በማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ጥበቃ ስምምነት መሠረት የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በአምስት ምድቦች ይከፈላሉ፡፡ በአፋዊ ትውፊቶችና መገለጫዎች ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል የሚተላለፉ ተረቶች፣ አፈ ታሪኮች፣ የቃል ግጥም፣ እንቆቅልሾች፣ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ይገኙበታል፡፡ በማኅበራዊ ክንዋኔዎች፣ ሥነ ሥርዓቶችና ፌስቲቫሎች ሥር፣ የተለያዩ ክብረ በዓላት፣ የምርት ሥራ መጀመር ወይም መጠናቀቅን አስመልክቶ የሚከበሩ የምሥጋና ወይም የተማፅኖ ሥርዓቶች፣ ከልደት፣ ሠርግና ሞት ጋር የተያያዙ ሥነ ሥርዓቶች፣ ባህላዊ የስፖርት ጨዋታዎች፣ ባህላዊ የዳኝነትና የዕርቅ ሥርዓቶች፣ ደቦና ዕድር የመሳሰሉ ነባር የኅብረት ሥራ ባህሎችና መረዳጃዎች፣ የዝምድና መመሥረቻ ሥርዓትና የሰውነት አጊያጌጥ ሲካተቱ፣ በአገር በቀል ዕውቀቶች ደግሞ ባህላዊ ሕክምና፣ ባህላዊ እርሻና የእንስሳት ዕርባታ፣ ባህላዊ የምግብና መጠጥ ዝግጅትና አጠባበቅ፣ ባህላዊ የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት፣ የአካባቢ ጥበቃና የሥነ ምኅዳር ዕውቀት ይመደባሉ፡፡ የቆዳ፣ የሸክላ፣ የሽመና፣ የእንጨትና የብረት ሥራ ዕውቀትና ክህሎት፣ ሌሎች የቅርፃ ቅርፅ፣ የንድፍ፣ የብራና አዘገጃጀትና አደጓጐስ ዕውቀትና ክህሎት፣ ከትውፊታዊ የዕደ ጥበብ ዕውቀቶችና ክህሎቶች ሲካተቱ፣ አገረሰባዊ ትውን ጥበባት ደግሞ አገረሰባዊ ጭፈራዎችንና አገረሰባዊ ቴያአትሮችን ያካትታሉ፡፡
(ቅርስ ባለስሥልጣን)