Monday, December 11, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ኢንሹራንስ በ2015 በጀት ዓመት 836 ሚሊዮን ብር የጉዳት ካሳ መክፈሉን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል ትልቁን የገበያ ድርሻ የያዘው አዋሽ ኢንሹራንስ አ.ማ., በተጠናቀቀው የ2015 ሒሳብ ዓመት 836 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ወጪ ፈጽሞ የተጣራ 5ዐ9 ሚሊዮን ብር አተረፈ።

አዋሽ ኢንሹራንስ ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ እንዳስታወቀው፣ በሒሳብ ዓመቱ የተጣራ 509.1 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል፡፡ ይህ የትርፍ ምጣኔ በኢንዱትሪው ውስጥ ከግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በከፍተኛነቱ የሚጠቀስ ትርፍ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ኩባንያው ያስመዘገበው የትርፍ መጠን ከቀዳሚው ዓመት የ52.5 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን የአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ገመዳ ለጠቅላላ ጉባዔው ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡ 

በሒሳብ ዓመቱ የተገኘው ትርፍ ኩባንያው ከፍተኛ የሚባል የጉዳት ካሳ ክፍያ ወጪ ባወጣበት ዓመት የተመዘገበ በመሆኑ ስኬትን ብቻ ሳይሆን የኩባንያውን ጥንካሬ ጭምር የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከፍተኛ የጉዳት ካሳ ወጪ ባያጋጥም ኖሮ የዓመቱ ትርፍ ከተጠቀሰው የላቀ ይሆን እንደነበር ገልጸዋል።

‹‹በበጀት ዓመቱ የተገኘው የተጣራ ትርፍ አስደሳች መሆኑ የማያጠያይቅ ቢሆንም፣ ይህ ትርፍ በዓመቱ ያጋጠሙንን እጅግ ከፍተኛ የካሳ ክፍዎችን ኩባንያችን በውሉ መሠረት በብቃት አስተናግዶ የተገኘ ውጤት መሆኑንም ሳንገልጽ አናልፍም፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ 

ኩባንያው በአንድ ፋብሪካ ቃጠሎ ሳቢያ ብቻ በሒሳብ ዓመቱ የ105 ሚሊዮን ብር የካሳ ጥያቄ ክፍያ አጋጥሞታል። በአጠቃላይ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ 836 ሚሊዮን ብር ካሳ መክፈሉ ታውቋል፡፡    

የአዋሽ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሒሳብ ዓመቱ የተገኘው ትርፍ የኩባንያው ባለአክሲዮኖችን የትርፍ ክፍፍል ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጓል፡፡ በዚህም መሠረት የኩባንያው ባለአክሲዮኖች በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በአንድ አክሲዮን የሚያገኙት የትርፍ ድርሻ 36 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኩባንያው ዓመታዊ አፈጻጸም ውጤታማ እንደነበር እንደማሳያ የተመለከተው፣ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ በዓረቦን ገቢው ከኢንዱስትሪው አማካይ የዓረቦን ዕድገት በላይ አዋሽ ኢንሹራንስ የዓረቦን ገቢውን ማሳደጉ ነው፡፡ የቦርድ ሰብሳቢው ገለጻ፣ በሁለቱም የኢንሹራንስ ዘርፍ የሁሉም የኢንሹንስ ኩባንያዎች ዓመታዊው የዓረቦን ገቢ 22.9 ቢሊዮን ብር ሲሆን, ይህም ከ2014 የሒሳብ ዓመት የ37.5 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በ2015 የሒሳብ ዓመት በጠቅላላ ኢንሹራንስ (ነን ላይፍ) የሥራ ዘርፍ እጅግ አመርቂ የሆነ የ40 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ የ21.46 ቢሊዮን ብር ጥቅል ገቢ ማግኘቱን፣ ይህም ገቢ ከቀዳሚው ዓመት የ19 በመቶ ዕድገት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

አዋሽ ኢንሹራንስ ግን በበኩሉ በጄኔራል ኢንሹራንስ (ነን ላይፍ) የ65.6 በመቶ በሕይወት ኢንሹራንስ ደግሞ 42.7 በመቶ ዕድገት በማሳካት በሁለቱም የሥራ ዘርፎች ከኢንዱስትሪው ላቅ ያለ የዕድገት ምጣኔ ሊያስመዘግብ መቻሉ ከፍተኛ ውጤት  ማስመዝገቡን ያሳያል በማለት ተናግረዋል፡፡   

በሕይወት ኢንሹራንስ (ላይፍ) የሥራ ዘርፍ ግን የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ የተመዘገበው ውጤት በጣም አነስተኛ የነበረ ያሉት የቦርድ ዳይሬክተሩ፣ በበጀት ዓመቱ የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ 7.9 በመቶ ዕድገት ብቻ ያስመዘገበ መሆኑንና ይህም ከቀደመው ዓመት የ28 ከመቶ ዕድገት ጋር ሲነፃፀር በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ጉልህ የሆነ የዕድገት ምጣኔ ማሽቆልቆል ታይቷል ብለዋል፡፡ በ2015 ዓ.ም. በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ በኢንዱስትሪ ደረጃ 1.46 ቢሊዮን ብር የተሰበሰበት ነበር፡፡ 

አዋሽ ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ ታካፉልን ጨምሮ በሁሉም የሥራ ዘርፎች፣ ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን 2.44 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በጄኔራል ኢንሹራንስ ብቻ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በማግኘት መቻሉ ተጠቅሷል፡፡ ይህም ከግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የገበያ መሪነቱን ሥፍራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ማስቻሉን የገለጹት አቶ ታደሰ፣ ከሕይወት ኢንሹራንስ ደግሞ የ325.6 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ ከኢንዱስትሪ የገበያ መሪነቱን ቦታ በሰፊ ልዩነት ለመያዝ መቻሉንም አክለዋል፡፡  

እንደ ኩባንያው የቦርድ ዳይሬክተር ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ ዘርፍ (በታካፉል) ከ21 በላይ ቅርንጫፎቻችንን ወደ ሥራ በማስገባት ወደ 40 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ በመዋጮ መልክ ለማሰባሰብ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡ ኩባንያው በተካፉል ዘርፍ የገበያ መሪነትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመያዝ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

ኩባንያው እያስመዘገበ ላለው ውጤት በተለይ ኩባንያው የቀረፀው የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ በአግባቡ ከመተግበር ጋር ተያያዘ መሆኑን የገለጹት የአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጉዲሳ ለገሠ፣ በቀጣይም በዚሁ መሪ ዕቅድ ላይ በመንተራስ የተሻለ ውጤት ይመዘገባል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡ 

በሁሉም አፈጻጸሞች በገበያው ውስጥ ከግል የኢንሹራስ ዘርፍ ብልጫ ለመያዝ ያበቁ ናቸው ብለው ከጠቀሷቸው ውስጥ፣ የኩባንያው ካፒታል ሊያድግ መቻሉ ነው፡፡ የካፒታል ዕድገት ኩባንያው አዋጪ በሚላቸው የኢንቨስትመት መስኮች ተጨማሪ ኢንቨስት በማድረግ የኩባንያው ገቢ የበለጠ እንዲጨምር ማድረግ ችሏል ብለዋል፡፡ 

የተሽከርካሪዎች ኢንሹራንስ (ሞተር) የሥራ ክፍል ዘንድሮም እንደ ሁል ጊዜው ከአጠቃላይ የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ የ58 በመቶ የገቢ ድርሻ ይዞ ዓመቱን አጠናቋል፡፡ የዚህ ንዑስ ክፍል ዕድገት በዓመቱ ውስጥ 80 በመቶ ያህል ነበር፡፡ የተሽከርካሪ የሥራ ክፍል ለአደጋ ካለው ተጋላጭነት አኳያ በመሪ ዕቅዱ በተመለከተው መሠረት ተገቢውን ቁጥጥር ለማድረግ እየተሠራ ይገኛልም ተብሏል፡፡

የኩባንያው የቦርድ ዳይሬክተር ባቀረቡት ሪፖርት ከተጠቀሷቸው እክሎች መካከል የፋይናንስ ተቋማት ገቢዎች ሚኒስቴር በአጠቃላይ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ተግባራዊ መሆን አለበት ያለው የትርፍ ክፍፍል ግብር ይገኝበታል።

‹‹የገቢዎች ሚኒስቴር በትርፍ ክፍፍል ላይ የ10 በመቶ ታክስ እንድንከፍል መታዘዛችን አዲስ ክስተት በመሆኑ ልናሳውቃችሁ የግድ ይለናል፤›› ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው፣ በተፈረመ አክሲዮን ግዥ ላይ የዋለ የትርፍ ድርሻ በሕጉ መሠረት ታክስ የማይደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ግን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለአክሲዮን ግዥ በዋለ የትርፍ ድርሻ ላይ 10 በመቶ ታክስ ከእነ ወለዱና ቅጣቱ እንዲከፈል ባቀረበው ጥያቄ ላይ ኩባንያው ለግብር ይግባኝ ሰሚ ኮሚሽን አቤቱታ አቅርቦ ውሳኔውን እየተጠባበቀ መሆኑን ለጠቅላላ ጉባዔ አሳውቀዋል፡፡ ባለ አክሲዮኖች በጉዳዩ ላይ የመፍትሔ ሐሳቦችን የሚያቀርቡ ከሆነ ይህንን በማያያዝ ጉዳዩን እንደሚከታተሉ የቦርድ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡  

ኩባንያው እያካሄደ ያለውን ኢንቨስትመንት በተመለከተ ከቀረበው ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለው ደግሞ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ያደረገው ኢንቨስት 3.13 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በተጨማሪም በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ የ 240.17 ሚሊዮን ብር

አክሲዮን ግዥ መፈጸሙ ተጠቅሷል፡፡  ከዓመታዊ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው ኩባንያው ከተሰማራበት 239.4 ሚሊዮን ብር የትርፍ ድርሻ ገቢ አግኝቷል፡፡ 

አዋሽ ኢንሹራንስ አጠቃላይ የቅርንጫፎቻችንና የአገናኝ ቢሮዎቻችን ቁጥር በዓመቱ መጨረሻ 66 ያደረሰ ሲሆን፣  አጠቃላይ መደበኛ ሠራተኞቹ ብዛት 717 ደርሷል፡፡ 

አዋሽ ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የተከፈለ ካፒታሉን ወደ 1.41 ቢሊዮን ብር አሳድጓል፡፡ ኩባንያው የካፒታል መጠኑን ወደ አራት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ቀደም ሲል መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንኑ ካፒታል ለማሟላት እየሠራ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ አጠቃላይ የሀብት መጠኑም 5.71 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች