Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹በጥቅምት አንድ አጥንት››

‹‹በጥቅምት አንድ አጥንት››

ቀን:

በመላው ዓለም የተለያዩ የምግብ ፌስቲቫሎች ይከናወናሉ፡፡ በምግብና በመጠጥ ደምቆ የሚከበረው የጀርመኑ ኦክቶበርፊስት፣ የጣሊያኑ ፒዛፊስት፣ የህንዱ ሆሊ ፌስቲቫል፣ የአሜሪካው በተለይም በቺካጎ የሚከበረው ቴስት ኦፍ ቺካጎ በደማቅነታቸውና ብዙዎች ከሚታደሙባቸው የምግብና የመጠጥ ፌስቲቫሎች ይጠቀሳሉ፡፡

በግዙፍነታቸው ከሚታወቁት የምግብ ፌስቲቫሎች በተጨማሪ አገሮች ባህላችንን፣ ወጋችንንና አኗኗራችንን ይገልጽልናል የሚሏቸውን የምግብና የመጠጥ ዓይነቶች በፌስቲቫል በማቅረብ ሕዝባቸውን ያስደስቱበታል፣ የማያውቋቸውን እንዲያውቋቸው ያደርጉበታል፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም እንዲህ ዓይነቱን ዝግጅት በማዘጋጀት ባህላቸውን የሚያስተዋውቁበትና እርስ በርስ የሚገናኙበት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ዝግጅት በኢትዮጵያም አልፎ አልፎ ሲከበር ይታያል፡፡ ክልሎች የተለያዩ ዝግጅቶችን አስታከው የባህል ምግባቸውን የሚያስተዋውቁበትን አጋጣሚም ተመልክተናል፡፡

ዓምና በድሬዳዋ ጎዳና የተካሄደው ‹‹የጎዳና ላይ የቁርስ ማዕድ›› ፌስቲቫልም ይታወሳል፡፡ ጥቅምት ወር በመጣ ቁጥር የሚወርደውን ቁር ለመቋቋም እናቶችና አባቶች ‹‹በጥቅምት አንድ አጥነት›› ሲሉ በብርድ ወቅት የሥጋን አስፈላጊነት የገለጹበት አባባልም ወደ ፌስቲቫልነት ተቀይሮ በአዲስ አበባ መከናወን ከጀመረ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

በእንደዚህ ዓይነት ፌስቲቫሎች በርካታ ሰዎች የሚታደሙ ሲሆን፣ ሰዎች  የሚገናኙበት፣ ማዕድ የሚጋሩበት፣ ጓደኝነት የሚመሠርቱበት ነው፡፡  

ሴንቸሪ ፕሮሞሽንና ኤቨንትስ ከስንቅ ማልታ ጋር በመተባበር ‹‹በጥቅምት አንድ አጥንት›› የተባለውን የአበው ብሒል ከጥቅምት 17 – 18 ቀን 2016 ዓ.ም. በተለይም ለሥጋ ወዳጆች የሚሆን ፌስቲቫል በኤግዚቢሽን ማዕከል አካሂዷል፡፡

የሴንቸሪ ፕሮሞሽንና ኤቨንትስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘውገ ጀማነህ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ ፌስቲቫል፣ በተለያየ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ዘና የሚሉበት ነው፡፡

የድሮ እናትና አባቶች ሲጠቀሙበት የነበረውን በጥቅምት አንድ አጥንት የሚል ብሂል በመጠቀም፣ ፌስቲቫሉ በየዓመቱ እንደሚካሄድ፣ ማኅበረሰቡ በአንድ ቦታ ተሰባስቦ አብሮ በመብላትና በመጠጣት የሚተዋወቅበት እንዲሁም አንድነት የሚጠናከርበት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በኤግዚቢሽን ማዕከል ለሁለት ቀናት በተካሄደው ፌስቲቫል በከተማዋ ዕውቅና ያላቸው ዘጠኝ ልኳንዳ ቤቶች የተሳተፉ ሲሆን፣ በልኳንዳ ቤታቸው ከሚሸጡበት ዋጋ በግማሽ  ዋጋ እንዲሸጡ በማድረግ ተገልጋዮች እንዲጠቀሙ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

የድሮ እናትና አባቶች ጥቅምት ላይ ያለውን ብድር ለመቋቋም ፍየል ወይም በግ አርደው ይበሉ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዘውገ፣ ይህንን ባህል ለማስቀጠልና ፌስቲቫሉን በዓመት ሁለት ጊዜ ለማካሄድ ዕቅድ መያዛቸውን  ተናግረዋል፡፡

በጥቅምት አንድ አጥንት ፌስቲቫል ቤተሰብ፣ ጓደኛሞች እንዲሁም ከተለያዩ ቦታ የተውጣቱ የማኅረበሰብ ክፍሎች በአንድነት ሆነው የሚዝናኑበት፣ የሚጫወቱበት ነው የሚሉት፣ የኤግዚቢሽን ማዕከል የገበያ ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ታደሰ ናቸው፡፡

ለስምንተኛ ጊዜ በተካሄደው ፌስቲቫል ታዳሚው ባለው አቅም ፍላጎቱን ያሟላበት እንደሆነ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ዝግጅቱን ወጥ በሆነ መንገድ ለማስቀጠል ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተርም ቅዳሜ ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በኤግዚቢሽን ማዕከል የተከፈተውን ፌስቲቫል ለመመልከት ችሏል፡፡

የጥሬ ሥጋ ፍቅር ያላቸው፣ በመሰል ዝግጅቶች መሳተፍ የሚያስደስታቸው የውጭ አገር ዜጎችና ሌሎችም የፌስቲቫሉ ታዳሚዎች ዝግጅቱን አድምቀውት አምሽተዋል፡፡ ፌስቲቫሉም በባህላዊና በዘመናዊ ሙዚቃዎች የታጀበ ነበር፡፡

በፌስቲቫሉ የታደሙ ልኳንዳ ቤቶች እያንዳንዳቸው ከ20 የሚበልጡ አስተናጋጆች የያዙ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ሰዎች ደግሞ ጥሬ ሥጋ ይመገቡ ነበር፡፡

በፌስቲቫሉ ከታደሙት፣ ተሰብስበው ሲበሉና ሲጠጡ ማየት ደስ እንደሚል፣ ይህንንም ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ የነገሩን አሉ፡፡

በተለይም የኑሮ ውድነት፣ ድርቅና በየቦታው የሚሰሙ ግጭቶችን ለመርሳት እንደዚህ ዓይነት ፌስቲቫሎች እንደሚያስፈልጉ፣ እንዲህ ያሉና ሌሎች ፌስቲቫሎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቢደረጉ የሚል አስተያየትም ሰንዝረዋል፡፡  

በጥቅምት አንድ አጥንት በተሰኘው ፌስቲቫል አንድ ኪሎ ጥሬ ሥጋ በ800 ብር የተሸጠ ሲሆን፣ ይህም ከውጭ ከሚሸጡ ልኳንዳ ቤቶች ጋር ሲነፃፀር የተሻለ መሆኑን ሪፖርተር ለመመልከት ችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...