Wednesday, November 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየሰላም ተስፋ ያልታየበት የብሊንከን የዓረብ አገሮች ጉዞ

የሰላም ተስፋ ያልታየበት የብሊንከን የዓረብ አገሮች ጉዞ

ቀን:

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ዓረብ አገሮች አጥብቀው በጠየቁት፣ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል የተጀመውን ጦርነት ማስቆምና የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ ላይ ከዓረብ አገሮች መሪዎች ጋር የመከሩት ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ነው፡፡

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በእስራኤልና ፍልስጤም መካከል ጦርነቱ ከተጀመረ ከአንድ ወር ወዲህ ከዓረብ አገሮች ባለሥልጣናት ጋር ለሁለተኛ ጊዜ ያደረጉትን ውይይት አጠናቀዋል፡፡ ሆኖም በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል የተጀመረውን ጦርነት ለማስቆም ከሚያስችል ስምምነት ላይ አልደረሱም፡፡

ሮይተርስ እንደዘገበው፣ ብሊንከን በመካከለኛው ምሥራቅ የነበራቸውን የአራት ቀናት ጉዞ ቢያጠናቅቁም፣ ጉዟቸው ይህ ነው የሚባል ለውጥ አላመጣም፡፡ መነሻው ሃማስ በእስራኤል ላይ የወሰደው ድንገተኛ ወታደራዊ ጥቃት ቢሆንም፣ እስራኤል በጋዛ ላይ እየወሰደች ያለችው የአየር ድብደባም ጋዛን እያፈራረሳት ነው፡፡

ቀድሞውንም በሰላም ኖረው የማያውቁት እስራኤልና ፍልስጤም፣ በተለይ ከጥቅምት 2016 ዓ.ም. መጀመርያ ጀምሮ የገቡበት ጦርነት እየተባባሰ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም፡፡     

በፍልስጤም ጋዛን የሚያስተዳድረው ሃማስ ወደ እስራኤል በድንገት ተኩሶታል በተባለው የሮኬት ጥቃት የተጀመረውና ዛሬ ላይ ከሁለቱም ወገን ከ12 ሺሕ በላይ ንፁኃን እንዲቀጠፉ ምክንያት የሆነው ጦርነት፣ በተለይ ጋዛን እያፈራረሳት ይገኛል፡፡

እስራኤል 1,400 ዜጎቿ ተገድለው 240 ያህል በሃማስ ሲታገቱባት፣ በፍልስጤም በኩል ከ4000 በላይ ሕፃናትን ጨምሮ ከአሥር ሺሕ በላይ ተገድለዋል፡፡

ከእስራኤል ጎን የቆመችው አሜሪካ በእስራኤልና ፍልስጤም መካከል ያለውን ጦርነት እንድታስቆም ከዓረብ አገሮች መሪዎች ግፊት ቢደረግም፣ ለውጥ አልታየም፡፡

በእስራኤል ጋዛ ጦርነት ከዮርዳኖስ፣ ከግብፅና ከሌሎች የዓረብ አገሮች የመከሩት ብሊንከን፣ ከዓረብ አገሮች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል አሜሪካ ለእስራኤል እያደረገች ያለውን ድጋፍ ዕፎይታ እንድታደርግ የሚለው ይገኝበታል፡፡

የዮርዳኖስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይማን ሳፉዲ፣ ‹‹ይህንን ዕብደት ለማስቆም አብረን መሥራት አለብን፤›› ሲሉ፣ የግብፁ አቻቸው ሳሜህ ሽኩሪ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም ይደረግ ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢኒያሚን ናታንያሁ፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም የሚለውን ባለመቀበል፣ በቅድሚያ ሐማስ ያገታቸውን እስራኤላውያን ይልቀቅ ብለዋል፡፡

በሐማስ በኩል ወታደሮችን ጨምሮ የታገቱ የእስራኤል ዜጎችን ለመልቀቅ በእስራኤል እስር ቤቶች የታጎሩ ከ6,000 በላይ ፍልጤማውያን መለቀቅ አለባቸው የሚል ሐሳብም ተነስቷል፡፡

ከተኩስ አቁሙ ስምምነት ለመድረስ ከእስራኤል ወገን በፍልስጤም ጋዛ የታገቱና፣ ከፍልስጤም ወገን በእስራኤል የታሰሩ ከ6000 በላይ ዜጎች ለመደራደሪያነት ይቅረቡ እንጂ፣ አሜሪካ አፅንኦት ሰጥታ ተኩስ ይቁም ያለችበት መድረክ አልተስተዋለም፡፡

ለእስራኤል ወታደሪዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ በማድረግ ለአሠርት ዓመታት አጋርነቷን የገለጸችው አሜሪካ፣ አሁን እየተካሄደ ላለው የእስራኤል ፍልስጤም ጦርነት እስራኤል ራሷን መከላከል አለባት በሚለው አቋሟ እንደፀናች ነች፡፡

ከዓረብ አገሮች ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ የመከሩት ብሊንከንም ተኩስ አቁሙ እንዲደረግ እንደሚገፉበት በግልጽ አልተናገሩም፡፡ ይልቁንም ‹‹አሜሪካ እስራኤል በጋዛ እየወሰደች ያለውን ወታደራዊ ዕርምጃ ብታቆም ሐማስ እንደነበረ እንዲቆይ፣ መልሶ እንዲደራጅ እንዲሁም ተመሳሳይ ጥቃት እንዲፈጽም ማስቻል ነው የሚል እምነት እንዳላት ገልጸዋል፡፡

‹‹ማንኛውም ሕዝብ፣ ማንኛችንም ይህንን [ተኩስ አቁሙን] አንቀበልም፡፡ የእስራኤልን መብት እናረጋግጣለን፡፡ እስራኤል ራሷን መከላከል አለባት፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ባልተለመደ መልኩ የዮርዳኖስና የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ከአሜሪካ አቻቸው ጋር የነራቸውን አለመስማማት ፊት ለፊት ያመጡት ሲሆን፣ በተለይ በአሜሪካ በኩል ‹‹ወደ ፊት ጋዛ ምን ትሁን?›› የሚለው ላይ ለመወያየት የተነሳው ሐሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

የዮርዳኖሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ‹‹ጋዛ እየወደመች ነው፡፡ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የአሁኑን ጦርነት ማስቆም እንጂ፣ በቀጣይ ጋዛ እንዴት ትሁን የሚለው አይደለም፤›› ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡

ጦርነት በሚቆምበት ሁኔታ መሥራትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ጦርነትና ጥቃት እንዳይቀጥል ኃላፊነት መውሰድ ይገባል ብለዋል፡፡

የእስራኤል መስፋፋትና የዜጎች ሠፈራ ፕሮግራም በፍልስጤም ዘንድ ሕገወጥ ነው ተብሎ መነገር ከጀመረ ዓመታት ያለፈውና ለጦርነት ዋና መነሻው ቢሆንም፣ አሜሪካም ሆነች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን መሠረታዊ ችግር ለመቅረፍ አልሠራም፡፡ ይህንን ሞግቶ የሚቃወመውና በፍልስጤም ጋዛን የሚያስተዳድረው ሃማስ በአሜሪካ የሽብር ቡድን ዝርዝር ውስጥ ከሰፈሩት አንዱ ነው፡፡

የዮርዳኖስ ንግሥት ራኒያ አል አብዱላሂ ከሲኤንኤን ጋር በነበራቸው ቆይታም ያነሱት፣ የእስራኤል ሕገወጥ መስፋፋት የችግሩ መሠረት መሆኑን ነው፡፡ ለዚህ መፍትሔ ሳይሰጥ ሰላም ለማስፈን አይቻልምም ብለዋል፡፡

‹‹መሠረታዊ ችግሩ ካልተፈታ ተዋጊዎችን መግደል ይቻል ይሆናል እንጂ ምክንያቱን ማጥፋት አይቻልም፡፡ ከሕንፃ ፍርስራሽ ሥር የተሻለና ቁርጠኛ የሆነ ቡድን ይወጣል፡፡ ሐማስ የሚፈጽመውን በተሻለ የሚፈጽም ይመጣል›› ሲሉም አክለዋል፡፡

እስራኤል እስከመጨረሻው ደኅንነቷን ለማረጋገጥ ከፈለገች በሰላማዊ መንገድ እንድታደርግ፣ ጠንካራ መከላከያ፣ የደኅንነት አቅም ወይም አይረንዶም ሰላም እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ በበኩላቸው፣ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ተማፅነዋል፡፡

በጋዛ የተከሰተው ቀውስ የሰብዓዊ ብቻ ሳይሆን ሰው ላይ የደረሰ ቀውስ ነው የሚሉት ዋና ጸሐፊው፣ ከአራት ሺሕ በላይ ሕፃናት መገደላቸውን፣ በየቀኑ በመቶ የሚቆጠሩ ሴትና ወንድ ልጆች የሚጎዱና የሚሞቱ እንደሆነም አክለዋል፡፡

በግጭቱ ውስጥ ያሉ አካላት ብሎም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ ሁሉንም እየጎዳ ያለውን ጦርነት የማስቆም ኃላፊነት አለበትም ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...