Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ኢሰመኮ ላይ የቀረበው ውንጃላ የመብት ጥሰትን የሚያባብስና ተበዳዮችን ፍትሕ የሚነፍግ ነው›› ...

‹‹ኢሰመኮ ላይ የቀረበው ውንጃላ የመብት ጥሰትን የሚያባብስና ተበዳዮችን ፍትሕ የሚነፍግ ነው›› የመብት ተቆርቋሪዎች

ቀን:

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰሞኑን ያወጣው ሪፖርት በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመሠረተና ሚዛናዊነት የጎደለው ነው በሚል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የሰጠው መግለጫ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የሚያባብስና ለተበዳዮች ፍትሕን የሚነፍግ ነው ሲሉ የመብት ተቆርቋሪዎች ገለጹ፡፡

ኮሚሽኑ በአማራ ክልል ለወራት በአገር መከላከያና በታጣቂዎች በቀጠለው ግጭት የአስገድዶ መድፈር ወንጀልና ከሕግ ውጪ የሚፈጸም ግድያ ተባብሶ መቀጠል እንዳሳሰበው፣ ከቀናት በፊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ የኮሚሽኑን ሪፖርት በተመለከተ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) ጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ በሕገ መንግሥቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የመከታተል ሥልጣን የተሰጠው መርማሪ ቦርድ ኃላፊነቱን በተሟላ ሁኔታ እየተወጣ ባለበት የኮሚሽኑ ሪፖርት በዚህ መልኩ መውጣቱ ገንቢና አዎንታዊ ሚና የለውም ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም መንግሥት በኢትዮጵያ ነፃና ገለልተኛ ተቋማት እንዲገነቡ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑንና ለዚህም ማሳያ አንዱ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መሆኑን ጠቅሰው፣ ነፃና ገለልተኛ መሆን ከአስፈጻሚ አካላት ብቻ ሳይሆን ከባዕዳንና ከሌሎች የውስጥ ሰርጎ ገቦች ሊሆን ይገባል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

የመንግሥትን መግለጫን በተመለከተ ሪፖርተር አስተያየት እንዲሰጡ የጠየቃቸው የኮሚሽኑ ሥራ ኃላፊዎች፣ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ይሁን አንጂ በኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት በሰብዓዊ መብቶች መከበር ዙሪያ እየሠሩ ያሉ ተቋማት ኃላፊዎችን አነጋግሯል፡፡

መግለጫው ይህ በመንግሥት የተሠራ ትልቅ ስህተት ነው ያሉት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለ ማርያም ናቸው፡፡ ይህ በአዋጅ የተቋቋመ የመንግሥት ተቋም ተጠሪነቱ ለፓርላማ የሆነን አንድን ትልቅ ኮሚሽንን በዚህ መንገድ መግለጽ አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹መግለጫው በመንግሥት በኩልም በደንብ የታሰበበት አይመስለኝም›› ያሉት አቶ ያሬድ፣ መግለጫው ኮሚሽኑ የማይታመን፣ በተለይም ሌሎች የመንግሥት አካላት እንዳያምኑት አድርጎ የወጣ ነው ብለዋል፡፡

የመንግሥት መግለጫ ኮሚሽኑ ካወጣው መግለጫ ፍሬ ነገር ይልቅ ገጸ ባህሪ መፍጠርና ተቋሙን በትክክለኛ መረጃ የማይሠራና በውስጥና በውጭ ኃይል የተጠለፈ አስመስሎ የቀረበበት መንገድ በጣም የስህተት ዕርምጃ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ‹‹በዚህ ጉዳይ ኮሚሽኑ በቀጣይ መግለጫ ይሰጥበታል ብዬ አስባለሁ፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥትም ተመልሶ የዚህን ተቋም ገጽታ የሚያስተካክል መግለጫ በመስጠት ቢሮክራሲው ውስጥ ላሉ ሰዎች ሌላ ሥራ ካልሠራ በቀጣይ የኮሚሽኑ መርማሪዎች ለሥራ በሚሄዱበት ሁሉ አሁን የቀረበባቸው ሰርጎ ገብ የሚል ስም የተቋሙን ሥራና ቁመና የሚያጎድፍ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡ በሌላ መንገድ አቶ ያሬድ እንደሚሉት ኮሚሽኑ ሥራውን በደንብ እየሠራ መሆኑንና እውነታን መሠረት አድርጎ የሚያመጣው መግለጫ ሥራውን አጥብቆ እየሠራ እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ መንግሥት ለሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ያለው ትኩረት ማነሱን፣ በሰብዓዊ መብት ጉዳይ የሚሰጠውን ምክረ ሐሳብ መቀበል እንደማይፈልግ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሕፃን በድሮን ተገደለ የሚል ሪፖርት ሲወጣ መንግሥት በራሱ ተቋም ዓለም አቀፍ ወንጀል ፈጽሟል መባሉ ያስደነገጣቸው የመንግሥት አካላት ይህን ለማስተባበል የተሰጠ አስደንጋጭና ትክክል ያልሆነ መግለጫ ነው ብለውታል፡፡

አቶ ያሬድ እንደሚሉት ከዚህ በፊት የነበረው አስተዳደርም በተመሳሳይ ተቋማት መግለጫ ሲያወጡ የሆነ ያህል ቁጥር ሰው ተገደለ ሲባል፣ እውነታውንና ቁጥሩን ይዘው እንደማይከራከሩና ይልቁንም ድርጅቱን ማጠልሸት ሥራ ይሠሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

‹‹አምንስቲን በምታጠለሽበት ቋንቋ የራስን ድርጅት ማጣጣልና ማጠልሸት አግባብ ባለመሆኑ መንግሥት ኮሚሽኑ ላወጣው ሪፖርት እንደዚህ ዓይነት ነውር የተቀላቀለበት መግለጫና ስህተት ይቅርታ መጠየቅ አለበት›› ብለዋል፡፡ በዚህ ልክ የኮሚሽኑን መግለጫ ማጣጣል ማለት የተበደሉ ሰዎችን በደል ዕውቅና መንፈግ፣ በደል ላደረሱት አካላት ሽፋን መስጠትና ተጠያቂ እንዳይሆኑ የማድረግ እንቅስቃሴ በመሆኑ መንግሥት ዕርምት ሊወስድ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳን ይርጋ በበኩላቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት በመግለጫው ሊያስተላልፍ የፈለገው አንድም የተጠቀሱት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አልተፈጸመም እያለ ነው፣ ወይንም የተፈጸመውን ጥሰት እየደበቀ ነው አልያም ደግመሞ ዕውቅና እየነፈገው ነው ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ በአዋጅ የተቋቋመ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋም ቢሆንም፣ መግለጫው ይህንን የሚገዳደርና ዕውቅና የሚነሳው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ይህ መግለጫ አግባብነት የሌለው በይፋ የትችትና ማስፈራራት የሚመስል መግለጫ ማውጣቱ የሚያሳስብ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በብዛት መሰል መግለጫዎች ኢሰመጉ ላይ የተለመዱ መሆናቸውን የገለጹት ዳን፣ አሁን በዚህ ደረጃ በአዋጁ የተቋቋመ ተቋም ላይ መግለጫ መውጣቱ ግን አሳሳቢ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ይህ ድርጊት እንደ መብት ተቆርቋሪ ትክክል አለመሆኑን በተለይም ከሕግ የበላይነት አንፃር፣ ከሰብዓዊነት አንፃር፣ ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አንፃር በመግለጽ ሁኔታውን የተመለከተ ሪፖርት እናወጣለን ብለዋል፡፡ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላትም በተቻለው አማራጭ ሁሉ በደብዳቤ፣ በአካል ወይም ከስልክ ቀርበው ለመነጋገር እንደሚፈልጉም ተናግረዋል፡፡

አቶ ዳን ይህ ማስፈራራትና ዕውቅና መንፈግ የአገሪቱን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ የሚከተው መሆኑን ጠቅሰው፣ በጣም አሳፋሪ ምልክት ነው ብለዋል፡፡ የሲቪክ ምኅዳሩ ዓውድ ተግዳሮቶች እያጋጠሙት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞች እየታሠሩ፣ የመብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ኢሰመጉን ጨምሮ ቢሮ እየተሰበረ፣ መርማሪ ማሰርና፣ የማስፈራራት አንቅስቃሴ ሁኔታውን የሚያባብሰው በመሆኑ መንግሥት ቆም ብሎ ሊያስብበት ይገባል ብለዋል፡፡

‹‹በአግባብ ሥራ ባልተሠራበት በዚህ ሰዓት እኛን ከጨዋታ ውጪ ማውጣት የሰብዓዊ መብት የማስከበር ሥራውን ገደል የሚከት በመሆኑ በአግባቡ ታስቦበት ሊሠራበት እንደሚገባ ጠይቀው፣ መግለጫው እንደ አገርም የሚመጥን አይደለም›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ኅብረት ዳይሬክተርና የሕግ ባለሙያው አቶ መስዑድ ገበየሁ በበኩላቸው ለሪፖተር እንደገለጹት፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መግለጫ በትክክልም የመንግሥት ወይስ የግለሰቦች አቋም የሚል ጥያቄ አጭሮባቸዋል፡፡

ኮሚሽኑ በአዋጅ ተቋቁሞ ለፓርላማው ተጠሪ ሆኖ እንዲያገለግልና መንግሥት ሰብዓዊ መብቶችን በተመለከተ የሚሠራቸውን ሥራዎች በሚመለከት ምክረ ሐሳብ የሚሰጥ፣ ተከታትሎ የሚገመግምና አጠቃላይ የሰብዓዊ መብት አፈጻጸም ሪፖርቶችን እያዘጋጀ ለፓርላማው የሚያቀርብ ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሆኖ ተቋም እያለ መግለጫ መውጣቱ ተገቢ አይደለም፡፡

ይህ ኮሚሽን ከተቋቋመ ጀምሮ ከዚህ በፊትም በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በትግራይም ጭምር ኮሚሽኑና ሌሎችም የመብት ተቆርቋሪዎች መግለጫ ሲያወጡ በማስረጃ ያልተደገፈ፣ ዓውዱን ያላገናዘበ ሌላ ፍላጎት ለማራመድ የወጣ ነው የሚል በርካታ መግለጫዎችን በማውጣት ሪፖርቶችን ሲያጣጥሉ እንደነበር አክለው ገልጸዋል፡፡

መግለጫ ኮሚሽኑ የተቋቋመለትን ዓላማ ለማሳካት ባለው አስቸጋሪ ዓውድ ውስጥ ከሚጠበቅበት ትንሹንም ሥራ እየሠራ ባለበት ዕውቅና መስጠት ሲገባ፣ ነቀፌታው ትክክል አይደለም ብለዋል፡፡ በመሆኑም ለዚህ ዕውቅና መስጠትና ምክረ ሐሳቦችን ሰምቶ ተግባራዊ ማድረግ ከአስፈጻሚው የሚጠበቅ ሆኖ ሳለ እንደዚህ ዓይነት የኮሚሽኑን ሥራና ድካም የሚያጣጥል መግለጫ ማውጣት አጠቃላይ ሥራው ላይ ተፅዕኖ የሚሳድር ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ምንም ዓይነት መግለጫ ቢያወጣ መንግሥት አይ የለም አልተፈጸመም የሚል ከሆነ፣ በማስረጃ ቁጭ ብሎ በመነጋገር መፍትሔ ለመስጠት ዕድል እያለ፣ ይህን መግለጫ ማውጣቱ ተፈጸመ የተባለውንም የመብት ጥሰት ዕውቅና መንፈግ ነው ብለዋል፡፡

ይህ ከመንግሥት የሚጠበቅ መግለጫ ካለመሆኑም በላይ በዚህ መግለጫ ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም ብለዋል፡፡ የኮሚሽኑ ሪፖርት ትክክል አይደለም ከተባለ ማስረጃ አቅርቦ ኮሚሽኑ ትክክል ካልሠራ መጠየቅ አለበት እንጂ፣ በሚዲያ ወጥቶ በማሳጣት መታለፍ እንደሌለበት አክለው አሳስበዋል፡፡

የሞቱ፣ የተጎዱ፣ የተፈናቀሉ፣ ንብረት ሀብታቸው የወደመ ዜጎች ፍትሕን ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡

በመንግሥት፣ በሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ ተቋማት መካከል ተፈጥሯዊ ውጥረቱ ቢኖርም በሕግ የተሰጣቸው ሥልጣን ግን ይህን ውጥረት የሚያስቀር ባለመሆኑ ችግሮችን በመቀራረብ ካልተፈቱ በመግለጫ ሊፈቱ እንደማይችሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹መንግሥት እኔ ራሴን ይተቸኝ፣ ያስተካክለኝ፣ ይሞከርኝ ብሎ ባቋቋመው ተቋም ላይ እንዲህ ዓይነት ክስ ሲያመጣ፣ እነዚህ ሰዎች ይህን እንዲሠሩ ካልፈቀደ እኮ ኮሚሽኑ ምንም አያስፈልግም ማለት ነው›› ምክንያቱም የመንግስት መግለጫ ከተቋቋመለት ዓላማ ጋር የሚጋጭም በመሆኑ ብለዋል፡፡

በመርህ ደረጃ እንደዚህ ዓይነት ለሰብዓዊ መብት መከበርም ይሁን ለአገር እንቅፋት የሚሆን መተማመን የሚያጠፋ፣ ዜጎች በመንግሥት ላይ ያላቸውን እምነት የሚሸረሽር መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ይሁን አንጂ መግለጫው ተጠያቂነት የለም ወይም አልጠየቅም ማለት እንደሆነና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የሚያባብስና የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት መብት የሚጥስ ስለመሆኑ ተረናግረዋል፡፡፡

መንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነቱን በተለይ ዜጎች ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ በሰላም እንዲኖሩ ማድረግን ባለመወጣቱ ምክንያት የተፈጸመውን ጉዳት አልተፈጸመም፣ አልጠየቅም ብሎ ማለት በማስረጃ ካልተደገፈ በስተቀር ነገሩን የፖለቲካ ጉዳይ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...