Sunday, December 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥታዊ ከወለድ ነፃ ባንክ እንዲቋቋም ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰባሰበው ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል

ከወለድ ነፃ አገልግሎት ባንክ አሁን ካለበት በስፋት ከፍ ብሎ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል፣ መንግሥታዊ ከወለድ ነፃ ባንክ እንዲቋቋም ጥያቄ ቀረበ፡፡ ጥያቄውን ያቀረቡት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼክ አብዱልከሪም ሼክ በድረዲን ናቸው፡፡

ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ በሲበኢ ኑር አስረኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ በተገኙበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ‹‹ካገኘናቸው ትሩፋቶች አንዱ እንዲሆን የምንፈልገው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥር ያለው፣ ሲቢኢ ኑር ከወለድ ነፃ አገልግሎት፣ እንደ ሌሎቹ እስላማዊ ባንኮች፣ በክብርና በታላቅ ትኅትና መንግሥታዊ ከወለድ ነፃ ባንክ ሆኖ እንዲቋቋም ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሸሪዓ አማካሪ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ሼክ መሐመድ ሃሚዲን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በተመሳሳይ ራሱን የቻለ ከወለድ ነፃ ባንክ መኖር እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ራሱን የቻለ የሸሪዓ መርህን የተከተለ፣ ራሱን የቻለ የመንግሥት ባንክ እንደሚመጣ ተስፋ እንደሚያደርጉም ገልጸው፣ በእነሱ በኩል የሚያቀርቡት ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል፡፡    

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት እያሳየ በመምጣት፣ በአሁኑ ወቅት ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱም ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቢኢ ኑር ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት 10ኛ ዓመት የክብረ በዓል ፕሮግራም ላይ የተገኙ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ አባል ወ/ሮ ያስሚን ወሃብረበ እንደገለጹት፣ ይህ ከወለድ ነፃ የሒሳብ ገንዘብ የተሰበሰበው አገልግሎቱን እየሰጡ ካሉ ከ20 በላይ ከሚሆኑ ባንኮች ነው፡፡

ከእነዚህ ባንኮች መካከል አራቱ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንኮች አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ በመስኮት ከወለድ ነፃ የባንክ 20 አገልግሎቱን የሚሰጡ ናቸው ብለዋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ባንኮች ካሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ ወደ ግማሽ ያህሉ ተቀማጭ ገንዘብ የተሰባሰበው በሲቢኢ ኑር በኩል መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ እነዚህ ባንኮች በአሁኑ ወቅት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ደንበኞቻቸው ቁጥር 18 ሚሊዮን መድረሱን ያመለከቱት ወ/ሮ ያስሚን፣ ዘርፉ በአጭር ጊዜ ዕድገት ያሳየ መሆኑን ያመለክታል ብለዋል፡፡ በአንፃሩ ግን የተሰበሰበውን ተቀማጭ ያህል ለብድር ወይም ለፋይናንስ ያልሆነ መሆኑን ግን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ እስካሁን ፋይናንስ የተደረገው (ብድር የተሰጠው) ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ ውስጥ አያደገ ስለመምጣቱ ያመለከቱት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንተ አቶ ኑር ሁሴን በበኩላቸው፣ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ የተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ከ98 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ከዚህ ከተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ ከ25.6 ቢሊዮን ብር ፋይናንስ (ብድር) መስጠቱን ገልጸዋል፡፡ የደንበኞችን ቁጥርም ከ6.4 ሚሊዮን በላይ ማድረሱንም ተናግረዋል፡፡ ባንኩ የሲቢኢ ኑርን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አገልግሎቱ እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡  

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገልግሎት ዕድገቱ እየጨመረ የመጣው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የበለጠ እንዲሰፋ ለማድረግ ግን በብሔራዊ ባንክ በኩል ተጨማሪ አስቻይ ሕጎች ሊወጡ እንደሚገባም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ከቁጠባ የሚሰበሰበውን ያህል ለብድር ማዋል ካልተቻሉባቸው ምክያቶች አንዱ ተጨማሪ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል ሕግ ባለመኖሩ ነው፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥባቸው በርካታ ዘርፎች ቢኖሩም በእነዚህ ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ ሕጉ የሚያስፈልግ ስለመሆኑ ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

በዓለም ላይ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ብዙ ዘርፎች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ አገልግሎት ላይ የዋሉ የተወሰኑ ናቸው ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚንት አቶ አቤ ሳኖ፣ ሌሎች አገልግሎቶች እየለመድናቸው ሲመጡ ወደ አገልግሎት የሚገቡ ይሆናል፡፡ ለዚህም የብሔራዊ ባንክ መመሪያዎች መሻሻል ይኖርባቸዋል በማለት የአቶ ኑሪን ሐሳብ አጠናክረዋል፡፡

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እዚህ የደረሰው በብዙ ውጣ ውረድ ቢሆንም፣ አሁንም ውጤቱ አስደሳች እየሆነ ስለመምጣቱ የጠቀሱት አቶ አቤ፣ በአገልግሎቱ ለመጠቀም በርካታ ፍላጎት ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ስላሉ፣ ዘርፉን ከዚህም በላይ ማሳደግ ይቻላል ብለዋል፡፡ በመጀመርያ በመስኮት ደረጃ ከዚያም ከፍ ብሎ ሙሉ ሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉ በእምነታቸው ምክንያት ወደ ባንክ ከደጃፍ መድረስ ያልቻሉትን ወደ ባንክ እንዲመጡ ማስቻሉንም አቶ አቤ ጠቅሰዋል፡፡  

አገልግሎቱ እምነትን ሳይለይ ሁሉንም የኅብረተሰቡን ክፍል መሳብ የሚችል መሆኑን የገለጹት፣ ወ/ሮ ያስሚን ‹‹ለአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገትና በዜጎች መካከል የሚታየውን የሀብት ክፍፍልና የገቢ አለመመጣጠን ችግር ለመፍታት ዕምቅ አቅም ያለ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም አገልግሎቱ አካታች የፋይናንስ ሥርዓት ለመዘርጋትና ኢኮኖሚያችንን ለማሳደግ፣ የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት ከመገንባት፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ኢንቨስትመንትን ለማበረታት የሚያግዝ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ስለመሆኑ አስታውሰዋል፡፡

አማራጭ የባንክ ሥርዓት ለመፍጠር፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ከግብር የሚገኘውን የመንግሥት ገቢ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስለሚያበረክት፣ በቀጣይነት መንግሥት የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራበት ዘርፍ መሆኑንም አስታውቋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች