Sunday, December 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ ዋጋ ለማረጋጋት ባዘጋጀው ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ከባንክ የሥራ መሪዎች ጋር መከረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዋናነት ዋጋ ለማረጋጋት ያስችለኛል ያለውን የሦስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ከንግድ ባንኮች ሥራ መሪዎች ጋር መከረ፡፡  

ባንኩ ትናንት ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ከባንክ የቦርድ መናብርትና ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር በስትራቴጂክ ዕቅዱ ላይ በመከረበት ወቅት፣ ባንኮች አሠራራቸውን ከዚህ ስትራቴጂክ ዕቅድ ጋር እንዲያጣጥሙ እንደተገለጸላቸው ሪፖርተር ከምንጮቹ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡  

ብሔራዊ ባንክ ዋጋ ለማረጋጋት ባዘጋጀው ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ከባንክ የሥራ መሪዎች ጋር መከረ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ

የኢትዮጵያ በሔራዊ ባንክ የሦስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ዋነኛ ዓላማ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የተረጋጋ ዋጋ ማስፈን ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተረረጋ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ በመሆኑ፣ ባንኮች በዚሁ አግባብ ስትራቴጂውን ግቡን እንዲመታ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተገልጾላቸዋል፡፡

ይህንን ስትራቴጂክ ዕቅድ ለማስፈጸም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወሰዳቸው ዕርምጃዎች እንደሚኖሩ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ይህም የባንክ ሕግና ሥርዓቶችን  መቆየር ጭምር ሊሆን ይችላል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ በትናንቱ ውይይት ላይ እንደተናገሩት፣ ‹‹በሒደት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ሕግና ሥርዓትን በመቀየር፣ ከመንግሥት ጋር በተቀናጀ ሁኔታ በመሥራት በዋጋ ማረጋጋት ላይ ትኩረት እንዲያደርግ አዲስ ስትራቴጂ አውጥተናል፤›› ማለታቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡  

ምንጮች እንደገለጹት፣ በንግድ ባንኮቹና በብሔራዊ ባንክ መካከል ትናንት የተደረገው ውይይት በአመዛኙ በስትራቴጂ ዕቅዱ ላይ መወያየት ቢሆንም፣ ከብሔራዊ ባንክ ገዥው ማብራሪያ መገንዘብ የቻሉት፣ ብሔራዊ ባንክ የሚያካሂደውን የቁጥጥር ሥራ የሚያጠብቅ መሆኑን ነው፡፡

በተለይ በአሁኑ ወቅት ባንኮች በሚሰጡት ብድር ጤናማነት ላይ እንዲሁም ከውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ እየታዩ ያሉ ችግሮችን ከዚህ በኋላ የበለጠ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ስለመሆኑ ለመገንዘብ መቻላቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት ለመፍጠር አንዱ መሣሪያው የቁጥጥር ሥራ በመሆኑ፣ የሚታዩ ክፍተቶችን በማየት ከዚህ ቀደም የነበረውን ቁጥጥርና ክትትል ያጠናክራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከምንጮቹ ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

አቶ ማሞ በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ የኢትየጵያ የፋይናንስ ሥርዓት የተዘረጋ እንዲሆን ለማስቻል ቁልፍ የሆኑ ማሣሪያዎች አሉት፤›› ማለታቸውም ተጠቁሟል፡፡

አንደኛው ቁልፍ መሣሪያ የቁጥጥር ሥርዓቱን ማጠናከር በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተለያዩ ሕጎችም፣ አሠራሮችንና ደንቦችን ተከትለው እንዲሠሩ ያደርጋል፡፡ ይህንን የቁጥጥር ሥርዓት ተከትሎም የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት ለማረጋገት የመቆጣጠር፣ የመከታተል፣ የመገምግና የባንኩ ሕግ በትክክል መተግበሩን የማረጋገጥ ሥራ የትንናንቱ የውይይት መድረክም ስትራቴጂክ ዕቅዱን ከማሳካት አንፃር የባንኮች የሚጠበቅባቸውን ሚና ስለመኖሩ ከማስገንዘብ አልፎ፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ችግሮች በዝምታ የማይታለፉና የዕርምት ዕርምጃ የሚወሰድባቸው ስለመሆን የባንኩ ሥራ መሪዎች እንዲገነዘቡ ለማድረግ እንደሆን ከውይይት መንፈስ ለመገንዘብ እንደቻሉ ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡

ይህም ቢሆን የኢትዮጵያ ባንኮች ወቅታዊ አቋም ጤናማነት የተረጋጉ ሆነው እየተጓዙ እንደሆነ ገዥው በውይይት መድረኩ ላይ መግለጻቸው ታውቋል፡፡

በመሆኑም ኅብረተሰቡ በኢትዮጵያ ባንኮች ላይ ሙሉ እምነት ሊኖረው እንደሚገባም አቶ ማሞ ገልጸው፣ ብሔራዊ ባንክም ከፍተኛ ቁጥጥር የሚያደርግ መሆኑንም ማውሳታቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡  

ባንኮች ከሚሰጡት ብድር ጋር በተያያዘ ያሉባቸውን ችግሮች በተመለከተ፣ በተለይም ከሚሰጡት የተወሰኑ ብድሮች ላይ ያተኮረ ሆኖ እንዲስተካከል የሚደረግበት ሁኔታ ላይ በዕለቱ ስለመምከራቸውም ታውቋል፡፡

ባንኮች እየሰጡ ያለው ብድር ከዓመት ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በመሆኑ፣ ብድሩን አካታች ለማድረግ ሊሠሩ የሚገባቸው ሥራዎች ላይም ብሔራዊ ባንክ እንደተቆጣጣሪነቱ ዕርምጃዎች የሚወስድ ስለመሆኑም አቶ ማሞ መናገራቸው ታውቋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ አዲስ የብድር መመርያ ሊያወጣ የሚችል ስለመሆኑ ጠቃሚ ነው የሚሉ ወገኖች ከዚህ ጎን ለጎንም በቅርቡ ያወጣውን የባንኮች የብድር ገደብ መመርያ መልሶ ሊከልስ ይችላል ይላሉ፡፡

ባንኮች ከመቶ በላይ የብድር ምጣኔያቸው ማደግ የለበትም የሚለው የባንኩ የቅርብ ጊዜ መመርያ፣ ምናልባትም በዘርፉ ተለይቶ የገደብ ምጣኔ ሊስተካከል እንደሚችልም በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች