የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን የቴኒስ ስፖርትን ለማስፋፋት ባደረገው እንቅስቃሴና የዓለም አቀፍ ውድድሮችን በማስተናገዱ ከዓለም አቀፍ ቴኒስ ፌዴሬሽን ሽልማት ተበረከተለት፡፡
50ኛው አፍሪካ ቴኒስ ኮንፌዴሬሽን ስብሰባ በተሰናዳበት ኬንያ ሽልማት የተበረከተለት ፌዴሬሽኑ፣ በአፈጻጸሙ ከምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ በመሆኑ ሽልማት እንደተቸረው ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን እ.ኤ.አ. በ2022 እና 2023 የቴኒስ ስፖርትን በኢትዮጵያ ለማስፋፋትና ስፖርቱን ተወዳጅ ለማድረግ፣ በታዳጊ ወጣቶችና በትምህርት ቤቶች እንቅስቃሴ እንደገና እንዲጀመርና ከዋና ከተሞች በዘለለ በክልሎች እንዲስፋፋ ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡
ከዚህም ባሻገር የባለሙያዎች አቅም ግንባታ በተከታታይ ለዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ለአሠልጣኞችና ለዳኞች፣ እንዲሁም ከጀማሪ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ሥልጠናዎችን የባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ እንዳሸለመው፣ የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታምራት በቀለ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ፌዴሬሽኑ በ2015 ዓ.ም ለመጀመርያ ጊዜ የወጣቶች እንዲሁም የአዋቂዎች ዓለም አቀፍ ውድድር በአዲስ አበባ በማዘጋጀት፣ ከ33 አገሮች የተወከሉ ተወዳዳሪዎችን በማወዳደርና 14 ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች እንዲወዳደሩ ማድረግ መቻሉ ተጠቅሷል፡፡
በአዲስ አበባ በተሰናዳው ውድድር ከ27 አገሮች በላይ የተሳተፉበት ኤምኤስ (MS) የአዋቂ ወንዶች ውድድር ወጣት ኢትዮጵያውያን ተካፍለውበታል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም የኢትዮጵያ ቡድን ሰኔ 2015 ዓ.ም. በዲሞክራቲክ ሪፐብክ ኮንጎ በተዘጋጀው በዴቪስ ካፕ ውድድር ላይ በመሳተፍ ከ23 አገሮች ሰባተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡
የቴኒስ ቡድን በሩዋንዳ ኪጋሊ በሴቶች ቢል ጂን ኪን ካፕ በተካሄደው ውድድር ለመጀመርያ ጊዜ በመሳተፍ፣ ከ13 አገሮች አምስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ ዓምና ዓለም አቀፍ የሜዳ ቴኒስ ውድድር ማሰናዳት የቻለው የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ዘንድሮም ውድድሩን የማስተናገድ ዕድል አግኝቷል፡፡
በዓለም ከሚዘወተሩ ስፖርቶች መካከል የሜዳ ቴኒስ ይጠቀሳል፡፡ የኦሊምፒክ ስፖርት የሆነው የሜዳ ቴኒስ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን በፈረንሣይ የተጀመረ ሲሆን፣ ዘመናዊው የቴኒስ ጨዋታ የተጀመረው በእንግሊዟ በርሚንገሃም እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ቴኒስ በኢትዮጵያ በመጀመሪያ የተዋወቀው በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን (1881-1909) በፈረንሣይ የምድር ባቡር ሠራተኞች አማካይነት እንደሆነ፣ በ1930ዎቹ መዘውተር መቀጠሉና ክለብም መቋቋሙ ይወሳል። በጊዜ ሒደትም በተለያዩ ዓበይት ከተሞች ቴኒሱን በግል ሆነ በቡድን የሚያዘወትሩ ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡
በኢትዮጵያ የሜዳ ቴኒስ በፌዴሬሽን ደረጃ የተቋቋመው በ1972 ዓ.ም. በስፖርትና የአካል ማሠልጠኛ ኮሚሽን አማካይነት ነው፡፡
የሜዳ ቴኒስ በሀብታሞች ብቻ እንደሚዘወተር ቢጠቀስም፣ በሁሉም የዕድሜ ክልል ይዘወተራል፡፡ ቴኒስ የሀብታም ስፖርት ተደርጎ የሚወሰድበት ምክንያት የቴኒስ መጫወቻ ቁሳቁሶች ውድ በመሆናቸው መሆኑ ይነገራል፡፡