Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትከብሔር ፖለቲካ እስረኝነት ለመገላገል መዘጋጀት እንደምን??

ከብሔር ፖለቲካ እስረኝነት ለመገላገል መዘጋጀት እንደምን??

ቀን:

(ክፍል ሁለት)

በበቀለ ሹሜ

በዕውቀትና በምክንያት የተኮተኮተ ህሊና በበረከተበት ኅብረተሰብ ውስጥ፣ በዕውቀትና በምክንያት በሚመራ ፖለቲካ ዴሞክራሲንና ፍትሕን ተባብሮ የማማጣቱና የመገንባቱ ዕምቅ አቅም ይኖራል፡፡ ማለትም ነባሩን መንግሥታዊ ሥርዓት በትግል አስጨንቆ በውድም በግድ ወደ ዴሞክራሲ ለመራመድ ዕድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡

ይህ እኛ ዘንድ የለም፡፡ ‹‹መማር›› እና መሃይምነት አንድ ላይ ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ሁለቱ ተዛመዱ ማለት፣ ዕውቀትና ምክንያታዊነት በማያርማቸው እስበቶችና ዘልማደኛነት ህሊና ተዳደረ ማለት ነው፡፡ በዕውቀትና በምክንያት የማይመራ የዚህ ዓይነት ‹‹ልሂቅነት›› በበረከተበት ሥፍራ፣  በአርቆ አስተዋይነት ኅብረተሰብን አስተባብሮ የመምራት የፖለቲካ አቅምም አይኖርም፡፡ ዴሞክራሲ ባልተገነባበት ሁኔታ ውስጥ እየተኖረ፣ ሕገ መንግሥትና ሕግ ላይ መብቶች ስለሠፈሩ ብቻ ‹‹የዴሞክራሲ መብታችንን አትጣስ!›› እያሉ ከማለት የላቀ ነገር በፖለቲከኞቻችን ዘንድ የማናየው በፖለቲካ አቅም ማነስ ምክንያት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት የአቅም ችግር ውስጥ የወደቀ የለውጥ ፈላጊነት ወደፊት ለመራመድ ማካካሻ ዘዴ መፈለግ አለበት፡፡ በተባበረ ትግል ሰላምን (የሕዝብ ደኅንነትን) ለማሟላት በመታገልና የመንግሥትን ሕግ አክባሪነት የሚፈታተኑ ግጭቶችንና ተኩሶችን በማዳከም መንግሥትን ለዴሞክራሲ ግንባታ ማደፋፈር፣ የራስንም በዕውቀት የተመራ ፖለቲካዊ አቅም በሒደት መገንባት አንድ ሁነኛ ዘዴ ነው፡፡

የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች በሕግ ስለተቀመጡ አብረውን አሉ ማለት አይደለም፡፡ በደርግ ሕገ መንግሥት ላይ ነበሩ ግን በሕይወታችን ውስጥ አልነበሩም፡፡ በኢሕአዴግ ሕገ መንግሥትም ውስጥ ተጽፈዋል፡፡ በኢሕአዴግ/ሕወሓት ገዥነት ጊዜም ሆነ አሁን ያሉን መብቶች በጣም ውስን ናቸው፡፡ በየአምስት ዓመት ካርድ ሳጥን ውስጥ ከመክተትና ለቁንጥጫ በማያበቃ ልክ ተደራጅቶ መንግሥትን ከመተቸት የራቁ አይደሉም፡፡ የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች (መሠረታዊ የሚባሉት እንኳ) አንዴ አይገኙም፡፡ ከኅብረተሰብ ባህልና ፍላጎቶች ከማደግ ጋር እየተበራከቱ/እየሰፉ የሚመጡ ናቸው፡፡ መብቶቹን የሚጨምርልንና የሚያሰፋልንም መንግሥት አይደለም፡፡ እኛው ኅብረተሰብ የምንባለው ነኝ የምናበራክታቸው፡፡ ማበራከት ማለት ደግሞ የጎደሉትን መፈለግ፣ የጠበቡት እንዲሰፉ መታገልና በሕግ የተቀመጡትን የኑሯችን አካል ማድረግ ነው፡፡ በሕግ ተቀምጠው የኑሮ ፍላጎቶቻችን ካልሆኑና የማንጠቀምባቸው ከሆነ መብቶቹን አናውቃቸውም፣ እነሱም አያውቁንም፡፡

1) የብሔርተኛ ፖለቲካን አዙሪት ለማምከንና ለማስወገድ ሴራ ማሰላሰል አያስፈልገንም፡፡ የሚያስፈልገን የብሔርኛነት አጫፋሪ ከመሆን መራቅና ብሔርተኞች ለመፈጸም የሚከብዳቸውን አውቀን በዚያ እነሱን መብለጥ ነው፡፡ ይህ ማለት በኢአግላይነት/በኢአንጓላይነት ከእነሱ ልቆ መገኘት ነው፡፡ የሁሉን ብሔረሰብ ባህሎችና ቋንቋዎች ያለ አድልኦኛነት እንደ ራስ ማክበር፣ የሁሉንም ማኅበረሰብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የተግባር ልምምዳችንና ንቃታችን አድርጎ ማባዛት ማለት ነው፡፡ በዚህም ጎዳና፣ መላ ኅብረተሰባችንን አንድ ላይ ለማትመም ተጋግዞ መሥራት ማለት ነው፡፡

በየትኛውም አካባቢ ያለ ሕዝባችን በሰላም ዕጦት መንገላታት በቃው!!! በኑሮ ውድነት የመጠበሱም ዋና መንስዔ ሰላም ማጣቱ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር የሚያስፈልገውን ትግል ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኛ ነን የሚል የጋራ አቋም መያዝ  ዛሬ እጅግ አስፈላጊያችን ነው፡፡ ለኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ያለን አመለካከትም ከላይኛው ለሕዝብ የመሳሳት አቋም ሊነጠል አይችልም፡፡ የፀጥታ ኃይሎቻችን አባላት በጥቅሉ ከመላ ኅብረተሰባችን የወጡ እንደ መሆናቸው ለእነሱ መሳሳት ለመላ ሕዝባችን ሰላም የመሳሳትም ጉዳይ ነውና፡፡ በትንሹም በትልቁም የፀጥታ ኃይሎቻችን ሕዝባዊ ስሜታቸውና የሙያ ትጋታቸው እንዳይዝል መንከባከብ፣ ኅብረተሰባዊና መንግሥታዊ ኃላፊነታችን ነው፡፡ በመከላከያ ኃይላት ውስጥ ተሰማርቶ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ አገርን ማገልገል የላቀና ልዩ ክብር የሚሰጠው ሙያ ነው፡፡ አሁን ያለው የመከላከያ ሠራዊታችን ግን በመደበኛ ሁኔታ ውስጥ ሙያውን የወደዱ የተሰባሰቡበት ዓይነት ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያ የዘለለ ታሪካዊ ወዘና አለው፡፡ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የጦር ኃይል ግንባታ ታሪክ ውስጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ የአገሪቱ ሕዝቦች በልባዊ ስሜት ተፈንቅለው ለአገራዊ ህልውናቸው ለመዋደቅ የተገማሸሩበት፣ ወላጆች ሴት፣ ወንድ ሳይሉ አፍላ ልጆቻቸውን መርቆ ለመስጠት የተረባረቡበት ማዕከል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ መከላከያ ሠራዊት ለእኛ ለዛሬ ኢትዮጵያውያን ከአንድ ውድ አገራዊ ተቋም በላይ ነው፡፡ መላ ኢትዮጵያ ከሁሉም አካባቢ ከሁሉም ብሔረሰብ ከሁሉም ሃይማኖትና ፆታ በአገር ፍቅር የተገማሸርንበት ማዕከል ነው፡፡ በመከለከያ ሠራዊት ውስጥ የሁላችንን ልጆች፣ የሁላችንን ተጋድሎ ነው የምናየው፡፡ በዚያ ውስጥ ያሉ ልጆቻችን መንከውከው፣ መድማትና መሰዋት የሁላችንም መድማትና መሰዋት ነው፡፡ በዚህ መልክ በመከላከያ ሠራዊትነት ውስጥ የራሳችንን ተጋድሎ ማየት ከቻልን፣ በሰላም መንገድ/በምክክርና በፖለቲካ ብልኃት ሊቃለሉ በሚችሉ ማለቂያ ያለሽ ትርምሶች ውስጥ ያለ ዕፎይታ ለዓመታት መከላከያችን እየባዘነ ሕይወት መክፈሉ ይቆጠቁጠናል፡፡ ውድ ሥጋዎቻችንን ውድ ደማችንን ማባከን፣ ተልዕኮን የመፈጸም ውድ ወኔና ቁርጠኝነታችንን፣ እንዲሁም የሕዝብ ተከባሪነታችንን ማቸርቸፍ ይሆንብናል፡፡ ማለቂያ ባጣ የግርግር አዙሪት ውስጥ የፀጥታ ኃይላችን ትኩስ ሕዝባዊ ተወዳጅነትና ትጉህ ወኔ መቸርቸፍ የዋዛ ኪሳራ አይደለም፡፡ ሥዕሉን ሙሉ አድርገን ከተረዳነው ደግሞ በሁለት በኩል የምንንከወከው፣ እየተታኮስን የምንወድቀው በውጤቱም ኑሯችን የሚማቅቀው የእኛው ነው፣ እኛው በእኛው በሆነ ጥፋት፡፡ በዚህ ዓይነት ጥፋት የራሳችንን ሰላም መጎድፈር አገራዊ ህልውናን ለውጪ ጥቃት እስከ ማጋለጥ አድርሶናልም፡፡ ይህን ያህል ጥፋታችን ከተሰማን ለውስጥ ትርምሶቻችን ከቃታ ውጪ የሆኑ መፍትሔዎች ለመፈለግ የጠነከረ ፍላጎት ይኖረናል፡፡

ከላይ የተቀመጡት ሁለት ነጥቦች በተግባር ዕውን ሊሆኑ የሚችሉት፣ በየትም የኢትዮጵያ ሥፍራ ጠመንጃ ይዞ ጫካና በረሃ የወረድንም ሆነ ገጠርና ከተማ እየተወዛወዘ የሚተኩስ ቡድንን (የፈለገውን ያህል በጎ አቋም አለኝ ቢልም) ያለማወላወል  መቃወም፣ ወደ ሰላም እንዲመጣ በይፋና በሥውር መወትወት፣ አልሰማ ካለም መሸሸጊያ ነፍጎ በርብርብ ማምከንን የኅብረተሰባችን አቋም አድርገን ማጎልበት ከቻልን ነው፡፡ በዚህ ጎዳና ውስጥ የተባበረ እንቅስቃሴ ማካሄድ ከቻልን በብሔርተኛ ከፋፋይነት የተቦረቦረ ህሊናና አስተሳሰባችን ይጠገናል፡፡ ሕዝቦችን አንድ ላይ ያያያዘ ትግላችን በራሱ ለአገር ውስጥ ሰላማችን ጠንካራ መሠረት ይሆናል፡፡ በሁሉም ሥፍራዎች ሰላምንና ፍትሐዊ አስተዳደርን ለማስፋፋት አቅም ይሆነናል (አንዱ ጋር ለስላሳና የተረጋጋ አስተዳደር የሚታይበትን፣ ሌላው ጋር ደግሞ ሥርዓት አልባነት፣ አፈናና ሙስና የሚዘባነንበትን ጉራማይሌ ማስተካከል ያስችለናል)፡፡ አብሮም ብሎም ሕገ መንግሥት በተሻሻለበት አኳኋን መብቶችና ግዴታዎች የተቻቻሉበት ሥርዓተ ኑሮን (የሕዝብ አስተዳደርን) መገንባት እንችላለን፡፡

አገራችንን እንወዳለን የሚሉ ሰላምን፣ ዴሞክራሲንና ግስጋሴን የምር ተልዕኳቸው ያደረጉ የፖለቲካ ቡድኖች ከዚህ አኳያ ፖለቲካቸውንና እንቅስቃሴያቸውን ማረቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአቋም እርቃቱና በአዲስ መንፈስ የተነቃቃ እንቅስቃሴ ማድረጉ፣ የፓርቲ አመራርን እስከ ማደስ (በአዳዲስ ብርቱ ግለሰቦች እስከ ማጠናከር) ከጠየቃቸው ይጠይቃቸው!!! ይህንን ለማድረግ ቆራጥ ይሁኑ! የፌዴራልና የአካባቢ አስተዳደሮችም በውስጣቸው ጠንካራ መሪዎች እንዳሉ ሁሉ ደካሞችም አሉባቸው፡፡ እናም ለአዲስ እንቅስቃሴ ቁርጠኛ ዝግጅት የማድረጉ ነገር እነሱንም ይመለከታል፡፡ 

2) የነቃ ህሊናዊ መሰናዶ ማድረግ ጀማምረንም ጥረታችን ሕግና ሥርዓት በማስከበር ሥራ በአግባቡ መታገዝ አለበት የሚል ንጭንጭ ሊጎበኘን ይችላል፡፡ አገራችን ውስጥ ያሉትን የሰላምና የደኅንነት ችግሮች ሁሉ በብሔርኛነት ሙሽትና በፖለቲካ ድህነት ብናመካኛቸው ሌሎች ድክመቶቻችንን የመሸፋፈን ጥፋት እንሠራለን፡፡ ሕግ አስከባሪነት ጥርዥ ብርዥ የሚል ወይም ውሽልሽል ከሆነ ሊናቅና በሕገወጥነት ሊደፈር ይችላል፡፡ ሕግ አስከባሪን ያላፈረ ሕገወጥ ተግባር ወንጃይ፣ ፈራጅና ቀጪ እስከ መሆን ድረስ ሊሄድና ሕዝብን ከሕዝብ የሚያነካካ ቀውስ ሊጭር ይችላል፡፡ በቅርቡ በሥልጤ ዞን ውስጥ በሆነ ሥፍራ በክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመው የዚህ ናሙና ነው፡፡ በሥልጤ ውስጥም ሆነ በወልቂጤና በቀቤና አካባቢ የተፈጠሩት የቅርብ ግጭቶች የመንግሥትን ሕግና ሥርዓት አስከባሪነት መናቅ ያለባቸው (ሕግ ጥሼ የደቦ ጥቃት ብፈጽም ከሕግ ተጠያቂነት ማምለጥ እችላለሁ የሚል መዳፈር የተንፀባረቀባቸው) ናቸው፡፡ መጨረሻ ላይ የተጠቀሰው ጥቃት እንዲያውም ለጥያቄዬ መልስ በቶሎ ለማግኘት ሰዎችን በማንነት አንጓሎ በሕይወታቸውና በንብረታቸው ላይ ጉዳት ማድረስ በታክቲክነት ይጠቅመኛል የሚል ጨካኝ ትምህርትም የቀሰመ ይመስላል፡፡ ይህ ግፈኛ ታክቲክ ውሎ ያደረና ዛሬም ያለ ነው፡፡ እነ ሸኔ የሚገድሉትና የሚዘርፉትም በዚሁ ታክቲክ ነው፡፡ የፖለቲካ ፍላጎትን/ጥያቄን በውድም በግድ ለማሳካት ሊጠቅም የሚችል ድርጊትን ሁሉ (ዘረፋና ንብረት ማቃጠልን፣ ርሸናና ማፈናቀልን ጨምሮ) በዘዴነት መጠቀም ከሰብዕና ዳር የወጣ ‹‹ዋይልድ ፕራግማቲዝም›› ነው፡፡ ይህ ነውረኛ አስተሳሰብ ኅብረተሰባዊ መተፋት እስካላገኘው ድረስም፣ እንደ ሸኔ ያሉ ግፈኞች መጠናቀቅ አይችሉም፡፡ በዚህ ግፍ ውስጥ ባንሳተፍም የግፉ የዝምታ ደጋፊ ከሆንን፣ ወይም የድርጊቱን ምልልስ እንደተለመደ ነገር ማለፍ ከለመደብን (ቢያንስ በምሬት ካልተንፈራፈርን) የዝቅጠት ተጋሪ መሆናችን ነው፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ውስጥና በአዲስ አበባ አካባቢ ተደረጉ ተብለው የምንሰማቸው ውንብድናንና ፖለቲካን ያጋባ የሥውር ቡድኖች መሹለክለክ አለ የሚያስብሉ ድርጊቶችም ጠንቃቸው ቀላል አይደለም፡፡ እከሌ የሚባል ሰው በዚህ ሥፍራ ውስጥ ከሕግ ውጪ ታስሮ ኖረ/አፍሶ መፍታትን ግለሰቦች በገንዘብ ማግኛነት ተጠቀሙበት/እንትና ታፍኖ ወደ እዚህ ቦታ ተወሰደ/ንብረቱ ተመዘበረ፣ ወዘተ የሚሉ ብሶቶች ያሉባቸው ወሬዎችና ገጠመኞች የሕግ ማስከበር ብቃታችንን ከዕርከን ዕርከን እንዳንተማመንበት የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የሰማነው፣ አግቶ ገንዘብ የመቀበል ወንጀል የፖሊስ መዋቅር ውስጥ እንደምን ቀዳዳ ሊያገኝ ቻለ? ዑስታዝ አቡበከር ሁሴን ላይ የደረሰው ሕጋዊነትን ተገን ያደረገ የዘረፋ ሙከራ እንደምን ሕጋዊ መድረክን ለመዳፈር ቻለ? በግለሰቡ አያያዝ ጊዜ ትራፊኮቹ ያሳዩት ጠንቃቃነትና የኮልፌ ፖሊሶች አስተዋይነት ሁሉም ቦታ አለ? አጭበርባሪዎቹ ለምን ጉዳያቸው ወደ ለቡ ፖሊስ ጣቢያ እንዲዛወር መረጡ? ማሳሳቻ ‹‹መረጃቸውን›› እንደምን በሲስተም ውስጥ ማስገባት ቻሉ? የዑስታዙ እውነተኛ መረጃና የተቆርቋሪዎች ድምፅ በኢንተርኔት ባይንጋጋ ኖሮ የፖሊስ ተቋማዊ ሲስተማችን ራሱ በራሱ ወንጀሉን ይደርስበት ነበር?

የእነዚህ ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ ሁለት መሰናዶዎችን ይፈልግብናል፡፡ በአንድ በኩል፣ በጥቅሉ የወንዝ ልጅነትና የብሔረሰብ ልጅነት የወንጀለኛና የቀማኞች መሸሸጊያ እንዲሆን በየትም አንፈቅድም የሚል ሕዝብ ገብ ቁርጠኝነትና ንቁ አጋላጭነትን ይጠይቀናል፡፡ በሌላ በኩል የሕግ አስከባሪ ተቋማት እንዲታመኑና እንዲታፈሩ የሚያደርግ ማስተካከያና የማይውሸለሸል የተግባር ፅናትን ይጠይቀናል፡፡ የሕግ ማስከበር መውሸልሸል የደቦ ጥቃትንና ግፈኛ ታክቲክን እየጋበዘና እያደፋፈረ አዙሪት ውስጥ እንደሚያቆየን ይነግረናል፡፡ እናም፣ ለሕዝብ መቀራረብና ዕርቅ እየተባለ፣ ግፍ የዋሉ ሰዎችና ቡድኖች ከተጠያቂነት የሚያመልጡበትን ልምምድ በሁለት መሰናዶ (በተባበረ የነቃ ትግልና በተቋማዊ የሥራ ትባት) ለከት ማስያዝ ይገባናል፤ ዕርቅና ቅጣትም ከአዙሪት ወደ መውጣት ውጤት በሚያደርሱን አኳኋን መግባባት አለባቸው፡፡

ጥቃቶች ተጠንስሰውና ተብላልተው የደቦ ወጀብ ከመፍጠራቸው በፊት የሚቀጭና በፍጥነት አፈፍ የሚያደርግ አቅም ላይ መድረስ ያስፈልገናል፡፡ እንዲህ ያለው አቅም የተቋማዊ አውታር የተሟላ ዝርግታንና ቀድሞ መረጃን የማነፍነፍ ብቃትንና ፈጣን እንቅስቃሴን የሚመለከት ነው፡፡ በጦርነት ብዙ ጥሪት ባራገፈና ገና ከጦርነት ነክ ሁኔታዎች በአግባቡ ላልተገላገለ አገር ይህንን መሳዩን አውታር በቶሎ ማሟላት የማይቻል ነው፡፡ የተቻለውን ያህል የፈጠነ ግንባታ ቢካሄድ እንኳ ትርምስና ሥርዓት አልባ ገብ የሆኑ ችግሮችን ተቆጣጥሮና አምክኖ መደበኛ ትድድር ውስጥ ለመግባት የሚጠይቀው የልፋት፣ የገንዘብና የመስዋዕትነት ወጪ (ከደኅንነት አውታር እስከ ፖሊስና መከላከያ ድረስ) እጅግ ውድ ነው፡፡

ይህንን ከባድ ወጪ ያለበት ተግባር አቅልሎና አሳጥሮ ስኬታማ የመሆን ጉዳይ፣ መልሶ ወደ ነቃ የፖለቲካ ሥራ ይወስደናል፡፡ ይህ ማለት፣ ብዙ ጣጣዎችን በፖለቲካ ብልኃትና መስተጋብር እየቀነስን፣ የተግባር ሸክሙን መንግሥት፣ አገር ወዳድ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና ሕዝብ የመፍትሔ አካል በሆኑበት የ‹‹50 ሎሚ›› ዘይቤ እንተጋገዝበት ማለት ነው፡፡ ይህ አነጋገር የመፍትሔ ጥረቱ የሁለት በኩል መሆን እንዳለበት የሚጠቁም ነው፡፡

አንደኛ በኢትዮጵያ ውስጥ ጠመንጃ ይዞ በማመፅ ሕዝቤ ያሉትን ወገን ኑሮ ማመስ፣ መሠረተ ልማቱንና ተቋማትን ለውድመት ማጋለጥ፣ በዛሬው ጊዜ ትክክለኛ የትግል ሥልት ነው የሚል ሰላምና አገር ወዳድ አለ? ከሌለ ጠመንጃ የሚተኩስ ‹‹ትግልን›› እንቢ ማለት የሁላችን ይፋ ግንዛቤ እናድርው፡፡ የታጠቀ ኃይል በአንድ መንግሥታዊ አውታር የሥራ ኃላፊነት ውስጥ ብቻ መግባትን የአገር ውስጥ ሰላም ይፈልጋል? በዚህ ላይ አዎንታዊ ስምምነት ካለን ይህንን አቋም የመላ ኅብረተሰባችን እናድርገው፡፡ በየትኛውም ጠመንጃ ያነሳ ትግል ተብዬ ላይ ተቃውሟችን የማያወላውል ይሁን፡፡

ፈሪሃ ፈጣሪና ግብረ ገብነት ያለን አገር ነን፡፡ ቀደም ባሉ ጊዜያት የፖለቲካ ጥያቄዎቻችን የተግባር ምላሽ እንዲያገኙ፣ የሰዎች ሕይወት መቅጠፍን እንደ ዘዴ የመጠቀምም ሆነ አድራጊዎቹን የማጀብ ታሪክ በሕዝብ ገብ ትግሎቻችን ውስጥ አልነበረም፡፡ ቡድኖች ግን እንታገለዋለን ያሉትን ኃይል ጭራቅ አድርጎ በሕዝብ ለማስጠመድ ሲሉ ግፈኛውን ዘዴ ተጠቅመውበታል፡፡ ሕዝብም በተንኮላቸው የተጭበረበረበት ታሪክ በውጭም በአገራችንም አዲስ አይደለም፡፡ ይህንን ግፈኛ ዘዴ እያወቁ ዛሬ በተራ ሰው ደረጃ ማጀብ ግን በቅርብ የመጣ ጉዳችን ነው፡፡ ይህ ጉድ ከግብረገብ እሴቶቻችንና ከሃይማኖቶቻችን ማዕቀፍ መውጣት፣ ከሰው ፍጡርነታችን መውረድ መሆኑ ሊሰማንንና ልናፍር አይገባንም? ካፈርንበት አምርረን እንቃወመው፡፡ ቅዋሜያችንንም ኅብረተሰባዊ ንቃት እናድርገው፡፡

የትኛውም የአካባቢና የአገር የፀጥታ ኃይል ኅብረተሰቡን በአግባቡ ካንፀባረቀ ጥንቅርና ለሙያው ከመታመን አንክሶ የሕዝቦች ሰላምና ኢአድሏዊ አያያዝን መንከባከብ ይቻለዋል? በእዚህ ላይ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር አንችልም? ግንዛቤያችንስ የኅብረተሰብና የመንግሥት ሆኖ ወደ ተግባር መለወጥ አይችልም? አካባቢያዊም ሆነ አገራዊ ነኝ ያለ ፓርቲ የተወሰኑ ማኅበረሰቦችን አቅርቦና አርቆ፣ (በዕይታውም፣ በአደረጃጀቱና በመስተንግዶውም አንጓልሎ)፣ የፍትሕና የእኩልነት ፓርቲ መሆን/የትስስብና የሰላማዊ አብሮነት አለምላሚ መሆን ይቻለዋል? በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የዛሬ ልሂቃን መግባባት ቢያቅተን የነገ አብሮነታችንን ማኩረፍ ይበጀናል? ባለፉ በደሎች ላይ መግባባት የዛሬ ትውልድ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው? ወይስ የዛሬዎቹ የተቻለንን የመግባባት መዋጮ የምናደርግበት ሒደታዊ ክንውን ነው? ኑሯችን በዕድገት፣ በመተሳሰብና በእኩልነት ግንኙነት እየጎለመሰ፣ ስሜቶቻችን እየሠለጠኑ ዕውቀታችን ሚዛናዊ እየሆነ ከመሄድ ጋር ማኅበራዊ መግባባታችን ይጨምራል? አይጨምርም? እነዚህን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ ግንዛቤና መግባባትን ለመፍጠር ከፖለቲከኛ እስከ ምሁራን፣ ከጋዜጠኞች እስከ ሥነ ጽሑፍ ሰዎች ድረስ የተሳመረ ሥራ ለመሥራት መቻል፣ የሰላምንና የለውጥ ሸክምን ተጋርቶ አገርን/ኅብረተሰብን መጥቀም እንጂ የመንግሥት/የፓርቲ ፖለቲካ አጫፋሪ መሆን አይደለም፡፡

ሁለተኛ የመላ ኅብተሰባችን የጋራ ግንዛቤ መሆን በሚገባቸው ዕሳቤዎች ላይ የመሥራቱን ተግባር በሃምሳ ሎሚ ዘይቤ ለመተጋገዝ መቻል፣ ቁርቁሶችን እጅግ በአያሌው በድርድርና በምክክር ለመፍታት ቅርብ ያደርገናል፤ ጥረታችንም ልባዊ እንዲሆን የሚያስችል አቅም ይሰጠናል፡፡ የምር ለሕዝብና ለአገር በተቆረቆረ ምክንያታዊነትና ዕውናዊነት መመካከር ከቻልንም የማንወጣው/የማናሸንፈው አለመግባባት አይኖርም ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ለሕዝቦችና ለአገራዊ ህልውናችን የተቆረቆረ ምክክራችን፣ ጥፋተኝነትን በሰፊው ተረድተን እንድንፀፀት ካስቻለንም፣ የራስ ለራስ የልቦና ድላችን ግዙፍ ነው፡፡ ሰዎችን በማኅበራዊ ማንነታቸው ማንጓለል ውስጥ የከተተን ብሔርተኝነት ነው፡፡ በየሠፈር አጣቦ መሬት መናጠቅ ውስጥ የከተተን ብሔርተኝነት/ጎጠኝነት ነው፡፡ ተበዳይነትን፣ ጥላቻንና ቂምን የፖለቲካ ንቃት አድርገን እንድንይዝ ያደረገን ብሔርተኝነት ነው፡፡ አውሬ አድርጎ የደቦ ቀጪ ያደረገንና ለደቦ ተቀጪነት የዳረገን ብሔርተኝነት ነው፡፡ በበቀልና በቁጣ አስክሮ ግጭትና ጦርነት ውስጥ የከተተንም እሱው ነው፡፡ በየትኛውም ወገን በኩል ሆነን የተገዳደልነው ብሔርተኝነት ባመጣብን ዳፋዎች ተጠምደን ነው፡፡ በየትኛውም ሥፍራ በየትኛውም በኩል ሆነን የወደቅነው የአንድ አገር ልጆች ነን፡፡ ይህ እውነታ በውስጣችን የደረሰውን መገዳደል በየትኛችንም በኩል ‹‹ዘራፍ እኔ ጀግናው!›› የሚል የማይኖርበት የሁላችን ሐዘን ያደርገዋል፡፡ ከጥፋታችን ተማርን ልንል የምንችለውና የብሔርኛነትን/የጎጠኝነትን ካቴና ሰብረን ለመውጣት ደፈርን የምንለው እንዲህ አስፍተን ገመናችንን መገንዘብና መፀፀት ስንችል ነው፡፡ የጥፋት ተጋሪነቱን ከእነ ፀፀቱና ከእነ ታራሚነቱ የሁላችን ማድረግ ከተሳካልን ከቅድሙ በበለጠ ደረጃ የማናሸንፈው አለመግባባት አይኖርም ብሎ በድፍረት መተማመን እንችላለን፡፡

የጥፋት ተጋሪነትና ፀፀት ውስጥ ከወዲሁ በምናብ እንግባበትና የማንረታው ነገር የለም ባይ ልበ ሙሉነታችንን ለስንትና ስንት ሰው መርገፍ መዘዝ በሆነውና መፍቻ ያጣ በሚመስለው የእነ ወልቃይት ጉዳይ ላይ እንፈትሸው፣ የቀላል አስተዋይነት (የ‹ሴንስቢሊቲ›) ጥያቄዎች በማንሳት፡፡

በአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ የእነ ወልቃይትን መሬት በነፃ አውጪነት አባዜ በኃይል ይዞ (አስለቅቆ) የ‹‹ሀ›› ወይ የ‹‹ለ›› ክልል አካል ማድረግና ማፅናት የሚቻልበት ዕድል አለ ይሆን? ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ በአሉታ የተሞላ ነው፡፡ ‹‹የእነ ወልቃይት የአማራነት ማንነት እንዲረጋገጥ›› የሚካሄድ ትግል፣ የአማራን ሕዝብ በተኩስ መታመስ (ሰላም ማጣት፣ ከልማት መሰናከልና በኑሮ መድቀቅ) ይሻል የሚል ጥያቄም መልሱ ብዙ የሚያከራክር አይደለም፡፡ የእነ ወልቃይት ይዞታ ሁለት ክልላዊ አስተዳደሮችን ሲያናቁር የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ረቺ ሆኖ ለመውጣት ይጠቅመኛል ያሉትን ድንጋይ ሁለቱም ከመፈንቀል አይመለሱም ብሎ መገመት ስህተት አይሆንም፡፡ በጥያቄዎቹ አፈታት ላይ የጋራ መግባባት ያጡትም አንድም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ አሁን ባሉበት ሁኔታ ቁርጥ ያለ መልስ መፈለግም ሆነ፣ ‹‹ቅድሚያ ይዞታው በትግራይ አስተዳደር ውስጥ ይግባ›› ባይነት መሬት ላይ የሚኖረውን ሁኔታ ለሚፈለገው ውጤት ከማመቻቸት ጋር የተያያዘ ይመስላል፡፡

‹‹ማንነታችን አማራ ነው›› የሚል ድምፅ እንደ ሰማን ሁሉ ‹‹ማንነታችን ትግራዋይ ነው›› የሚል ድምፅም ሰምተናል፡፡ ‹‹ወልቃይት ወልቃይቴ ነው፣ ራያም ማንነቱ ራያ ነው›› የሚል ድምፅም ለጆሯችን እንግዳ አይደሉም፡፡ እውነት የት ጋ እንዳለች መርምሮ አጣርቶ ለማወቅም የጊዜ ርቀት ብዙም ችግር አይደለም፡፡ ገለልተኛና አስተማማኝ ምስክርነት መስጠት የሚችሉ አዛውንቶች፣ የታሪክ ተመራማሪዎችና የታሪክ መዛግብትም አይታጡም፡፡ ሲፋጠጡ ከቆዩት ተከራካሪዎች ውጪ የሆኑና በአድልኦ የማይታሙ የታሪክና የሕግ ሊቃውንት፣ የሰነዶችንና የቃል ምስክርነቶችን አገናዝበውና መርምረው የእውነቱን አካባቢ ለማወቅና ለመወሰን የሚያግዝ ነገር ቢያበረክቱና የሁለቱን አካባቢ ሕዝቦች ምክክርና መተሳሰብ ግብዓቱ ያደረገ ውሳኔ ቢከተል ሰላምን ሳያፀና አይቀርም፡፡ የሊቃውንት መለኝነትና የሕዝብ ለሕዝብ ምክክር ዛሬ ካለው የእኔ የእኔ ባይ ግብግብ ውጪ የሆነም የመፍትሔ አማራጭ ይዞ ይመጣ ይሆናል፡፡ ያ ባይሆንና መወዛገቢያ ሆነው የቆዩት ሥፍራዎች ወደ አንዱ ወይ ወደ ሌላው አካባቢ ቢያመሩ እንኳ እስከ መጨረሻ ደም ጠብታዬ እታኮሳለሁ ከሚል መንገድ ይልቅ፣ ለሁሉም የሚበጀው በየትም የኢትዮጵያ ሥፍራ የማንነት መከባበር፣ ፍትሐዊነት፣ ፍትሕ፣ የትም ሠርቶ መኖር የተረጋገጠበት ሥርዓት ዕውን እንዲሆን መታገል መሆኑን ማስተዋልና መቀበል ብዙ አይተናነቀንም፡፡ ይህንን መሳይ ውጤት በሚፈልቅበት ጎዳና ውስጥ ተቋማትን በአግባቡ እየገነባን በአጠቃላይ ልማት ውስጥ ሰውንም ዴሞክራሲያዊ ትድድርንም ማለምለም ከቻልን፣ ለሕግ ታምኖ ማስተዳደርም ሕግንና ሥርዓት ማስከበርም የዜጎች ሕግ አክባሪነትም መደበኛ የኑሮ ዘይቤ ወደ መሆን ይሸጋገራሉ፡፡ በዚህ ዓይነት የኑሮ ዓውድ ውስጥ መብቶችን፣ ግዴታዎችን፣ በጎነቶችን፣ ምክንያታዊነትን፣ ዕውቀትን አለላ ያደረጉ የሥልጡን ዜግነት እሴቶችም በተግባራዊ ኑሮ ውስጥ ይታነፃሉ፡፡ እየታነፁ፣ እየተቡና እየተስፋፉም በሕይወት ጉዞ ቅብብላችን ውስጥ የእኛኑ ሰብዕናና ተራክቦ ያበለፅጋሉ፣ ይንከባከባሉ፡፡                    (ይቀጥላል)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...