Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ለአዕምሮ ሕሙማን አስተማማኝ የመድኃኒት አቅርቦት እንዲኖር እንፈልጋለን››

ወ/ሮ እሌኒ ምሥጋናው ተወልደው ያደጉትና የመጀመርያና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአዲስ አበባ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመርያ፣ በሶሲዮሎጂ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በሥራ ዓለምም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም በተለያዩ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ባለትዳርና የአንድ ልጅ እናት የሆኑት ወ/ሮ እሌኒን በማኅበሩ እንቅስቃሴና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ መቼና እንዴት ተቋቋመ? የአባላቱስ ብዛት ምን ያህል ነው?

ወ/ሮ እሌኒ፡- ማኅበሩ የተቋቋመው ኅዳር 2011 ዓ.ም. ነው፡፡ የተቋቋመውም የአዕምሮ ጤና ሕመም አጋጥሟቸው ሕክምና እየተከታተሉና ከሕመሙ እያገገሙ ባሉ አምስት መሥራቾች ነው፡፡ አንድ ሰው ወደ ማኅበራችን ሲመጣም በጣም ደስ ብሎን እንቀበላለን፡፡ ምክንያቱም ያለውን አሉታዊ አመለካከት ወይም የሚደርስበትን መገለል ጥሶ ስለሚመጣ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ 50 የሚጠጉ አባላትን ማኅበሩ አቅፏል፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበሩን ዓላማ ሊገልጹልን ይችላሉ?

ወ/ሮ እሌኒ፡- የማኅበሩ ዓላማ በዋነኛነት የአዕምሮ ጤና ሕመም ከሌላው አካላዊ ሕመም በተለየ ትኩረት እንዲሰጠው ነው፡፡ የማኅበሩ አባላት እርስ በርሳቸው መደጋገፊያ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎችን ማከናወን ሌላው ዓላማ ነው፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች የሚከናወኑት በኅብረተሰቡ ውስጥና በአባላት መካከል ነው፡፡ ይህ በኅብረተሰቡ ውስጥም ሆኑ በአባላቱ መካከል ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ የሚንፀባረቀውን የተሳሳተ አመለካከትና እምነት ለማስወገድ የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ጉዳዩ በዋናነት ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላትና ከሌሎች አጋሮቻችን ጋር በትብብርና በቅንጅት በመንቀሳቀስ ላይ ነን፡፡ የአድቮኬሲ  (ጉትጎታ) ሥራም እናከናውናለን፡፡  

ሪፖርተር፡- በአገር ውስጥና በውጭ አገር ካሉት ተመሳሳይ ተቋማት ጋር የፈጠራችሁት ግንኙነት አለ?

ወ/ሮ እሌኒ፡- አዎ፡፡ የሰመረ ግንኙነት ፈጥረናል፡፡ በዚህም የተነሳ  ዋና መሥሪያ ቤቱ እንግሊዝ ከሚገኘው ግሎባል ሜንታል ሔልዝ አክሽን ኔትዎርክ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ የሚገኘውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተቋቋመው ግሎባል ሜንታል ሔልዝ ፒር ኔትዎርክ አባል ነን፡፡ ከእነዚህም መካከል ግሎባል ሜንታል ሔልዝ አክሽን ኔትዎርክ በአድቮኬሲ (ጉትጉታ) ሥራ ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፣ በአዕምሮ ጤና ዙሪያ ለመንቀሳቀስና ለመሥራት ፍላጎት ያላቸው ድርጅቶችና ግለሰቦችን በአባልነት ያቅፋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ 3,000 አባላትን አቅፏል፡፡ ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው ግሎባል ሜንታል ሔልዝ ፒር ኔትዎርክ ደግሞ የአዕምሮ ጤና እክል ያለባቸውን ሰዎች በአባልነት ያቀፈ ሲሆን፣ እስካሁንም 175 የሚጠጉ አባላት አሉት፡፡  

ሪፖርተር፡- በመድኃኒት አቅርቦት ዙሪያ ያጋጠመ ችግር ይኖር ይሆን?

ወ/ሮ እሌኒ፡- በተለይ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጊዜም ለአዕምሯዊ ጤና አገልግሎት የሚውለው ሊቲየም የተባለ መድኃኒት እጥረት ተፈጥሮ ነበር፡፡ የአዕምሮ ሕክምና መድኃኒቶች በበቂ ሁኔታ ወደ አገር ውስጥ እየገቡ አልነበረም፡፡ በዚህም የተነሳ የችግሩን አሳሳቢነት ለጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በጽሐፍ አሳወቅን፡፡ በዚህም ክትትል ማድረጉን ተያያዝነው፡፡ ጉዳዩም ወደ ኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ተመራ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ለአዕምሮ ጤና አገልግሎት የሚውል መድኃኒት ስቶክ ውስጥ ተገኘ፡፡ ይህም መድኃኒት በሙሉ ወጥቶ የአዕምሮ ጤና ሕክምና ለሚሰጡ የመንግሥት ሆስፒታሎች እንዲታደል ተደረገ፡፡ ከዚህም ሌላ እንዲሁ የመድኃኒት እጥረት ሲያጋጥም ትብብር ይደረግላቸው የሚል ደብዳቤ በማጻፍ ወደ አገልግሎቱ ተመራልን፡፡ እኛም ክትትላችንን አላቋረጥንም፡፡ በተደረገውም ክትትልና በመንግሥት ጥረትና ትብብር ተፈላጊ መድኃኒት ገባልን፡፡ በተረፈ አብዛኛውም ሰው የጤና መድኅን ተጠቃሚ ስለሆነ በዚያም ይስተናገዳል፡፡ ሌላው ግን በግል የሚገዛው መድኃኒት በጣም እየተወደደ ነው፡፡ አንዳንዴም መድኃኒቱ ይጠፋል፡፡ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው አልፎ ከሼልፍ የተወገዱም አሉ፡፡ ይህም ሲሆን በምትኩ አዲስ መድኃኒት ለማስገባት ክፍተት ፈጥራል፡፡   

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ አስተማማኝ የመድኃኒት አቅርቦት አለ ለማለት ይቻላል?

ወ/ሮ እሌኒ፡- አስቸጋሪ ነው፡፡ አስተማማኝ ለማለት አይቻልም፡፡ በተለይ ብዙ ጊዜ መድኃኒቶች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያልፋል፡፡ በምትኩ ሌላ አዲስ መድኃኒት እስከሚገባ ድረስ ክፍተት ይፈጠራል፡፡ መድኃኒቱ ተስማምቷቸው፣ የተረጋጋ ኑሮ የሚመሩ ሰዎች መድኃኒት ሲጠፋ ተመሳሳይ መድኃኒትን መጠቀም ግድ ይሆንባቸዋል፡፡ ተመሳሳይ መድኃኒቶችን እስከሚለማመዱና ሰውነታቸውም እስከሚቀበለው ድረስ በጣም ከባድ ነገር ያሳልፋሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ሕመሙ እንደገና ያገረሻል፡፡ እኔ የግሌን ተሞክሮ ብናገር አብዛኛውን ሲያመኝ የነበረው በሕመሙ ምክንያት ሳይሆን የተስማማኝን መድኃኒት ከገበያ ላይ አጥቼ ሌላ መድኃኒት ሲቀየር ወይም በሌላ ሲተካ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ሕመሙ ያገረሽብኝ ነበር፡፡ ስለሆነም ከባድ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ደግሞ ብዙ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ የለም፡፡ ጠብቁ እንባላለን፡፡ ከዚህ አኳያ እውነት ለመናገር አዕምሮ ጤና መድኃኒት በመንግሥት በኩል ብዙም ትኩረት እንዳልተሰጠው ነው፡፡ ይህም የሆነው ገዳይ ለሆኑ በሽታዎች ብቻ ትኩረት በመስጠቱ ነው፡፡ ነገር ግን የአዕምሮ ሕምም ሌሎችንም የሰውነት ክፍሎች የሚቆጣጠር ነው፡፡ ስለሆነም ከሌሎቹ እኩል ትኩረት መስጠት አለበት ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ታካሚዎቹ የጤና መድኅን ተጠቃሚ ቢሆኑም በአንፃሩ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የአቅም ማነስ ችግር የሚታይባቸው አሉ፡፡ ለእንደዚህ ዓይነት ወገኖች ማኅበሩ ምን እያደረገላቸው ነው?

ወ/ሮ እሌኒ፡- ብንደርስላቸው ወይም ብናግዛቸው ጥሩ ነበር፡፡ ግን ማኅበራችን እዚያ ደረጃ ላይ ገና አልደረሰም፡፡ እየተንቀሳቀሰ ያለው በአባላት ወርኃዊ መዋጮ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን መድኃኒት የመግዛት አቅም ለሌላቸው አባላት የተወሰነ የምንረዳበት አካሄድ አለ፡፡ የተፈለገውን ያህል ግን አይደለም፡፡ ሁለት በጣም ተቸግረው ማኅበራዊ ዋስትና መክፈል ላልቻሉና ለተቸገሩ ተማሪዎች ረድተናል፡፡ በተረፈ ግን ቋሚ ድጋፍ ለማድረግ ማኅበራችን ለጊዜው አቅም የለውም፡፡ 

ሪፖርተር፡- የአዕምሮ ጤና የሕክምና አገልግሎት ከሚሰጡ የመንግሥት ጤና ተቋማትና በአዕምሮ ሕመም ዙሪያ ከሚንቀሳቀሱ ማኅበረሰብ ነክ ድርጅቶች ጋር ማኅበራችሁ ግንኙነት ፈጥሯል?

ወ/ሮ እሌኒ፡- ከሆስፒታሎችና ማኅበረሰብ ነክ ከሆኑ ድርጅቶች ጋር መልካም ትብብር ፈጥረናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ትብበር ከፈጠርንባቸው ድርጅቶች መካከል መቆዶኒያ፣ ጌርጌሴኖን፣ ሶሊሆም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ አንድ ሰው አዕምሮ ሕመም ቢደርስበት ትልቁ ሸክም የሚያርፈው በቤተሰብ ላይ ነው፡፡ ስለሆነም በተጠቀሱት ድርጅቶች ውስጥ እንክብካቤ የሚደረግላቸው የአዕምሮ ሕሙማን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክም ሆነ በሌላ መንገድ ለማግናኘት ጥረት በተደረገ ቁጥር ማኅበረሰባችን ለጥረቱ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ከአዲስ አበባ ውጪማለትም በተለያዩ ክልሎች ለመድረስ የምታደርጉትን ጥረት እንዴት ይገመግሙታል?

ወ/ሮ እሌኒ፡- ከአዲስ አበባ ውጪ በተወሰኑ ክልሎች አባላት አሉን፡፡ ትኩረታችን አዲስ አበበ ላይ ብቻ ሳይሆን ክልሎችንም ያካትታል፡፡ ለዚህም ማኅበሩ ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ የተመዘገበው በፌዴራል ደረጃ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በሁሉም ክልሎች ኔትዎርኮች እንዲኖሩን እናስባለን፡፡ ምክንያቱም ችግሩ ያለው አዲስ አበባ ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው የአገሪቱ ሥፍራዎች ነው፡፡ የከፋ ችግር ያለው ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ክልሎች ነው፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተመለከቱ የሚደውሉልን ብዙዎች ናቸው፡፡ ‹‹የት ልሂድ? አማኑኤል ስፔሻላይዝ ሆስፒታል መምጣት አለብኝ ወይ?›› እያሉ ይጠይቁናል፡፡ እኛ በአቅራቢያቸው በሚገኘው ጤና ተቋም እንዲስተናገዱ ምክር አዘል ጥቆማ እንሰጣቸዋለን፡፡ የማኅበሩ አቅም ከፍ ባለ ቁጥር በክልሎች አንድ ቻፕተር ከፍተን በኔትዎርክ የማያያዝ ሐሳብ አለን፡፡ ይህም በማኅበሩ ስትራቴጂክ ዕቅድ ውስጥ ተከትቷል፡፡  

ሪፖርተር፡- በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከብሮ በሚውለው የአዕምሮ ጤና ቀን ብቻ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ሲከናወን ይስተዋላል፡፡ በተረፈ ቀጣይነት የለውም፡፡ በዚህ ላይ ያለዎትን አስተያየት ቢያካፍሉን?

ወ/ሮ እሌኒ፡- በእርግጥም አንድ መሪ ቃል ተመርጦለት ግንዛቤ የማስጨበጡ ሥራ ማከናወን ጥሩ ነው፡፡ ግን ቀጣይነት እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡ የአዕምሮ ጤና የአንድ ቀን ጉዳይ አይደለም፡፡ አብሮን የሚኖር ችግር ነው፡፡ መገለሉና አድልኦው በየቀኑ የሚገጥመን ችግር ነው፡፡፡ ይህ ዓይነት ችግር ያለበትን እክል በዓመት አንዴ በዘመቻ መልክ አጣርተነው የምንተው ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ መሪ ቃል መኖሩና ትኩረት መስጠቱ ጥሩ ነው፡፡ ግን የአንድ ቀን ጉዳይ ሳይሆን በየቀኑና በየጊዜው በመደበኛነት የምናወራው መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ስለአዕምሮ ጤና ብዙ በተወራ ቁጥር ነው ችግር ያለባቸው ሰዎች ወደ ሕክምና ለመምጣት የሚደፍሩት፡፡ ልክ እንደ አካላዊ ሕመም አዕምሮ ሕመም ትኩረት መስጠት የሚቻለው በየቀኑ በመገናኛ ብዙኃን፣ በቤተሰብና ማኅበረሰብ ውስጥ ስለ አዕምሮ ጤና መናገር ስንችል ነው፡፡ እንደ ማኅበር አጽንኦት መስጠት የምንፈልገው ችግሩ ከተከሰተ በኋላ መፍትሔ ለመፈለግ መሯሯጥ ብቻ ሳይሆን መካላከሉ ላይም እንዲሠራ ነው፡፡ በተለይ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ላይ ስለአዕምሮ ጤና ቢወራና ግንዛቤ ቢሰጥ ለአዕምሮ ሕመም የሚዳረገውን ሰው መቀነስ ይቻላል፡፡ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ አንዱ የትኩረት አቅጣጫና የመከላከያ ዘዴ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ሕክምና የጀመሩ ብቻ ናቸው የማኅበሩ አባል መሆን የሚችሉት?

ወ/ሮ እሌኒ፡- ማኅበራችን ለማንም ክፍት ነው፡፡ በተለይ ሕክምና የጀመሩና ከበሽታቸውም ያገገሙ ሁሉ የማኅበሩ አባል እንዲሆኑ ግብዣችንን እናቀርባለን፡፡፡ አባል መሆን ደግም ‹‹ከአዕምሮ ሕመም ጋር የሚኖረው ለካ ብቻዬን አይደለሁም የሚል አመለካከት በውስጡ ይሠርፃል፡፡ ከማኅበረሰቡ ጋር ጥሩ መግባባትና ቀረቤታ ይፈጥራል፡፡ ከአባላቱ ጋር በጤናቸውና በሕክምና አሰጣጡ ዙሪያ ተሞክሮና ልምድ የመለዋወጫ መድረክም ይፈጥርላቸዋል፡፡ በተለይ የአቻ ለአቻ ድጋፍ ራሱን የቻለ የሕክምና ዓይነት ስለሆነ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ይህንን መልካም አጋጣሚ እንዲጠቀሙ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የቆመው የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን

የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት ለአገራቸው የሕይወት መስዋዕትን ለመክፈል የወደዱ፣ ለአገራቸው ክብር ዘብ የቆሙና ውለታን የዋሉ ናቸው፡፡ እነኚህ የአገር ጌጦች በአገሪቱ በተከሰተው የሥርዓት ለውጥ...

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...