Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአማራና የትግራይ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች በነዋሪዎች የሚመረጥ አስተዳደር ይቋቋም ተባለ

የአማራና የትግራይ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች በነዋሪዎች የሚመረጥ አስተዳደር ይቋቋም ተባለ

ቀን:

  • ሕግማስከበር ሥራው ለፌዴራል መንግሥት ይተላለፋል

‹‹የሚቋቋመው አስተዳደር የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አካል መሆን አለበት››

አቶ ጌታቸው ረዳ

የአማራና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ አንስተው የሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ዕጣ ፈንታ በሕዝበ ውሳኔ እስከሚለይ ድረስ፣ በአካባቢዎቹ በነዋሪዎች የሚመረጥ አስተዳደር እንዲቋቋም አቅጣጫ ማስቀመጡን የፌዴራል መንግሥት አስታወቀ። 

የፌዴራል መንግሥት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የተፈረመበት አንደኛ ዓመትን አስመልሰክቶ ሰኞ ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያወጣው መግለጫ የፌዴራል መንግሥት ስምምነቱን ለመፈጸም ከሚጠበቅበት ርቀት በላይ መጓዙን ይዘረዝራል።

ለአብነትም ሕገ መንግሥቱ ለፌዴራል መንግሥት የሰጠው መብት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ላይ የፌዴራል መንግሥት በመቀሌ ከተማ በርካታ የታጠቁ የፀጥታ ኃይሎቹን ማሰማራት እንደሚችል በተደጋጋሚ የተገለጸ ቢሆንም፣ መንግሥት በሆደ ሰፊነት ይህንን ከማድረግ መቆጠቡን አስታውቋል።

በሰላም ስምምነቱ መሠረት የፌዴራል መንግሥቱን የሚመራው ገዥ ፓርቲ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የመወከል መብት ቢኖረውም፣ መንግሥት በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን፣ ክልሉ በፍጥነት እንዲያገግምና በፍጥነት ወደ መደበኛ ሁኔታ እንዲሸጋገር ለማድረግ በማሰብ ገዥው ፓርቲ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የሚኖረውን መቀመጫ እንዲተው ማድረጉን አስታውቋል።

መተማመንን ለመፍጠር በማሰብም የፌዴራል መንግሥት በሰላም ስምምነቱ ላይ የተቀመጡትን አጠቃላይ የጦር መሣሪያዎች የሚፈቱበት የጊዜ ሰሌዳ እንዲከበር ከመወትወት መቆጠቡንም መግለጫው አመልክቷል።

የአማራና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ አንስተው የሚወዛገቡባቸውን አካባቢዎች ጉዳይ ለመፍታትም፣ የፌዴራል መንግሥት ሁለቱ ክልሎችን በማቀራረብ የሚወዛገቡባቸው አካባቢዎችን በተመለከተ ሰላማዊና ሕጋዊ መፍትሔ እንዲቀመጥ ማድረጉን መግለጫው ያስረዳል።

ውዝግቡን ለመፍታትም የአገሪቱ ሕገ መንግሥትን መሠረት በማድረግ ግልጽ መፍትሔ መቀመጡን፣ ከእነዚህም መካከል አንዱና ቀዳሚ የነበረው ሁለቱ ክልሎች ከሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ነበሩበት ቀዬ ተመልሰው የግብርና ሥራቸውን እንዲቀጥሉ የሚል አቅጣጫ እንደሆነ መግለጫው አመልክቷል።

መግለጫው አክሎም፣ ‹‹የእነዚህ አከራካሪ አካባቢዎች ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠትም ደረጃ በደረጃ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ አቅጣጫ ተቋምጧል፤›› ብሏል።

ዘላቂና የመጨረሻ መፍትሔው ወደፊት በሚካሄድ ሕዝበ ውሳኔ እስኪለይ ድረስ፣ ደግሞ ውዝግብ የተነሳባቸው አካባቢዎች በነዋሪዎች የሚመረጡ አካባቢያዊ አስተዳደሮች እንዲቋቋሙና የአካባቢዎቹ የፀጥታና የሕግ ማስከበር ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ለፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እንዲተላለፍ መወሰኑን መግለጫው አስታውቋል። 

የፌዴራል መንግሥት ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ጥረቶችን ቢያደርግም፣ በዚያኛው ወገን (በሕወሓትና በጊዜያዊ አስተዳደሩ) በኩል እግር የመጎተት አዝማሚያ እንደሚታይ ያመለከተው መግለጫው፣ ‹‹ይህ ግን ዘላቂ ሰላምን፣ ብልፅግናንና የሕዝቦችን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት አያረጋግጥም፤›› ብሏል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳም በተመሳሳይ ሰኞ ዕለት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አንደኛ ዓመትን አስመልክቶ ለክልሉ ሚዲያ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፣ በዚህም የይገባኛል ውዝግብ ስለተነሳባቸው አካባቢዎችና ከእነዚህ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን በተመለከተ የተቀመጠው መፍትሔ ላይ የአስተዳደሩን አቋም አንፀባርቀዋል። 

የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ብቻ ሳይሆን በዚያው አካባቢ የሚገኙ የትግራይ ተወላጅ ነዋሪዎችም ጭምር ምቹ ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት፣ ይህ ምቹ ሁኔታም ተፈናቃዮቹን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ሙሉ እምነትና መተማመን የሚሰጣቸው መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል።

‹‹ነዋሪዎችን አስገድደው በማፈናቀልና በመግደል የተሳተፉ ሰዎች በእነዚህ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ ተፈናቃዮችን ወደ ሥፍራዎቹ መመለስ ተገቢ ሊሆን አይችልም፣ እንዲያውም አጥፊ ነው፤›› ብለዋል።

ስለሆነም ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በአካባቢዎቹ የተቋቋሙ የአማራ ክልል የአስተዳደር መዋቅሮችን የማፍረስና በአካባቢዎቹ የሚገኙ የኤርትራ ሠራዊትን ጨምሮ የአማራ ክልል ታጣቂዎችን የማስወጣት ኃላፊነቱን የፌዴራል መንግሥት ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስና የአስተዳደር መዋቅሮችን ለማቋቋም የሚያስፈልገውን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣ ከፌዴራል መንግሥት ጋር እየሠራ መሆኑን፣ ይህንን ጉዳይ የሚከታተል ኮሚቴም መቋቋሙን ገልጸዋል። 

‹‹ውዝግብ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች በነዋሪዎች ምርጫ የሚቋቋመው አስተዳደር የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አካል መሆን አለበት ብለን እየተሟገትን ነው፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ምክንያቱም ይህ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር የትግራይን የአስተዳደር ወሰን ወደ ነበረበት መመለስ አይቻልም፤›› ሲሉ አክለዋል። 

አቶ ጌታቸው ውዝግብ የተነሳባቸው አካባቢዎች ቀጣይ ዕጣ ፈንታን ለመወሰን ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ አቅጣጫ መቀመጡን በአዎንታ እንደሚቀበሉት፣ ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ መሠረት መካሄድ እንዳለበት ተናግረዋል።

‹‹የእነዚህ አካባቢዎች ጉዳይ በሕዝበ ውሳኔ ይመለስ ከተባለ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህንን ሕዝበ ውሳኔ ሊያካሂድ አይችልም። በዚህ ጉዳይ ሕገ መንግሥቱ ግልጽ ነው። ሕዝበ ውሳኔ የሚካሄድ ከሆነ ሒደቱ የሚሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የውሳኔ ሐሳብ ሲያሳልፍና የክልሉ ምክር ቤቱ በውሳኔ ሐሳቡ ላይ ሲስማማ ነው። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልል ምክር ቤት የለም። እኔ የምመራው ጊዜያዊ አስተዳደር ደግሞ ሕዝበ ውሳኔ የማካሄድ ሥልጣን የለውም፤›› ብለዋል። 

ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስፈላጊ ከሆነው በላይ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይበት ምንም ምክንያት እንደሌለው የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ከአሁን ጀምሮ እስከ ሦስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ አስፈላጊ ነገሮችን መሥራትና በመቀጠልም በመላው ትግራይ ምርጫ ማካሄድ ከቻለ በሥልጣን ላይ ረዥም ጊዜ የሚቆይበት ምክንያት እንደማይኖር አስረድተዋል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህንን ማድረግ ከቻለ ሥልጣኑን በሕዝብ ለተመረጠ አስተዳደር እንደሚያስረክብ፣ ይህ በሕዝብ የተመረጠ አስተዳደርም ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ እንደሚችል ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...