በኢትዮጵያ የመንግሥት አገልግሎት የሚሰጠው የሲቪል ሰርቪስ ቁመና ከብቃትና ከችሎታ ይልቅ ለፖለቲካ ሥርዓት አቀንቃኝ መሆንና ብሔር ተኮር ጉዳዮች ላይ መጠመድ፣ ሕዝብ የሚጠብቀውን አግልግሎት እንዳያገኝ ማድረጉ ተገለጸ፡፡ የፖለቲካ ጫናው ሚናውን እንደገደበበትም ተጠቁሟል፡፡
ጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. መልካም አስተዳደር ለአፍሪካ የተሰኘው ድርጅት በኢትዮጵያ የሚገኘው ቢሮው ‹‹ተቋማዊ ልማት፣ አደረጃጀትና መልካም አስተዳደር በኢትዮጵያ›› የተሰኘ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በመድረኩ ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ ምሁራን የተገኙ ሲሆን፣ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕብሊከ አድሚንስትሬሽን እና ዲቨሎፐመንተ ማኔጅመንት ትምህርት ከፍል መምህር ብርሃኑ ተመስገን (ዶ/ር)፣ ‹‹የሲቨል ሰርቪስ አደረጃጀት አገልግሎት አሰጣጥና መልካም አስተዳደር በኢትዮጵያ›› በሚል የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ በዳሰሳ ጥናታቸው ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው የተቋማት አለመርጋት፣ በየጊዜው መለዋወጥና መቀያየር ጠንካራና በጊዜ ሒደት የማይናወጥ ሲቪል ሰርቪስ እንዳይፈጠር ስለማድረጉ ገልጸዋል፡፡ በአጠረ ጊዜ ውስጥ የሚደረግ የመንግሥት ተቋማት መታጠፍ፣ መዋሀድ ወይም ተጠሪነት መቀያየር አስፋጻሚውን የመንግሥት አካል በረዥም ርቀት አቅዶ የሚሠራና የተረጋጋ ቁመና እንዳይኖረው ስለማደረጉም ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በፌዴራልና በክልል ተቋማት ውስጥ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ብዛት 2.2 ሚሊዮን መድረሱን የገለጹት መምህሩ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ጉዳይ ከብዛትም ሆነ ከጥራት አኳያ የራሱ የሆነ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው ብለዋል፡፡ ከአጠቃላይ ሠራተኞች ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉት ወጣት የሚባሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በመንግሥት ተቋማት ተቀጥረው ከሚሠሩ የመንግሥት ሠራተኞች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት የዲፕሎማና የዲግሪ ምሩቅ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከአጠቃላይ የመንግሥት ሠራተኞች 75 በመቶ የሚሆኑት ከ12 ሺሕ ብር በታችው ደመወዝ የሚከፈላቸው መሆኑን የገለጹት መምህሩ፣ ይህ ወርኃዊ ደመወዝ የመንግሥት ሠራተኛውን ውጤታማነት የሚወስንና አሳሳቢ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የመንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥ በሚፈለገው ጥራትና መጠን እየተሰጠ አይደለም ያሉት ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ የፖለቲካ ጥገኝነት የሌለበት ሲቪል ሰርቪስ መፈጠር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ከተቻለ ቀጥታ ከዩኒቨርሲቲ በመመልመል ፖለቲካ፣ ብሔርና ማንነትን መሠረት ሳይደረግ ሙያና ብቃት ላይ የተመሠረተ የሠራተኛ ምደባ መኖር አስፈላጊነቱን አስረድተዋል፡፡ ከብሔር ይልቅ ለሙያው የሚሞግት ሠራተኛ መፈጠር መቻል አለበት ብለዋል፡፡ የአገርን ቁልፍ ችግር የማይፈታ የዘመቻ ሥራም መቆም እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ለምሳሌ ሙስናን ለመዋጋት በሚል በዘመቻ የፀረ ሙስና ኮሚቴ በማቋቋም ሌላ ሥራ መጀመር፣ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽንን ሚና ማሳጣት ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
ጥናታቸውን በሚያዘጋጁበት ወቀት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ለጥናቱ መረጃ እንዲሰጥ ቢጠየቅም ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ በውይይቱ ላይ እንዲገኙ የተጠሩ የክልልና የፌዴራል የመንግሥት ተቋማት መገኘት አልቻሉም ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ውብዓምላክ እሸቱ የተባሉ በዘርፉ በአማካሪነት የተሰማሩ ባለሙያ ሕዝብ በአገልግሎት ጥራት ማነስ እየተማረረ መሆኑን አውስተው፣ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ቅንጦት እየሆነ ስለመምጣቱ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ከጥራት ወይም ከብዛት አንፃር ምን ዓይነት ስትራቴጂ እየተከተለ ነው የሚለው ጉዳይ ግልጽ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሹመት የሚሰጣቸው ሚኒስትሮች የፖለቲካውን ዘርፍ መምራት እንጂ፣ ተቋማት ውስጥ እየገቡ ልምራ ማለት የለባቸውም ብለዋል፡፡ ጫና በበዛበት የመንግሥት አገልግሎት ማደግና በሚጠበቅበት ልክ መቆም ተስኖት ባለበት በዚህ ወቅት፣ ተገልጋይ ወደ አገልጋይ መሥሪያ ቤት ሲሄድ አገልግሎት ሰጪ ከተገልጋዩ የተሻለ ዕውቀትና ልምድ እንደሌለው ስለመታየቱም ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ይረዳ ዘንድ አንድ ተቋም ሲቋቋም ብቃት ያለው የሰው ኃይልና የተሟላ አደረጃጀትን በመያዝ መሆን እንዳለበት፣ የአገልግሎት ተቋማት ገልለተኛ ሆነው በራሳቸው የሚቆሙ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
መልካም አስተዳደር ለአፍሪካ ምሥራቃዊ አፍሪካ ዳይሬክተር ዘሪሁን መሐመድ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፣ በኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር ችግር በሰፊው የሚነሳ ዓብይ የኅብረተሰብ እሮሮ መሆኑ የአዳባባይ ሚስጥር ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም እሮሮ በምክንያትነት የሚጠቅሱት የመፈጸምና የማስፈጸም አቅማቸው ውስን የሆኑ የመንግሥት ተቋማት በብዛት መኖራቸው ነው፡፡
የመንግሥት ተቋማት ምንም እንኳ ከጊዜው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና የቴክኖሎጂ ዕድገት ደረጃ ጋር ተጣጥመው ማደግና ለውጥ ማሳየት አንዱ ባህሪያቸው ቢሆንም፣ አዲስ የፖለቲካ ሁኔታ በመጣ ቁጥር ፈርሰው እንደ አዲስ መሠራትና መገንባት ተቋማዊ ቀጣይነታቸውን አደጋ ውስጥ የሚጥልና በሒደት የካበተ ልምድና አሠራርን የሚበትን መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በውድድር ሊያዙ የሚገባቸው ቦታዎች ከውድድር ውጪ በሹመት መሰጠት መቆም አለበት ያሉት ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ ፖለቲካ በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ከገባ ሥራ ሊሠራ እንደማይችልና በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ምናልባት ሲቨል ሰርቪስ የሕዝብ ወካይ ተቋም ይሁን ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን ዕውቀትና ችሎታን ወደኋላ በመተው መሆን የለበትም፤›› በማለት አሳስበዋል፡፡ በዚህ ዓይነት የውክልና ጥያቄና የፖለቲካ ሚና መደበላለቅ የተነሳ፣ በየተቋማቱ አገልግሎት አሰጣጡን በዕውቀትና በችሎታ ያልተደገፈ አድርጎታል ብለዋል፡፡
የቀድሞው የብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር)፣ የብሮድካስት ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት ያጋጠማቸውን ችግር በማንሳት በየመሥሪያ ቤቱ ስለሪፎርም እንደሚነገር፣ ነገር ግን በትክክል ለውጥ እየተካሄደ ነው ወይ ሲባል ለውጥ እየተካሄደ ነው በሚል ብቻ ለማስመሰል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ስለመኖራቸው ተናግረዋል፡፡ ለሚዲያ ፍጆታ የሚሆን በየመሥሪያ ቤቱ አንዳንድ ሰዎች ጣል ጣል ቢደረጉም አብዛኛውን ችግር አይቀይረውም ያሉት ጌታቸው (ዶ/ር)፣ እነዚህ በየመሀሉ የሚሰኩ ግለሰቦች ቀድሞ በተሰመረላቸው መስመር እንዲጓዙ እንጂ፣ በብቃታቸው መሠረት አዲስ አሠራር፣ የራሳቸው የሆነ ጥሩ ዕሳቤና ልምድ በማካፈል ለውጥ የሚባለውን የማስቀጠል ዕድሉ የላቸውም ብለዋል፡፡
ለአብነትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የራሳቸውን ካቤኔ በመሾም እንደሚያደራጁት ሁሉ፣ አንድ የተቋም ኃላፊ ግን ተቋማዊ ሥራውን ሊያግዘው የሚችል አንድ ምክትል ማምጣትና ተቋምን የማደራጀት ሥልጣን የለውም ብለዋል፡፡ አንድ ኃላፊ ለተቀመጠበት ቦታ ተጠያቂ ለማድረግ ሥልጣኑን ከመብትና ከግዴታ ጋር አብሮ መስጠትና በነፃነት መሥራት መቻል አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በተቋማት ብቃትና ችሎታ ሲታሰብ ‹‹እኔን›› ተቀብሎ የማይታዘዝ ሰው ይመጣል በሚል ሥጋት ‹‹እሺ›› ብሎ የሚታዘዝ ሰው ይሻለኛል በሚል ሠራተኛ እንደሚቀጠር ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለውጥ የሚባለው ጉዳይ ከዓመታት በፊት ሲመጣ የታየው ንፋስ ወደኋላ ተመልሶ የሄደበት ምክንያት፣ ሥልጣንን የማቆየትና ያለ ማቆየት ጉዳይ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹በለውጡ ወቅት ከውጭ አገር፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከተለያዩ ተቋማት ወደ መንግሥት ቀርበው እንሥራ ሲሉ ከነበሩት አሁን ስንቶቹ አሉ? የሚያሠራ በመጥፋቱ በዚህ ሳምንት እንኳ ወደ ውጭ የተመለሰ ሰው አውቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡
ጌታቸው (ዶ/ር) ለዚህ እንደ ምክንያት የሚጠቅሱት በተቋማት አካባቢ ያለው የማያንቀሳቀስ አየርና የሥራ ሁኔታ ጥሩ አለመሆን፣ ለለውጥ ዝግጁ የሆኑ ሰዎች መጥፋት፣ ለውጡ ተገዳዳሪ መሆንና ራሳቸውን ለማኖር የሚያስቡ መብዛት፣ በራሳቸው የማይተማመኑና በብቃታቸው ያልተመደቡ ለለውጥ የመጣውን ሁሉ ሥጋት ነው ብለው ካሰቡ ባለው የፓርቲ መስመርና ኔትወርክ በመወንጀል ወደ ውጭ እንደሚገፉ ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው ጉዳይ ሠራተኛው በተቋም ውስጥ የሾመውን ወይም ኃላፊነት የሰጠውን ሰው ከመስማት፣ በብሔሩ አልያም በፓርቲ ተዓማኒነቱ ብቻ የተቀመጠውን ሰው የመስማት አባዜ በመኖሩ ይህ ሠራተኛውን በራሱ እንዳይተማመን ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ጌታቸው (ዶ/ር) ለውጥ እንዳይመጣ የሚያደርግ ነው ያሉት ሌላው አሠራር በየተቋሙ በፓርቲ መስመር የተቀመጡ ሰዎች መብዛት፣ የፓርቲ ቦታን መንካት ሥርዓት አንደ መድፈር የሚቆጠር በመሆኑ፣ አይነኬውን መንካት በብዙዎች ዘንድ የሚያስፈራ ከመሆኑ፣ መሠራት ያለበት ሥራ ሳይሠራ በሥጋት ባለበት ይቆማል ብለዋል፡፡