Sunday, December 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሐሰተኛ የግዥ ሰነድና በኮንትሮባንድ የሚገባ የግንባታ ብረት የአገር ውስጥ አምራቾችን እያንኮታከተ ነው ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • መንግሥት በቢሊዮኖች ገቢ እያጣ እርምጃ ባለመውሰዱ ተወቅሷል

የግዥ ወጪን በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ የተዘጋጀ ሐሰተኛ የግዥ ሰነድ በማቅረብ (under invoice) የአርማታ ብረትን ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የማስገባት ሒደት በመንሰራፋቱ የአገር ውስጥ አምራቾችን እያንኮታኮተና ለኪሳራ እየዳረገ ነው የሚል አቤቱታ ቀረበ።

አቤቱታውን ያቀረቡት የአገር ውስጥ ብረት አምራች ኢንዱስትሪዎችና አጠቃላይ የአገር ውስጥ ብረት ኢንዱስትሪን የሚወክለው የአገር ውስጥ ብረት አምራቾች መሠረታዊ ማኅበር ናቸው።

በተለይም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ሐሰተኛ የግዥ ሰነድ በማቅረብ ከፍተኛ መጠን ያለው የአርማታ ብረት በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር መግባቱ እንዳስደነገጣቸው ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የአገር ውስጥ የብረት አምራቾች ገልጸዋል።

አቤቱታውን ያቀረቡት የአገር ውስጥ የግንባታ ብረት (የአርማታ ብረት) አምራቾች ማኅበር ሲሆን፣ በተለይ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ሐሰተኛ የግዥ ሰነድ በማቅረብ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ የተደረገ የግንባታ ብረት መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ገበያውን በመቆጣጠር የአገር ውስጥ አምራቾችን ህልውና አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል በመሆኑ መደንገጣቸውን ገልጸዋል። 

ያነጋገርናቸው የአገር ውስጥ አምራቾች እንደሚሉት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ሐሰተኛ የግዥ ሰነድ በማቅረብ 300,000 ቶን የአርማታ ብረት ወደ አገር ውስጥ ገብቷል። ይህንንም የሚገልጽ ማስረጃ እንዳላቸው የሚጠቅሱት አምራቾቹ፣ በአሁኑ ወቅት አንድ ቶን የአርማታ ብረት በዓለም አቀፍ ገበያ የሚሸጥበት አማካይ ዋጋ 560 ዶላር መሆኑን ይህም የማጓጓዣና የኢንሹራንስ ወጪዎችን እንደማይጨምር ያስረዳሉ።

በቅርቡ ወደ አገር የገባው 300,000 ቶን የአርማታ ብረትን ከውጭ ለመግዛትና ለማጓጓዝ 261 ሺሕ ዶላር ወይም 14 ሚሊዮን ብር ብቻ ወጪ መደረጉን የሚገልጽ ሐሰተኛ ዴክላራሲዮን ለጉምሩክ ኮሚሽን ቀርቦ በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ውስጥ እንደገባ አምራቾቹ ገልጸዋል። ሪፖርተር የተመለከተው የሰነድ ማስረጃም ይህንኑ አምራቾቹ ያቀረቡትን አቤቱታ የሚያስረዳ ነው። 

ወደ አገር የገባው ይህ 300,000 ቶን የአርማታ ብረት የተመረተው በቱርክ አገር ሲሆን በአሁኑ ወቅት በቱርክ ያለው የአርማታ ብረት አማካይ ዋጋ በቶን 560 ዶላር መሆኑን የአገሪቱ ስታትስቲክስ ተቋም ወቅታዊ መረጃ ያስረዳል። በዚህ ዋጋ መሠረት በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል የተባለው የአርማታ ብረት አጠቃላይ ዋጋ (የማጓጓዣ ወጪን ሳይጨምር) 168 ሚሊዮን ዶላር ወይም 9.3 ቢሊዮን ብር ይሆናል። በመሆኑም መንግሥት ከተጠቀሰው የአርማታ ብረት በቢሊዮኖች የሚገመት ገቢ ከግብር መሰብሰብ ያስችለው ነበር። ነገር ግን በቀረበው ሐሰተኛ የግዥ ሰነድ ምክንያት መንግሥት ያገኘው ገቢ 11 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደሆነ ቅሬታውን ያቀረቡት አምራቾች ሰነዶችን ዋቢ አድርገው አስረድተዋል። 

መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ግብር ፈቅዶ ሊተው ይችላል ያሉት እነዚሁ አምራቾች፣ ነገሩ ግን በፈቃድ የተተወ ካለመሆኑ ባሻገር የአገር ውሰጥ አምራቾችን በከፍተኛ ደረጃ እያዳካመ የሚገኝ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል።

‹‹ምርቱ በሐሰተኛ የግዥ ሰነድ (ጉምሩክ ሰነድ) በስፋት እየገባ መሆኑ ኮንትሮባንድ ሕጋዊ ሆነ ወይ ያስብላል›› ሲሉም ቅሬታቸውን በጥያቄ መልክ አቅርበዋል።

ሪፖርተር ከፍተኛ መጠን ያለው የአርማታ ብረት በሐሰተኛ የግዥ ሰነድ ወደ አገር ውስጥ እየገባ መሆኑን በመጥቀስ ምላሽ እንዲሰጡ የጠየቃቸው የጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አዘዘው ጫኔ፣ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ገልጸው አጭር የጽሑፍ ምላሽ በስልክ ሰጥተዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ በሰጡት ምላሽም፣ ለጉምሩክ የሚቀርብ የግዥ ሰነድ ላይ የተቀመጠው የግብይት ዋጋ አነስተኛ ከሆነ ኮሚሽኑ ሰነዱን ውድቅ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

‹‹ጉምሩክ የሚመለከተው ነገር ቢኖር የቀረበው የግብይት ዋጋ አነስተኛ ከሆነ ይህን ዋጋ ውድቅ በማድረግ ኮሚሽኑ በየጊዜው በሚያደራጀው ወቅታዊ የገበያ ዋጋ ላይ በመመሥረት በሕግ የተቀመጠውን ቀረጥና ታክስ ይሰበስባል፤›› ብለዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ፣ የአርማታ ብረትን በሐሰተኛ የግዥ ሰነድ ማስገባት አንደኛው ገጽታ እንደሆነ ገልጸዋል።

ችግሩ መልከ ብዙ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፣ በሐሰተኛ የግዥ ሰነድ (under invoice) ከሚገባው በተጨማሪ በኮንትሮባንድ እንዲሁም ለአንድ ጊዜ ብቻ የተፈቀደ የቀረጥ ነፃ መብትን በመጠቀም በተደጋጋሚና ለረዥም ጊዜ የሚገባው የአርማታ ብረት መጠን ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

የአርማታ ብረት ብቻ ሳይሆን ቆርቆሮን ጨምሮ ለግንበታ የሚውሉ ሌሎች የብረት ምርቶችም ከላይ በተጠቀሱት ሕገወጥ መንገዶች ወደ አገር እየገቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የአርማታ ብረትና ሌሎች የግንባታ ብረቶችን ከውጭ ለሚያስገቡ አካላት የሚጠቀሙበትን የውጭ ምንዛሪ ለአገር ውስጥ አምራቾች ማቅረብ ቢቻል የምርቶቹን የአገር ውስጥ ፍላጎት በአገር ውስጥ አምራቾች መሸፈን እንደሚቻልም አስረድተዋል። 

በዚህ አሳሳቢ ጉዳይ ላይ ለመወያየትም የማኅበሩ አባላት በመጪው ዓርብ፣ ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ለአስቸኳይ ስብሰባ መጠራታቸውን ገልጸዋል።

የአገር ውስጥ አምራቾች በዘርፉ መዋዕለ ነዋያቸውን ያፈሰሱትና ማስፋፊያ ያደረጉት እንዲሁም ሰፊ የሥራ ዕድል ለኢትዮጵያውያን መፍጠር የቻሉት ከባንክ ተበድረው በመሆኑ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንጂ ጉዳታቸውን እያስተዋለ በዝምታ ማለፍ የለበትም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ76 በላይ የአገር ውስጥ አምራቾች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፣ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች በዓመት አሥር ሚሊዮን ቶን የማምረት አቅም የፈጠሩ ሲሆን፣ ከ50 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያን የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም ገልጸዋል። 

አብዛኛው የአርማታ ብረት ከቱርክ አገር ተገዝቶ በሕገወጥ መንገድ የሚገባ ቢሆንም፣ ከህንድና ቻይና የሚገባው የምርት መጠንም አነስተኛ የሚባል እንዳልሆነ አቶ ሰለሞን ጠቁመዋል። 

ቱርክ በ2015 ዓ.ም. ከጥር እስከ ሐምሌ ባለው ጊዜ ውስጥ (በሰባት ወራት ብቻ) 1.73 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የአርማታ ብረት ኤክስፖርት ያደረገች ሲሆን በዚህም በድምሩ 1.15 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ሪፖርተር የተመለከተው የአገሪቱ ስታትስቲክስ ተቋም መረጃ ይጠቁማል። በተጠቀሱት ሰባት ወራት ውስጥ የቱርክ የአርማታ ብረት ኤክስፖርት መዳረሻ ከሆኑት አሥር አገሮች መካከል ኢትዮጵያ በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በተጨማሪም፣ በተጠቀሱት ሰባት ወራት ወደ ኢትዮጵያ የተላከው የአርማታ ብረት መጠን 145,671 ቶን ሲሆን ይህ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ ከገባው 50,048 ቶን ጋር ሲነፃጸር የ191 በመቶ ብልጫ እንዳለው የአገሪቱ ስታትስቲክስ ተቋም መረጃ ያመለክታል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች