Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበውኃና በአካባቢ ንፅህና ላይ የሚተገበር የ90 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

በውኃና በአካባቢ ንፅህና ላይ የሚተገበር የ90 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

ቀን:

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) በአየር ንብረት ለውጥ ለተጎዱ አካባቢዎች፣ በውኃና በአካባቢ ንፅህና ላይ ለመሥራት፣ የ90 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡

ፕሮጀክቱ ዓርብ ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. በሀያት ሬጀንሲ ሆቴል ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ የቆይታ ጊዜው እ.ኤ.አ. ከ2022 እስከ 2027 ወይም የንፁህ ውኃ መጠጥ ሽፋንን ለማሳደግና የአካባቢ ንፅህና ለመጠበቅ በስፋት ለመሥራት መጀመሩ ተገልጿል፡፡

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት የመጠጥ ውኃ ንፅህና አጠባበቅና የሥነ ንፅህና ባለሙያ አቶ ደጀኔ ኩመላ እንደተናገሩት፣ የአሜሪካ መንግሥት የንፁህ ውኃ መጠጥ ሽፋንን ለማሳደግ ድጋፍ ከሚያደርግባቸው 21 አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡

የመጀመሪያው ፕሮጀክት በአሥር ሁለተኛ ደረጃ ከተማ በሚባሉት ላይ እንደሚተገበር፣ ይህም ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ወደ ሥራ መገባቱን አቶ ደጀኔ ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በከተሞች የንፁህ ውኃ ተደራሽነት በተጨባጭ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የዳሰሳ ጥናት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

የንፁህ ውኃ ተደራሽነት ተግባራዊ የሚደረግባቸው ከተሞች አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ሐዋሳ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌ፣ ባህር ዳር፣ ሻሸመኔ፣ ደሴና ኮምቦልቻ እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ ደጀኔ ገለጻ፣ ፕሮጀክቱ በሚቀጥሉት ሦስትና አራት ወራት ውስጥ ጥናቱ ተጠናቆ ወደ ትግበራ ይገባል፡፡

በተጠቀሱት ከተሞች የንፁህ ውኃ መጠጥ የቁጥጥርና የክትትል ማዘመን የፕሮጀክቱ አንድ አካል መሆኑን፣ በከተሞቹ ምን ያህል የመጠጥ ውኃ ተደራሽ ሆኗል? ምን ያህል ይቀራል? የሚለው መረጃ በተደራጀ ሁኔታ እንደሚጠናከርም ጠቁመዋል፡፡

የአካባቢ ንፅህና መጠበቂያ ውኃ ፕሮጀክት ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በድርቅ በተጎዱት በሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋርና በሌሎችም ቆላማ አካባቢዎች ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ይህንንም ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ከአየር ፀባይ ጋር ተስማሚ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ዘላቂ መፍትሔ ማዘጋጀት ዓላማ ማደረጉን አስረድተዋል፡፡

በቆላማ አካባቢዎች ላይ ተግባራዊ የሚደረገው የአካባቢ ንፅህና መጠበቂያ ውኃ ፕሮጀክት ደግሞ ባለፈው ነሐሴ ወር ላይ የተጀመረ መሆኑን ገልጸው፣ ሁለቱም ፕሮጀክቶች ለአምስት ዓመታት የሚቆዩ ናቸው ብለዋል፡፡

ለንፁህ የመጠጥ ውኃ 45 ሚሊዮን ዶላር፣ በአየር ንብረት ለውጥ በተጎዱ አካባቢዎች የሚተገብረው የአካባቢ ንፅህና መጠበቂያ ውኃ ደግሞ 45 ሚሊዮን ዶላር በአጠቃላይ 90 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደተደረገ ገልጸዋል፡፡

 ፕሮጀክቱን በጋራ የሚያከናውኑት ደግሞ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴርና የመስኖናና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር መሆናቸውን፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ሀብት በአግባቡ ከመጠቀም አኳያ ደግሞ የገንዘብ ሚኒስቴር በበላይነት እንደሚቆጣጠር አስረድተዋል፡፡

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሳኒቴሸን መሠረተ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኑረዲን መሐመድ፣ በከተሞች የንፁህ ውኃ መጠጥ ችግር ክፍተት እንዳለና ይህ ፕሮጀክትም አካባቢዎቹን ትኩረት አድርጎ ከመሥራት አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ሁለተኛው ፕሮጀክት በዋናነት በድርቅ የሚጠቁ አካባቢዎች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን የገለጹት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፣ በእነዚህ አካባቢዎች ያሉትን መሠረተ ልማቶች የማጠናከርና ግንባታ ማካሄድ ዓላማው አድርጎ እየተሠራ ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ 500,000 ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ፣ ከእነዚህ ውስጥ 350,000 የሚሆኑት ንፁህ ውኃ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡ 120 የውኃና የንፅህና መጠበቂያ ላይ የሚሠሩ ተቋማትን ማጠናከር ከፕሮጀክቱ ግቦች መካከል ይጠቀሳል፡፡

በኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ሕዝብ ግማሽ የሚሆነው ብቻ መሠረታዊ የውኃ አገልግሎት እንደሚያገኝ፣ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ መሠረታዊ የንፅህና መጠበቂያ አገልግሎት የሚያገኙት ከጠቅላላው ሕዝብ ውስጥ አሥር በመቶ ብቻ መሆናቸውንም ያክላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...