Sunday, July 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከምድር ወደ ባህር!

ከሳሪስ ወደ ስታዲዮም ልንጓዝ ነው። ከረጅም ጥበቃ በኋላ የተገኘ ዶልፊን ሚኒባስ ተጨናንቀን ተሳፍረናል፡፡ ‹‹ምነው እባክህ ባህር እንደሚያሻግር ሕገወጥ ደላላ የምትጠቀጥቀን? ሰው እኮ ነን…›› ትላለች ፊቷን ወደ ተሳፋሪዎች አዙራ ሞተር ላይ የተሰየመች የዋህ ቢጤ። ወያላው የወየበ ጥርሱን በከፊል ገለጥ እያደረገ፣ ‹‹ሰላማዊ የባህር በር ጥያቄያችንን ከምኔው ወደ ስደተኝነት ቀይረሽ ታሳጪኛለሽ››። ይላታል እያሾፈ። ‹‹ከሳሪስ ስታዲየም ስደት መሄድ እንዳልሆነማ አውቃለሁ፣ ግን አንተ ምኑን አውቀህ ነው ፖለቲካው ውስጥ ዘው ብለህ የገባኸው…›› ስትለው፣ ‹‹አንዳንድ የአዲስ አበባን ነዋሪዎችን ከእነ ስሜታቸው ቀጥ አድርገን የያዝን እኛ ነን እኮ…›› ብሎ ሾፌሩን ሳበው አለ። ሾፌሩ በማሾፍ ስሜት ውስጥ ሆኖ፣ ‹‹እሷን ከምትነዘንዛት ለምን ሬዲዮ ላይ አታነበንብም? እኔስ አሁን የሰለቸኝ ያንተ አጉል መንጠራራት ነው…›› ይለዋል። ‹‹አጉል መንጠራራት? አገር ዘራፊ ሌባ በነፃነት ዘመናዊ መኪና በሚለዋውጥባት አገር ውስጥ ምስኪን የታክሲ ተሳፋሪዎችን አግባብቼና አጠጋግቼ በጫንኩ፣ ያለ ስሜ ስም ተሰጥቶኝ የሰው አዘዋዋሪ ደላላ ስባል ዝም ልበል ታዲያ?›› ብሎ ሲስቅ፣ አሳሳቁ በየዋሆች ላይ እየቀለዱ እንጀራቸውን እንደሚያበስሉ የዘመኑ አክቲቪስት ተብዬዎችን ይመስል ነበር፡፡ ወይ መመሳሰል!

ጉዟችን ተጀምሯል። ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመ ወጣት በተደጋጋሚ በረዥሙ እየተነፈሰ አጠገቡ ያሉትን ተሳፋሪዎች ሰላም ነሳ። ‹‹ጎበዝ በምግብ ዋስትና ራሷን ችላለች በምትባለው አገራችን የምግብ እጥረት የሚያሰቃየን ሳያንስ፣ ዓይናችን እያየ ሳያልፍልን በከንቱ ልንቀር ነው እንዴ?›› ብሎ አጠገቡ የተሰየመውን ጎልማሳ ሆን ብሎ ሊያናግረው ቢሞክርም፣ ወጣቱ አንገቱን እንዳቀረቀረ ተራ በተራ እያማተርን አየነው። ደብተር የምታህል ታብሌቱ ላይ ፈተና እንደ ደረሰበት ተማሪ በተጨነቀ ስሜት ተወጥሮ አፍጧል። ‹‹ኧረ ምን ጉድ ሰምተህ ነው?›› አለው ጎልማሳው ድምፁን ከፍ አድርጎ። ‹‹በትንፋሽ ሱናሚ ልትጨርሰን እኮ ነው…›› ሲለው ወጣቱ፣ ‹‹ምን እባክህ ሳይሉኝ የማይሆን ኢምፓየር እገነባለሁ ብዬ ፍዳዬን አየሁ እኮ…›› አለው። ‹‹ጉድ ፈላ የምን ኢምፓየር?›› አለ ጎልማሳው በርግጎ። ዘንድሮ አስበርጋጊው በዝቶ በርግገን አለቅን እኮ!

መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ ሁለት ዩኒፎርም የለበሱ ሴት ተማሪዎች ደግሞ፣ ‹‹አንቺ ኢምፓየር ፊልምን አስታወሽው? ኦ ማይ ጋድ በእሱ ሙቪ…›› ብለው ጣቢያ ደባለቁ። ‹‹ቆይ እስኪ ልጆች? አንዴ እዚህ እንጨርስና ወደ እናንተ እንመጣለን። እዚህ ሰው በህቡዕ ኢምፓየር ሊመሠርትና ሲያደራጅ እየሰማችሁ እናንተ ስለፊልም ታወራላችሁ?›› ጎልማሳው ቀልባቸውን ገፈፈው። ተማሪዎቹ ግን ደንግጠው ዝም አላሉም። ‹‹ሲሪየስሊ?›› ብላ አንደኛውን ጎልማሳውን በግልምጫ ጠረባ አጣጣለችና ከጓደኛዋ ጋር ወሬያቸውን ቀጠሉ። ጎልማሳውም በረጅሙ እየተነፈሰ ያስጨነቀው ወጣት ‘ኢምፓየር’ መሥራች ጉዳይ ቀልቡን አሸፍቶበት ወደ እሱ ዞረ። ‹‹አይ የዘንድሮ ልጆች አየሃቸው? ሌላ ዝባዝንኬ ሳይናገሩ ዘግተውን ጉዳያቸውን ሲቀጥሉ አየህልኝ? እኛ የመናገር መብት አለ እንልና ስንናገር ስድብ፣ ስንናገር ጥላቻ፣ ስንናገር ዛቻ…›› ብላ ከጎኔ የተሰየመች ዘመናይ የቤት እመቤት ሹክ ትለኛለች። ‘በኢግኖራስና በብሎክ’ ከታጀበ ፖስት የንግግር ነፃነት ተግባራዊነትን አዳንቀን ካወራን እንግዲህ ምን ቀረን ይባል ይሆን? ወይ ታክሲና ተሳፋሪ!

ጉዟችን ቀጥሏል። ከጎልማሳው አጠገብ የተቀመጠው ወጣት አላስቀምጥ ሲለው፣ ‹‹ነገርዬው አገር የማስተዳደር ጌም ነው፣ ግን እንደምታስበው ቀላል አይደለም፣ ተለክፌያለሁ…›› አለው። ‹‹የማንን አገር ነው የምታስተዳድረው?›› ሰቅዞ ይዞታል። ‹‹የራስህን መሬት ይዘህ ሕዝብ እያሠፈርክ፣ ሕዝቡ በየጊዜው እንደ ደረጃው የሚፈልገውን እያሟላህ ያለ አመፅ ማስተዳደር አለብህ። አሁን እኔ ይኼውልህ እዚህ ጋ የሕዝቦቼን የምግብ ፍላጎት ማሟላት ስላልቻልኩ እያመፁ ነው…›› እያለ ከአንጀቱ ሲያብራራ፣ አንዱ በጥቅሻ ሌላው በከንፈሩ እያሽሟጠጠ እንደ ተረት አባት ያዳምጡታል። ጎልማሳው፣ ‹‹ጎሽ ታዲያ መጀመሪያውንም እንደዚያ ብትለን ኖሮ ሌላው ቢቀር በትንፋሽ እናግዝህ ነበር። ግን እኔ ምልህ? የምትመራቸው የአንተ አገር ሰዎች እንዲህ እንደኛ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሲያነሱ እንዴት ነው የምትመልሰው?›› ሲለው ጋቢና የተሰየመ ተሳፋሪ ይኼን ሰምቶ በሳቅ እያሽካካ፣ ‹‹አዳሜ የቆመበትን ርስት የራሱ ማድረግ ሲያቅተው፣ በቁም ቅዠት የራሱን ምናባዊ አገር መፍጠር ጀመረላችሁ። ዕድሜ ለቴክኖሎጂ…›› እያለ አጅቡኝ ይላል። ጊዜው የአጀብ ስለሆነ እናጅበው እንጂ ሌላ ምን እናድርግ ታዲያ!

መነጋገሪያ የሆነው ወጣት ግራና ቀኝ የሚባለውን አያዳምጥም። የያዘው ጨዋታ ልቡን አጥፍቶት ስምጥ ብሎ ለጎልማሳው ያብራራል። ‹‹ይኼውልህ እዚህ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር፣ ግጭት፣ ዕገታ፣ ግድያ፣ ውድመትና ዘረፋ የሚባሉ የቃላት ጨዋታዎች የሉም። ያለው የሕዝብ ፍላጎት ነው። የሕዝብን ፍላጎት ማሟላት ትችላለህ? ከቻልክ ጨዋታው ይቀጥላል። ካልቻልክ የሠራኸው ሁሉ ይፈርሳል…›› ይላል። ጎልማሳው ደግሞ ሳያስበው ቀልቡ መሸፈት ጀምሯል። ‹‹ይኼውልህ ይህን ሁሉ ለመሥራት ሁለት ወራት ፈጅቶብኛል…›› ሲለው ጎልማሳው በርግጎ፣ ‹‹ዳያስፖራ ነኝ በለኛ…›› ብሎ ተሳፋሪዎችን ፈገግ አደረጋቸው፡፡ በገሃድና በተምኔት መሀል ያለችው ቀጭን መስመር ገና ብዙ የምታስተዛዝበን ይመስላል። በዘውድ ሆነ በጎፈር መጫወቱ የማይታወቅ በዚህ የሕይወት ጎዳና ከትዝብት አያመልጥም፡፡ ለነገሩ ማን ትዝብት ፈርቶ!

ወያላችን ሒሳብ ተቀብሎን እንዳበቃ ጎልማሳው በስሜት ስለሆሊውድ ፊልም የሚጫወቱት ታዳጊዎች ዘንድ ዞሮ፣ ‹‹አንድ ጥያቄ አለኝ…›› አላቸው። ‹‹ዋት?›› አለችው አንደኛዋ። ‹‹የአንጎላ ዋና ከተማ ማን ትባላለች?›› ሲል ሁለቱም ከት ብለው ሳቁበት። ‹‹እንዲህ ካሳቅኩማ እንግዲህ ኮሜዲያን ልሁን…›› ሲላቸው አንደኛዋ ቀበል አድርጋ፣ ‹‹ከዚያ እንደ ምንም አሜሪካ ገብተህ ‘አሳይለም’ ለመጠየቅ?›› ብላ ሽቅብ ስትመልስለት፣ ‹‹ከልጅ ጋር አትጫወት ይወጋሃል በእንጨት አሁን መጣ…›› ብሎ ዝም አለ። ‹‹የምን እንጨት ነው? ሀቅ መሰለኝ። የጠየቅከን በምን ‘ሞቲቭ’ እንደሆነ ገብቶናል። ፊልሙና ሙዚቃው ላይ እንደምትንቀለቀሉት መጀመርያ የአካባቢያችሁን፣ ከዚያ የአኅጉራችሁን ጂኦግራፊ አጥኑ ልትለን ነው። አገሬ… አገሬ… እያሉ መጨረሻው አሜሪካ መግባት ነው። ያ መሰለኝ የዘመኑ ትምህርት። ለዚያ ደግሞ አሜሪካና ባህሏን እያጠናን ነው…›› ስትለው አንደኛዋ ጎልማሳው ኩምሽሽ አለ። በስንቱ ኩምሽሽ እንበል!

ይኼኔ አጠገባቸው የተሰየመ ተሳፋሪ፣ ‹‹ወይኔ በደጉ ጊዜ አርቲስት መሆን ስችል እንቢ ብዬ፣ ዛሬ ማንም ከኋላዬ ተነስቶ ላዬ ላይ ድራማ ሲሠራ እያየሁ ፈዝዤ ልቅር?›› ይላል። ‹‹ምን ያስፈዝዝሃል? አሁንም ቢሆን አልመሸም…›› ይለዋል ከወይዘሮዋ ጎን የተቀመጠ። ‹‹ከዚህ በላይ እንዴት ይምሽብን? እኛ ለአገር የሚጠቅሙ ሐሳቦችን ስናነሳ ከሽሙጥና ከሐሜት የዘለለ አስተያየት አይቀርብም፡፡ ይኸው የቀይ ባህር በር ጉዳይ ሲነሳ ከአሉባልታ ጋር የተጋመደ ልግጫ ነው የሚሰማው፡፡ የእኛ ሰው እንዴት፣ ለምን፣ መቼ፣ የት እያለ ከመከራከር ይልቅ በቧልተኞች ተከቦ በራሱ ላይ ይቀልዳል…›› እያለ ይበሳጫል አንዱ። ‹‹ወይ ሰፊው ሕዝብ፣ ከምንም ነገር በላይ የሰፊው ሕዝብ አካል በመሆኔ እኮራለሁ…›› ስትል ደግሞ እመቤቲቱ ከአጠገቤ፣ ‹‹ምን ዋጋ አለው ብለሽ ነው? የተረፈን በእኛ ስም በውጭና በውስጥ የጥቂቶችን ምቾት ማሳመር ነው…›› አላት ጎልማሳው። አገር ተረስቶ ለስደት የሚጣደፈው ከመቼው በዛ እናንተ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። የጥንት ዘናጭ የነበረችው ስታዲየም አሁንም አምሮባት ስንቃረባት ለጉድ የጎለተው አሮጌ ኳስ መጫወቻዋ ግን ጭር ብሏል። ‹‹አቤት ይኼ ዘመን ስንቱን አሳየን?›› ይላል ጎልማሳው። ‹‹ማየት ምን ዋጋ አለው ካላስተማረ? ልብ ካላስገዛ? ሁሌም ፌዝ፣ ሁሌም ዳንኪራ፣ ሁሌም ዋዛ የራስ አይሆን…›› እመቤቲቱ ቦርሳዋን እያስተካከለች አስተያየት ሰጠች። ‹‹እስኪ አስቡት በዚህ በሠለጠነ ዘመን፣ ሳይንስ ለሁሉም ነገር በተጨባጭና በተሞክሮ ማስረጃ ማቅረብ በሚችልበት ዘመን ጉም እየዘገንን ስንጠላለፍ አያሳዝንም?›› ጎልማሳው ጨርቁን መጣል ቀርቶታል። ‹‹ማንን ሰምቶ፣ ማንን አምኖ፣ ማንን ተቀብሎ፣ ማንን ጥሎ መጓዝ እንዳለበት የተወናበደበት ማኅበረሰብ ጭንቀት አምጦ ጭንቀት ሲተነፍስ ይውላል። ሁሉም ተነስቶ ያሻውን ሲወሸክት ይህን የምትለው አንተ ማን ነህ? ከወዴትስ ነህ? መሠረትህስ የት ነው? የሚል ጠፍቷል…›› የሚሉት አንዲት እናት ናቸው፡፡ ‹‹እናታችን ምድሪቱን እየከበድናት መሰለኝ…›› ሲላቸው ያ ጎልማሳ በመከፋት ስሜት ውስጥ ሆኖ፣ ‹‹አይዞህ ምድር ሁላችንንም በየተራ መሸኘት ትችልበታለች፣ ይልቁንስ እንዳናሰለቻት ወደ ባህሩ ጠጋ ብንል ነው የማይከፋው…›› ብለው ሳቅ ሲሉ ሁላችንም በሳቅ አጀብናቸው፡፡ ወያላው ‹‹መጨረሻ…›› ብሎ ባያሰናብተን ኖሮ ወጉ በሰፊው ይቀጥል ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት