Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት በአንዳንድ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ተቋማት የቀረበው ቅድመ ሁኔታ ሉዓላዊነትን የሚጥስ ነው...

መንግሥት በአንዳንድ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ተቋማት የቀረበው ቅድመ ሁኔታ ሉዓላዊነትን የሚጥስ ነው አለ

ቀን:

አንዳንድ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተቋማት በኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ማኅበረሰቦች የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ ያስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች የአገሪቱን ሉዓላዊነት እንደመጣስ የሚቆጠር በመሆኑ፣ ተቀባይነት አይኖረውም ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ አንዳንድ ዓለም አቀፍ የተራዕዶ ተቋማት የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ የሰብዓዊ ዕርዳታን በማቅረብና ባለማቅረብ መካከል ሲያመነቱ ይታያሉ ብለዋል።

የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትና ፖለቲካ መቀላቀል እንደሌለባቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ያምናል ያሉት ለገሠ (ዶ/ር)፣ ‹‹ይህ ፈጽሞ ስህተት ነው፣ ለተቸገሩ ሰዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚቀርበው ሰዎች ስለሆኑ ብቻ ነው። ሰብዓዊ ዕርዳታን የትኛውም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ የሚያቆመው አይደለም፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡  

ይሁን እንጂ በስም ያልጠቀሷቸው አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ‹‹በቀበሌና በወረዳ ገብተን፣ አስተዳደር ተክተን የዕርዳታ ማከፋፈል ሥራውን ካልሠራን›› የሚል ቅድመ ሁኔታ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። እነዚህ ተቋማት ያቀረቧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ‹‹የአንድን አገር ሉዓላዊነት እንደመጣስ ይቆጠራል፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ በዚህም ምክንያት ያቀረቡት ቅድመ ሁኔታ ተቀባይነት አይኖረውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቱን ሉዓላዊነት ጠብቆ ሁሉንም አቅሞቹን በማስተባበር፣ እንዲሁም ከምንጊዜም አጋሮቹ ጋር በመሆን ዜጎቹን ከችግር ለመታደግ ርብርብ የሚያደርግ መሆኑን ሊያጤኑ ይገባል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) እና የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (USAID) ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የሰብዓዊ ድጋፍ ማቋረጣቸውን ተከትሎ፣ የፌዴራል መንግሥት ተጎጂዎችን ለመታደግ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

እነዚህ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተቋማት ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ድጋፍ ማቆማቸውን ተከትሎ የፌዴራል መንግሥት 3.7 ሚሊዮን ለሚሆኑ ተረጂዎች 798,607 ኩንታል የምግብ ዕርዳታ ማከፋፈሉንና በዚህም በዋናነት በትግራይ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ለሚገኙ ተረጂዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። አክለውም የፌዴራል መንግሥት አሁንም ርብርብ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ለትግራይ ክልል የሚያቀርበው ሰብዓዊ ዕርዳታ ለተጎጂዎች ሳይደርስ የተደራጀ ዘረፋ እንደተፈጸመበት ማረጋገጡን በይፋ ገልጾ፣ የዕርዳታ አቅርቦቱን በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም. ማቋረጡ ይታወሳል። በኋላም የዓለም የምግብ ፕሮግራምና የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (USAID) በጋራ ሆነው ባደረጉት ምርመራ ለተጎጂዎች የሚቀርብ ሰብዓዊ ዕርዳታ በትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎችም ሲፈጸም መቆየቱን እንዳረጋገጡ ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡

በመጀመሪያ በትግራይ ክልል ባደረጉት ማጣራት ከ7,000 ሜትሪክ ቶን በላይ ስንዴና 215,000 ሊትር የምግብ ዘይት መዘረፉንና በክልሉ የንግድ ገበያዎች ማግኘታቸውን፣ በኋላም ከ12 በላይ በሚሆኑ አካባቢዎች በተለያየ ደረጃ የሚገለጽ ዘረፋ መፈጸሙን ይፋ አድርገዋል።

ይህንንም ተከትሎ ሁለቱም ተራድኦ ተቋማት ለኢትዮጵያ የሚቀርቡትን አጠቃላይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ከሚያዚያ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሙሉ በሙሉ አቋርጠዋል።

የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (USAID) ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ድጋፍ ካቋረጠ ከአምስት ወራት በኋላ፣ በመስከረም ወር 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ለተጠለሉ የውጭ አገር ስደተኞች ብቻ ዕርዳታውን ለማቅረብ ወስኗል።

በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች የምግብ ዕርዳታ አቅርቦቱን ለመቀጠል የተወሰነው የኢትዮጵያ መንግሥትና ተባባሪ አጋሮቹ፣ ለስደተኞች የሚቀርብ የምግብ ዕርዳታ የሚሠራጭበት መዋቅር ላይ ማሻሻያ ካደረጉ በኋላ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለስደተኞች የሚቀርብ የዕርዳታ ምግብ ሥርጭት ላይ ያካሄደው ማሻሻያ ክትትልና ቁጥጥርን የሚያጠናክርና የተጠቃሚዎችን ምዝገባ ሒደቶች ያሻሻለ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት ለስደተኞች የሚቀርብ ዕርዳታን የማጓጓዝና የማከፋፈል፣ እንዲሁም የማከማቻ መጋዘኖችን የመቆጣጠር ኃላፊነት ለፈጻሚው የዓለም ምግብ ፕሮግራም በማስተላለፉ ለስደተኞች የሚቀርብ ዕርዳታ እንደገና እንዲጀመር ለመወሰን ማስቻሉን አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ሰብዓዊ ዕርዳታ የማቅረብ ሥራ እንዲጀመር ቢወሰንም፣ በመላው ኢትዮጵያ የምግብ አቅርቦት ችግር ለገጠማቸው ማኅበረሰቦች የሚደረገው ድጋፍ ለታለመላቸው ተረጂዎች እንደሚደርስ ማረጋገጫ እስከሚገኝ ድረስ እንደተቋረጠ የሚቆይ መሆኑን የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) በመግለጫው አመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...