Wednesday, December 6, 2023

የባህር በር ጉዳይና ዓለም አቀፍ ሕጎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ወደ 169 የዓለም አገሮች የፈረሙበትና እ.ኤ.አ. በ1982 የወጣው ዓለም አቀፍ የባህር ሕግ (United Nations Convention on the Law of the Sea/UNCLOS)፣ የዓለም አገሮች የባህር ክልልና ወሰንን በምን መንገድ መጠቀም እንደሚገባቸው መሠረታዊ መርሆዎችን አስቀምጧል፡፡ ኢትዮጵያ ባታፀድቀውም ሕጉን እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 8 ቀን 1984 መፈረሟ ታውቋል፡፡ በጊዜው ኤርትራ በኢትዮጵያ ሥር ትተዳደር የነበረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ሰፊ የባህር በር ባለቤት የሆነች አገር ነበረች፡፡ ኢትዮጵያን ወክሎ ስምምነቱን የፈረመው የያኔው የደርግ መንግሥት ቅሬታ ባሳደሩበት የስምምነቱ አንቀጾች ላይ ያለውን አቤቱታም እንደገለጸ በሰነድ ላይ ሠፍሯል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በጊዜው በዋናነት በቀይ ባህር ግዛቴ ናቸው በሚላቸው ደሴቶች ላይ የየመን መንግሥት የሕጉን ክፍተት ተጠቅሞ ችግር እንዳይፈጥር ነበር በሕጉ ላይ ያለውን ሐሳብ የገለጸው፡፡

ይህን የዓለም አቀፍ የባህር ሕግ እንደ ኤርትራ፣ አሜሪካ፣ እስራኤል፣ ቱርክ፣ ሶሪያን ጨምሮ 15 የዓለም አገሮች ከናካቴው አልፈረሙትም፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ደግሞ አንዳንድ አገሮች ቢፈርሙትም አላጸደቁትም፡፡ ይሁን እንጂ ስምምነቱ በዓለም ደረጃ ከታዩ ገዥ የሆኑ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ውስጥ ዝርዝር ጉዳዮችን በማካተት የተሻለው ሕግ ስለመሆኑ በሰፊው ይነገርለታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1994 ወደ ሥራ የገባው ሕጉ የጠረፍንና የዓለም አቀፍ ውኃ ክልልን ምንነትና አጠቃቀም፣ እንዲሁም በባህር ወሰኖች የሚነሱ ውዝግቦችና የችግር አፈታት ሒደቶችን በዝርዝር አሥፍሯል፡፡

የአንድ አገር የውኃ ክልል ከባህር ጠረፍ እስከ 22 ኪሎ ሜትር ድረስ ያለውን የውኃ አካል ያጠቃልላል ይላል ይህ ሕግ፡፡ በዚህ የአንድ ሉዓላዊ የአገሮች የባህር ክልል ላይ የትኛውም አገር ለሰላማዊ ጉዳይ እስከሆነ መተላለፊያ ሊከለከል እንደማይችል ተመልክቷል፡፡ ከአንድ አገር የብስ ወይም የባህር ጠረፍ ተነስቶ እስከ 370 ኪሎ ሜትር በሚረዝመው የባህር አካል ላይ ደግሞ፣ አንድ የባህር በር ያለው አገር የራሱን የኢኮኖሚ ዞን (exclusive economic zone-EEZ) መመሥረት እንደሚችል ተገልጿል፡፡ ጥቂት የዓለም አገሮች ይህን አንቀጽ መሠረት በማድረግ ሰፊ የዓለም የባህር ክልልን ለራሳቸው ብቻ መጠቀሚያ ሊያደርጉት ሲሞክሩ ይታያል፡፡ ሰው የማይኖርበት አነስተኛ አለታማ ደሴትን ግዛቴ ነው እያሉ በዙሪያው ያለ የባህር አካልን የግል ኢኮኖሚያዊ ዞኔ ነው ማለት፣ በአንዳንድ አገሮች የተለመደ ብልጣ ብልጥነት መሆኑ ይነገራል፡፡

‹‹ኤክስክሉሲቭ ኢኮኖሚክ ዞን›› በሚባለው የባህር ወሰን ላይ አንድ አገር የባህር ሀብት አውጥቶ መጠቀምን ጨምሮ ሰፋፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊና የምርምር እንቅቃሴዎችን ማካሄድ እንደሚችል ተመላክቷል፡፡ በሕጉ መሠረት ‹‹ኤክስክሉሲቭ ኢኮኖሚ ዞን›› በሚባለው የባህር ወሰን ውስጥ ባለቤቱ የሆነው አገር ፈቅዶና ወዶ ሌሎች አገሮችም የባህር ሀብቱን እንዲጋሩ ማድረግ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለ ባለቤቱ አገር ፈቃድ የባህር ሀብቱን መጋራት እንደማይቻል ተገልጿል፡፡ በዚህ የባህር ክልል ውስጥ ዓለም አቀፍ ንግድ የሚያካሂዱ መርከቦችም ሆነ ሰላማዊ የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ የተፈቀደ መሆኑ ተደንግጓል፡፡

ከአንድ አገር የባህር ጠረፍ ከ370 ኪሎ ሜትር በላይ የሚያልፈው የባህር ክልል ዓለም አቀፍ የባህር ክልል (Continental shelf) ተብሎ እንደሚታወቅ ነው በሕጉ የተደነገገው፡፡ ሕጉ በዓለም አቀፍ የባህር ክልል ውስጥ እንደ ልብ የመንቀሳቀስ መብት ለሁሉም አገር በእኩል የተፈቀደ መሆኑም ተካቷል፡፡

የባህር በር ያላቸው አገሮች መብትና ዓለም አቀፍ ግዴታን በግልጽ የሚያስቀምጠው ይህ ሕግ በተለይ ከአንቀጽ 24 እስከ 26 ባለው ክፍል የባህር በር ባለቤት ነኝ በሚል ብቻ፣ አገሮች እንዳሻቸው የመሆንና የማድረግ መብት እንደሌላቸው በቀጥታ ያብራራል፡፡ የባህር ወሰናቸውን ለሰላማዊ እንቅስቃሴ እስከሆነ ድረስ ለሌሎች አገሮች ዝግ ማድረግ በፍጹም እንደሚከለከሉ ያትታል፡፡ የባህር ክልላቸው ለባህር እንቅስቃሴ ሰላማዊና ምቹ ስለመሆኑ ለመላው ዓለም መረጃ የመስጠት ግዴታ አለባቸውም ይላል፡፡ በሌላ በኩል በባህር ድንበራቸው ላይ ነዳጅ መሙላትን ጨምሮ የወደብና የትራንዚት አገልግሎት ለሚፈልግ መርከብ ያለ ልዩነትና ያለ አድልኦ ባወጡት ተመን ምክንያታዊ ክፍያ በመሰብሰብ አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ ይፈቅዳል፡፡ በአጠቃላይ አገሮች የባህር በር አለን በሚል ብቻ በሌሎች አገሮች ላይ ጫና እንዳያሳድሩ ሕጉ ልጓም አበጅቷል፡፡  

በክፍል ዘጠኝ ላይ ይኸው ሕግ ዙሪያቸው በከፊል ወይም በሙሉ በየብስ ስለተከበበ (Enclosed or Semi-Enclosed Seas) የባህር አካላት ጠቃሚ ድንጋጌዎችን ያስቀምጣል፡፡ የባህር ቦይ፣ የባህር መገናኛ፣ ባህረ ሰላጤ፣ ወይም ባህረ ገብና የባህር ወሽመጥ በሚባሉ የባህር አካላት ላይ የሚኖርን አጠቃቀም በዚሁ ክፍል አንቀጽ 122 እና 123 በልዩ ሁኔታ ይደነግጋል፡፡

ይህ ድንጋጌ እንደ ቀይ ባህር ስላሉ ጠባብ የባህር መተላለፊያዎች፣ የአገሮች ትብብርና የውኃ አጠቃቀም የሚመለከት መሆኑ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ በእንዲህ ዓይነት ጠባብ የባህር መተላለፊያዎች ተዋሳኝ የሆኑ አገሮች ቀጣናዊ የጋራ ተቋም ከመፍጠር ጀምሮ በባህር ንግድ ቁጥጥር፣ በሳይንሳዊና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም በባህር ሀብት ጥበቃ ሥራዎች ላይ ሊተባበሩ እንደሚገባ ሕጉ ዝርዝር ሐሳቦችን ይሰጣል፡፡ በክፍል 10 ከአንቀጽ 124 ጀምሮ እስከ አንቀጽ 133 ድረስ የባህር በር የሌላቸው አገሮች መብቶች፣ እንዲሁም የባህር በር ካላቸው አገሮች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነቶች በዝርዝር ሰፍሮ ይገኛል፡፡

በተለይ አንቀጽ 125 ከተራ ቁጥር 1-3 ባለው ክፍል የባህር በር የሌላቸው አገሮች የባህር በር ባላቸው አገሮች በኩል በማንኛውም ዓይነት የመጓጓዣ መንገድ ከባህር ጋር የሚገናኙበት ነፃነት አላቸው ሲል ያስቀምጣል፡፡ የባህር በር የሌላቸው አገሮች ከባህር በር ጋር የሚገናኙበት መንገድ ምን ይሁን፣ እንዲሁም የባህር መተላለፊያ የማግኘት ነፃነታቸውን እንዴት ይጠቀሙ የሚለው ጉዳይ የባህር በር ካለው አገር ጋር በሚደረግ ድርድርና ስምምነት እንደሚወሰንም ነው ሕጉ አክሎ  የሚያስረዳው፡፡

በልዩ ሁኔታ የባህር በር እንዲያገኙ የተደረጉ አገሮችን ሕጉ እንደማያካትት ያመለክታል፡፡ የባህር በር የሌላቸው አገሮች ባንዲራን የሚያውለበልቡ አገሮች የባህር በር ባላቸው አገሮች ከሌላው አገር መርከብ እኩል አገልግሎት ያገኛሉ ይላል፡፡ በማንኛውም ሁኔታ የባህር በር ያለው አገር የባህር በር የሌለውን አገር የባህር ንግድ እንቅስቃሴ ማወክ እንደማይችል ያስረግጣል፡፡ የወደብና ትራንዚት አገልግሎት ላይ ሆን ብሎ መጓተት መፍጠር፣ ከጣሪያ በላይ ላስከፍል ማለትም ሆነ ከስምምነት ውጪ የሆኑ ነገሮችን ካላስፈጸምኩ ማለት የተከለከለ መሆኑንም ያመለክታል፡፡ ሕጉ የባህር በር ያላቸው አገሮች የባህር በር የሌላቸው አገሮችን ህልውናና ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ ከማድረግ መቆጠብ እንዳለባቸውም ነው የሚያስታውቀው፡፡

የዓለም የባህር ሕግን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ዓለም አቀፍ ሕጎችና ድንጋጌዎችን አጣቅሰው ኢትዮጵያ የባህር በር ሊኖራት ይገባል የሚለውን አቋም የሚያስተጋቡ ምሁራን በርካታ ናቸው፡፡ ‹‹አሰብ የማን ናት የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ›› የሚል ተጠቃሽ መጽሐፍ ያበረከቱት የዓለም አቀፍ ሕግ ምሁሩና ፖለቲከኛው ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ/ር) ከእነዚህ ወገኖች ቀድመው ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ‹‹በታሪክም ሆነ በሕግ አሰብ ወደብ የኢትዮጵያ መሆኑን የሚደግፉ ብዙ ማስረጃዎች ቢኖሩም፣ በደርግ ውድቀት ማግሥት አገሪቱን የመሩ ባለሥልጣናት በተለይም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ይህን ፍጹም ባለመፈለጋቸው ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት አገር ሆና ቀረች…›› ሲሉ ያዕቆብ (ዶ/ር) የዛሬ አምስት ዓመት ለአንድ መገናኛ ብዙኃን ገልጸው ነበር፡፡

‹‹በቀይ ባህር በተለይ በአሰብ ወደብ እንደ ኑክሌር ያለ መሣሪያ ቢጠመድበት፣ ለኢትዮጵያ ህልውና ሥጋት የሆነ አደጋ ቢፈጠርበት፣ ኢትዮጵያ ይህን ለመከላከል የምትችልበት ዕድል የለም፤›› ብለው በመጽሐፋቸው ማስፈራቸውን ያስታወሱት ያዕቆብ (ዶ/ር)፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ ሥጋት አፍጥጦ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ እንደ ኢራን ያሉ አገሮችን ጨምሮ ለኢትዮጵያ ቅርብ በሆነው በቀይ ባህር ቀጣና በርካታ ኃያላን አገሮች የኃይል ፉክክርና ጂኦ ፖለቲካዊ ጥቅም የማስጠበቅ ሽኩቻ ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ኢትዮጵያ እንድትሸነፍ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ የገዛችው መሣሪያ በጂቡቲ ወደብ እንዳይገባ ፈረንሣዮች በመከልከላቸው ነው፡፡ ዛሬ ጅቡቲን ጨምሮ ዙሪያችንን የዓረብ ሊግ አባል የሆኑ አገሮች ከበውናል፡፡ የባህር በር ሳይኖረን ከአንዱ የዓረብ ሊግ አገር ጋር ብንጋጭ መውጫ መግቢያችንን ይዘጉብናል›› በማለትም ያክላሉ፡፡   

‹‹አሰብ ከጂቡቲ ወደ 200 ኪሎ ሜትር ለአዲስ አበባ ይቀርባል፡፡ አሰብ ኤርትራ የሚባለው ግዛት በኢጣሊያ ቅኝ ገዢዎች ከመፈጠሩ በፊት ኢብራሂም በተባለ የአካባቢው ባላባት ነበር የተሸጠው፡፡ አሰብን የገዛው ደግሞ ሩቢቴኖ የተባለው የጣሊያን ኩባንያ ነበር፡፡ የአሰብ አካባቢ ሕዝብም ከኢትዮጵያ አፋር ክልል ሕዝብ ጋር የተዛመደ ነው፡፡ ጣሊያን ኤርትራ የተባለውን ቅኝ ግዛት ከፈጠረች ከ15 ዓመታት በኋላ ነው አሰብ ወደ ኤርትራ የተጠቃለለው፡፡ አፄ ምኒልክ በዙሪያቸው የከበቧቸው ቅኝ ገዥዎች መስፋፋት ለኢትዮጵያ እንደሚያሠጋ በመገንዘብ ነበር ብዙ ስምምነቶችን ከቅኝ ገዥዎቹ ጋር የተፈራረሙት፡፡ ምኒልክ እስከ ቀይ ባህር የኢትዮጵያ ወሰን እንደሆነ አመልክተው የጻፏቸው ደብዳቤዎች ዛሬም ድረስ ይገኛሉ፡፡ በካይሮ እ.ኤ.አ በ1964 የቅኝ ግዛት ስምምነት ተጠብቆ እንዲቆይ የሚያደርግ ስምምነት ተፈርሟል፡፡ መላው ዓለም ባይቀበላቸውም ኤርትራውያን የኢትዮጵያ ቅኝ ተገዥ ነን ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ ጣሊያን የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን ጥሶ ነበር ኢትዮጵያን የወረረው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ በ1947 እነዚህን የቅኝ ግዛት ውሎች ሽሯቸዋል፡፡ በ1952 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ደግሞ በነጋሪት ጋዜጣ እነዚህ ስምምነቶች በይፋ ተሽረዋል፤›› የሚሉት የሕግ ምሁሩ፣ ኢትዮጵያ አሰብን ይዛ ለመቆየት የምትችልበት ሰፊ ዕድል መኖሩን አመልክተዋል፡፡  

በሌላም በኩል ኤርትራ ነፃ ስትወጣ አሰብ ራስ ገዝ አስተዳደር ተብላ በኢትዮጵያ ይዞታ ሥር መቆየቷን ያወሳሉ፡፡ በዚህ ሁሉ መነሻነት አሰብ ወደ ኤርትራ መጠቃለል እንዳልነበረባት የሚሞግቱት ያዕቆብ (ዶ/ር)፣ በስተመጨረሻ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ማግሥት በተፈረመው የአልጀርስ የሰላም ስምምነት ደግሞ ታሪክንም ሆነ ሕግን የሚያዛባ ውል በመፈረም ኢትዮጵያ የባህር በሯ መነጠቁን ይከራከራሉ፡፡

ይህን የበለጠ የሚያጠናክር አስተያየት የሚሰጠው የሕግ ባለሙያው አቶ አንዷለም በዕውቀቱ ገዳ በበኩሉ፣ የፖለቲካ ፍላጎት ቢኖር ኖሮ ኢትዮጵያ የባህር በር እንደማታጣ ይገልጻል፡፡ ‹‹ኤርትራ በተገነጠለችበት ጊዜ የኤርትራ ራስ ገዝ አስተዳደር፣ የአሰብ ራስ ገዝ አስተዳደርና የኦጋዴን ራስ ገዝ አስተዳደር ነበሩ፡፡ በቅኝ ግዛት ስምምነት መሠረት ኤርትራ የነበራትን የቆዳ ስፋት ይዛ መሄድ ሲገባት የአሰብ ራስ ገዝ አስተዳደርን ጨምራ እንድትገነጠል መደረጉ ትልቅ ስህተት ነበር፤›› ይላል፡፡

‹‹በኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ወቅት ኢትዮጵያ በግጭትም ባይሆን ከግጭቱ በኋላ በተተገበረው የአልጀርስ ስምምነት ዳግም የባህር በር ማግኘት የምትችልበት ዕድል የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን ኢትዮጵያን የወከሉት 14 የሕግ አማካሪዎች ይህን ማድረግ አልቻሉበትም፤›› ሲልም ያክላል፡፡ ‹‹የአልጀርስ ስምምነት እ.ኤ.አ. በ1900፣ በ1902 እና 1908 የተደረጉ የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ እነዚህ ስምምነቶች አፍሪካን ለመቀራመት በሚል በኢትዮጵያም ላይ ጫና ሲያሳድሩ ከነበሩ ቅኝ ገዥዎች ጋር በጫና የተደረጉ ውሎች ናቸው፡፡ ውሎቹ በተደጋጋሚ በራሳቸው በቅኝ ገዥዎቹ ጭምር የተጣሱ ናቸው፤›› የሚለው አቶ አንዷለም፣ በሞተ ውል የተፈረመ ስምምነት መሆኑን አስረድቷል፡፡

‹‹ፋሺስት ኢጣሊያ ውሉን ጥሶ ኢትዮጵያን ወሮ ከተሸነፈና ከተባረረ በኋላ የጣሊያን ቅኝ ግዛቶችን እንዲያስተዳድሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ አሜሪካና ሶቪየት ኅብረት ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድ ጋር የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለበት በፓሪስ እ.ኤ.አ. በ1947 የተደረገ ስምምነት አለ፡፡ ይህ ብቻም አይደለም የኢትዮጵያ መንግሥት በ1952 ዓ.ም. ባወጣው ትዕዛዝ ቁጥር 6/1952 በሚባለው ሕግ የቅኝ ግዛት ውሎች ውድቅ መሆናቸውን ደንግጓል፤›› በማለትም የሕግ ባለሙያው ይገልጻል፡፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ለረዥም ዓመታት ተዳፍኖ ቢቆይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አጀንዳው ቁልፍ ጉዳይ ሆኖ እየተነሳ ነው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች መለያየት ከአፍንጫቸው አርቀው በማያስቡ መሪዎች የመጣ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በር የተዘጋባት አገር ሆና መኖሯ የማይቆረቁረው ዜጋ የለም፤›› ሲሉ የሚናገሩት ያዕቆብ (ዶ/ር) ጉዳዩ ይዋል ይደር እንጂ መነሳቱ የማይቀር ነጥብ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡  

ያዕቆብ (ዶ/ር) ይህን የተናገሩት የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ዳግም የመታደስ ምልክት ባሳየበት ወቅት ነበር፡፡ ሁለቱ አገሮች መታረቃቸው የባህር በር ጉዳይን የተመለከተ አዲስ ዓይነት የሰላም ስምምነት ይፈጥራል የሚል ተስፋ አሳድሮ ነበር፡፡ በጊዜው በመሪዎች ማለትም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተጀመረው መልካም ግንኙነት ወደ ተሻለ ሁለንተናዊ ጉርብትና ይሸጋገራል የሚል ተስፋ ጭሮ ነበር፡፡  

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በአዲሱ የሰላም ግንባታ ሒደት ላይ መነሻና መድረሻ ሆኖ መቅረብ አለበት በማለት በወቅቱ ብዙ ምሁራን ሲሞግቱ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ የአሰብ ወደብን ዳግም ለመጠቀም ኢትዮጵያና ኤርትራ ተስማሙ ሲባል ነበር፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) እና ኢሳያስ በወቅቱ ከፈጠሩት መግባባትና ቅርርብ አኳያ፣ የኢትዮጵያ የባህር በርም ሆነ የወደብ ጥያቄ በቀላሉ ምላሽ እንደሚያገኝ ተገምቶ ነበር፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የወደብ አማራጮችን ለማስፋት ሰፊ ጥረት ስታደርግ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ እንደ በርበራ ባሉ የሶማሌላንድ ወደቦች ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቱ ኩባንያ ዲፒ ወርልድ ጋር በጣምራ ድርሻ ለመግዛት መንቀሳቀሷ ትኩረት ስቦ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ብዙም ሳይዘገይ ከኤርትራ ጋር የተፈጠረው ዳግም ግንኙነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ መሸጋገር ሳይችል ቀረ፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መፈጠር ደግሞ የአገሮቹን ቅርርብ በግልጽ ወደ የማይታወቅ ገጽታ ቀየረው፡፡ የበርበራ ወደብ ድርሻ ግዥም ቢሆን ሳይሳካ መቅረቱ ነው የተነገረው፡፡

አሁን የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ገፍቶ መምጣት የቻለውም ሆነ ጉዳዩ አጀንዳ ለመሆን የበቃው ከሰሞኑ ከተፈጠሩ ሁነቶች ጋር በተያያዘ ብቻ አለመሆኑን ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በቅርቡ የባህር በር ጉዳይን ፊት ለፊት እንነጋገርበት ብለው በአደባባይ ይፋ ማድረጋቸው የፈጠረው ተፅዕኖ ቀላል አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን አጀንዳ መንግሥታቸው አገራዊ ጉዳይ ማድረግ ከጀመረ መከራረሙ ነው የሚነገረው፡፡     

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሎጂስቲክስ መምህሩ ማቲዎስ እንሰርሞ (ዶ/ር)፣ የወደብ ጉዳይ በአጠቃላይ የባህር በር አጀንዳ በብሔራዊ ሰነዶች ላይ መካተት ከጀመረ መከራረሙን ይጠቅሳሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2019 በወጣውና በሚኒስትሮች ምክር ቤት በፀደቀው የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ ላይ የወደብ አማራጭ ጉዳይ በግልጽ መሥፈሩን ይናገራሉ፡፡ አገሪቱ ቢቻል የራሷ የሆነ የባህር በር ገዝታም ሆነ ተኮናትራ ወደብ ልታለማ እንደሚገባ ተመላክቷል ይላሉ፡፡ ካልተቻለም በጋራ ወደብ በማልማት በነፃነት የመጠቀም አስፈላጊነት ተቀምጧል ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እ.ኤ.አ በ2020 በወጣው ብሔራዊ የትራንስፖርት ዘርፍ ፖሊሲ የወደብና የባህር በር ጉዳይ በተመሳሳይ ሁኔታ መቀመጡን ያስረዳሉ፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መርሆዎችና ይዘት›› በሚል ርዕስ ባለፈው ዓመት መገባደጃ ለውይይት የቀረበው ሰነድም ይህንኑ የባህር በርና የወደብ ጉዳይ በግልጽ አስቀምጦት ይታያል፡፡ ይህ ሰነድ በማጠቃለያው ላይ ‹‹የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና እያጋጠመው ያለውን ውስብስብ፣ ተለዋዋጭና ሁለገብ ፈተና ለመቋቋም፣ በአፍሪካ ቀንድ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) አቅም ማጠናከርና ማዳበር ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ሥራ መሥራት አስፈላጊ ነው። ኢጋድ እንዲጠናከርና በቀጣናው ሰላምና ፀጥታም ሆነ የኢኮኖሚ ትስስር ሥራዎች የመሪነት ሚና እንዲጫወት ማገዝ ትኩረት የሚሰጠው ሥራ ይሆናል፤›› በማለት ያስረዳል፡፡

ሰነዱ በመደምደሚያው ላይ ደግሞ፣ ‹‹በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የአፍሪካ ቀንድና የቀይ ባህር ቀጣናን የኃያላን አገሮች የጂኦ ፖለቲካ፣ ጂኦ ኢኮኖሚና ጂኦ ስትራቴጂ ፉክክር ሰለባና መናኸሪያ ይሆን ዘንድ እየታዩ ያሉ አደገኛ እንቅስቃሴዎች ለቀጣናው ሰላምና የኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋት የሚሆኑበት ደረጃ እንዳይደርሱ ከቀጣናው አገሮችና ክልላዊ ተቋማት ጋር በትብብር መሥራት፣ አስተማማኝና ዘላቂ የወደብ አገልግሎትን ማረጋገጥ፣ በቀይ ባህርና በኤደን ባሕረ ሰላጤ አካባቢ የመጠቀም መብታችንን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ጂኦ ስትራቴጂካዊ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም የሚያስችልና ወደቦችን በጋራ በማልማት አገራችንን የሚያገናኙ መሠረተ ልማቶችን ለማጠናከር የሚያስችል ድጋፍ ማስገኘት ይገባል። ከዚህ በተጨማሪም የአፍሪካ የውኃ ሀብቶችና በአኅጉሩ የባህር ወይም የውቅያኖስ ዳርቻዎች ላይ በሚታዩ ጂኦፖለቲካዊ ክስተቶች ላይ የአፍሪካ ኅብረት የመሪነት ሚና ሊኖረው ይገባል፤›› በማለት ቃል በቃል አስቀምጦታል፡፡

ከእነዚህ ብሔራዊ ሰነዶች በመነሳት እንዲሁም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በቅርብ ሰሞን ከሚያደርጉት ይፋዊ ንግግር አኳያ፣ የባህር በርና የወደብ አማራጭ የማግኘት ጥያቄ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን መናገር ይቻላል፡፡ በርካታ ምሁራን ደግሞ የባህር በርም ሆነ ወደብ የማግኘት ጥያቄ አገሪቱ ካላት ታሪክ አንፃር በቀላሉ መሳካት የሚችል ስለመሆኑ እየተናገሩ ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ዓለም አቀፍ ሕጎችም እንደሚደግፉት እየገለጹ ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ1879 ቦሊቪያ ከፔሩ ጋር ተባብራ ከቺሊ ጋር ውጊያ ገጥማ ነበር፡፡ ‹‹ዋር ኦፍ ዘ ፓሲፊክ›› በተባለው በዚህ ጦርነት በመጨረሻ ቺሊ አሸናፊ ሆነች፡፡ ቺሊ በጦርነቱ ከማሸነፍ፣ በላይ የሁለቱን አገሮች ወደቦች በኃይል ጠቀለለች፡፡ ፔሩ ተለዋጭ ወደብ ስለነበራት አልተቸገረችም፡፡ ቦሊቪያ ግን ከዚያን ጊዜ ወዲህ የባህር በር የሌላት አገር ሆና ቀረች፡፡

ቺሊ በጎረቤቷ ቦሊቪያ ላይ በር ለመዝጋት አልፈለገችም ነበር፡፡ አንቶፋጋስታና አሪካ ወደቦችን እንድትጠቀም ለቦሊቪያ ፈቀደች፡፡ ወደብ ብቻ ሳይሆን ከወደብ መገናኛ መተላለፊያም ተፈቅዶላት ነበር፡፡ ቦሊቪያ ግን ሉዓላዊ የሆነ የራሴ የባህር በር ካልተመለሰልኝ በማለት ከቺሊ ጋር ለረዥም ዘመናት ግንኙነት አቋርጣ መኖሯ ይነገራል፡፡

ቦሊቪያዊያን የባህር በራቸውን ከተነጠቁ ቢቆዩም በየዓመቱ የባህር ቀን ብለው በብሔራዊ ደረጃ ያከብራሉ፡፡ በዕለቱ የባህር በራቸውን የተነጠቁበትን ሁኔታ አስበው ይውላሉ፡፡ አገሪቱ የባህር በር ሳይኖራት ቲቲካካ ሐይቅ ላይ የሠፈረ 5,000 የባህር ኃይል ጦር አላት፡፡ ቦሊቪያዎች የባህር በር ጥያቄያቸውን ለማስመለስ ያልሄዱበት ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የለም፡፡ አይሲሲ የዛሬ አምስት ዓመት ጥያቄውን ተቀብሎ የተመለከተው ሲሆን፣ ቺሊ ለቦሊቪያ ሉዓላዊ ወደቦቿን ለመመለስ የምትገደድበት አንዳችም የሕግ አግባብ የለም ብሎ ውሳኔ መስጠቱን አልጄዚራ ዘግቦታል፡፡

ከዚህ በተለየ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ሕጎችና ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋን ማስመለስ ትችላለች የሚሉ ምሁራን ግን፣ ከቺሊና ከቦሊቪያ ውጪ የሌሎች አገሮች በጎ ልምዶች መኖራቸውን እየተናገሩ ነው፡፡

ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆኑት ያዕቆብ (ዶ/ር) እ.ኤ.አ ጁን 24 ቀን 2018፣ ‹‹የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ማንም ኢትዮጵያዊ የሚዘለው ጉዳይ አይደለም›› በሚል ርዕስ ከተነበበው ከሪፖርተር ዕትም ጋር ባደረጉት ቆይታ የሚከተለውን ብለው ነበር፡፡  

‹‹ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የቬርሳይ ስምምነትን የአውሮፓ አገሮች ሲፈራረሙ ፖላንድ ወደብ አልባ ነበረች፡፡ እናም ከጀርመን መተላለፊያ (ኮሪዶር) ተሰጥቷት ወደብ እንድታገኝ ተደረገ፡፡ አፍሪካ ውስጥም ለምሳሌ ኮንጎ ኪንሻሳና ኮንጎ ብራዛቪልን ማንሳት ይቻላል፡፡ ኮንጎ ኪንሻሳ የቤልጂየም ግዛት ነበር፡፡ ብራዛቪል ደግሞ የፈረንሣዮች ነበር፡፡ ኮንጎ ብራዛቪል ወደብ አልነበረውም፡፡ ሁለቱም ተስማምተው ከኮንጎ ኪንሻሳ የተወሰነ መሬት ወስደው ኮንጎ ብራዛቪል ወደ ባህር እንድትዘልቅ ተደረገ፡፡ ይህ ከመጀመሪያው ኢትዮጵያ ውስጥ መነሳት የነበረበት ጉዳይ ነው፡፡ ለድርድርና ለስምምነት መቅረብ ነበረበት፡፡ ለኢትዮጵያ እንዲያውም ትልቁና አንገብጋቢው ጉዳይ እሱ ነው፡፡ የወደብ ጥያቄ ድርድሩ ላይ አለመነሳቱ ለወደፊቱም የሰላም ጠንቅ ሊሆን የሚችል ነገር ነው፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር ኢትዮጵያ በዓለም ወደብ አልባ ከሚባሉ አገሮች ትልቋ ነች፡፡ ሁለተኛዋ ኡጋንዳ ስትሆን፣ የኢትዮጵያን አንድ ሦስተኛ ሕዝብ ነው ያላት፡፡ በኢትዮጵያ ወሰንና በባህሩ ጠርዝ መካከል ያለው ርቀት ከ60 ኪሎ ሜትር ያነሰ ነው፡፡ በዓለም ትንሹ ርቀት የሚባለውም ይኼው ነው፤›› በማለት ነበር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -