሥት የተወለወለ ብርጭቆ መስለው የሚታዩት ሠርተው ባገኙት ደመወዝ በልተውና ጠጥተው ነው? እንዴት ነው በተሾሙ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ባለ ቪላና ባለ ፎቅ የሚሆኑት? ልጆቻቸውን በመቶ ሺሕ እየከፈሉ የሚያስተምሩት? ይህ እንግዲህ በጎን የሚያወጡት ሌላ ወጪ ከሒሳብ ሳይገባ ነው፡፡ ለመሆኑ ሕዝብ የማያውቀው ገበና አለ?
ብልሹ አስተዳደር
በሌሎችም አገሮች ቢሆን፣ ማንኛውም ሠራተኛ በሥልጣኑ ሥር እንዲንበረከክና መጥፎ ድርጊት ሲፈጸም «አሜን» ብሎ እንዲቀበለው ለማድረግ በልዩ ልዩ የቢሮክራሲ ሥልቶች መጠቀም ጥንትም ሆነ ዛሬ የተለመደ ነው፡፡ ይልቁንም በበርካታ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በመንግሥት ሀብትና ንብረት፣ እንዲሁም ሥልጣን በንግድም ሆነ በሌላ መንገድ ለመጠቀም በጥቅሉ የማይፈነቀል ድንጋይ የለም ማለት ይቻላል፡፡ በእነዚህ የልማት ድርጅቶች ግልጽነት የጎደለውን አሠራር በማስፈን የሚፈጸመው ደባ እንዲህ በቀላሉ መተንተን አስቸጋሪ ነው፡፡ ሁነኛ ሰዎችን በዋና ዋና መዋቅሮች እንዲሁም ሕዝባዊ ማኅበራት በማስቀመጥ፣ በልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞች በመያዝ፣ የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸው በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ በማሰለልና አደገኛ ሆነው ካገኟቸው ምንም ያህል ለድርጁቱ ጠቃሚ ዕውቀት ይኑራቸው ልዩ ልዩ ስሞችን በመቀባትና የሐሰት ወሬ በማስወራት፣ እነሱ ከሳሽ እነሱ ፈራጅ በመሆን በከፍተኛ ወንጀል በመቅጣት፣ አንገታቸውን እንዲደፉ ማድረግ ወይም በመንግሥት ሀብትና ንብረት ጠበቃ ቀጥረው መቀመቅ እንዲወርዱ በማድረግ፣ በኃላፊነት ያሉትን በማንኛውም ጊዜ ሊያፈናቅሏቸው እንደሚችሉ በማስፈራራት፣ ለዕንባ ጠባቂዎቻቸው አግባብ ያልሆነ ወረታ በመክፈል፣ የሕዝብንና የመንግሥትን አደራ ወደጎን ትቶ በሥልጣን በመባለግ፣ ያላግባብ የደመወዝ ዕድገት በመስጠት፣ ዘመድ አዝማድን በቀጥታ ወይም በተለዋጭ በመቅጠር፣ የሙስና/ጉቦ ሥልትን አስፋፍቶ መኖርም አለ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ባለጉዳዮችን ማጉላላት፣ ሕግን አጣሞ ለመተርጎም መሞከር፣ ለጉዳዩ ቁም ነገር አለመሰጠት፣ ባለጋራን ለመጥቀም የተነሱ መስሎ መታየት፣ ተስፋ ለማስቆረጥ መሞከር፣ ጉዳዩ በእጃቸው እያለ በሌሎች እንዳለ አስመስሎ መንገር፣ ሰዎች በቀላሉ አግኝተው የሚያነጋግሯቸው ሰዎች በእነሱ አማካይነት ለመደለል ሐሳብ ማቅረብ፣ መልካም ፍፃሜ ያገኘውን ጉዳይ እንዳላለቀ፣ ገና ብዙ እንደሚቀረው እየተነተኑ ለጉቦ ማዘጋጀት ጥቂቶቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡
የውሸት ባለሥልጣንነት
ባለሥልጣናት ጥሩዎች፣ በጣም ጥሩዎችና እጅግ በጣም ጥሩዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በአንፃሩ መጥፎዎች፣ በጣም መጥፎዎችና እጅግ በጣም መጥፎዎች የሚሆኑበት ሁኔታ አለ፡፡ መጥፎዎቹ ባለሥልጣናት አሠራራቸው ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበትና በማንኛውም ጊዜ የፈለጉትን ሊወጥኑ፣ የወጠኑትን ሊያፈርሱ ይችላሉ፡፡ ድሮውንም ለምን እንደወጠኑት አያውቁትምና ሥራቸው ግልጽነት ሊኖረው አይችልም ከሕግ የበላይ ናቸውና የሚጠይቃቸው የለም፡፡ ከውሸት ባለሥልጣናት የሚመደቡ ናቸው፡፡
‹‹ሪል ላይፍ ሀቢት ኦፍ ሰክሰስ›› በሚል ርዕስ መጽሐፍ እንዳሳተሙ የሚነገርላቸው ጀፍሪ ቤንጃሚን፣ ‹‹ሰዎች የሀቅ መሪዎች ነን ብለው ያውጁ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የውሸት መሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤›› በማለት ይጀምሩና ዓይነታቸውን በ12 ይከፍሉታል፡፡ በጀፍሪ ቤንጃሚን ትንታኔ መሠረት የመጀመርያዎቹ አስመሳዮች ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉት ባለሥልጣናት የሚናገሩት ከሚያደርጉት ፍፁም ተቃራኒውን ነው፡፡ ስለሆነም በእነዚህ ሰዎች የአስመሳይነት ንግግር ከመስማት ይልቅ ፊታቸውን መመልከት ይሻላል፡፡ ሁለተኛው ዓይነት አስመሳይ መሪ መብለጭለጭ የሚወድና በዚያ አብለጭላጭ ሐሳብ የሰውን ስሜት ለመማረክ የሚፈልግ ነው፡፡ እንደዚህ ያሉ መሪዎች የሰውን መልካም ምኞትና ፍላጎት መሠረት በማድረግ፣ ‹‹ይህን እናደርጋለን፣ ይህን እንሠራለን፣ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያስችል መንገድ ሠርተናል፡፡ ድልድይ አበጅተናል፤›› ሊሉ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ መናኛ ነገሮችን በማሳየትና የእነሱ ጋሻ ጃግሬ ምሁራንን እንዲወሸክቱ በማድረግ፣ ‹‹በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ሰዎችን ወደ ህዋ እናመጥቃለን፤›› ሊሉ ይችላሉ፡፡ ጀፍሪ ቤንጃሚን እንደሚሉት ሦስተኛዎቹ ባለሥልጣናት ላልተከናወነው ተግባር መፍትሔ መፈለግ ሲገባቸው፣ ድሮውንም አስበው ያቀዱት ስላልነበረ ባይሳካላቸው ጥፋታቸውን ወደ ሕዝብ የሚያላክኩ ናቸው፡፡ እነዚህ ባለሥልጣናት፣ ‹‹እኛ እንዲህ ለማድረግ ፈልገን ነበር፡፡ ነገር ግን ከፊታችን የተጋረጡ ጠላቶቻችን ሊያሠሩን አልቻሉም፡፡ ሕዝቡም የእኛን አመራር መቀበል ሲገባው የእነሱ ምርኮኛ ሆኖ ተገኘ፡፡ ስለሆነም በሕዝብ ምክንያት የገባነውን ቃል ለመፈጸም አልታደልንም፤›› በማለት የሽቀባ ጽንሰ ሐሳብ ያራምዳሉ፡፡
አራተኛዎቹ የሐሰት ባለሥልጣናት ሕዝብን አሳምኖ ለማሠራት ከመሞከር ይልቅ አስገድደው ለማሠራት ይፈልጋሉ፡፡ ድዋይት አይዘንአወር የተባሉት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት (1890-1969)፣ ‹‹ጥሩ አመራር (ባለሥልጣን) ማለት የምትፈልገውን እንዲሠራልህ ፈልጎ እንዲሠራለት ለማድረግ የሚችል ጥበብ ያለው ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ የውሸት መሪዎች ግን ሠራተኛ መስለው ለመገኘት ሰውን በኃይለኛ ቁጥጥር ለማሠራት የሚሹ ናቸው፡፡ አምስተኛዎቹ ዓይነቶች ስለታላቅነታቸው ራሳቸው ለራሳቸው የሚመሰክሩ፣ ወይም በተራ አባባል ጉራቸውን የሚቸረችሩ ዓይነት ናቸው፡፡ በአንፃሩም ምርጥ መሪ የራሳቸውን ጥቅም የማያስቀድሙ፣ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉና ብዙ ቢሠሩም ብዙ እንደሚቀራቸው ለራሳቸው የሚመሰክሩ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን የጓዶች ሥራ ሊያድግና ሊመነደግ የሚችለው አለቆች የተሠራውን ሥራ አድናቂና ምሥጋና ለሚገባቸውም አመሥጋኝ ሆነው ሲገኙ ቢሆንም፣ ስድስተኛዎቹ የውሸት አመራሮች ግን ሌላ ሰው የሠራውን ሁሉ ራሳቸው የሠሩት አስመስለው የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ ሰባተኛዎቹ የውሸት መሪዎች ቃላቸውን የሚያጥፉ (ከሃዲዎች) ሲሆኑ፣ እነዚህ ባለሥልጣናት ‹‹አደርገዋለሁ፣ እፈጽመዋለሁ፣ አከናውነዋለሁ›› ብለው ቃል የገቡትን፣ ‹‹አላልኩም፣ አልወጣኝም፣ እንዴት ተብሎ›› በማለት የሚሸመጥጡ ወይም፣ ‹‹ዓይኔን ግንባር ያድርገው›› ብለው የሚምሉ ናቸው፡፡ ቻይናውያን፣ ‹‹መንግሥትህን ስትመራ ትንሽ ዓሳ የምታበስል ቢሆን በተመጣጣኝ የእሳት መጠን ይሁን፤›› በማለት የሚሰጡት ምክር ለሐሰተኛ መሪ አይሠራም፡፡ ስምንተኛዎቹ የውሸት መሪዎች ‹‹እሠራዋለሁ›› ብለው ያልሠሩት ድሮውንም ሊሠሩት እንደማይችሉ እያወቁ ቢሆንም ላለመሥራታቸው ምክንያት መደርደር ያበዛሉ፡፡
እነዚህ ባለሥልጣናት በሚያከናውኑት ተግባር ለተጠያቂነትን መርህ ባዕድ በመሆናቸው በማናለብኝነት ምክንያት ይደረድራሉ፡፡ አሜሪካዊው ፕሬዚዳንት ቤንጃሚን ፍራንክሊን (1706-1790) ግን፣ ‹‹ምክንያትን የሚያበዛ አብዛኛውን ለምንም ጥሩ አይደለም፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡ ዘጠነኛዎቹ የውሸት ባልሥጣን ዓይነቶች ለሁሉም ጥያቄ መልስ ያላቸው ዓይነቶች ሲሆኑ፣ የእውነተኛዎቹ ግን የሌሎችን ሐሳብ የሚያዳምጡ ናቸው፡፡ ከ370 ዓመታት ቅድመ ልደት የነበረውና ፕሌቶ የሚባለው ግሪካዊ ፈላስፋም ‹‹መታዘዝን ያልተማረ ጥሩ አዛዥ ሊሆን አይችልም፤›› በማለት ይተቸዋል፡፡ አሥረኛው ዓይነት የውሸት ባለሥልጣን ለበታቾቹ ምንም ዓይነት ክብር የለውም፣ የፈለገውን ሊላቸው ይችላል፡፡ ማክበር ሲገባው ያዋርዳል፣ መደገፍ ሲገባል ይጥላል፣ ያጣጥላል፡፡ አሥራ አንደኛዎቹ የውሸት ባለሥልጣናት የሚተኳቸውን ሰዎች ማፍራት ሳይሆን የሚከተሏቸውን ቢያፈሩ ይመርጣሉ፡፡ እንዲፈሩ ማድረግ ዓይነተኛ መርሐቸው ነው፡፡ የውሸት ባለሥልጣናት አሥራ አምስተኛ ባህሪ የሚቃረናቸውን፣ የሚሞግታቸውን፣ ከእነሱ የተሻለ የሚመስላቸውን ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም መበቀል ነው፡፡ ይህም ሁሉ ስለእውነት የሚናገሩት እነሱ፣ ስለአዎንታዊ አስተሳሰብ የሚናገሩት እነሱ፣ ስለብሩህ ተስፋ የሚናገሩት እነሱ ይሆናሉ፡፡ አለመታደል ሆነና እነዚህ ከውሸት ባለሥልጣናት ጋር የሚመደቡት ናቸው፡፡
ማስታወሻ
በዚህ ጽሑፍ ‹‹ሌባ፣ አጭበርባሪ፣ አድሏዊ፣ ተውሳክ (ጥገኛ)፣ ከሃዲ፣ አስመሳይ፣ ጉቦኛ፣ ሙሰኛ፣ ወዘተ.›› ብለን የምንጠራው ባለሥልጣን በየትኛውም አገር ሊኖር የሚችል ባለሥልጣን እንጂ በአንድ አገር ወይም በአንድ አካባቢ የተወሰነ አለመሆኑን ጸሐፊው ለማሳወቅ ይፈልጋል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡