Wednesday, December 6, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

መንግሥት ለሰብዓዊ መብት ተቋማት ልዩ ትኩረት ይስጥ!

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል እየተፈጸሙ ስላሉ የመብት ጥሰቶችና ሕገወጥ ድርጊቶች የሚመለከት መግለጫ ካወጣ በኋላ፣ በመንግሥት በኩል የኮሚሽኑን ሪፖርት በደፈናው የሚያጣጥልና ጥያቄ የሚያስነሳ ምላሽ መሰጠቱ እርምት ያስፈልገዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ በርካታ ተቋማት ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በተነፃፃሪ ኃላፊነቱን ለመወጣት ብርቱ ጥረት እያደረገ ያለን ተቋም፣ ስህተት ወይም ጥፋት ቢገኝበት እንኳ ነጥብ በነጥብ ችግሩን በተገቢው ቦታ አንስቶ መነጋገር ሲገባ በደፈናው ያቀረበውን ሪፖርት ማጣጣል ከመንግሥት የሚጠበቅ ተግባር አይደለም፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባገኙ ሥነ ዘዴዎች ምርመራ በማድረግ የሚታወቅ ተቋምን፣ በቅጡ ሊሞግት በማይችል ያልተብራራ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ለማጣጣል መሞከሩ የሚያሳዝን ነው፡፡ የአገር ውሎና አዳርን በትጋት በሚከታተሉ ዜጎችም ሆነ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ሊፈጠር የሚችለውን ተቃውሞም ሆነ ትችት በቅጡ መገንዘብ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ኮሚሽኑ መነካትም ሆነ መተቸት የለበትም እየተባለ እንዳልሆነ ነው፡፡

ነገር ግን የኮሚሽኑን ተግባርና ኃላፊነት የሚቆጣጠረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግልጽ ውይይት፣ እያንዳንዱን ዕርምጃውን በመከታተል ስህተቶቹን ነቅሶ መነጋገር ይቻላል፡፡ ነገር ግን እንዲያው በደፈናው ኮሚሽኑ ያወጣው ሪፖርት ለአንድ ወገን ያደላ፣ በሐሰተኛ መረጃ ላይ የተመሠረተና ከዓውዱ ውጪ የቀረበ ነው ሲባል መንግሥትን ትዝብት ላይ ይጥለዋል፡፡ ሪፖርቱ የኮሚሽኑ ተዓማኒነት፣ ገለልተኝነትና ነፃነት የሚጋፋ ነው ተብሎ በመንግሥት አፍ ሲነገር አብሮ ዘርዘር ያለ ማጣቀሻና ማሳጫ ቢቀርብ የተሻለ ነበር፡፡ ሳይሆን ቀርቶ ግን መንግሥትን እንደ ልቡ ሊያናግረው የሚችል ነገር በመጥፋቱ ትዝብት ላይ ጥሎታል፡፡ በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ አማካይነት ከቀረበው የመንግሥት አቋም ውስጥ መልካሙ ነገር፣ ሪፖርቱን በደፈናው ከማጣጣል ውጪ መንግሥት ኮሚሽኑን ፀጥ ለማሰኘት ፍላጎት እንደሌለው መነገሩ ነው፡፡ ይሁንና በገለልተኝነትም ሆነ ጉዳዬ ብለው የሰሞኑን ጉዳይ የሚከታተሉ ወገኖች፣ መንግሥት አንድ ለእናቱ የሆነውን ኮሚሽን በዚህ ደረጃ ካብጠለጠለ ማንን ሊታገስ ነው የሚሉ ድምፆች እየተሰሙ ስለሆነ ልብ ይባል፡፡

ከበፊት ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገር ቤት በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ በኢትዮጵያ ላይ ሪፖርቶች ወይም መግለጫዎች ሲወጡ፣ በየፈረቃ ሥልጣን ላይ የሚወጡ አካላት መግለጫዎችንም ሆነ ሪፖርቶችን ላለመቀበል የሚሄዱበት ርቀት አሳዛኝ ነው፡፡ በደርግ፣ በኢሕአዴግም ሆነ በብልፅግና ጊዜያት እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሒዩማ ራይትስዎችና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ምን ይገጥማቸው እንደነበር አይረሳም፡፡ በአገር ውስጥ ከበፊት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) እና አሁን ደግሞ ኢሰመኮ፣ የሚያወጧቸው ሪፖርቶች ወይም መግለጫዎች ይብጠለጠላሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነው ኢሰመኮ የሚያወጣቸው መግለጫዎች ወይም ሪፖርቶች፣ ብዙ ጊዜ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ባሉ የመገናኛ ብዙኃን የዜና ሽፋን አያገኙም፡፡ ከሰብዓዊ መብት ተቋማት ጋር እንዲህ ያለ ተቃርኖ ውስጥ እየተገባ እንዴት ተሁኖ ነው ስለመብቶችና ነፃነቶች መነጋገር የሚቻለው? መንግሥት ይህንን ጊዜ አይሰጤ ችግር በፍጥነት መፍታት ይጠበቅበታል፡፡

ኢሰመኮም ሆነ ሌሎች የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ምርመራ ሲያደርጉ መንግሥት ተባባሪነቱን በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ ሪፖርት ሲያቀርቡም የማያስደስቱ ወይም የተሳሳቱ ነገሮች ሲኖሩም በሰከነ መንገድ መነጋገር ይኖርበታል፡፡ በሪፖርቶቻቸው ውስጥ ዘወትር የሚጠቀሱት በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት ተባባሪ ለመሆን ፈቃደኛ እንደማይሆኑ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ከማንም በላይ ተባባሪ መሆን ያለበት መንግሥት ለምርመራ ተባባሪ ካልሆነ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ በምርመራ ጊዜ የማይተባበር ማንኛውም አካል በአንድም ሆነ በሌላ የችግሩ ተሳታፊ ነው ተብሎ ቢደመደም ሊገርም አይገባም፡፡ ነገር ግን አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከበፊቶቹም ሆነ ከራሱ ስህተቶችና ጥፋቶች ተምሮ፣ ከሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ጋር እሰጥ አገባም ሆነ ተቃርኖ ውስጥ መግባት አይጠበቅበትም፡፡ የመንግሥት ኃላፊነት መሆን ያለበት የመብት ጥሰቶች ምርመራዎች በአግባቡ እንዲካሄዱ በማገዝ፣ በሚገኙ አሳማኝ ማስረጃዎች ላይ በመመሥረት ጥፋተኞችን ለሕግ ማቅረብ ነው፡፡ አላስፈላጊ ንትርኮችና ውዝግቦች ለአጥፊዎች ምቹ መደላድል ከመፍጠር የዘለለ ፋይዳ የላቸውም፡፡

‹‹አንድ ጥርስ ቢኖራት በዘነዘና መወቀር አማራት›› እንደሚባለው ዕድሜ ጠገብ አባባል፣ ለአገሪቱ መንግሥታዊ ተቋማት መልካም ምሳሌ ሊሆን የሚችል የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን በዘፈቀደ ማጣጣል ተገቢ አይደለም፡፡ መንግሥትም እንዲህ ዓይነቱን አቋሙን በመመርመር እርምት ያድርግ፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ እጁ ላይ ያሉትን መረጃዎች በግልጽ ለሕዝብ ይፋ እያደረገ፣ መደነጋገርና መተረማመስ የሚፈጥሩ ያልጠሩ ጉዳዮችን ያጥራ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ውስጥ በአብዛኞቹ አካባቢዎች ሰላም ስለመስፈኑና እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው በደፈናው ሲነገር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ያለው ሁኔታ ከዚህ በተቃራኒ እንደሆነ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ሲስተጋባ በመሀል ሕዝብ የማወቅ መብቱ እየተጎዳ ነው፡፡ በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ በተቃርኖ የተሞሉ መረጃዎች ሲለቀቁ፣ ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ተዓማኒነት ያለው መረጃ የማሠራጨት ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል፡፡ ሥራን በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ ማከናወን ሲቻል ከየትኛውም አካል የሚወጣ ሪፖርትም ሆነ መግለጫ፣ በሕዝብ የህሊና ዳኝነት እየተመዘነ ብስሉ ከጥሬው ይለያል፡፡ መንግሥት ለሕዝብ በገባው ቃል መሠረት ኃላፊነቱን ከተወጣ ሌላው ዕዳው ገብስ ነው፡፡

የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልል ብሔራዊ መንግሥታት ኃላፊነታቸውን በሕጉ መሠረት የመወጣት ግዴታ አለባቸው፡፡ ከማናቸውም ዓይነት ብልሹ አሠራሮች በመራቅ ኃላፊነታቸውን በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ መሠረት ኃላፊነታቸውን ሲወጡ በሰብዓዊ መብቶች አከባበር፣ በዴሞክራሲያ መብቶች ጥበቃና በመሳሰሉት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት አይሰንፉም፡፡ እንደ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትና ለመሳሰሉ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ጋሻና መከታ ይሆናሉ፡፡ የአንድ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት መገለጫም ለእንዲህ ዓይነቶቹ ተቋማት ከለላ መሆን መቻል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ለመስማት የሚዘገንኑ አሳዛኝ ድርጊቶች በተለያዩ አካላት ይፈጸማሉ፡፡ መንግሥት የዴሞክራሲ ተቋማቱን ሪፖርቶችና ምክረ ሐሳቦች በአንክሮ በመከታታል አጥፊዎች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማገዝ አለበት፡፡ ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት ግን ቅንነትና ሆደ ሰፊነት ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ መንፈስ ማሰብ ሲቻል ምንም ነገር ከአቅም በላይ አይሆንም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለሰብዓዊ ተቋማት ልዩ ትኩረት ይስጥ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...