- ከፍተኛው የፈቃድ ክፍያ 36 ሺሕ ዶላር መሆኑ ተገልጿል
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ግለሰቦችና ድርጅቶች ለማመልከቻ፣ ለፈቃድና ለዕድሳት አገልግሎት መፈጸም ያለባቸውን የክፍያ ተመን የሚገልጽ ረቂቅ መመርያ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ለሚያቀርበው አገልግሎትና የሥራውን ወጪ ለመሸፈን የሚያስችል የክፍያዎችን ተመን በመመርያ በማዘጋጀት፣ የሕዝብ አስተያየት እንዲካተትበት ይፋ ማድረጉን፣ የባለሥልጣኑ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ዮሐንስ አረጋ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የክፍያ መመርያ የማውጣት መብቱን መሠረት በማድረግ፣ ‹‹የማመልከቻ ክፍያ፣ የፈቃድ ክፍያና የዕድሳት ክፍያ›› በማለት የካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢዎች ለባለሥልጣኑ የሚከፍሉትን ክፍያ በመመርያ ይፋ ማድረጉ ተመልክቷል፡፡
አድሏዊ ባልሆነ መንገድ ክፍያዎችን ለመሰብሰብ፣ አሠራሩን ግልጽና ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግና የሚፈጽሙት ክፍያዎች ከሌሎች ተመጣጣኝ ገበያዎች ጋር በምክንያታዊነት የተጣጣሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑ በመመርያው ተጠቅሷል፡፡
በካፒታል ገበያ አገልግሎት ክፍያ ረቂቅ መመርያ መሠረት ባለሥልጣኑ የካፒታል ገበያ ተዋንያን ለተለያዩ አገልግሎቶች የተለያየ መጠን ያለው ክፍያ በመወሰን በውጭ ምንዛሪ ያስቀመጠ ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ግለሰቦችና ድርጅቶች በብሔራዊ ባንክ ዕለታዊ ምንዛሪ ተመን ተሠልቶ እንደሚከፍሉ አቶ ዮሐንስ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በመጀመሪያው ምዕራፍ ሁለተኛ ሰንጠረዥ ላይ ከተገለጹት 54 ዓይነት አገልግሎቶች መካከል ፈቃድ ለመውሰድ እንደ ባንክ የሚወሰዱ የኢንቨስትመንት ባንኮች (Investment Bank-within a Banking Group)፣ የአገልግሎት ፈቃድ ለመውሰድ የሚጠየቀው ከፍተኛ ገንዘብ 36 ሺሕ ዶላር ሲሆን፣ ዝቅተኛ ክፍያ ደግሞ ተወካይ ለመሾም (Appointed Representative) የማመልከቻ ክፍያ 250 ዶላር እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ (Ethiopian Security Exchange) ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የአገልግሎት ፈቃድ ለመውሰድ 36 ሺሕ ዶላር እንደሚከፈል በመመርያው በመግለጽ፣ የሰነድ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ ከጠቅላላ ገቢው አንድ በመቶውን ዓመታዊ የፈቃድ እድሳት ክፍያ እንደሚከፍል ይገልጻል።
አዋጅ ቁጥር 1248/2013 መሠረት በማድረግ የተቋቋመው የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የሰነድ ሙዓለ ንዋይ ግብይትን የሚያቅፍ በመሆኑ፣ የሰነድ ሙዓለ ንዋይ አክሲዮንን ብቻ ሳይሆን ቦንድና ሌሎች ‹‹ኢንስትሩመንቶችን›› የሚያካትት መሆኑ ይታወቃል፡፡
የካፒታል ገበያ ግብይትና ካፒታል ማሰባሰብን (Capital Fund Raising) የሚያካትት ሲሆን፣ ካፒታል ገበያ ካስፈለገባቸው ጉዳዮች አንዱ ገንዘብ የሚውልበትን ሌላ አማራጭ በመፍጠር የኢንቨስተሮች ሥጋቶችን የሚቀንስ፣ ለኩባንያዎችና ገንዘብ ለሚያስፈልጋቸው ደግሞ ተጨማሪ የፋይናንስ ጥቅም እንዲያገኙ ወይም የባንክ ብድር ዓይነት ድጋፍ እንዲያገኙ እንደሆነ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ከመሪ ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ አስረድተዋል።
የካፒታል ማርኬት ተሳታፊ የሚባሉ ደላሎች፣ ነጋዴዎች፣ የኢንቨስትመንት ባንኮች፣ አካውንቶች የፈንዱን ፍሰት የሚያግዙ ተዋንያን ናቸው፡፡ የተቀላጠፈ የካፒታል ገበያ ዕውን የሚሆነው በቴክኖሎጂ በታገዘ መሠረተ ልማት አማካይነት ሲሆን፣ ለዚህም ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች የመጀመሪያው የኤሌክትሮኒክስ ሥርዓትን የሚጠቀም የግብይት መድረክ መሆኑን ብሩክ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተቋቋመው የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ (Ethiopian Security Exchanege) በካፒታል ገበያ ውስጥ የሚሳተፉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ዋጋ ባለው መንገድ ሳይጭበረበሩ ግብይቱ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፍበትን መንገድ የሚያመቻች ሲሆን፣ የሚገበያዩት ግለሰቦችና ድርጅቶች የሰነድ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ የምዝገባ ክፍያ እንደሚከፍሉ በመመርያው ተጠቅሷል፡፡
የመንግሥት ቦንድን (የኮርፖሬት ቦንድ) እና የከተማ አስተዳደሮች ለሚጠቀሙት የብድር አገልግሎት የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የምዝገባ ክፍያ ከሚያገኙት አገልግሎት ውስጥ ከ0.002 በመቶ እስከ 0.2 በመቶ ይከፍላሉ፡፡ በተጨማሪም የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ለሚያከናውናቸው ተግባራት የትራንዛክሽን ክፍያ ያስከፍላል፡፡
ረቂቅ መመርያው የሕዝብ አስተያየት ከታከለበት በኋላ እንደሚፀድቅና ተግባራዊ እንደሚደረግ አቶ ዮሐንስ አስረድዋል፡፡