የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የዕርዳታና የሥራ ኤጀንሲ ኮሚሽነር ጄኔራል ፊሊፕ ላዛሪኒ የሕፃናት አድን ድርጅት (ሴቭ ዘ ችልድረን) መረጃን ጠቅሰው፣ ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ካደረጉት ንግግር የተወሰደ፡፡ ኮሚሽነር ጄኔራሉ በተጨማሪም ጋዛ ውስጥ ካለቁት ፍልስጤማውያን 70 በመቶ ያህሉ ሕፃናትና ሴቶች መሆናቸውን አክለዋል፡፡ የተመድ የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) መረጃን ዋቢ በማድረግም በየቀኑ 420 ሕፃናት እየተገደሉ ወይም እየቆሰሉ መሆናቸውን ለፀጥታው ምክር ቤት አስረድተዋል፡፡ እስካሁን በእስራኤል ጥቃት ከስምንት ሺሕ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለው ከ19 ሺሕ በላይ ሲቆስሉ፣ ሐማስ በፈጸመው ጥቃት ደግሞ ከ1,400 በላይ እስራኤላውያን ተገድለው 239 መታገታቸውን ከተለያዩ የዜና አውታሮች ዘገባ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በምሥሉ ላይ የሚታዩት ከጥቃት የተረፉ ፍልስጤማውያን ሕፃናት ናቸው፡፡ (ፎቶ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ)