Sunday, December 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዕውቅና ላልተሰጣቸው አገልግሎቶች ማስታወቂያ የሚያስነግሩ ድርጅቶች ዕውቅና ያገኙበትን አገልግሎት ይነጠቃሉ ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ዕውቅናና የጥራት ማረጋገጫ ባላገኙባቸው አገልግሎቶች፣ ዕውቅናውን እንዳገኙ አስመስለው ማስታወቂያ እያስነገሩባቸው በመሆኑ፣ ከዚህ ድርጊታቸው ካልታቀቡ፣ ዕውቅና ያገኙበት አገልግሎት እንደሚነጠቅ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት ኃላፊዎች ገለጹ፡፡

ድርጅቶቹ በአንድ ወይም በሁለት አገልግሎቶች ብቻ ዕውቅናና ማረጋገጫ ከብሔራዊ አክሬዲቴሽን አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስትትዩትና ከኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅቶች የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት ወስደው፣ በሁሉም አገልግሎቶቻቸው ላይ ዕውቅናውን እንዳገኙ አድርገው ማስተዋወቃቸውን ነው እየገጠሙን ያሉ ችግሮች ሲሉ ተቋማቱ ያስታወቁት፡፡

የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦንሳ ባይሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ድርጅቶች በርካታ አገልግሎት እየሰጡ በተወሰኑ ዘርፎች ብቻ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ሲያገኙ በሁሉም የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ዕውቅናውን እንዳገኙ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡

በማስታወቂያዎች ላይ ከብሮድካስት ባለሥልጣን ጋር ተቋማቸው አብሮ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው፣ ሚዲያዎችና የማስታወቂያ ተቋማትም ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ነው አቶ ቦንሳ ያስረዱት፡፡ ‹‹በጣም በሚገርም ሁኔታ ትልልቅ ሚዲያዎችም ጭምር ስፖንሰር ስላደረጓቸው ብቻ ማስታወቂያ ያስነግሩላቸዋል፤›› ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ድረስ በትምህርትና በምክር መታለፋቸውን የተናገሩት አቶ ቦንሳ፣ ከዚህ በኋላስ ስለሚወሰዱ ዕርምጃዎች ሲናገሩ፣ ‹‹ለሁሉም አገልግሎቶቻቸው ዕውቅና እንዳገኙ አድርገው ማስታወቂያ የሚያስነግሩ ከሆነ አንዱ ዕውቅና ያገኙበት አገልግሎት እንዲነጠቅ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ዕውቅና የሚሰጠው በተወሰኑት ባመለከቱባቸው አገልግሎቶች ነው እንጂ በሁሉም አይደለም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2023 በኬንያ በተካሄደው የአፍሪካ አክሬዲቴሽን ትብብር ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በተላለፈው ውሳኔ መሠረት፣ ለሁለት ተጨማሪ አገልግሎቶች ለሚሰጠው የዕውቅና ሥራ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ተሰጥቶታል፡፡ በዚህም መሠረት አገልግሎቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያገኘባቸው የሚሰጣቸው የዕውቅና አገልግሎቶች ቁጥር ወደ ስድስት አድጓል፡፡

በርካታ አገልግሎቶችን በአገር ውስጥ ዕውቅና የሚሰጠው አገልግሎቱ፣ ስድስቱ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያገኘባቸው የአክሬዲቴሽን አገልግሎቶች የሕክምና ላቦራቶሪ፣ የፍተሻ ላቦራቶሪ፣ የኢንስፔክሽን፣ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት፣ የካሊብሬሽን ላቦራቶሪና የምርት ሰርተፊኬሽን ናቸው፡፡

አገልግሎቱ ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በዋና መሥሪያ ቤቱ ባካሄደው መርሐ ግብር፣ ለስድስት የአገር ውስጥ ድርጅቶች ለተወሰኑ አገልግሎቶቻቸው አክሬዲቴሽን ሰጥቷቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በማይክሮ ባዮሎጂ ላቦራቶሪ፣ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በጂን ኤክስፐርት፣ በማይክሮ ባዮሎጂና ቢኤኤፍቢ ማይክሮ ላቦራቶሪዎች፣ የመቱ አጠቃላይ ካርል ሆስፒታል በቫይራል ሎድ፣ የቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል በክሊኒካል ኬሚስትሪና ሄማቶሎጂ ላቦራቶሪዎች፣ የሳቢያን አጠቃላይ ሆስፒታል፣ የጨራንቶ የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል፣ እንዲሁም የገብረፃዲቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታል በጅን ኤክስፐርት ላቦራቶሪዎች ነው የአክሬዲቴሽን ዕውቅና ከአገልግሎቱ የተሰጣቸው፡፡

አገልግሎቱ ከ40 በላይ ለሆኑ ድርጅቶች የአክሬዲቴሽን ዕውቅና አገልግሎቶች የሰጠ ሲሆን፣ በሒደት ላይ ያሉ ሌሎች በርካታ ድርጅቶችም እንዳሉ አቶ ቦንሳ ገልጸዋል፡፡ በህንድ የሚገኝ አንድ ተቋምም ከአገልግሎቱ የዕውቅና አገልግሎት ያገኙ መሆኑን ያሳወቁት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከጋናም ተመሳሳይ ጥያቄ እየቀረበላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች