የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ፣ የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት በአስቸኳይ ካልቆመ በመካከለኛው ምሥራቅ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግ በግልጽ መጣሱ በጣም እንደሚያሳስባቸው ከተናገሩት የተወሰደ፡፡ ማንም ሰው ከዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግ የበላይ መሆን አይችልም ያሉት ጉተሬስ፣ ለሰላማዊ ሰዎች የሚደረገው ጥበቃ ከምንም ነገር በላይ መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡ በጋዛ በፍልስጤም ሕፃናት ላይ እየደረሰ ያለው ፍጅትና ጉዳትም እንዲቆም በመጠየቅ፣ ‹‹ጋዛ የሕፃናት መካነ መቃብር መሆኗ ያሳስባል›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ሐማስ በፈጸመው የሽብር ጥቃት ያደረሰውን ጉዳት ያወገዙት ዋና ጸሐፊው፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በፍጥነት ያገታቸውን ሰዎች እንዲለቅ በድጋሚ ጥሪ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ ሰላማዊ ሰዎችን መጉዳት፣ ማሰቃየት፣ መግደልና ማገት ፍትሐዊ ሊሆን አይችልም ብለዋል፡፡ ከመካከለኛው ምሥራቅ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከአሥር ሺሕ በላይ ፍልስጤማውያን ሲሞቱ፣ የሕፃናቱ ቁጥር ከአራት ሺሕ በላይ ሲሆን፣ በእስራኤል በኩል 1,400 ያህል ተገድለው ከ200 በላይ ሰዎች በሐማስ ታግተዋል፡፡