- በአገር አቀፍ ደረጃ የሳይንስና ኢንጂነሪንግ ውድድር ሊካሄድ ነው
በአዲስ አበባ ከሚገኙ አሥር የመንግሥትና የግል ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች መካከል የፈጠራ ሥራ ዝንባሌ ላላቸውና በኤሌክትሮኒክስና በኮምፒዩተር ሳይንስ ለሁለት ወራት የንድፈ ሐሳብና የተግባር ሥልጠና ለተከታተሉ 46 ወጣቶች ዕውቅና ተሰጠ፡፡ ከእነዚህ 16ቱ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ሲሆን፣ በቀጣዩ ሳምንት በሚከናወነው አገር አቀፍ የሳይንስና ኢንጂነሪንግ ውድድር ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ስቲምፓወር ከተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን ይህንኑ ሥልጠና ተከታትለው ካጠናቀቁት መካከል በቡድንና በተናጥል ባጎለበቷቸው የፈጠራ ሥራዎች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ 16 ወጣቶች ተሸልመዋል፡፡
ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. በአካዴሚው በተከናወነው የዕውቅናና የሽልማት አሰጣጥ ሥርዓት ወጣቶቹ ያጎለበቷቸው የፈጠራ ሥራዎች በወላጆቻቸውና በተጋባዥ እንግዶች ተጎብኝተዋል፡፡
ለሽልማት ከበቁት የፈጠራ ሥራዎች መካከል የታክሲዎችን ሥምሪት ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል መተግበሪያ የተገጠመለት ካሜራ ይገኝበታል፡፡ በታክሲዎች መነሻና መድረሻ ቦታዎች የሚቆመው ይህ ዓይነቱ ካሜራ ወረፋቸውን የሚጠባበቁ አገልግሎት ፈላጊዎችንና በቦታው የተመደቡትን ታክሲዎች ብዛትና ማነስ እየመዘገበ የተሳለጠ ሥምሪት እንዲኖር ለሥምሪት ተቆጣጣሪዎች፣ ለተራ አስከባሪዎችና ለአሽከርካሪዎች ያሳውቃል፡፡ መተግበሪያው ተግባራዊ እንዲሆን ከተፈለገ አሁን በሥራ ላይ ያለው የታክሲዎች ሥምሪት ቀርቶ ከመተግበሪያው ጋር በተጣጣመ መልኩም መቀየር አለበት፡፡
ሌላው የፈጠራ ሥራ የተሽከርካሪ ማቆሚያ (ፓርኪንግ) አገልግሎት ለሚሰጡ ድርጅቶች የሚጠቅም ሲሆን፣ ጂፒኤስ ወይም የኢንተርኔት ሲስተም በሌለበት አካባቢ ለሚጓዝ ተሸከርካሪ ጥቅም ይሰጣል የተባለ የፈጠራ ሥራ ይገኝበታል፡፡ ይህ በስማርት ካርድ የሚሠራ ሲሆን፣ ከተነሳበት ቦታ ጀምሮ እስከሚደርስበት ሥፍራ ድረስ ያለውን አካባቢ መዝግቦ የሚይዝ ቴክኖሎጂ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ መስፍን እንግዳወርቅ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ወጣቶቹ ላከናወኗቸው የፈጠራ ሥራዎች ግብዓት ማሟያ የሚውል ከ150‚000 ብር በላይ ወጪ ሆኗል፡፡ ወጪውን የሸፈነውም አካዳሚው ቀደም ሲል ላቋቋማቸው ቤተ ሙከራዎች መገልገያ ዕቃዎችን ያሟላው ስቲምፓወር ነው፡፡
በፈጠራ ሥራዎቹ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ወጣቶች መካከል ሦስቱ በአዲስ አበባ ከጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ቀናት በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው አገር አቀፍ የሳይንስና ኢንጂነሪንግ ውድድር ማዕከሉን ወክለው እንደሚወዳደሩ ተናግረዋል፡፡
ከስቲምፓወር ጋር በመተባበር ውድድሩን በዋናነት የሚያዘጋጀው ትምህርት ሚኒስቴር እንደሆነ፣ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጀት (ዩኔስኮ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያከብረው የሳይንስ ቀን ጋር እንደሚያያዝም አክለዋል፡፡
እንደ አቶ መስፍን፣ በየክልሉ በሚገኙ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የፈጠራ ሥራ ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶች በብዛት አሉ፡፡ ነገር ግን በተጠቀሰው ሥልጠና ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ ከፍተኛ በጀት ይጠይቃል፡፡ የሚፈለገው ድጋፍ ከተገኘ የሚሳተፉበት መንገድ ይመቻቻል፡፡