Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹የመጣነው በኢትዮጵያ የሚገኙ የማርሻል አርት ስፖርቶችን ለማሳደግ ነው›› ግራንድ ማስተር ሔኖክ ግርማ

‹‹የመጣነው በኢትዮጵያ የሚገኙ የማርሻል አርት ስፖርቶችን ለማሳደግ ነው›› ግራንድ ማስተር ሔኖክ ግርማ

ቀን:

በኢትዮጵያ ከ30 በላይ የስፖርት ፌዴሬሽኖች በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ስፖርት ማኅበራት ምዝገባ ድጋፍና ቁጥጥር አማካይነት ተደራጅተው እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ፌዴሬሽኖቹም እንደየስፖርቱ እንቅስቃሴ በአገር ውስጥ፣ በአኅጉር አቀፍ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ደረጃ በሚከናወኑ ውድድሮች ይሳተፋሉ፡፡ ፌዴሬሽኖቹ ውድድሮቹን ከማሰናዳት ባሻገር፣ በማኅበረሰብ ውስጥ ያለው ታዳጊና ወጣት አልባሌ ሥፍራ እንዳይውልና የበለፀገ አዕምሮ እንዲኖረው የስፖርት እንቅስቃሴ መፍጠር ግባቸው እንዲሆን የስፖርት ፖሊሲ ያስቀምጣል፡፡ በርካታ የስፖርት ዓይነቶች በክልልና በከተማ አስተዳደር፣ እንዲሁም ክለቦች እየተዘወተሩ ወደ ፌዴሬሽኖች ለማደግ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ በቅርቡ ከስድስት የማርሻል አርት ፌዴሬሽኖች ጋር በጋራ በመሆን፣ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዴሚ ውድድር አሰናድቶ የነበረው ሌጀንድ ማርሻል አርት፣ በኢትዮጵያ የማርሻል አርት ስፖርት ላይ የተለያዩ ሥራዎች ለመሥራት መሰናዳቱንና እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የማርሻል አርት ስፖርቶችን በተመለከተ ዳዊት ቶሎሳ ከሌጀንድ ማርሻል አርት ማኅበር ፕሬዚዳንት ግራንድ ማስተር ሔኖክ ግርማ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ሌጀንድ ማርሻል አርት በኢትዮጵያ እንቅስቃሴውን መቼ ጀመረ?

ማስተር ሔኖክ፡- ሌጀንድ ማርሻል አርት በአሜሪካ ዕውቅና ያለው ፌዴሬሽን ነው፡፡ ስፖርቱ ከኮሪያ ማስተሮች ጋር በጋራ በመሆን ይሠራል፡፡ በኢትዮጵያ በስፖርት ማኅበር ተደራጅቶ የሚገኘው ሌጀንድ ማርሻል አርት፣ ከስድስት ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽኖች ጋር በጥምረት ይሠራል፡፡ ስድስቱም ፌዴሬሽኖች የማርሻል አርት ፌዴሬሽኖች በአፍሪካ ማርሻል አርት ላይ መሥራት ፍላጎት ስላላቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሠራ ጥናቱ እ.ኤ.አ. 2020 ተሰጠን፡፡ ጊዜው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ የነበረበት ወቅት ስለነበር የኦንላይን (Virtual) ውድድር ማድረግ ቻልን፡፡ በዓለም ላይ ከሚገኙት ስድስት ፌዴሽኖች ጋር በቅርበት መሥራት ቀጠልን፡፡ ከዚያም በዘለለ ኢትዮጵያ ካሉት ፌዴሬሽኖች፣ እንዲሁም ማኅበር ጋር ሊሠሩ የሚችሉ ተግባራት ላይ እየተመካከርን መሄድ ቀጠልን፡፡ ከዚያም ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዴሚ ስድስት ዓይነት የማርሻል አርት ስፖርት፣ እንዲሁም በኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ስፖርት ምድብ ውድድር አሰናድተን እንቅስቃሴውን ጀመርን፡፡    

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ስፖርት አካዴሚ ሐምሌ ወር የተከናወነውን ውድድር የማሰናዳቱ ሒደት እንዴት ነበር?

ማስተር ሔኖክ፡- ውድድሩ ለመጀመርያ ጊዜ ስድስት ዓይነት የማርሻል አርት ውድድር በቴኳንዶ ስፖርት ምድብ፣ በአዋቂና ታዳጊ የመወዳደሪያ ዓይነት ለሁለቱም ፆታ የተሰናዳ ነበር፡፡ ውድድሩን ከማሰናዳታችን አስቀድሞ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ፌዴሬሽኖች ጋር ተወያይተን ነበር ወደ ዝግጅት የገባነው፡፡ ባለው ባለሙያ መሠረት እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር ወጪ ያስወጣናል የሚል ግምት ነበረን፡፡ በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ ከሚገኙ ፌዴሬሽኖች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረምን፡፡ ከዚያ ወደ ውድድር ገባን፡፡ ወደ ውድድር ከገባን በኋላ የተወሰኑ ችግሮች ቢፈጠሩም እየፈታን ውድድሩን አከናወንን፡፡ በውድድሩ ላይ ከ900 በላይ ተወዳዳሪዎች መካፈል ችለዋል፡፡ እኛ ቀድመን ገምተን ከነበረው የሁለት ሚሊዮን ብር ወጪ በላይ አምስት ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ውድድሩ እየተካሄደ የተፈጠረው አለመግባባት ምን ነበር?

ማስተር ሔኖክ፡- ውድድሩን ለማከናወን ከሦስት ወራት በፊት ነበር ዝግጅት ስናደርግ የነበረው፡፡ አብዛኛው ተካፋይ ውድድሩ ሦስት ቀናት ሲቀረው ነው የተመዝገበው፡፡ በአንፃሩ ሙያተኞች፣ እንዲሁም ዳኞች ውድድሩ ከተጀመረ በኋላ ‹‹ክፍያ ያንሰናል›› የሚል ቅሬታ ማሰማት ጀመሩ፡፡ ቀድሞ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመን ብንገባም ጥያቄው ተነሳ፡፡ ከዚያም ክፍያውን ለማሻሻል ተስማማን፡፡ ወዲያው ካልተከፈለን አሉ፡፡ ለስድስቱም ፌዴሬሽኖችና ማኅበራት ዳኞች፣ እንዲሁም አንዳንድ የክልል ፌዴሬሽን ሰዎች ክፍያ ፈጸምን፡፡ በአንፃሩ ውድድሩ ሊጀመር ቀናት ሲቀሩትና ውድድሩ እየተከናወነ ባለበት ወቅት ከውድድሩ ሊያስተጓጉሉብን ጥረት ሲደርጉ የነበሩ አካላት ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- የሌጀንድ ማርሻል አርት በኢትዮጵያ ሊተገብረው የሚያቅደው ምንድነው?

ማስተር ሔኖክ፡- የሌጀንድ ማርሻል አርት ዓላማ የተሻለ ዜጋ መፍጠር ነው፡፡ አብዛኛው ወጣት ሺሻ ቤት፣ ጫት ቤት፣ እንዲሁም መጠጥ ቤት ነው ያለው፡፡ ይህን ለምን ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ፌዴሬሽኖቹ ለወጣቱ በቂ የውድድር ዕድል መፍጠር ካልቻሉ ወጣቱን ለሱስ ያጋልጡታል፡፡ ስለዚህ ሌጀንድ ማርሻል አርት ሊሠራ ያቀደው ለወጣቱ የውድድር ዕድል መፍጠር፣ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ማሰናዳት፣ እንዲሁም በተለያዩ አገር አቀፍ፣ አኅጉር አቀፍ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ መሳተፍ የሚችሉ ስፖርተኞችን ማብቃት ግቡ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ስፖርት በውስን ስፖርቶች ላይ ብቻ ነው የምትካፈለው፡፡ ሌጀንድ ማርሻል አርት በኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ጨዋታ አማራጭ የስፖርት ዓይነቶች እንዲኖራት ይሠራል፡፡  

ሪፖርተር፡- ሌጀንድ ማርሻል አርት ፌዴሬሽን ለማቋቋም እንቅስቃሴ ጀምሯል?

ማስተር ሔኖክ፡- ፌዴሬሽን ለማቋቋም የሚያስፈልገው ቅድመ ዝግጀት በተመለከተ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሚጠይቀውን መሥፈርቶች እያሟላን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቀድመው የተቋቋሙ ፌዴሬሽኖች እየተከተሉትና እየሄዱበት ያለውን መንገድ ተመልክተናል፡፡ በዚህም መሠረት ሌጀንድ ማርሻል አርት በሲዳማ፣ በደቡብ፣ በአማራ፣ በድሬዳዋና አዲስ አበባ ላይ የተደራጀ አባል አፍርቷል፡፡ በርካታ ክለቦችና አሠልጣኞችም አፍርተናል፡፡ ስለዚህ የሚያስፈልገውን አካሄድ እየተከተልን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአንፃሩ ሌጀንድ ማርሻል አርት ሁሉንም ፌዴሬሽኖች ሊጨፈልቅ፣ እንዲሁም ፌዴሬሽኖችን ለመገንጠል ነው የመጣው የሚል ጥያቄ የሚያነሱ አሉ?

ማስተር ሔኖክ፡- ለእኛ ሁሉም የማርሻል አርት ወይም የቴኳንዶ ስፖርት እኩል ነው፡፡ አንዱ ከአንዱ እንዲያነስ እንዲሁም እንዲበልጥ አንፈልግም፡፡ ምክንያቱም ያደግንበት ስፖርት ነው፡፡ ስለዚህ የሚነሳው ቅሬታ ውኃ የሚያነሳ አይደለም፡፡ ሌጀንድ ማርሻል አርት ለሁሉም የማርሻል አርት ስፖርቶች አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግና በዓለም አቀፍ ደረጃ ውድድሮች ተሳትፎ እንዲኖር የሚሠራ ነው፡፡ በዘህም መሠረት በዓለም ላይ ያሉ ማስተሮችን ወደ አገር ውስጥ በማስመጣት የልምምድና የዕውቀት ሽግግር እያደረገ ይሠራል፡፡ እኛ  በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለን ተቀባይነት፣ በኢትዮጵያ ያሉትን የማርሻል አርት ስፖርቶች ልንደግፍ ነው የመጣነው፡፡ ከዚያም ባሻገር ባለሙያው የልፋቱን እንዲያገኝ፣ ሙያውን እንዲያዳብር፣ እንዲሁም ተፎካካሪ እንዲሆን ነው እየሠራን የምንገኘው፡፡ እኛ ግላዊ ጥቅም የለንም፡፡ ከማንኛውም የአገር ውስጥ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከሦስት ፌዴሬሽኖች ወጪ ዕውቅና ያላቸው ፌዴሬሽኖች የሉም የሚል ደብዳቤ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ሌጀንድ ማርሻል አርትም ዕግድ እንደተጣለበት ተጠቅሶ ነበር፡፡ ታግዳችሁ ነበር?

ማስተር ሔኖክ፡- ማንም አላገደንም፡፡ እሱ ስህተት ነው፡፡ ፌዴሬሽን ለማቋቋም መተዳደሪያ ደንቡን ተከታትለን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ሙያችን ነው፡፡ ሁሉም ስፖርት የግለሰብ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የሌጀንድ ማርሻል አርት ቀጣይ ዕቅድ ምንድነው?

ማስተር ሔኖክ፡- ዘንድሮ የሚከናወን ትልቅ የውድድር መርሐ ግብር አለን፡፡ ውድድሩ አፍሪካን ያማከለ ነው፡፡ በውድድሩ ላይ በርካታ የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች፣ ዶክተሮች፣ እንዲሁም ፕሮፌሰሮች ይገኙበታል፡፡ በኮሪያም፣ በኢትዮጵያ በስፖርቱ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም ውድድር ማሰናዳት ይሻላል? ወይስ ሥልጠና መስጠት ይሻላል? የሚለውን ጥናት እያደረግንበት እንገኛለን፡፡ ውድድሩ ለሁሉም ፌዴሬሽንና ባለሙያዎች ክፍት ነው፡፡ ውድድሩ ኢትዮጵያ ላይ ይደረጋል፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ይካፈሉበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...