የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ፣ የባንኮችንና የማክሮ ፋይናንስ ተቋማትን ተቀማጭ ገንዘብ በአግባቡ ባለማስተዳደር ለሚከሰት ችግርና ኪሳራ ምክንያት የሆኑ የሥራ ኃላፊዎችን ለሕግ የማቅረብ ሥልጣን እንደተሰጠው ተገለጸ፡፡
የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ በይፋ ሥራ መጀመሩን አስመልክቶ ሰሞኑን በተሰጠ መግለጫ፣ በባንክና በማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የሚገኝ የተቀማጭ ገንዘብን የመድን ሽፋን ለመስጠት መቋቋሙ ተገልጾ፣ ከዚህ ባሻገር የተቀማጭ ገንዘብ አስተዳደርንም የሚከታተልና እንደሚቆጣጠር ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ቦርድ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ እንደገለጹት፣ ተጠያቂነትን ከማስፈንና ዲሲፕሊን ከማስረፅ አኳያ ለፋይናንስ ተቋማት መክሰር ምክንያት እንደሆኑ የሚጠረጠሩትን አካላት ተጠያቂ የማድረግ ኃላፊነት ለፈንዱ ተሰጥቷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የፋይናንስ ተቋማት ችግሮች ሥር ሰደው ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት፣ ፈንዱ ችግራቸውን አስቀድሞ የሚተነብይና በፍጥነት ጣልቃ የሚገባበት አሠራር እንደሚኖረውም አብራርተዋል፡፡ ይህም የፋይናንስ ተቋማት ሴፍቲኔት በማቋቋም የሚተገበር ይሆናል ብለዋል፡፡ የፋይናንስ ሴፍቲኔት አንድ የሚከስር የፋይናንስ ተቋም በመክሰሩ ምክንያት ምንም ዓይነት ችግር ሳይፈጠርና ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ሳያሳድር እንዲከስም የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የፋይናንስ ተቋማት ሴፍቲኔት ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከፍርድ ቤትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር በመተባበር ለቀውሱ ምላሽ ይሰጣሉ ያሉት አቶ ሰለሞን፣ የፈንዱ መቋቋም የአስቀማጮችን ገንዘብ የመድን ሽፋን በመስጠት የከሰሩ ተቋማት ችግር ሳይፈጥሩ እንደከሰሙ የሚያደርግ ጭምር ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ ዋና ሥራ አፈስፈጻሚ አቶ መርጋ ዋቅወያ በሰጡት ማብራሪያ፣ የፈንዱ ዋነኛ ዓላማ አንድ የባንክ ወይም የፋይናንስ ተቋም ቢወድቅ ለገንዘብ አስቀማጮች ጥበቃ ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ፈንዱ ውስጥ ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩ በተለይ አነስተኛ ቁጠባ ላላቸው አስቀማጮች አስተማማኝ የመድን ሽፋን ለመስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡ አስቀማጮች ጥበቃ የሚደረግላቸው ተቋሙ መውደቁ ከተረጋገጠ በኋላ ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ አስቀማጭ ፈንዱ እስከ 100 ሺሕ ብር ላለው ተቀማጭ ገንዘብ ዋስትና እንደሚሰጥም ጠቅሰዋል፡፡
በኪሳራ ምክንያት ከገበያ ለሚወጡ የፋይናንስ ተቋማት ለአስቀማጮቻቸው የሚመለሰው ገንዘብ የሚሰበሰበው ከእያንዳንዱ ባንክና የፋይናንስ ተቋም ከአማካይ ዓመታዊ ተቀማጭ ገንዘብ 0.3 በመቶ በማሰባሰብ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዚህም መሠረት ፈንዱ በ2015 የበጀት ዓመት ወደ ስድስት ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ አቅዶ በመጀመርያው ሩብ ዓመት 1.6 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንም አቶ መርጋ አብራርተዋል፡፡ ከተቋማቱ የሚሰበሰበው ገንዘብ ያለ ሥራ እንዳይቀመጥ ኢንቨስትመንት ላይ በማዋል የፈንዱን አቅም ለማሳደግ የሚሠራ መሆኑን፣ ዘንድሮ የሰበሰበውን 1.6 ቢሊዮን ብር የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ በመግዛት ትርፍ ያገኝበታል ተብሏል፡፡ ከዚህም በኋላ ፈንዱ በየዓመቱ የሚሰበስበውን ገንዘብ በዋናነት የመንግሥትን የግምጃ ቤት ሰነድ በመግዛት የገንዘብ አቅሙን እያጠናከረ እንደሚሄድ አቶ መርጋ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
የፈንዱ ተጠቃሚ ማነው በሚለው ጉዳይ ላይ አቶ መርጋ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ በእያንዳንዱ ባንክና የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ተቀማጭ ገንዘብ ያላቸው ሙሉ በዚህ መድን ሽፋን ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
የመድን ሽፋኑ እስከ መቶ ሺሕ ብር ላለው ተቀማጭ ገንዘብ ብቻ የሚሰጠው ፈንዱ ባደረገው ጥናት በባንክና በማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት አስቀማጮች የቁጠባ መጠን ከ100 ሺሕ ብር በታች በመሆኑ ነው፡፡ ከ100 ሺሕ ብር በላይ ተቀማጭ ያላቸው ግን ጥቂቶች ቢሆኑም ከመቶ ሺሕ ብር በላይ ለሚሆነው ተቀማጭ ገንዘባቸው ተመላሽ ሊሆን የሚችለው የከሰረው ተቋም ሀብት ተሽጦ ትርፍ የሚኖር ከሆነ ይሰጣል ተብሏል፡፡ የፈንዱ መቋቋም የአስቀማጮችን መተማመን የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ፣ ለፋይናንስ ዘርፉ ጤናማነትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የሥራ ኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡