Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ለአንድ ትውልድ በመልካም መታነፅም ሆነ ብልሽት ወላጆች ቀዳሚውን ሥፍራ ሲይዙ፣ ማኅበረሰብና መንግሥትም የድርሻቸውን ኃላፊነት ይወስዳሉ፡፡ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከወላጆች ባልተናነሰ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በአንድ  ወቅት  በተወሰኑ  ትምህርት  ቤቶችና  በወላጆች  መካከል  መቃቃሮች  እየተፈጠሩ በየሚዲያው  ሲወነጃጀሉ  ይሰሙ  ነበር፡፡ ወላጆች  ትምህርት  ቤቶች  ጥራት  ያለው  ትምህርት  አለመስጠታቸውንና  የማያቋርጥ  የክፍያ  ጭማሪ  ማድረጋቸውን ሲወቅሱ፣ ትምህርት  ቤቶችም  የራሳቸውን  ምክንያት  ይደረድራሉ፡፡ ጭቅጭቁ  አሁንም  እንደሚኖር ይገመታል፡፡

የትምህርት ነገር ሲነሳ አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ የተማሪዎችን  ሥነ  ምግባር  ጉድለት  በተመለከተ  በወላጆችና  በትምህርት  ቤቶች  ላይ  ከፍተኛ  ስሞታዎች  ሲሰሙ  ነበር፡፡ ትምህርት  ቤቶች  ውስጥ  ሲጋራ  ማጨስ፣    ቁማር  መጫወት፣ በግልጽ  ፆታዊ  ግንኙነት  መፈጸም፣  ከመምህራንና  ከአስተዳደር  ሠራተኞች  ጋር  መጋጨት፣  ወዘተ.  የተለመዱ የተማሪዎች  መገለጫ  ሆነዋል  የሚሉ  ቅሬታዎችም ሲቀርቡ ነበር፡፡ የእኔ  የእዚህ  ሳምንት  ገጠመኝ  ይኼንን  ይዳስሳል፡፡

ከአንድ ዓመት  በፊት  ከብሔራዊ  ቴአትር  ወደ  ፒያሳ  ነፋሻማውን  አየር  እየተመገብኩ  በእግሬ  ሳዘግም  ቴዎድሮስ  አደባባይ  አካባቢ ደረስኩ፡፡  በምቾት  እንደሚኖሩ  የሚያስታውቁ  እጅግ  ውድ በሆኑ  አልባሳትና  መጫሚያዎች  የተዋቡ  ወንድና  ሴት  ተማሪዎች  ተቃቅፈው  ከንፈር ለከንፈር  እየተሳሳሙ  ውድ  መኪናዎች  ውስጥ  ሲገቡ  አየሁ፡፡  አዲስ  አበባ  ውስጥ  ሳይሆን  ፓሪስ  ውስጥ  ያሉ  የሚመስሉት  የእዚያ  አካባቢ  ታዋቂ  ትምህርት  ቤት  ተማሪዎች መሆናቸውን  ነጋሪ  አላስፈለገኝም፡፡  ምክንያቱም  ብዙዎቹ  ተማሪዎች  በየምሽት  ክበቡ፣ በየካፌውና  በየጥጋጥጉ  እንዲህ  ዓይነት  ድርጊት  እንደሚፈጽሙ  አውቃለሁ፡፡  በጣም  የገረመኝ  ግን  እነዚህ  ለግላጋ  ወጣቶች  መኪኖቻቸውን  ተደግፈው  ሲሳሳሙ  የጎዳና  ላይ ወሲብ  በከተማው  ውስጥ  የተጀመረ  ማስመሰላቸው ነው፡፡  የወጣቶቹን  ሁኔታ  በማዘንና  በመገረም  ካየሁ  በኋላ  ወደ  ፒያሳ  ጉዞዬን  ስቀጥል፣  እንደ እኔው  ወደ እዚያ የሚጓዝ ሰው ያነጋግረኝ ጀመር፡፡

የዕድሜ እኩያዬ የሚሆነው  ሰው፣  ‹‹የትውልዱ  ነገር  አሳሳቢ  ሆኗል፡፡  ተጠያቂነቱንና  ኃላፊነቱን  መውሰድ  ያለባቸው  ግን  ቤተሰብ  በተለይም  ወላጆች  ናቸው…›› ብሎኝ፣  ‹‹ወንድሜ  እዚህ  ትምህርት  ቤት  ብቻ  መሰለህ  እንዴ  ችግሩ  ያለው?  እዚህ ከተማ  ውስጥ  አንድ  ታዋቂ  ትምህርት  ቤትን  ብትመለከት  ትደነግጣለህ፡፡  ተማሪዎቹ  ከፍተኛ  ወጪ  ወጥቶባቸው  እንዲማሩ  ቢላኩም፣  ከትምህርት  ቤቱም  ከመምህራንም  አቅም  በላይ  ሆነዋል፡፡  በተለይ  ከፍተኛ  ሁለተኛ  ደረጃ  ላይ  ያሉ  የተወሰኑ  ሴት  ተማሪዎች  ድርጊት  ዕውን  እነዚህ  ወላጅ  ወይም  አሳዳጊ  አላቸው  ወይ  ያሰኝሀል…›› እያለኝ ለዚህ ጽሑፍ የሚከብዱ አጓጉል ድርጊቶቻቸውን ነገረኝ፡፡ እኔም ችግሩ የተማሪዎቹ ብቻ አለመሆኑንና እኛ ወላጆችም ሆንን የሚመለከታቸው ሁሉ ተጠያቂዎች መሆናችንን አንስቼለት እያወራን መንገዳችንን ቀጠልን፡፡ 

በአዲስ  አበባ  ከተማ  ውስጥ  በበርካታ  ትምህርት  ቤቶች  ዙሪያ  መጠጥ  ቤቶች፣  አልቤርጎዎች፣  የጫት  መቃሚያና  የሺሻ  ማጨሻ  ቤቶች፣  የአደንዛዥ  ዕፅ  መጠቀሚያዎች፣  ወዘተ.  እንዳሉ ይኼው  ሰው  አወጋኝ፡፡  በአንዳንድ  የመንግሥት  ትምህርት  ቤቶች  መግቢያና  መውጪያዎች  ላይ  የጠላ፣  የጠጅና  የአረቄ  መሸጫዎች  ከመኖራቸውም  በላይ  ግቢዎቻቸው  ውስጥ  ትምባሆ  እንደሚሸጡ  ነገረኝ፡፡  ከዚህ  በተጨማሪ  በሀብታሞቹ  ትምህርት  ቤቶች  በራፍ  ላይ  እጅግ  በጣም  ውድ  የሆኑ  ዘመናዊ  መኪኖችን  የሚያሽከረክሩ  ወጣት  ሀብታሞች  ተማሪዎችን  እንደሚያባልጉ  ዘረዘረልኝ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ከወላጆችም ሆነ ከትምህርት ቤቶቹ የሚሰማ ድምፅ አለመኖሩ እንዳስገረመው ነገረኝ፡፡

በተለይ ንፋስ አመጣሽ ገቢ ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን  ትምህርት  ቤት  መላካቸውን  እንጂ  የት  እንደሚውሉ  እንደማያውቁ  ነግሮኝ፣  አንዳንዶቹ  ልጆቻቸውን  በከፍተኛ  ወጪ  እያስተማሩ  ለአንድ  ከፍተኛ  ኤክስፐርት  ከሚከፈል  ደመወዝ  በላይ  ሳምንታዊ  አበል  ከመመደብ  ውጪ፣  ከልጆቹ  ጋር  እንደማይግባቡም  ነገረኝ፡፡  ልጆቹ  የገዛ  ቋንቋቸውን  ረስተው  ካልተማረው  ነገር  ግን  በአጋጣሚ  ሀብት  ካገኘ  ወላጅ  ጋር  መግባባት  እንዳቃታቸው  አስረዳኝ፡፡  ልጆቹ  ቋንቋን  እንጂ  ዕውቀትን  መገብየት  አለመቻላቸውንም  አተተልኝ፡፡ የ12ኛ ክፍል ፈተና ደካማ ውጤትንም በምሳሌ ጠቃቀሰልኝ፡፡

ይኼ  ሰው  በምንወያየበት  ጉዳይ  ላይ  ጠለቅ  ያለ  ግንዛቤ  እንዳለው  ያወቅሁት  ይኼንን  ሲነግረኝ  ነው፡፡  ‹‹በርካታዎቹ  ወላጆች  ልጆቻቸው  እንግሊዝኛ  ወይም  ፈረንሣይኛ  ቋንቋ  በመናገራቸው  ብቻ  ያወቁና  የተመራመሩ  እንደሚመስላቸው  በጫት፣  በመጠጥና  በወሲብ  ሱሶች  መለከፋቸውን  የተረዱ  አይመስለኝም፡፡ ሀብታሞቹ የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች ሳይቀሩ ነው እኮ በፈተና እየተረፈረፉ ያሉት….›› አለ፡፡ ‹‹ በተለይ ምንጩ የማይታወቅ ሀብት የሚያጋብሱ ቤተሰቦች ለልጆቻቸው የሚመድቡት   ሳምንታዊ አበል፣  የአንድ  መካከለኛ  ቤተሰብ  የዓመት  ቀለብ  ሊሆን  ይችላል  ሲለኝ  ደነገጥኩ፡፡  ልጆቹ  በከፍተኛ  ደረጃ  በመበላሸታቸው  ምክንያት  መምህራንን  ይሰድባሉ፣  አስተዳዳሪዎችን  ይዘልፋሉ፣  የትምህርት  ቤቱን  ማኅበረሰብ  ይበጠብጣሉ፣  ከእነሱ  በታች  ያሉትን  ሕፃናት  ያበላሻሉ…››  ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ በአንዳንድ የሀብታም  ትምህርት  ቤቶች  የመምህራንና  የተማሪዎች  ትምባሆ  ማጨሻ ቦታ  መኖሩን  ሲነግረኝ  ግራ ገባኝ፡፡ ተማሪና አስተማሪ ትምባሆ እየተቀባበሉ እንደሚያጨሱ ሲነግረኝ ጎመዘዘኝ፡፡   

ጉዟችን ተጠናቆ  ልንለያይ  ስንል፣  ‹‹ወንድሜ  ለዚህ  ሁሉ  ችግር  ተጠያቂዎቹ  እኛ  ነን፡፡  ወላጆች፣  መምህራን፣  ማኅበረሰቡና  መንግሥት…››  አለኝ፡፡ በመቀጠልም፣  ‹‹አንድ የቀረ  ነገር  ልንገርህ?››  በማለት  ወደ  ጆሮዬ ተጠጋ፡፡  ምን  ይሆን  ብዬ  ጆሮዬን  ሳውሰው፣  ‹‹ልጆቹ  እኮ  መረን  ከመለቀቃቸው የተነሳ የሚማሩባቸውን  ክፍሎች  ግድግዳዎች  የብልግና  መዝገበ  ቃላት አድርገዋቸዋል…››  ሲለኝ ተጠያቂዎቹ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ እኛም ነን ብዬ  ደመደምኩ፡፡ ለነገሩ አገር ለማጥፋት የተነሱ ኃይሎችስ ልጆቻችንን ከጉያችን እየነጠቁ አይደለም ወይ ግድያና ውድመት ውስጥ የሚከቷቸው? እኛስ ልጆቻችንን መቆጣጠር አቅቶን አይደለም ወይ ለጥፋት ያጋለጥናቸው? አዲሱ ትውልድ ዓይናችን ሥር በሞራል ዝቅጠት ችግር ውስጥ ሲገባ እኛ እንዴት ንፁህ መሆን ይቻለናል? ትውልዱ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እኮ ከጥፋት መከላከል ነው፡፡

(ዘሪሁን ጣሰው፣ ከፓስተር)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...