የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 15ኛውን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ አከናውኗል፡፡
በጠቅላላ ጉባዔ ከቀረቡት የተለመዱ ዓመታዊ ሪፖርቶች ባሻገር በርካታ ጉዳዮች ተነስተውበታል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ የደረሰበት ደረጃና መሻሻል ስለሚገባቸው ጉዳዮች ከጉባዔተኛው አስተያየት ተነስቶ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ፌዴሬሽኑ፣ ከክልሎች፣ ከከተማ አስተዳደሮች፣ ከክለቦች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ጋር በጋራ ሆኖ መሥራት ስለሚገባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በጠቅላላ ጉባዔው በዋነኛነት ከተነሱት ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በጋራ በመሆን ይፋ ያደረጉት የተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ ይጠቀሳል፡፡
አባል አገሮች ወጥ የሆነ መተዳደሪያ ደንብ እንዲኖራቸው በማስፈለጉ ፊፋ እ.ኤ.አ. 2022 ላይ የተሻሻለ ደንብ ማውጣቱለ ለጠቅላላ ጉባዔው ተብራርቷል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ እንዲስተካከል አስፈላጊ ሆኖ፣ ግንቦት 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ያፀደቀው የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ፣ ፊፋ ከላከው መደበኛ የማሳያ ሕጎች (Standard Sample Statutes) ጋር ሲነፃፀር 85/86 በመቶ የሚያሠራና መለወጥ የማይገበው ሆኖ ቢገኝም፣ ቀሪው ፊፋ በሚያስቀምጠው ሕግ መሠረት መስተካከል የሚገባው እንደሆነ በጥናቱ ቀርቧል፡፡
በዚህም መሠረት በፊፋ ባለመያዎች መሠረታዊ ለውጥ እንዲደረግባቸው ምክረ ሐሳብ ከቀረበባቸው የመተዳደሪያ ደንብ አንቀጾች መካከል፣ የቀድሞ አንቀጽ 29 የአሁኑ አንቀጽ 27 የአባላት ድምፅና ውክልና ይጠቀሳል፡፡
ይህም ጠቅላላ ጉባዔው 121 ተወካዮች እንዲኖሩት ያስቀምጣል፡፡ በዚህም መሠረት እያንዳንዱ ክለብ ወይም ቡድን አንድ ድምፅ ያለው ሆኖ እያንዳንዱ 16 የፕሪሚየር ሊግ ክለብ አንድ ተወካይ (አጠቃላይ 16 ድምፆች) እንደሚኖራቸው ያስቀምጣል፡፡
ከዚህም ባሻገር እያንዳንዱ ክለብ ወይም ቡድን አንድ ድምፅ ያለው ሆኖ እያንዳንዱ 35 የከፍተኛ ሊግ ክለብ አንድ ድምፅ ያለው ተወካይ ይኖረዋል፡፡
በጠቅላላ ጉባዔ ላይ ከቀረቡና በተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል፣ ክልሎች በሥራ አስፈጻሚው ውስጥ ስለሚኖራቸው ውክልናና ዕጩ ሆነው ከሚቀርቡ የፕሬዚዳንት ምርጫ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
‹‹የክልል ውክልና በጉባዔ ውስጥ እንጂ በሥራ አስፈጻሚ ውስጥ ግዴታ መሆን የለበትም›› የሚል ሐሳብ የቀረበ ሲሆን፣ ይህም በኢትዮጵያ የክልሎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ፣ የሥራ አስፈጻሚው ቁጥር እየተበራከተ ስለመጣ ፊፋ ማስተካከያ እንዲደረግበት ማዘዙን ተከትሎ እንደሆነ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ አብራርተዋል፡፡
በዚህም መሠረት ከሦስት ዓመት በኋላ ከሚደረገው ምርጫ ጀምሮ ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ ሆኖ የሚቀርበው ሰው በራሱ መለኪያና መሥፈርት ወደ ክልል ወርዶ ሥራ አስፈጻሚውን መርጦ ራሱን ብቻ ለምርጫ ያቀርባል ተብሏል፡፡
ቀድሞ እያንዳንዱ ተወዳዳሪ አምስት የክለብና የክልል ድጋፍ ማቅረብ ከቻለ፣ ለፕሬዚዳንትነት ምርጫ ዕጩ ሆኖ መቅረብ የሚችልበት አሠራር የነበረ ሲሆን፣ ለሥራ አስፈጻሚነት ከክልል የሚላኩ ዕጩዎች በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ነበር የሚመርጡት፡፡
በአንፃሩ አሁን በተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ማንኛውም ዕጩ ራሱን ለመሸጥና ጉባዔውን ለማሳመን ጠንካራ አጋሮችን ይዞ መምጣት ይገባዋል ተብሏል፡፡ ሆኖም ተወዳዳሪ አብረውኝ ይሠራሉ ብሎ ከሚመርጣቸው የሥራ አስፈጻዎች መካከል ሦስቱ ሴቶች መሆን እንዳለባቸው ያስገድዳል፡፡
በሌላ በኩል በጠቅላላ ጉባዔው ከተሻሻሉ ደንቦች መካከል የፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ የቀድሞ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 47 የአሁኑ አንቀጽ 44 በተቀመጠው መሠረት፣ የፌዴሬሽን ጽሕፈት ሥራ አስፈጻሚ፣ አስተዳደርና ሕግ አውጪ አካል ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኦፊሰር በሚያስቀምጡት አቅጣጫ መሠረት፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራዎችን እንደሚያከውን አስቀምጧል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጣዊ ደንቦች መሠረት መገዛት እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡
በመደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ ከመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ባሻገር፣ የፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የማሟያ ምርጫ የተከናወነ ሲሆን ከትግራይ፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ከአፋር ክልሎች ስምንት ዕጩዎች ቀርበዋል፡፡
በዚህም መሠረት የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባላት የማሟያ ምርጫ አወል አብዱራሂም (ኮሎኔል) ከትግራይ ክልል በ92 ድምፅ፣ አቶ ኢብራሂም ሙክታር ከአፋር ክልል በ80 ድምፅ፣ እንዲሁም አቶ ማዕረጉ ሀብተ ማርያም ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በ76 ድምፅ ተመርጠዋል፡፡
ሌላው በጉባዔው ሲነሱ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል ጥምር ዜግነት አንዱ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲነሳበት የቆየውን የትውልደ ኢትዮጵውያውን ጉዳይ ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ የትውልደ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ በጠቅላላ ጉባዔው የሚወሰን ሳይሆን፣ ይልቁንም በአገሪቱ ሕገ መንግሥት የሚታይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
‹‹የጥምር ዜግነት በአገሪቱ ሕግ መንግሥት መሠረት መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፣ ሆኖም እጃችንን አጣጥፈን አልተቀመጥንም፡፡ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ እያየን ነው፤› በማለት አቶ ኢሳያስ በስብሰባው ላይ አብራርተዋል፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ ፌዴሬሽኑ ጉዳዮን በጠበቆቹና በባለሙያዎች እየተከታተለ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከቀጣይ የውድድር ዓመት ጀምሮ በፕሪሚየር ሊግ እየተሳተፉ የሚገኙ ማንኛውም ክለብ የሴት ክለብ መያዝ ግዴታው እንደሆነ ተገልጿል፡፡
እንደ ብሔራዊ ፈዴሬሽኑ ማብራሪያ ከሆነ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ማንኛውም ክለብ የሴት ቡድን መያዝ እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጦ ጫና እያደረገ እንደሚገኝ ፕሬዚዳንቱ አንስተዋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ዓመታዊ ሪፖርቱን ያቀረበ ሲሆን፣ የሜዳ ጉዳይ፤ የክለቦች ፈቃድ (Club Licensee) የታዳጊዎች ውድድር፣ ከተለያዩ አገሮች ፌዴሬሽኖች ጋር የተደረጉ ስምምነቶችን በሚመለከት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ተብራርቷል፡፡
ሜዳ የመገንባት የፌዴሬሽኑ ሥራ ባይሆንም ችግሩን ለመፍታት እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁሟል፡፡ ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለብሔራዊ ቡድኑ የሚያደርገው ቅናሽ አነስተኛ መሆንና መስተንግዶ ላይ ማሻሻያ ይደረግ የሚል አስተያየት ተሰንዝሯል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በ2015 ዓ.ም. የውድድር ዘመን ለወንዶች ብሔራዊ ቡድን 66 ሚሊዮን ብር ወጪ ሲያደርግ፣ ለሴቶች ብሔራዊ ቡድን ደግሞ 40 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን በሪፖርቱ አቅርቧል፡፡
ከዚህም ባሻገር ወሎ ሠፈር የሚገኘው የፌዴሬሽኑ ዋና ጽሕፈት ቤት ስም አዘዋውሮ ካርታውን በእጁ መያዙን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአኅጉር አቀፍና አገር አቀፍ ተሳትፎን በተመለከተ፣ ክለቦች ብዙ መሥራት የሚጠበቅባቸው የቤት ሥራ እንዳለ የተጠቆመ ሲሆን፣ በተለይ በብሔራዊ ሊግና ከፍተኛ ሊግ የሚካፈሉ ክለቦች ቡድናቸውን በታዳጊዎች መሙላት ይጠበቅባቸዋ ተብሏል፡፡
ሌሎች አገሮች የብሔራዊ ቡድን በጀት በፓርላማ እንደሚያፀድቁ በምሳሌነት ተነስቶ፣ ኢትዮጵያ ለብሔራዊ ቡድን መንግሥት ሊበጅት እንደሚገባና ፌዴሬሽኑ ቴክኒካል ድጋፍ ብቻ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ተነስቷል፡፡