Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበትግራይ ክልል አገራዊ ምክክር ለማድረግ የሚረዳ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

በትግራይ ክልል አገራዊ ምክክር ለማድረግ የሚረዳ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

  • ‹‹ሕወሓትና ሌሎች የክልሉ ፓርቲዎች በምክክሩ እንደሚሳተፉ እናምናለን›› አገራዊ የምክክር ኮሚሽን

በዳንኤል ንጉሤ 

አገራዊ ምክክሩን በትግራይ ክልል ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ መደላድል መፍጠር እንደሚያስፈልግና ለዚህም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

‹‹በምክክር ሒደቱ መሳተፍ ካለባቸው ክልሎች አንዱ የትግራይ ክልል ነው፤›› ያሉት የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን የሚዲያ፣ ኮሙዩኒኬሽንና አጋርነት ዘርፍ ኃላፊና የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ፣ በተለይ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር የተለያዩ ግንኙነቶች ለማድረግ ሲሞከር እንደነበር፣ አሁን በክልሉ ባለው አንፃራዊ ሰላም ምክንያት የመጀመርያ ደረጃ ግንኙነት ለመፍጠር የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. መቀሌ በመሄድ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

‹‹የመጀመሪያ ደረጃ ግንኙነቱ በዋነኝነት ያተኮረው ምክክሩን ማካሄድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መሆኑን የተገናገሩት አቶ ጥበቡ፣ የትግራይ ክልል ነባራዊና ወቅታዊ ሁኔታን ግምት ውስጥ ያስገባ ምክክር ማካሄድ በሚቻልበትና በክልሉ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ባለድርሻ አካላት እንደተቀሩት የኢትዮጵያ ክፍሎች ሁሉ ተሳታፊ የሚሆኑበትን መንገድ ለመፍጠር የታሰበ ግንኙነት ነው፤›› ብለዋል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ትግራይ ክልል ድረስ ተጉዘው ባደረጉት የመጀመሪያ ደረጃ ግንኙነትም፣ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳና ከጥቂት የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር መምከራቸውን አስታውሰዋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አገራዊ ምክክሩ አስፈላጊና መካሄድ አለበት የሚል እምነት እንዳለው፣ የክልሉን ማኅበረሰብና ባለድርሻ አካላት በሒደቱ ማሳተፍ ጠቃሚ መሆኑንና ለዚህም ምቹ መደላድል መፍጠር እንደሚገባ ከኮሚሽነሮቹ ጋር መግባባት ላይ መድረሳቸውን ጠቅሰዋል።

‹‹ከጦርነቱ በኋላ በትግራይ ክልል ውስጥ መስተካከል ያለባቸው ብዙ ሁኔታዎች እንዳሉ እናምናለን፤›› ያሉት አቶ ጥበቡ፣ በክልሉ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ያገናዘበ ምክክር እንዴት መካሄድ እንደሚችል ተወያይቶ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ተገቢነትን አስረድተዋል።

‹‹የትግራይ ክልል ከጦርነቱ በኋላ በብዙ ችግሮች ውስጥ ሆና ለማገገም ጥረት ላይ ያለ ቢሆንም፣ የምክክር ጉዳይ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ በክልሉ ያሉ ችግሮች እስከሚቃለሉና ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ ድረስ  መጠበቅ የራሱ የሆነ ችግር ይፈጥራል፤›› ሲሉ የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ገልጸዋል።

አክለውም የክልሉ ማኅበረሰብ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ቢሆንም፣ በአገራዊ ምክክሩ መሳተፍ የሚገባው መሆኑን በማጤን ጊዜያዊ አስተዳደሩና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ለምክክሩ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መሥራት አለባቸው ብለዋል። 

ኮሚሽኑም የትግራይ ክልል ካለበት ጊዜያዊ ፈታኝ ሁኔታ አኳያ የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ቃል መግባቱን አቶ ጥበቡ ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ ሁለተኛ ዙር ውይይት ለማድረግ በቅርቡ ወደ ትግራይ ክልል እንደሚያመራም ተናግረዋል። በሁለተኛው ዙር ውይይትም ከክልሉ ጊዜያዊ አስደተዳደር ካቢኔ፣ እንዲሁም በክልሉ ከሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የመምህራን፣ የሴቶች፣ የወጣቶችና ከመሳሰሉት ጋር በሌሎች ክልሎች እንደተደረገው ሁሉ ምክክር እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ሕወሓት ሕጋዊ ሰውነቱን ያጣ የፖለቲካ ፓርቲ ከመሆኑ አኳያ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ለማካሄድ ያቀደው የምክክር ሒደት ላይ ዕክል ይፈጥር እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ጥበቡ፣ በትግራይ ክልል የሚካሄደው አገራዊ ምክክር የተሳካ እንዲሆን ምቹ መደላደል መፍጠር ያስፈልጋል ሲባል እነዚህና መሰል ጉዳዮች ለመፍታት እንደሆነ አስረድተዋል።

‹‹የምክክር ኮሚሽኑ ሁሉን ነገር አይሠራም፣ ሕወሓት ሕጋዊ ነው አይደለም የሚለውን የሚወስነው ምርጫ ቦርድ ነው፤›› ብለዋል። ከሕወሓት ዕውቅናና ምዝገባ ጋር የተያያዙ ነገሮችን የመፍታት ኃላፊነት የምክክር ኮሚሽኑ ሳይሆን የምርጫ ቦርድ መሆኑን የገለጹት አቶ ጥበቡ፣ ሕወሓት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሳተፉና በዚህ ስምምነት መሠረት በተቋቋመው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ተሳታፊ መሆኑም አስታውሰዋል።

‹‹ሕወሓት ዕቀባ ላይ የነበረ ፓርቲ መሆኑ ይታወቃል፣ ከዚያ ለመውጣት የመጣበት ሒደትም አለ፣ በምርጫ ቦርድ የመመዝገብና ዕውቅና የማግኘት ጉዳይም አለ፤›› ያሉት አቶ ጥበቡ፣ ‹‹የትግራይን ሁኔታ ከሌሎቹ ለየት አድርጎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በሒደት ነገሮችን እያጠራን እንሄዳለን፤›› ብለዋል። አክለውም ‹‹በእኛ እምነት ሕወሓትን ጨምሮ ሁሉም ፓርቲዎች በዚህ የምክክር ሒደት ላይ ይሳተፋሉ ብለን ነው የምንጠብቀው፤›› ሲሉ አስረድተዋል። 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...