በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ገንዘብ ለሚያስቀምጡ ደንበኞች የዋስትና ሽፋን ለመስጠት በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመው ‹‹የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ›› በይፋ ሥራ መጀመሩን በዚህ ሳምንት አስታውቋል፡፡ ፈንዱ ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ባንክ ሲሆን፣ ሕጋዊ ሰውነት ኖሮት የመክሰስና የመከሰሰ መብት ያለው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አምስት የቦርድ አባላት ያሉት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ፣ የባንክ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር፣ የባንኩ አነስተኛ ሱፐር ቪዥን ዳይሬክተር፣ የባንኮች ማኅበር ተወካይና የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ማኅበር ተወካይ የቦርዱ አባል የሆኑበት ነው፡፡ ዳዊት ታዬ የፈንዱ የመጀመርያው የቦርድ ሰብሳቢ ከሆኑት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ ጋር በፈንዱ አገልግሎትና አጠቃላይ የሥራ ሒደት ዙሪያ ያደረገውን አጭር ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ሪፖርተር፡- የዚህ ፈንድ አስፈላጊነት እንዴት ይገለጻል? አጠቃላይ አሠራሩንና የሥራ ሒደቱን ቢገልጹልኝ?
አቶ ሰለሞን፡- በመጀመርያ የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ በኢትዮጵያ ውስጥ ተቋቁሞ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በፋይናንስ ዘርፉ እየተደረጉ ከሚገኙ ትልልቅ ሪፎርሞች መካከል አንዱ የዚህ ፈንድ መቋቋምና ወደ ሥራ መግባት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ አልነበረንም፡፡ በሌላ አገላልጽ ግልጽ የሆነ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ አልነበረንም፡፡ ምናልባትም አይበለውና አንድ የፋይናንስ ተቋም ኪሳራ ገጥሞት ቢወድቅ ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ችግር ያስከትል ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት መንግሥት ኃላፊነት ስላለበት ከግብር ከፋዮች ገንዘብ ወስዶ ለአስቀማጮች ገንዘባቸውን የመክፈል ግዴታ ይወድቅበት ነበር፡፡ ይህንን የምለው መንግሥት አስቀማጮችን የመታደግ ኃላፊነት ስላለበት ነው፡፡ የመድን ፈንዱ ሳይኖር የፋይናንስ ተቋማት ከስረው ቢሆን ኖሮ መንግሥት ብዙ ኪሳራ ገብቶ የሕዝብን ገንዘብ የሚመልስበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችል ነበር፡፡ አሁን ግን ግልጽ የሆነ የመድን ሽፋን መዘርጋቱ ለፋይናንስ ዘርፉ ትልቅ እምነት የሚፈጥር ነው። የተቋቋመው ፈንድ በመንግሥት የሚተዳደር ነው፡፡ በአንዳንድ አገሮች በግል ኩባንያዎች የሚሰጥ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ግን ፈንዱ በመንግሥት እንዲተዳደር ሆኖ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ በፈንድ ማቋቋሚያ ሕግ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ባንኮችንና የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት የፈንዱ አባል መሆን ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ ስለዚህ የዚህ ፈንድ ጠቀሜታ ምንድነው? ከተባለ የመጀመሪያና ዋነኛው ጉዳይ የፋይናንስ ዘርፉን ጤንነት መጠበቅ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የገንዘብ አስቀማጮችን ጥቅም የሚጠብቅ ይሆናል፡፡ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ አንዱ የፋይናንስ ተቋም ላይ ችግር ከተፈጠረ ሌሎቹንም የሚነካና ተያይዞ መውደቅን የሚያስከትል ነው፡፡ ስለዚህ የፋይናንስ ተቋማትን ጤንነትና መረጋጋት ለማረጋገጥ የተቋቋመው ፈንድ የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ለገንዘብ አስቀማጮች መተማመን የሚፈጥር ስለሚሆን እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የፈንዱ ሌላው ተግባር ችግር የሚገጥማችሁን ተቋማት ከማስተዳደር አንፃር የፋይናንስ ተቋማት ሴፍቲኔ ይቋቋማል፡፡ አራት አባት የሚኖሩት ሆናል፡፡ ይህም የፋይናንስ ተቋማት ሴፍቲኔት ይባላል ችግር ቢገጥም ለቀውሱ ምላሽ የሚሰጥ ይሆናሉ፡፡ ኢንዱስትሪው ውስጥ አንድ ተቋም ቢወድቅ ደግሞ ምንም ዓይነት ችግር ሳያስከትል ኮሽታ ሳያሰማ ኢኮኖሚው ሳይረበሽ ቀስ ብሎ እንዲወጣ የሚሠራ ይሆናል፡፡ በባንኩ ገንዘብ ያስቀመጡ ደንበኞችም ለችግር ሳይጋለጡ ፈንዱ በሦስት ወራት በመድን የተሸፈነውን የተቀማጭ ገንዘብ ለአስቀማጮቹ ይመልሳል፡፡ ሦስት ወር ቢባልም ከሰባት ቀናት ጀምሮ ለአስቀማጮች ገንዘቡን የሚመልስበት አሠራር የሚኖረው ይሆናል፡፡ ከሚጣራው የፋይናንስ ተቋሙ ንብረት ፈንዱ ተካፋይ ነው የሚሆነው፡፡ ለአስቀማጩ በከፈለው ልክ ገንዘቡን ያገኛል ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ሞራል ሃዛርድ የሚባለውን ነገር ለመቀነስ እንዲቻል በተለያዩ መንገዶች በባንኮችና በአነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት የሚቀመጡ የቁጠባ፣ የተንቀሳቀሽ፣ በጊዜ የተገደበ የተቀማጭ ገንዘቦችን ሙሉ በሙሉና መካከለኛና ከፍተኛ የገንዘብ ተቀማጮችን በከፊል ለመሸፈን አቅም እንዲኖረው ተደርጎ ከአንድ መቶ ሺሕ ብር የሚያንስ ውስን ወይም ከፊል የተቀማጭ ገንዘብ የመድን ሽፋን የሚሰጥ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አገልግሎቱን በተመለከተ በሰጣችሁት ማብራሪያ ፈንዱ የእያንዳንዱን አስቀማጭ እስከ መቶ ሺሕ ብር የሚሆን ገንዘብ ብቻ ነው የመድን ሽፋን የሚሰጠው ተብሏል፡፡ ከአንድ መቶ ሺሕ ብር በላይ ለሚሆነው ገንዘብ ተቀማጭ ያላቸው አስቀማጮች እንዴት ነው እንዲህ ባለው የመድን ሽፋን ማግኘት የሚችሉት? ከአንድ መቶ ሺሕ ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ያላቸው አስቀማጮች ገንዘባቸውን ያጣሉ ማለት ነው? ከዚህ ቀደም እስከ 200 ሺሕ ለሚሆነው ተቀማጭ ሽፋን ነበርና ይህስ ለምን ተቀየረ?
አቶ ሰለሞን፡- የመድን ፈንድ መጠኑ እስከ መቶ ሺሕ ብር ለሚደርስ ተቀማጭ ያላቸው አስቀማጮች የመድን ፈንድ ለመስጠት የተወሰነ ነው፡፡ በጥናት ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ በአገራችን በባንክና በማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ያሉ አስቀማጮች ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከ100 ሺሕ ብር በታች ተቀማጭ ያላቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ የፈንዱ አሁን ባለው አቅም እስከ መቶ ሺሕ ብር ላለው ተቀማጭ ሽፋን እንዲሰጥ ተወስኖ ነው ወደ ሥራ የገባው፡፡ አሁን ዓረቦኑ (ፕሪሚየሙን) እንዳለ ሰብስበን መልሰን እስከ መቶ ሺሕ ብር ለመስጠት ነው፡፡ ለዚህ ይበቃናል ብለን ስላሰብን ነው፡፡ ከዚያ በላይ እንሂድ ካልን አቅሙ አይኖረንም፡፡ ሁለተኛ ትልልቅ የሆኑ ተቀማጮች ስላሉ እሱን የመሸፈን አቅም የለንም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ትልልቅ ገንዘብ አስቀማጮች ግን ሙሉ በሙሉ ሽፋን አያገኙም ማለት አይደለም፡፡ ካላቸው ተቀማጭ በመድን ፈንድ የሚሸፈነው አንድ መቶ ሺሕ ብሩን ይወስዳሉ፡፡ ከዚያ በላይ ያለው ላይ ነው አቅም የለንም የምንለው፡፡ ከዚያ ባሻገር ግን ከሰረ ከሚባለው የፋይናንስ ተቋም ቀሪ ሀብት ላይም ፈንዱ ድርሻ የመጠየቅ መብት ይኖረዋል። ሌሎችም የድርሻ ጥያቄ የሚያነሱ አካላትም ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱ ካደረጉ በሕግ መሠረት ድርሻቸውን ካገኙ በኋላ የሚተርፍ ቀሪ ሀብት ካለ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ይተርፋል ወይ የሚለውን ጉዳይ ነው ማየት ያለብን። የሚተርፍ ካለ ግን ትልልቅ አስቀማጮች ገንዘባቸውን ያገኛሉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አሁን የሚሰበሰበው ፈንድ እያደገ ከመጣና የሚፈለገው ደረጀ ላይ ከደረሰ የፋይናንስ ተቋማቱ በዓረቦን መልክ ለፈንዱ ማስገባት ያለባቸው መጠን እንዲቀንስ ሊደረግ ይችላል፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ ዕርምጃዎችም የሚወሰዱ ይሆናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ የሚሰበሰበው ፈንድ ኢንቨስትመንት ላይ ይውላል፡፡ በዘንድሮው የመጀመርያ ሩብ ዓመት ወደ 1.6 ቢሊዮን ብር ዓረቦን ሰብስበን ኢንቨስት አድርገናል፡፡ በቀሪዎቹ ሦስት ሩብ ዓመት ወደ ስድስት ቢሊዮን ብር አካባቢ ለመሰብሰብ አቅደናል፡፡
ሪፖርተር፡- ፈንዱን ሥልጣንና ኃላፊነት በመተለከተ መርዳት እንደቻልነው በባንኮች ያለው ተቀማጭ ገንዘብ ዋስትና እንዲኖረው ከማድረግ ባሻገር ለአንድ ባንክ መክሰርና ከገበያ መውጣት ምክንያት ናቸው የተባሉ ኃላፊዎች በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ኃላፊነትም ለፈንዱ ተስጥቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ብሔራዊ ባንክ ባንኮችን የሚቆጣጠርበት የራሱ ሕግ ያለው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ለባንኩ ወይም ለማክሮ ፋይናንስ ተቋሙ መክሰር ተጠያቂ ናቸው የሚባሉትን ሰዎች በብሔራዊ ባንክና በፈንዱ የሚጠየቁ ይሆናል ማለት ነው?
አቶ ሰለሞን፡- ሁለቱም ሱፐርቫይዝ ያደርጋሉ፣ ብሔራዊ ባንክም ሆነ ፈንዱ በየራሳቸው የቁጥጥሩን ሥራ ይሠራሉ፣ ይከታተላሉ፡፡ ፈንዱ ተቀማጭ ገንዘብን የተመለከተ ክትትል ያደርጋል። ተቀማጭ ገንዘቡ ምን እየሆነ ነው? እየወረደ ነው ወይስ እየጨመረ የሚለውን ይከታተላል፡፡ በተጨማሪም የፋይናንስ ተቋማቱ የሰበሰቡትን ተቀማጭ ገንዘብ እንዴት እያስተዳደሩት ነው የሚለውን ሁሉ ትኩረት ሰጥቶ ይከታተላል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ደግሞ አጠቃላይ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ጤንነት ከላይ ሆኖ ይቆጣጠራል፡፡ ስለዚህ የባንክ ሥራ መሪዎች የተቀማጭ ገንዘብን በደንብ እንዲያስተዳድሩ ነው ወይ? ወይስ ዲፖዚት ኢንሹራንስ አለ ብለው ዝም ብለው ሪስክ እየወሰዱ ነው የሚለውን የተቋቋመው ፈንድ የመከታተል ሥራ ይሠራል ማለት ነው፡፡ ችግር ካለም እንዲያስተካክሉ ይደረጋል፡፡ ቀውስ ከተፈጠረ በኋላ መሯሯጥ ሳይሆን ቀውሱ ከመከሰቱ በፊት የሚከታተልበትና ከፋይናንስ ዘርፉ ዓረቦን የሚሰበስብበት አሠራር ይኖረዋል፡፡ ተጠያቂነትን ከማስፈን አንፃርም አንድ የፋይናንስ ተቋም እንዲወድቅ ምክንያት ናቸው ተብለው የሚጠራጠሩ አካላትን ለፍርድ ለማቅረብና ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል ሥልጣን ፈንዱ ተሰጥቶታል፡፡ ለአንድ የፋይናንስ ተቋም መውደቅ ምክንያት ነው ተብሎ የሚጠረጠር ሰው ካለ ፈንዱ ይህንን ተከታትሎ እስከመጨረሻው ድረስ በመሄድ በሕግ ተጠያቂ ያደደርገዋል፡፡ ችግሮች ሥር ሰድደው ከፍተኛ ጉዳት ከማደረሳቸው በፊት ፈንዱ የፋይናንስ ተቋማትን ችግር አስቀድሞ የሚተነብይ፣ በፍጥነት ተገቢ መፍትሔ የሚሰጥና የሴፍቲኔት ማዕቀፍ አካል ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ለአንድ ባንክ ወይም የፋይናንስ ተቋማት መክሰር ምክንያት ናቸው የተባሉ የሥራ ኃላፊዎች ለአንድ የፋይናንስ ተቋማት ምክንያት ከሆኑ ወይም የተጠረጠሩን ፈንዱ እስከመጨረሻው ተከታትሎ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰደባቸው ያደርጋል ከተባለ ይህ ሕጋዊ ዕርምጃ የሚወስድባቸው አስተዳደራዊ ነው ወይስ ሌላ የሚጠየቁበት መንገድ አለ?
አቶ ሰለሞን፡- በፍርድ ቤት ነው የሚጠየቁት፡፡ ኬዝ ባይ ኬዝ ጉዳዩ እየታየ ምን አድርጎ ነው የጣለው? ምን ሠርቶ ነው? ምን ያልተገባ ነገር ፈፅሞ ነው? ባንኩ ወይም ማይክሮ ፋይናንስ ተቋሙ እንዲወድቅ ያደረገው? የሚለውን በፍርድ ቤት ይታያል፡፡ ይከራከራል፡፡ ራሱን እንዲከላከል ያደርጋል፡፡ እውነት ሆኖ ከተገኘ በሕጉ መሠረት ይቀጣል ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ባንኮች እስካሁን ጤናማ ሆነው መቀጠላቸው ይታመናል፡፡ ከስሮ ከገበያ የወጣ ባንክ የለም፡፡ ከዚህ በኋላ ኪሳራ ያጋጥማቸዋል የሚል ሥጋት አለ? የዚህ ፈንድ መቋቋም ምናልባትም በቅርቡ በአንዳንድ ባንኮች እየገጠማቸው ካለው የገንዘብ እጥረት ጋር የተያያዘ ነው?
አቶ ሰለሞን፡- ሥጋት የለም፣ ሥጋት ሙሉ በሙሉ ይጠፋል ማለት ግን አይደለም፡፡ የቁጥጥር ሥራውን ዲፖዚት ኢንሹራንስ ፈንድ ሥጋቱን ለመቀነስ ነው፡፡ በሌላው ዓለም ትልልቅ ባንኮች ከስረው ሲወጡ ዓይተናል፡፡ ይህ እንዳይሆን ቀድሞ መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ በእኛ ሁኔታ አሁን ሥጋቱ ይቀንሳል የምንልበት ዋናው ምክንያት ሴፍቲኔት በሌለበት እስካሁን ቆይቷል፡፡ አሁን ሴፍቲኔት ባለበት ሁኔታ ወይም ደግሞ ዲፖዚት ኢንሹራንስ መጥቻለሁ እያለ መተማመን የሚጨምር ሁኔታ ሲፈጠር መረጋጋቱ በሚጨምርበት ጊዜ የመውደቅ ዕድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው የአገራችን ፋይናንስ ተቋማት ሁኔታ ሥጋት የለም፡፡
ሪፖርተር፡- ከባንኮቹ በየዓመቱ ዓመታዊ አማካይ የቁጠባ መጠናቸው ታይቶ ከዚያ በላይ በአማካይ የቁጠባቸው 0.3 በመቶ ተሠልቶ ለፈንዱ በየዓመቱ በዓረቦን መልክ ገቢ ያደርጋሉ፡፡ ይህ አሁን ካለው ተቀማጭ ገንዘብ አንፃር ሲታይ ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ እስካሁን ካደረጋችሁት እንቅስቃሴ መረዳት እንደተቻለው ወደ 1.6 ቢሊዮን ብር ሰብስባችኋል፡፡ በዓመቱ ውስጥ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ደግሞ ለማሰባሰብ አቅዳችኋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ፈንዱ በየዓመቱ በቋሚነት የሚሰበሰበው ገንዘብ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ገንዘብ መጠን ግን በየጊዜው እያደገ ይሄዳልና ይንን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ አሰባስባችሁ ምንድነው የምታደርጉት በፈንዱ የሚሰበሰበው ገንዘብ ከሚፈለገው በላይ ቢሆንስ ምን ለማድረግ ታስቧል?
አቶ ሰለሞን፡- ዋናው ዓላማ ለገንዘብ አስቀማጮች ጥበቃ መስጠት ነው፡፡ ገንዘብ አስቀማጮች ገንዘባቸውን ምንም ሳይቀነስ ሳይሸራረፍ ማግኘት እንዲችሉ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ አቅም ካለ መቶ በመቶ በሙሉ እስኪመለስ ይካሄዳል፡፡ ዓለም አቀፍ መመዘኛ መሠረት የሚሰባሰበው ፈንድ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ከደረሰ ሊወሰዱ የሚችሉ ዕርምጃዎች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ የፋይናንስ ተቃማቱ የሚከፍሉትን የፕሪሚየም (ዓረቦን) መጠን ዝቅ ለምን አናደርግም የሚለውን ነገር በሒደት ሊመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ ጫና በማይፈጥር መልኩ ሁኔታዎች እየታዩ የተለያዩ ዕርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡
ሪፖርተር፡- በየዓመቱ ባንኮችና ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ከአማካይ ዓመታዊ ተቋማት ገንዘባቸውን 0.3 በመቶ ለዓረቦን የሚያወጡ መሆኑ እንደተባለው ከፍተኛ ገንዘብ ነውና በዚህ መመርያ አተገባበርና አጠቃላይ አሠራሩን በተመለከተ ከባንኮችና ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር መክራችሁበታል? ያገኛችሁስ ምላሽ?
አቶ ሰለሞን፡- ከመጀመሪያው ከጥናቱ ጀምሮ የፋይናንስ ተቋማትን አሳትፈናል፡፡ በረቂቁ ላይ እስከመጨረሻ መድረስ ሐሳብ እንዲሰጡበት ተደርጓል፡፡ ሌላው ቀርቶ የዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅት በረቂቁ ላይ ሐሳባቸውን የሰጡበትና ስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ ነው፡፡ አስፈላጊ መሆኑም ታምኖበት ወደ ተግባር የተገባበት ጉዳይ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እንደዚህ ዓይነት ተቋም መፈጠሩ ለአስቀማጮች ገንዘብ ዋስትና ከመስጠት ባለፈ ችግር የገጠማቸው የፋይናንስ ተቋማት አማሟታቸው እንዲያምር ያደርጋልም ብለዋልና ይህንን አባባልዎትን ቢያፍታቱልኝ?
አቶ ሰለሞን፡- የፋይናንስ ተቋማት እንደ ሰው ይታመማሉ፡፡ ኮማ ውስጥ ይገባሉ፡፡ አንድ የፋይናንስ ተቋማት ታምሞ መድኃኒት ተሰጥቶት የሚድን ከሆነ ይቀጥላል፡፡ ካልዳነ ደግሞ ይሞታል፣ ይቀበራል፡፡ የቀብር ሥርዓቱ ደግሞ ኢኮኖሚውን የማይጎዳ መልኩ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ ካሉት የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ምንም ችግር የሌላባቸው ተቀማጭ ገንዘቦች አሉ፡፡፡ ችግር የሌለባቸው አሴቶች አሉ፡፡ እነዚህን ጤናማ በመሆናቸው ችግር ያለባቸውን ደግሞ በሥርዓቱ ለአስቀማጮቹ አስፈላጊውን ነገር ሰጥተን በሥርዓቱ ኮሽታ ሳይኖር አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርግ ሥራ ይሠራል ለማለት ነው፡፡ ችግር የገጠመውና የከሰረ ተቋም በሕግ አግባብ በሥርዓቱ እንዲዳኝ ይደረጋል፡፡ ችግር የሚያመጡ ነገሮች ይጣላሉ ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የፋይናንስ ተቋማቱ ለፈንዱ በየዓመቱ ከተቀማጭ ገንዘባቸው ለፈንዱ ዓረቦን የሚገዙበት የገንዘብ መጠን እንዴት ነው የሚሠላው?
አቶ ሰለሞን፡- የዓረቦን ቀመር ክፍያ ከሚፈጸምበት ቀን በፊት ባሉት 12 ወራት የፋይናንስ ተቋማት አማካይ ተቀማጭ ገንዘብ 0.3 በመቶ እንደ ዓመታዊ ዓረቦን አድርጎ በማስከፈል ነው፡፡ አንድ የፋይናንስ ተቋማት በሚወድቅበት ጊዜ አወዳደቅን የሚያሳምር ማለት ይህ ነው፡፡ መስተካከል የሚችለውን እንዲያስተካክል መንገድ በመፈለግ ይሠራል፡፡ መከበር ያለበትን ደግሞ የቀብር ሥርዓቱን ብዙ ኮሽታ ሳያሰማ ስሙዝ በሆነ ሁኔታ የቀብር ሥርዓቱን የሚፈጸም አካልም አለ ማለት ነው፡፡