Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበሰላም ዕጦት የተፈተነው ቱሪዝም በ‹‹ቱሪዝም ሳምንት››

በሰላም ዕጦት የተፈተነው ቱሪዝም በ‹‹ቱሪዝም ሳምንት››

ቀን:

በዳንኤል ንጉሤ

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ፈተናዎች ሲያጋጥሙት ይስተዋላል።  ኢትዮጵያ በርካታ ባህል፣ ቅርስ፣ አስደሳች መልክዓ ምድርና የልዩ ታሪካዊ ሥፍራዎች ባለቤት ብትሆንም፣ የጎብኚዎች ቁጥር በማሽቆልቆሉ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን ለመሳብ ስትጣጣር ይስተዋላል።  

በኢንዱስትሪው ከተጋረጠው እንቅፋት አንዱና ዋነኛው ከግጭት ጋር ተያይዞ የአገሪቱ ገጽታና ስም በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በበጎ መልኩ አለመነሳቱ ነው፡፡ አብዛኛው ሚዲያዎች በአገሪቱ ስላለው የፖለቲካ አለመረጋጋትና ግጭቶች መዘገባቸው፣ ጎብኚዎች ኢትዮጵያ ያላትን ውበትና ብዝኃነት እንዳይመረምሩና እንዳይጎበኙ ስለማድረጉ እንደ አንድ ምክንያት ሊነሳ ይችላል፡፡

በሰላም ዕጦት የተፈተነው ቱሪዝም በ‹‹ቱሪዝም ሳምንት›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የመሠረተ ልማት ውስንነትም ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዕድገት ትልቅ ፈተና ነው፡፡ በኢትዮጵያ በርካታ አካባቢዎች መንገድ፣ አየር ማረፊያና አመቺ የትራንስፖርት አውታር የሌላቸው መሆኑም ጎብኚዎች ራቅ ብለው የሚገኙ መስህቦችን እንዳይጎበኙ አድርጓል።

ጉድለቶቹ ኢትዮጵያ ያሏትን የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ሙሉ በሙሉ እንዳትጠቀምበት፣ ለኢኮኖሚዋም ትልቅ አቅም እንዳይሆንና ለሥራ ዕድል እንዳይፈጥር አድርጓል።

ከሦስት ዓመታት በፊት የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩም ይነሳል፡፡ እንደሌሎች የዓለም አገሮች ሁሉ ኢትዮጵያም በጉዞ ገደብ፣ በቁጥጥር ዕርምጃዎችና በቫይረሱ ፍራቻ ምክንያት ጎብኚዎች አገሪቱን መጎብኘት ባለመቻላቸው የዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ቁጥር እንዲቀንስ አድርጓል። 

በሰላም ዕጦት የተፈተነው ቱሪዝም በ‹‹ቱሪዝም ሳምንት›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የድንበር መዘጋትና የዓለም አቀፍ በረራዎች መቋረጥ የቱሪስቶችን ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ በማስተጓጎል በቱሪዝም ዘርፍ ለሚሰሩ የንግድ ተቋማት የገቢ ማሽቆልቆል ምክንያትም ሆኖ አልፏል።

ኢትዮጵያም በዚህ ሁሉ የቱሪዝም ችግር ውስጥ ሆና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበረውን የቱሪዝም ቀን ‹‹ቱሪዝም ለአረንጎዴ ልማት አረንጓዴ ልማት ለቱሪዝም›› በሚል ከጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶችና ዓውደ ርዕይ በመስቀል አደባባይ አክብራለች፡፡

የቱሪዝም ቀንን በማስመልከት ከመቶ በላይ የተለያዩ የቱሪዝም ተዋናዮችና የቱሪዝም ተቋማት በቦታው የተገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል የዕደ ጥበብ አምራቾች፣ አስጎብኚ ድርጅቶችና ሙዚየሞች ይገኙበታል።

‹‹ይህ ዓውደ ርዕይ ተቋሞቹ ከኅብረተሰቡ ጋር የሚገናኙበት፣ በውስጣቸው ያለውን አገልግሎትና የቱሪዝም ሀብት የሚያሳዩበት ጥሩ መድረክ ነው›› ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና የአገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፋት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን አይናቸው ናቸው፡፡

በዓውደ ርዕዩ የተለያዩ ዝግጅቶች የተደረጉ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ሲምፖዝየም፣ ቶክ ሾው፣ የጥያቄና መልስ ውድድር፣ የሀይኪንግ የእግር ጉዞና የባህላዊ ቁንጅና ውድድር እንዲሁም ሌሎች ግንዛቤ ይፈጥራሉ ተብለው የታሰቡ መርሐ ግብሮች ይገኙበታል።

በባህላዊ የቁንጅና ውድድርም፣ የኢትዮጵያ ባህላዊ ልብሶችና እሴቶች የተዋወቁበት መድረክም ነበር፡፡ አሸናፊዎችም የከተማው የቱሪዝም አምባሳደር ሆነው የአዲስ አበባን የቱሪዝም ሀብቶች የሚያስተዋውቁ ይሆናል፡፡

የዘንድሮው የቱሪዝም ሳምንት ሲከበር እንደ አገርም እንደ ከተማም የተለያዩ ስኬቶች የተገኘበት መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸው፣ እንደ አገር በዓለም የሳይንስ ትምህርትና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡበት እንዲሁም ከአፍሪካ ብዙ ቅርሶች በማስመዝገብ ቀዳሚ የተሆነበት፣ አዲስ አበባም የዓለም ቱሪዝም ከተሞች ፌዴሬሽን አባል የሆነችበት በመሆኑ የዘንድሮው የቱሪዝም ሳምንት ለየት እንደሚል አክለዋል፡፡

የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በተለይ ማሽቆልቆል የጀመረው ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኋላ መሆኑን ያስረዱት አቶ ሳምሶን፣ የዓለም አገሮች በወሰዱት የማገገሚያ ዕርምጃ መነቃቃት ቢጀምርም፣ እንደ አገር በየጊዜው የሚያጋጥሙ የሰላም ችግሮች ቱሪዝሙ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከማሳደራቸውም በላይ የቱሪዝም ፍሰትና ገቢ ላይ ከፍተኛ ብክነት አድርሷል ብለዋል።

‹‹እንደ ከተማ አስተዳደር ከቱሪዝም ዘርፍ ተዋናዮች ጋር እየሠራናቸው ያሉ በርካታ የልማት ሥራዎች አሉ›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ከእነዚህም የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማልማትና ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ፣ የአገር ውስጥና የውጪ ጎብኚ ቁጥር እንዲጨምርና ወደ ከተማ ኢኮኖሚ ፈሰስ የሚሆነውን ገቢ የማሳደግ ሥራዎች እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

ቱሪዝም ሰው ተኮር እንደመሆኑ መጠን በዘርፉ የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት፣ ማኅበረሰቡ ከዘርፉ ትሩፋት የሚቋደስበት ሥራዎችም እየተሠሩ መሆኑን አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል አስጎብኚ ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ ትኩ፣ የአገርን ገጽታ ግንባታ ከመግለጽ አኳያ የሚችሉትን አስተዋጽኦ ለማድረግ በዓውደ ርዕዩ መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ዮናስ፣ ‹‹ከውጭ አገር የሚመጡ ቱሪስቶች በአገሪቷ ፀጥታ መደፍረስና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በመመናመኑ፣ ቱሪዝሙን ለማነሳሳትና ወደነበረበት ደረጃ ለመመለስ ዓውደ ርዕዮችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡  

መድረኩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በመሰብሰብ የአገራቸውን የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲያውቁ ስለሚያደርግ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

‹‹ዝግጅቱን ሰዎች መጥተው እንዲጎበኙ በሚዲያዎች የማስተዋወቅ ሥራ አልተሠራም›› ያሉት የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ፣ ዓውደ ርዕዩ በሥራ ቀናት በመዋሉ ብዙ ሰዎች መጥተው ማየት እንዳይችሉ ማድረጉን፣ እንደዚህ ዓይነት ፕሮግራሞች በሚከናወኑበት ወቅት የዕረፍት ቀናትን አስታኮ ቢሠራ ጥሩ እንደሆነ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ለቱሪዝም ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱት ሆቴሎችም በመድረኩ ተገኝተው ነበር። 176 አባላት ያለው የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማኅበር በየቱሪዝም ሳምንት በዓል ላይ ከአሥር በላይ የሚሆኑ ሆቴሎችን አሳትፏል፡፡ የማኅበሩ ጽሕፈተ ቤት ኃላፊ ኤፍራታ አባተ፣ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያላቸውን ሚና ለማሳወቅና ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንደተጠቀሙበት አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሆቴል ኢንዱሰትሪ ከ20 ሺሕ በላይ ሠራተኞች ይዞ እየሠራ መሆኑን፣ ኢንዱስትሪው ምን ያስፈልገዋል የሚለውን ከመንግሥት አካላት ጋር ተገናኝቶ መምከር እንደሚያስፈልግና ለዚህም መንግሥት መድረክ እንዲያመቻች ጥሪ አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...