Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉኢኮኖሚው የተመሰቃቀለው ከጎረቤት አገሮች እኩል መካከለኛ ገቢ ተርታ ለመሠለፍ በተደረገ ሩጫና የሐሰት...

ኢኮኖሚው የተመሰቃቀለው ከጎረቤት አገሮች እኩል መካከለኛ ገቢ ተርታ ለመሠለፍ በተደረገ ሩጫና የሐሰት መረጃ ምክንያት ነው

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

በወረቀት ላይ የሚቀርቡ ሪፖርቶች መረጃና ምድር ላይ ያለው ሀቅ እንደ ሰማይና ምድር የተራራቁ ናቸው በማለት የሰጠሁትን ጥቆማና አስተያየት መንግሥት አልሰማ ብሎ አንገቱ በዕዳ ታነቀ፣ አበዳሪ አገሮችና ድርጅቶች እግር ሥር ወደቀ፡፡ ከሰው ኃይል ጋር ተጣምሮ የቁሳዊ ምርት ዕድገት መሠረት የሆነው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ካፒታል ወድሞና የውጭ መዋዕለንዋይ እየሸሸ ባለበት ወቅት፣ ዘንድሮ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ተቋማት ጥንቆላ በ6.1 በመቶ ታድጋለችና በመንግሥት ምኞት በ7.9 በመቶ ታድጋለች ተባለ፡፡ የዚህን የተለመደ የሐሰት ቁጥር የመቆለል መረጃ አንድምታ ለማገናዘብ እንዲቻል ከሁለት ዓመት በፊት በሪፖርተር ጋዜጣ አቅርቤው የነበረውን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ለሕዝብ ቁጥር ተካፍሎ የሚገኘውን ነፍስ ወከፍ ገቢ በአዲስ መረጃ በድጋሚ አቅርቤ በመተንተን፣ ወደ ዋናው ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (GDP) አለካክ ውጥንቅጥ ጉዳይ እገባለሁ፡፡

አገራችን 1,200 ዶላር ነፍስ ወከፍ ገቢ ውስጥ ገብታ ከእነ ኬንያ፣ ኡጋንዳና ታንዛንያ እኩል ባለመካከለኛ ገቢ አገሮች ተርታ ለመሠለፍ በሚቀርቡት የኢኮኖሚ ዕድገት ሪፖርቶች መሠረት እጅግ በጣም በፍጥነት ስትሮጥ ኖራለች፡፡ በ2014 ዓ.ም. የተደረሰበትን 1,218 ዶላር ነፍስ ወከፍ ገቢን ወደ ብር ለመቀየር በምንዛሪ ምጣኔው 56 ብር ብናበዛ 68,208 ብር ነው፡፡ ይህንን ወደ ቤተሰባዊ ገቢ ለመቀየር በአምስት ሰው የቤተሰብ አባላት ስናበዛው 341,040 ብር ነው፡፡ የዓመቱን ወደ የወር ገቢ ለመቀየር ለ12 ብናካፍል 28,420 ብር ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሚኖረውን 120 ሚሊዮን ሕዝብ ለአምስት ስናካፍል የቤተሰብ ቁጥር 24 ሚሊዮን ነው፡፡ ከዚህ የቤተሰብ ቁጥር ውስጥ ስንት አባወራ በወር 28,420 ብር ይዞ ወደ ቤቱ ይገባል፡፡

አንድ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ወይም ሐኪም ወይም ተመራማሪ ፕሮፌሰር የተጣራ አሥር ሺሕ ብር እያገኘ የየትኛውና ስንት ቤተሰብ አባወራ ነው 28,420 ብር ወርኃዊ ደመወዝ የሚያገኘው፡፡ በብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት እንደተመለከተው (ሪፖርቶቹን ዓይቶ ማረጋገጥ ይቻላል) የነፍስ ወከፍ ገቢ ለሀበሻ ሲሆን በብር የሚሰላው በምሥላዊ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (Nominal GDP) ነው፡፡ ለውጭ ሰዎች በዶላር ሲሰላ ግን በእርግጣዊ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (Real GDP) ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በዶላር ምሥላዊ ዋጋ 1‚218 ዶላር ነፍስ ወከፍ ገቢ ያሉትን በብር እርግጣዊ ዋጋ 22,542 ብር ነው ይላሉ፡፡ ከላይ በምንዛሪ ምጣኔ ከለካነው 68,208 ብር ጋር እንደሚራራቅ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ይበሉ በዚያ የምርት መጠን መለኪያ ዋጋ መነሻ ዓመት ሲከለስ እርግጣዊውና ምሥላዊው እኩል እንደሚሆኑ ዘግየት ብሎ ይቀርባል፡፡

የጥቅል አገር ውስጥ ምርት አለካክ ሥርዓት

ወደ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት አለካክ ዘይቤ ስንመጣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የብሔራዊ ኢኮኖሚ ሒሳብ አያያዝ ሥርዓትን (National Income Accounting System) መሠረት አድርጎ የሚለካው ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በገበሬው፣ በወዛደሩ፣ በፀጥታ አስከባሪው፣ በመከላከያ ሠራዊት አባሉ፣ በዳኛው፣ በጋዜጠኛው፣ በመምህሩ፣ በሐኪሙ፣ በቢሮ ሠራተኛው፣ በነጋዴው፣ በሙዚቀኛው፣ በፀጉር አስተካካዩ፣ በቤት ሠራተኛው፣ በሾፌሩ፣ በጥበቃው፣ በጫማ አሳማሪው፣ በዳንስ አስተማሪው፣ በጭፈራ ቤት ሥርዓት አስከባሪው፣ ወዘተ. ተመርቶ በሸቀጥ መልክ ለገበያ የቀረበ ወይም ለገበያ እንደቀረበ ተቆጥሮ ዋጋው የተተመነ ቁሳዊ ዕቃና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምርት መጠን አለካክ ሥርዓትን መሠረት አድርጎ በነፃ ገበያ የካፒታሊስት አገሮች የሚለካው ምርት ዓይነት ዋጋቸውን ለመተመን በሚያዳግቱ ለግልና ለዘመድ በነፃ ከሚሠሩ ሥራዎችና አገልግሎቶች በቀር የማንኛውም የግል አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ሥራዎችና አገልግሎቶችም ሆኑ እንደዚሁም የሕግ አገልግሎት፣ የፀጥታ ማስከበር አገልግሎት የሕዝብ ማስተዳደር አገልግሎት፣ የመከላከያ ሠራዊት አገልግት የልማት ሥራ አገልግሎት የመሳሰሉ የመንግሥት ሥራዎችን የሚያካትት ነው፡፡ ስለሆነም አንድ የለሊት ጭፈራ ቤት ሲከፈትም አንድ ጫት መሸጫ ሱቅ ሲከፈትም ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን የዚያን ጭፈራ ቤትና ጫት መሸጫ ንግድ ቤት ተጨማሪ እሴት ያህል ያድጋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ ቁጥር በበዛ ልክም የምርቱ መጠን ይጨምራል፡፡

ዓለም በኮሙዩኒስትና በካፒታሊስት ኢኮኖሚ ሥርዓት በተከፋፈለችበት በቀድሞ ጊዜ በዓለም ላይ ሁለት ዓይነት የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት አለካክ ሥርዓት ነበር፡፡ ለምሳሌ በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረትና ሌሎች ኮሙዩኒስት አገሮች በግል ድርጅቶች የሚሰጡ እንደ የመዝናኝያ አገልግሎቶች፣ የሕዝብ መጓጓዥያ ትራንስፖርት አገልግሎቶች፣ በመንግሥት የሚሰጡ እንደ የሕግ አገልግሎት፣ የፀጥታ ማስከበር አገልግሎት፣ የመከላከያ ሠራዊት አገልግሎት፣ የሕዝብ ማስተዳደር አገልግሎት ወዘተ. በአገር ውስጥ ጥቅል ምርት አይካተቱም እነዚህ አገልግሎቶች እንደ ምርት ሳይሆን እንደ ፍጆታ ነበር የሚቆጠሩት፡፡

በሶቭየት ኅብረትና በመሰል ሶሻሊስት አገሮች አመለካከት የቁሳዊ ዕቃዎች ምርትና ለቁሳዊ ዕቃዎች ምርት በቀጥታ ድጋፍ የሚሰጡ ከግል ድርጅቶች የኢኮኖሚ አገልግሎቶች ውስጥ እንደ የሸቀጥ ማጓጓዣ ትራንስፖርት አገልግሎት፣ የንግድ አገልግሎት፣ የመጋዘን አገልግሎት ወዘተ፣ የመሳሰሉትና ከመንግሥት አገልግሎቶች ውስጥም የጤና ጥበቃና የትምህርት አገልግሎቶች፣ ወዘተ. የመሳሰሉት በተዘዋዋሪ መንገድ የቁሳዊ ዕቃዎች ምርትን የሚያሳድጉ ልማታዊ ሥራዎች ብቻ ነበሩ እንደ አዲስ ምርት የሚቆጠሩት፡፡

በሶሻሊስት አገሮች እምነት የሕዝብ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ግለሰቡ ሌሎች ሥራዎች ሠርቶ በሚያገኘው ገቢ ገንዘቡን ለመዝናናትም ይሁን ዘመድ ለመጠየቅ ለፍጆታ የሚጠቀምበት ሁኔታ ነው የሚል ነው፡፡ የትራንስፖርት ድርጅቱ ገንዘቡን በክፍያ መልክ ከተጓዡ ቢያገኝም ክፍያው ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የመግዛት አቅምን በማስተላለፊያ ክፍያ (Transfer Payment) መልክ አዘዋወረ እንጂ በአገር ውስጥ በሚመረተው ምርት መጠን ላይ ምንም የሚጨምረው ነገር የለም የሚል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ሶሻሊስቶች የሕዝብ ትራንስፖርትን እንደ ምርት ሳይሆን እንደ ፍጆታ ነበር የሚቆጥሩት ማለት ነው፡፡ ምግብህን ስትገዛውም፣ ስታበስለውም፣ ስትበላውም መልሰህ መላልሰህ አትቆጥረውም እንደ ማለት ነው፡፡ መንግሥታዊ፣ አስተዳደራዊና ሕግ የማስከበር አገልግሎትም እንደ ፍጆታ እንጂ እንደ ምርት አይቆጥሩም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ከካፒታሊስት አገሮች ጋር ሲነፃፀር በጣም አነስተኛ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአገር ውስጥ ምርት አለካክ ሥርዓትን ተከትላ በየዓመቱ የአገር ውስጥ ምርት መጠንን መረጃ ታጠናቅራለች፡፡ በአጠቃላይ የአገር ውስጥ የምርት መጠንን መረጃ ለማጠናቀር ከሚገጥሙት የመረጃዎች ውሱንነት ዓለም አቀፋዊ ችግር ባሻገር በታዳጊ አገርነቷ በመረጃዎች አሰባሰብ በሚገጥመው ችግር ምክንያት፣ የአገር ውስጥ ምርት መጠን መረጃ ግምታዊ እንጂ እርግጠኛ አይደለም፡፡ ሆኖም ዓለም አቀፉን የመረጃ አሰባሰብ ደረጃና የትመና ደንብ ጠብቆ የሚሠራ ስለሆነ መረጃው በአገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ኖሮት የአገሪቱን የዕድገት ደረጃ በመለካትና ዓለም አቀፍ ንፅፅር ለማድረግ፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መዋጮን ለመክፈል አቅም መገመቻ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ዕርዳታና ብድር ለማግኘትና ብድርን ለመክፈል የሚያስችል አቅም መኖር አለመኖርን ለመገመትም ይረዳል፡፡

በዚህም መሠረት በየዓመቱ የተመረተው ምርት መጠን መረጃዎች በሪፖርቶች ውስጥ ተጽፈው እንመለከታለን፡፡ የተመረተውን ምርት ለማገበያየት የሚበቃ ጥሬ ገንዘብም የኅብረተሰቡን ፍላጎት መሠረት አድርጎ በብሔራዊ ባንክና በንግድ ባንኮች አማካይነት በገበያው ውስጥ ቀርቧል፡፡ ሆኖም በአንድ በኩል ከሚመረተው ጠቅላላ ምርት ውስጥ እስከ ሰላሳ በመቶ የሚደርሰው የግብርና ምርት ውጤት ለአምራቹ የግል ፍጆታ የሚውልና ገበያ ውስጥ የማይገባ ስለሆነ፣ ይህን ምርት የሚያገበያይ ጥሬ ገንዘብ ስለማያስፈልግ በሌላ በኩል በሶሻሊስት አገሮች እንደ ምርት የማይቆጠሩት አንዳንድ የግልና የመንግሥት ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ከጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ድርሻቸው ከፍተኛና በከፍተኛ ደረጃ እያደጉ ከመሆናቸውም በላይ፣ ደመወዛቸው እንደ የምርት መጠን የሚቆጠርላቸው የመንግሥት አገልግሎቶች በፍላጎትና በአቅርቦት መስተጋብር የተለካ የገበያ ዋጋ ስለሌላቸው ተፈላጊነት ባላቸው ሸቀጦች ላይ ዋጋ በየጊዜው እንዲወደድ አድርጓል፡፡

ዛሬ በልፅገዋል የሚባሉ የአውሮፓና የአሜሪካ አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ የሚያመለክተው ከአገር ውስጥ ምርት መጠን ክፍለ ኢኮኖሚያዊ ድርሻ ውስጥ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ድርሻ ቀንሶ በፋብሪካ ምርት ድርሻ ዕድገት መተካቱን ነው፡፡ የግብርናና የፋብሪካ ምርት የፍጆታ ዕቃዎች ከተሟሉላቸው በኋላ ቴክኖሎጂ በከፍተኛ ደረጃ ስለመጠቀና ምርታማነት ስላደገ ጥቂት ሠራተኞች የግብርናውና የፋብሪካውን ምርት ፍላጎት በሙሉ ማቅረብ በመቻላቸው፣ በአሁኑ ጊዜ ከስልሳ እስከ ሰባ በመቶ የሚሆነው ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ድርሻ የሚገኘው ከአገልግሎት ክፍለ ኢኮኖሚ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን ከአገር ውስጥ ምርት የግብርና ምርት ውጤት ድርሻ ሲቀንስ የተካካሰው በፋብሪካ ኢንዱስትሪ ምርት ሳይሆን በአገልግሎት ምርት ዕድገት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በአንድ በኩል ምርታችን አነስተኛ ነው እንላለን፣ በእርግጥም የቁሳዊ ዕቃዎች ምርት እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ በሌላ በኩል በገበያ ዋጋ የተለካ ጠቀሜታ የሌላቸውን የግልና የመንግሥታዊ አገልግሎቶች መጠን ከልክ በላይ አብዝተን ከእዚሁ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ጥሬ ገንዘብ ወደ ገበያው ውስጥ መግባቱ ለዋጋ ንረት ምክንያት ስለሆነ፣ የምርት ዓይነትና መጠን ትርጉም አወዛጋቢነት ኢኮኖሚያችንን እንዳመሰቃቀለው የሚያመለክት ነው፡፡ የጥቅል አገር ውስጥ ምርት መጠንን ግማሽ የሆነው የአገልግሎት ክፍለ ኢኮኖሚ ከቁሳዊ ዕቃ ምርት ድርሻ እየበለጠ መሄዱና ለኑሯቸው በዚህ የኢኮኖሚ ዘርፍ ለመጠለል የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር መበርከት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚያሳስብ ጉዳይ ነው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ሥራ ለግላቸውና ለቀጣሪዎቻቸው እንጂ ለአገር ምንም ዓይነት ማኅበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባይኖረውም በሚያገኙት ደመወዝና ትርፍ ልክ የአገር ውስጥ ምርት ያድጋል ይባላል፡፡

በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በቆዳ ስፋት ከአዲስ አበባ ከተማ ሁለትና ሦስት እጥፍ በሚበልጡ ወረዳዎች በሕዝብ አስተዳደር ሥራ የተሰማሩ አንድ ወረዳ ገዥ፣ አንድ ዳኛ፣ ሁለትና ሦስት ፖሊሶች እያንዳንዳቸው ከሃምሳ ብር በማይበልጥ የወር ደመወዝ ሰላምና ፀጥታ አስከብረው ስለሚያስተዳድሩ፣ እንደ ዛሬው መንግሥታዊ አካላት የጥቅል የአገር ውስጥ ምርትን የማሳበጥም ሆነ ነፃ ገበያውን የመበጥበጥ አቅም አልነበራቸውም፡፡ ዛሬ በየክልሉ ሕግና ፀጥታ ሳያስከብሩ ደመወዛቸው እንደ ምርት የሚቆጠርላቸው የሚሊሻ፣ የልዩ ኃይልና ሌሎች የመንግሥት አስተዳደራዊ አገልግሎት ሰጪዎች፣ የግለሰቦችና የድርጅቶች ጠባቂና አጃቢ ደመወዝተኞች የአገር ውስጥ ጥቅል ምርቱን ምን ያህል እንደሚያሳብጡት አንባቢ ይገምተው፡፡ በእነዚህ የአገልግሎት ሥራዎች የተሰማራው የሰው ኃይል ወደ ልማትና ቁሳዊ ዕቃ ምርት የኢኮኖሚ ዘርፍ ካልተዛወረ አገሪቱ ከፍተኛ የድህነት አረንቋ ውስጥ ትገባለች፡፡ 

የጥቅል አገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ መነሻ ዋጋ ክለሳ

የምርት መጠንን ከሚያሳብጡ ዋና ምክንያቶች አንዱና በዚህ ጽሑፍ የሚዳስሰው የምርት መጠን መለኪያ መነሻ ዓመት ዋጋ ክለሳ ነው፡፡ ይህን የአለካክ ሥርዓት መሠረት አድርጎ የሚለካ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠንና የምርት መጠን መለኪያ ዋጋ መነሻ ዓመት ክለሳ (Rebasing) ለኢኮኖሚያችን መመሰቃቀል ምክንያት እንደሆነ ለማገናዘብ፣ በሰንጠረዥ አስደግፌ መስከረም 2007 ዓ.ም. ባሳተምኩት ግላዊና ብሔራዊ ኢኮኖሚያችን መጽሐፍ የዳሰስኩትን ጉዳይ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡  

ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በአንድ በተወሰነ መነሻ ዓመት ቋሚ ዋጋና በተመረተበት ዓመት በጊዜው ዋጋ በሁለት መንገድ እንደሚለካ ይታወቃል፡፡ ሁሉም አገሮች ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠንን በመነሻ ዓመት ዋጋ (Constant Price) እና በጊዜው ዓመት ዋጋ (Current Price) ይለካሉ፡፡ በመነሻ ዓመት ዋጋ የተለካው እርግጣዊ የጥቅል ምርት መጠን (Real GDP) ሲባል በጊዜው ዋጋ የተለካው በዋጋ ንረት ምክንያት ስለሚያብጥ ምሥላዊ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (Nominal GDP) ይባላል፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላም የመነሻ ዓመት ቋሚ ዋጋው ስለሚከለስ በዋጋ ንረቶች ምክንያት ምሥለ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት የነበረው እርግጣዊ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ይሆናል፡፡ ክለሳው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥርዓት ስለሆነ በራሱ ችግር የለበትም፡፡ ነገር ግን የዋጋ ንረት ሁለትና ሦስት በመቶ ብቻ የሆነባቸው አገሮች ዋጋ ሲከለስ ልዩነቱ ትንሽ ሲሆን የዋጋ ንረቱ ሃያና ሰላሳ በመቶ የሆነባቸው አገሮች ትልቅ ሆኖ ኢኮኖሚው ስለሚያብጥ፣ በወረቀት ላይ የሚቀርበው የጥቅል ምርት መጠን ሪፖርትና በምድር ላይ ያለው የጥቅል ምርት መጠን ተለያይተው ኢኮኖሚው ይመሰቃቀላል፣ የዋጋ ንረት ይስፋፋል፣ ቀውስ ይፈጠራል፡፡ 

በግላዊና በብሔራዊ ኢኮኖሚያችን መጽሐፌ ውስጥ ባመለከትኩት መረጃ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በ2003 ዓ.ም. በተከለሰው መነሻ ዓመት ቋሚ ዋጋ የተለካው የ2003 ዓ.ም. 469.5 ብር እርግጣዊ የአገር ውስጥ ምርት በራሱ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በቀድሞውና ባልተከለሰው በ1992 መነሻ ዓመት ቋሚ ዋጋ የተለካውን የ2003 ዓ.ም. 157.5 ቢሊዮን ብር እርግጣዊ የአገር ውስጥ ምርትን በሦስት እጥፍ ይበልጣል፡፡

እርግጣዊ የአገር ውስጥ ጥቅል  ምርት  በ1992 እና በ2003 ቋሚ ዋጋዎች በቢሊዮን ብር

 

2001

2002

2003

2004

በ1992 ዋጋ

 በ2003 ዋጋ

ግብርና

55.1

59.3

64.7

212.5

222.9

ኢንዱስትሪ

16.6

18.4

21.2

49.8

58.3

አገልሎሎት

57.6

65.2

73.4

207.2

229.1

ጠቅላላ

127.9

141.4

157.5

469.5

510.3

             

 

* በተስተካከለ የብሔራዊ ባንክ መረጃ መሠረት

በተከለሰ ዋጋ የተለካው የ2003 ዓ.ም. ምሥላዊም እርግጣዊም የምርት መጠን 515 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ወደኋላ ተኪዶ የቀድሞ ዓመታት ምርት መጠንም ተከልሷል፡፡  

ለዚህ ምክንያቱ በ1992 መነሻ ዓመት ቋሚ ዋጋ የተለካው እርግጣዊ የአገር ውስጥ ምርት ለአሥር ዓመታት በአማካይ አሥራ አንድ በመቶ ቢያድግም ምሥላዊ የአገር ውስጥ ምርት ግን በዓመት በሰላሳና አርባ በመቶ ያድግ ስለነበር፣ የአገር ውስጥ ምርት መለኪያ መነሻ ዓመት ወደ 2003 ዓ.ም. ሲከለስ ምሥላዊ የአገር ውስጥ ምርት እንደ እርግጣዊ ምርት ስለተቆጠረ ነው፡፡ በተከለሰው የ2003 መነሻ ዓመት ቋሚ ዋጋ የተሠላውን የ2003 ዓ.ም. 6,267 ብር ነፍስ ወከፍ ዓመታዊ ገቢ በብሔራዊ ባንክ በ1992 መነሻ ዓመት ቋሚ ዋጋ መሠረት በተዘጋጀው (2010/11 የብሔራዊ ኢኮኖሚና ሶሻል መለኪያዎች) ጥናት ውስጥ ከምናገኘው የ2003 ዓ.ም. አንድ ሺሕ ዘጠኝ መቶ አርባ ስድስት ብር ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢ ጋር ሲነፃፀርም ልዩነቱ ሦስት እጥፍ ነው፡፡

በብሔራዊ ባንክ ጥናት እርግጠኛ የአገር ውስጥ ምርት ነፍስ ወከፍ ገቢ 1,946 ብር በዚያው ጥናት ውስጥ በተሰጠው የዓመቱ የአንድ ዶላር ምንዛሪ 16.50 ብር ሲመነዘር እርግጣዊ የአገር ውስጥ ምርት ነፍስ ወከፍ ገቢው 118 ዶላር ነው፡፡ ነገር ግን በዚያው ጥናት ውስጥ ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢው በምሥላዊ የአገር ውስጥ ምርት ተሠልቶ 382 ዶላር ሆኗል፡፡ ልዩ ልዩ የብሔራዊ ኢኮኖሚ መለኪያዎች ከምሥላዊ የአገር ውስጥ ምርት ጋር ሲነፃፀሩና ከእርግጣዊ የአገር ውስጥ ምርት ጋር ሲነፃፀሩ የሚኖራቸውን ልዩነት የቀረቡት የመረጃዎች ልዩነቶች ያመለክታሉ፡፡

በቋሚ መነሻ ዓመት ክለሳው ምክንያት የአገር ውስጥ ምርትና ነፍስ ወከፍ ምርት በቁጥር ደረጃ ኢኮኖሚያችን ወደ መካከለኛ ኑሮ ደረጃ እየተጠጋ ነው፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ግን በዋጋ ንረት ምክንያት የብራችን የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ ስለሚቀንስ ኑሮው በማዘቅዘቁ ከመካከለኛ ኑሮ ደረጃ እየራቀ ነው፡፡ በ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት የኢትዮጵያ እርግጣዊ የአገር ውስጥ ምርት አሥር ቢሊዮን ብር ገደማ ነበር፡፡ የ2003 ዓ.ም. 470 ቢሊዮን ብር ከመነሻው ከ1980ዎቹ ዓመታት አሥር ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር ሃምሳ ጊዜ እጥፍ ሆኗል፣ የዘንድሮ መረጃዎች ተገኝተው ቢተነተኑ ሦስት መቶ እጥፍ ይሆናሉ፡፡

እንግሊዝ በኢንዱስትሪ አብዮቷ ዘመን ኢኮኖሚዋን እጥፍ ለማድረግ ስልሳ ዓመታት ፈጅቶባታል፡፡ አሜሪካ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ገደማ ኢኮኖሚዋ መመንጠቅ ሲጀምር እጥፍ ለማድረግ ሃምሳ ዓመታት ፈጅቶባታል፡፡ በርካታ በፍጥነት ያደጉ የምሥራቅና የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ኢኮኖሚያቸውን እጥፍ ለማድረግ አሥር ዓመታት ፈጅቶባቸዋል፡፡ የእኛ በወረቀት ሪፖርት ላይ በሃያና በሰላሳ ዓመታት ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ ጊዜ እጥፍ ቢያድግም ምድር ላይ ያለው ሀቅ ግን ይህንን አይመሰክርም፡፡ ያደግነው መሬት ላይ በሚታየው ልክ እንጂ ወረቀት ላይ በተጻፈው መጠን አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ምድር ላይ የሌለ በሪፖርት ብቻ የምናየውን ሐሰተኛ መረጃ ካላረመች የጨዋነት ባህላችንን አጥተን ሙስና፣ ሽሚያ፣ ንጥቂያ ይህ አካባቢ የእኔና የወገኖቼ ብቻ ነው ስስት የጨረለት ተግባራችን ሆኖ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መመሰቃቀል ተባብሶ ይቀጥላል፡፡ ‹‹ምከረው እንቢ ካለህ መከራ ይምከረው›› ቢባልም፣ የሕዝብ ረሃብ ስለሚያሳስበኝ አስተያየት ከመስጠትና ከመምከር አልቦዘንኩም፡፡

በየአሥር ዓመቱ ይከለስ የነበረው የምርት መጠን መለኪያ መነሻ ዓመትን ወደ አምስት ዓመት ዝቅ ለማድረግ ተፈልጎ በ2008 ዓ.ም. የጥቅል ምርት መጠን መለኪያ ዓመቱ ስለተከለሰ፣ እንደ ገና እርግጣዊው የምርት መጠን ከምሥላዊው የምርት መጠን እኩል አንድ ትሪሊየን አምስት መቶ ስልሳ ስምንት ቢሊዮን ብር እንደሆነ የብሔራዊ ባንክን ዓመታዊ ሪፖርት ተመልክቶ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በየአምስት ዓመቱ ለመከለስ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ከ2008 ዓ.ም. በኋላ ለመከለስ የተቻለ አይመስለኝም፡፡ ስላልተከለሰም በብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት ውስጥ የቀረበው የ2012 ዓ.ም. ምሥላዊ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ሦስት ትሪሊየን ሦስት መቶ ሰባ አምስት ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ቢከለስ ኖሮ እኩል መሆን ይገባው የነበረው እርግጣዊው ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ሁለት ትሪሊየን አንድ መቶ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ በ2018 ግን የ2008 ክለሳ አሥር ዓመት ስለሚሞላው ተከልሶ እርግጣዊው የምርት መጠን በሰላሳ በመቶ የአሥር ዓመታት ዓመታዊ የዋጋ ንረቶች አብጦ ከምሥላዊው ጥቅል የአገር ምርት መጠን ጋር እኩል ዘጠኝና አሥር ትሪሊየን ብር ይሆናል፡፡ ነፍስ ወከፍ ገቢያችንም ከሦስት ሺሕ ዶላር በላይ ወይም ይህ ዋጋ በጊዜው የብር ምንዛሪ ምጣኔ ተሠልቶ ሁለት መቶ ሺሕ ወይም ሦስት መቶ ሺሕ ብር ነፍስ ወከፍ ገቢ ይሆናል፡፡

የጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠንን መለኪያ ዋጋ በየአምስት ዓመቱ ለመከለስ እንደታቀደው ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ከላይ በመግቢያው ላይ የቀረበው የ2012 ዓ.ም. አንድ ሺሕ ሁለት መቶ አሥራ ስምንት ዶላር ነፍስ ወከፍ ገቢያችን ወደ ሁለት ሺሕ ዶላር አካባቢ ደርሶ በብር ሲመነዘር ስልሳ ስምንት ሺሕ ብር በመሆን ፋንታ አንድ መቶ አሥራ ሁለት ሺሕ ብር ይሆን ነበር፡፡ ይህም የአንድ አባወራን ወርኃዊ ገቢ ከሃያ ስምንት ሺሕ አራት መቶ ብር ወደ አርባ ሰባት ሺሕ ብር ያስጠጋ ነበር፡፡ ይህ የሪፖርቶች መረጃ ትንታኔ ሲሆን ምድር ላይ ያለው ሀቅ ግን የአንድ ኢትዮጵያዊ አባወራ አማካይ ወርኃዊ ገቢ አምስት ሺሕ ብር መሙላቱም ያጠራጥራል፣ አንባቢ ምድር ላይ ያለውን ዓይቶ በተረዳው ይፍረድ፡፡ 

ይህን የሚያህል ትልቅና መሠረታዊ ጉድለት በኢኮኖሚው ውስጥ እያለ እኛ ኢኮኖሚስቶች የኮቪድ ንዝረት ውጤት (Covid Shock Effect)፣ የስንዴ ምርት ኤክስፖርት ፖሊሲ ንዝረት ውጤት (Wheat Export Policy Shock Effect) በሚሉና መሰል ጠብ በማይሉ ጥቃቅን የኢኮኖሚ ጉዳዮች ጥናት ላይ እንረባረባለን፡፡ እስኪ ትንንሹን ጉዳይ ትተን በቅድሚያ በዋናውና ሥር ነቀል ለውጥ በሚያመጣው ላይ እንረባረብ፡፡ ሳልፈራ ደፍሬ እናገራለሁ ኢኮኖሚውን መሬት ላይ በሚታየው ልክ ለማድረግ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (GDP) በቀድሞ የተፈለገና የተመረጠ ዓመት አጠቃላይ የዋጋ ደረጃ አመልካች (General Price Level Index) እንዲረክስ (Deflate) ተደርጎ መለካት አለበት፡፡

ለምሳሌ በ120 አጠቃላይ የዋጋ ደረጃ አመልካች የተለካ የ2015 ዓ.ም. ጥቅል ምርት መጠን 600 ብር ቢሆን፣ የጥቅል ምርት መጠኑን በ100 የ2010 ዓ.ም. አጠቃላይ የዋጋ ደረጃ አመልካች ለመመለስ ብንፈልግ ጥቅል ምርቱን 600 ብር በ120 የጥቅል ምርት ርካሽ (GDP Deflato) አካፍለን በ2010 ዓ.ም. የጥቅል ምርት ዋጋ ብናበዛ 500 ብር ይሆናል፡፡ ጥቅሙ የምርት መጠኑ መቀነሱ ሳይሆን በምርት መጠኑ ላይ ተመርኩዞ የሚለኩት ትክክለኛ መረጃን አውቆ እንደ ነፍስ ወከፍ ገቢ መጠን፣ የድህነት ምጣኔን የጥሬ ገንዘብ ፍላጎትና አቅርቦት መጠንን፣ ፍጆታን፣ ቁጠባን፣ መዋዕለ ንዋይን፣ የመንግሥት በጀትን፣ ኢምፖርት/ኤክስፖርትን የመሳሰሉትን ለማቀድ ትክክለኛ የፖሊሲ ዕርምጃ ለመውሰድ ነው፡፡

ያኔና ያኔ ብቻ ነው የጤፍ ዋጋ ወደ ነበረበት በፍላጎትና በአቅርቦት መስተጋብር የተወሰነ ትክክለኛ የገበያ ማጣሪያ ዋጋ (Market Clearing Price) የሚመለሰው፡፡ አንድ ከፍተኛ ምሁር በደመወዙ አንድ በግ ሊገዛ የማይችልበት አገር በዓለም ላይ ታይቶ አይታወቅም፡፡ ያለፈ ስህተት ካልታረመ ወደፊት መሄድ አይቻልም፡፡ ይህንን በማድረጋችን የምናጣው ነገር ቢኖር ከኬንያ እንበልጣለን፣ ከኡጋንዳ እንበልጣለን የግብዝ ጉራችንን ነው፡፡ ለነገሩ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ሲቀንስ የብር አቅርቦትም አብሮ ስለሚቀንስ ብር ጠንካራ (Appreciated Revalued) ሆኖ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርቱ በዶላር ሲለካ አይቀንስም፡፡ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርትን ወደኋላ በትክክለኛ ዋጋ መከለስ ዛሬ ያለምኩት ሐሳብ ሳይሆን፣ በ2010 ዓ.ም. ግንቦት ወር ለሁለተኛ ጊዜ ባሳተምኩት “የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከየት ወዴት” መጽሐፌ ላይ የጨመርኩት አንድ ርዕስ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getachewasfaw240@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...